Sunday, 04 September 2016 00:00

“ጳጉሜን ለጤና” ነጻ የምርመራ አገልግሎት ሊጀመር ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ሴንተር በየዓመቱ የሚያከናውነውና “ጳጉሜን ለጤና” የተሰኘው ነፃ የምርመራ አገልግሎት የፊታችን ማክሰኞ ይጀምራል፡፡
ማዕከሉ ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና የፓናል ውይይት ላይ የማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ያለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ላለፉት ሰባት ዓመታት የሲቲስካን፣ ኤምአርአይ እና ሌሎች የተለያዩ የምርመራ አገልግሎቶችን ገንዘብ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ህሙማን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ የሚመጡና የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች በሀኪሞቻቸው ታዞላቸው በገንዘብ ማጣት ምክንያት ምርመራውን ለማግኘት ያልቻሉ ህሙማን፤ ከጳጉሜ 1-5/ 2008 ዓ.ም ድረስ በማዕከሉ በሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ማዕከሉ ላለፉት ሰባት ዓመታት በየዓመቱ በሚሰጠው በዚህ ነፃ የምርመራ አገልግሎት፣ ከ15ሺህ በላይ ህሙማን ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም አገልግሎቱን በስፋት ለመስጠት ዕቅድ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ ዓመቱን ሙሉ ገንዘብ ከፍለው አገልግሎቱን ማግኘት ለማይችሉ ወገኖች ከሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መሪ ቃል፣ በየዓመቱ በሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት ከ800-1000 ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል፡፡ የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች በሃኪሞቻቸው ታዞላቸው በአቅም ማጣት፣ አገልግሎቱን ማግኘት ያልቻሉ ህሙማን በተጠቀሱት ቀናት ወደ ማዕከሉ በመሄድ፣ ምርመራውን በነፃ ማግኘት እንደሚችሉም አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በክፍለ ከተማው ለሚኖሩ ወገኖች ነፃ የአንቡላንስ አገልግሎትን ከመስጠቱም ሌላ የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች የለሚያስፈልጋቸው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች መታወቂያቸውን ይዘው በመቅረብ፣ የ20 በመቶ ቅናሽ ለማግኘት እንደሚችሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

Read 2758 times