Saturday, 03 September 2016 10:34

Hysteroscopy...የማህጸን ምርመራ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(14 votes)

Hysteroscopy የተሰኘውን የምርመራ ዘዴ በአገራችን እውን ለማድረግ የዛሬ ስድስት አመት ገደማ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንድ ስልጠና ተሰጥቶ ነበር። ስልጠናው የተሰጠው በማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻላይዝድ ላደረጉ ከፍተኛ ሐኪሞች ነበር።
 ይህ የHysteroscopy የህክምና ዘዴ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ምን ያህል በስራ ላይ ውሎአል? የሚለውን ጥያቄ በጊዜው ሰልጣኝ ለነበሩት ለዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በዘርፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋክልቲ መምህርት አቅርበናል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም አንዳንድ ሰነዶች ያወጡትን ቁምነገር ወደአማርኛ መልሰን ለንባብ ብለነዋል። ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ እንደሚገልጹት፡-
 Hysteroscopy ማለት ሄስነሮስኮፕ የተባለ ቀጭን መሳሪያ ጫፍ ላ ናሜራ በተገጠመለት ቱቦ በመጠቀም ትንንሽ ነገሮችን በካሜራ እይታ አጉልቶ ማከም ነው። የHysteroscopy ስራው የማህጸን ውስጥ ማለትም ልጅ የሚቀመ ጥበትን እና እንቁላል የሚተላለፍበትን ቧንቧ በማህጸን በኩል ማየት ነው። ምናልባትም ከLaparoscopy የህክምና ዘዴ የሚለየው Laparoscopy በሆድ እቃ በኩል ገብቶ ለሁሉም የሰውነት ክፍሎች የሚያገለግል የቀዶ ሕክምና ዘዴ ሲሆን Hysteroscopy ግን ለማህጸን ብቻ በብልት ወይም በማህጸን በር በኩል ወደላይ የውስጥ የማህጸን ክፍሎችን የእንቁላል ማምረቻዎችን ጭምር ለማየትና ለማከም የሚረዳ መሆኑ ነው። Hysteroscopy የተሰኘው ምርመራ Laparoscopy ሊያየው የማይችለውን የማህጸን ችግር ለማየት የሚያስችል የምርመራ እና የህክምና ዘዴ ነው።
በHysteroscopy የህክምና ዘዴ በማህጸን አካባቢ የሚታከሙት ፡-
መውለድ ያልቻሉ ሴቶች ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳል፣
የእንቁላል ማስተላለፊያው ቧንቧዎችና የማህጸን ቀዳዳ በትክክል መገናኘቱን ለማወቅ ይረዳል፣
ከትክክለኛው ጊዜ ውጪ የሚታይ የደም መፍሰስ የወር አበባ ኡደትን ሳይጠብቅ ወይንም የወር አበባ ከተቋረጠ በሁዋላ የሚታይ የማህጸን መድማትምክንያቱን ለማወቅ ያስችላል፣
ማህጸን ተገቢውን መጠን ሳይጠብቅ የእብጠት ወይንም ሌላ ምልክት ካሳየ፣
የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦዎች በስነስርአት መስራታቸውን ማየት ያስችላል።
መጥፎ ፈሳሽ ያለባቸው የወር አበባ መዛባት እና ሕመም ለሚታይባቸው ምክንያቱን ለመፈለግ ይረዳል፣
በተለምዶ ሉፕ ህ የተሰኘው የእርግዝና መከላከያ ቦታውን ለቅቆ ካልተፈለገ ስፍራ ከተቀመጠ ለማስተካከል ይረዳል። ...ወዘተ
 ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ሰዎችም በHysteroscopy የህክምና ዘዴ ዘላቂ የሆነውን መከላከያ ማለትም የማህጸን መቋጠርን ለመስራትም ይረዳል። ከምርመራው ባሻገርም ሕክምናውን በመስጠቱ በኩል በማህጸን ውስጥ ጠባሳ ወይንም እጢ የመሳሰሉት ችግሮች የሚገኙ ከሆነ ለማከም ጥሩ ክኖሎጂ ነው።
 ዶ/ር ማህሌት እንደሚሉት በHysteroscopy የህክምና ዘዴ በማህጸን ውስጥ የሚኖር ኢንፌክሽን ወይንም ባክሪያ የመሳሰሉትን ሌላውን የሰውነት ክፍል ሳይጎዱ ሕመሙ የትጋነው ያለው? ምን ደረጃ ላይነው ያለው? አይነቱስ ምንድነው? የሚለውን በመሳሪያው አማካይነት በሌቪዥን እስክሪን እየተመለከቱ በቀላሉ ለማወቅና ለማከም ይረዳል። አንዳንድ ጊዜ በቀላሉ የማይገኙ ግን ትንንሽ ቦታዎችን የሚይዙ ለምሳሌም አንድ ሴንቲሜትር የሚያህል የካንሰር ሕዋስ በሌላ መሳሪያ ለማየት አስቸጋሪ ሲሆን በHysteroscopy ግን በቀላሉ በአይን ማየትና ማከም ይቻላል። Hysteroscopy ለምርመራ ከማገዙም በላይ በራሱ የቀዶ የህክምና ዘዴ ሲሆን ሙሉ ማደንዘዣ የማይፈልግ እና በተመላላሽ ሕክምና የሚሰራ በመሆኑ እጅግ ጠቃሚና ዘመናዊ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ፣ ሕመምን የቀነሰ ፣ውጤቱ በጣም ጠቃሚ የሆነ የህክምና ዘዴ ነው።
 በአሁን ወቅት በአገራችን ሕክምናው ምን ያህል ይሰጣል ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ ሲመልሱ፣ “ምንም እንኩዋን በዘርፉ ተገቢው ስልጠና ተሰጥቶ የነበረና ስራውንም ጀምረነው ውጤቱን ያየን ቢሆንም የHysteroscopy ሕክምና በአሁን ወቅት አይሰጥም ማለት ይቀለኛል። ይህ የማህጸን ሕክምና ሲሆን አገልግሎት የሚሰጡትም የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች በተለይም በዚህ ሙያ የሰለጠኑት ናቸው። አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን የትኛውም ሆስፒታል እየተሰጠ አይደለም። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በምርመራ ደረጃ የምንጠቀምበት የነበረ መሳሪያ በብልሽት ምክንያት ከቆመ ጀምሮ አገልገሎቱ አይሰጥም። በእርግጥም ስልጠናው በመሰጠቱ ከሙያው ጋር ቅርበትን ፈጥረን ደረጃ አሳድገናል። ከሶስት አመት ጀምሮ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በእድሳት ላይ ከመሆኑ በፊት በነበረው ጊዜ ምናልባትም ለሁለት አመታት ያህል መውለድ ላቃታቸው እንዲሁም በተለያየ የማህጸን ሕመም ለሚሰቃዩ እናቶች አስፈላጊውን እርዳታ አድርገን ውጤቱን ተመልክተናል። ምናልባት ይህ ሆስፒታል እድሳቱን ጨርሶ ወደ ሙሉ ስራው ሲመለስና የሐኪሙም ኃይል ሲጠናከር እንደገና ወደስራው የምንመ ለስበትን ሁኔታ እናመቻቻለን ብለን እንጠብቃለን።
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና መምህርት በስተመጨረሻው እንደተናገሩት ፡-
“...ሁል ጊዜ የሚቆጨኝ ነገር አለ። ምክንያቱም ከመናገር ባለፈ ተግባራዊ ሲደረግ ስለማልመለከት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካንሰር ሕመም ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዘው የማህጸን በርና የጡት ካንሰር ነው። ይህ ደግሞ የሴቶች በሽታ ነው። በእርግጥ የጡት ካንሰር ወንዶች ላይም ሊታይ ቢችልም እሱ በጣም ጥቂት እንዲያውም የለም በሚያሰኝ ሁኔታ የሚከሰት ነው። እናም እናት፣ እህት፣ ሚስት የሌለው እንዳለመኖሩ አባቶች፣ ወንድሞች፣ ባሎች ይህንን ተገንዝበው ጉዳዩን ለሴቶቹ ብቻ በመተው ቸል ሳይሉ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ምክንያቱም ችግሩ በዘገየ ቁጥር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቡናዊ..ወዘተ የሚያደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ስለዚህም ሴቶች ቢያንስ በአመት አንድ ጊዜ ስለጤናቸው የህክምና ምርመራ ማድረግ አለባቸው። የማህጸን ካንሰር ከቁስለቱ ወደ ካንሰር ደረጃ ለመለወጥ ጊዜ ይሰጣል። ምናልባትም አስርእና አስራ አምስት አመት ድረስ ሊቆይ ይችላል። ስለዚህም በአንድ አመት አንድ ጊዜ የሚደረገው ምርመራ በጊዜው ስለሚደረስበት ለማከም በጣም ይረዳል። ከዚህም ባለፈ አስቀድሞ ለመከላከልም የሚረዳውን የአመጋገብንም ሆነ የአኑዋኑዋርን ሁኔታ በማስተካከሉ ረገድ ወንዶች ችላ ማለት አይገባቸውም። ሴቶችም እንደዚሁ በራሳቸው ሕይወት ደህንነት ላይ አስቀድመው ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባቸው የጤና መጉዋደል እስኪሰማቸው ድረስ መጠበቅ ሳይሆን በየትኛውም አቋራጭ የሕክምና ክትትል ማድረግ ይገባ ቸዋል። ” ብለዋል።
የHysteroscopy ሕክምና ምርምራ ከሚያደርግባቸው ችግሮች አንዱ ሴቶች መውለድ አልችል ሲሉ ምክንያቱን ለማወቅ የሚረዳ ነው። አንዳንድ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት ሴቶች ልጅ የመውለድ ችግር ሲገጥማቸው ወደሕክምናው ከመሄድ አስቀድሞ እራሳቸው ከሚወስዱዋቸው እርምጃዎች የሚከተሉት ይገኙበታል።
ጤናማ ምግብ መመገብ፡-
ስብ የበዛባቸውን ምግቦች በማስወገድ አትክልትና ፍራፍሬ የመሳሰሉትን በመመገብ ከእንስሳት የሚገኘውን ፕሮቲን ከፍራፍሬና አትክልት ምግቦች ለማግኘት መሞከር
በስኩዋርና በካርቦሀይድሬት የበለጸጉ ምግቦችን መቀነስ እና የእህል ዘሮችን እንደ አኩሪ አተር የመሳሰሉትን መመገብ
ክብደትን መቆጣጠር፡-
በማንኛውም ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ክብደትን በመቀነስ እርግዝናውን መሞከር ውጤቱ ጥሩ ይሆናል። በእርግጥ ከተገቢው በላይ ቀጭን መሆንም እርግዝና እንዳይከሰት ሊያደርግ ይችላል። እናም ውፍረትን በመለካቱ ሂደት በሚመከረው መንገድ የሰውነትን አቋም ማስተካከል ይገባል።
ጭንቀትን መከላከል፡-
በሙያው የተሰማሩ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጨቃጨቁበት እንደቆዩት ከሆነ እርግዝናና ጭንቀት አይገኛኝም የሚል ነው። ነገር ግን አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚመሰክሩት ደግሞ ጭንቀት ያለባቸው ሴቶች ጭንቀታቸውን ሲያስወግዱ የማርገዝ እድሉን እንዳገኙ እውነታውን ተናግረዋል።
 በአጠቃላይም ልጅ ለማርገዝ ጠቃሚ መንገዶች ናቸው የሚባሉትን በቅርብ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ወደ ሕክምናው ከመሄድ አስቀድሞ በራስ የሚደረጉ ሙከራዎችን መጠቀም ተገቢ ነው።

Read 7968 times