Sunday, 04 September 2016 00:00

መንግሥት የኃይል እርምጃ አቁሞ ህዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ ሰመጉ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

     በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚወሰድ አላስፈላጊ የኃይል እርምጃ እንዲቆምና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዲከበር የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) የጠየቀ ሲሆን የመብት ጥሰቶችን በማጣራት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎቹም በመንግስት እየታሰሩበት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች የደረሱ የመብት ጥቃቶችን አጣርቶ ማቅረቡን በመጥቀስ፤ አሁንም በአማራ ክልል በጎንደርና  ባህር ዳር ከተሞች ጨምሮ ተቃውሞና ግጭት በተፈጠረባቸው የክልሉ ከተሞች የበርካታ ሰው ህይወት ማለፉን ባገኘው መረጃ አንዳረጋገጠ መቁሞ መንግሥት የኃይል እርምጃ ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡
ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ወደ ግጭት እየቀየረ ያለው በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች የሚወሰድ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ መሆኑን የጠቀሰው ሰመጉ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ኃይማኖትና ብሄርን አላማ ያደረገ ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውን ጠቁሞ ሁሉም ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቋል፡፡
መንግስት፤ የፀጥታ ኃይሎችን ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ አስቁሞ ህዝብን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ የተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራና አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ እንዲሁም ህይወታቸው ላለፈ ዜጎች ቤተሰብና በግጭቱ ለተጎዱ ካሳ እንዲከፈል፣ ከህግ አግባብ ውጪ የታሰሩ እንዲፈቱ ሰመጉ በመግለጫው አጥብቆ ጠይቋል፡፡
ተቋማት አቶ ተስፋ ቡራዩ፣ አቶ አበበ ዋከኔ፣ አቶ ተስፋዬ ታከለ እና አቶ ቡልቲ ተሰማ የተባሉ አባላቱና አመራሮቹ እንደታሰሩበት ያስታወቀው የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፤ በአባላቱ ላይ በተለያየ መንገድ የሚረገው ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅና ወከባ እንዲቆም ጠይቋል፡፡ መንግስት ለሰብአዊ መብቶች  ጥበቃ የማድረግና ድጋፍ የመስጠት አለማቀፍ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ሰመጉ አሳስቧል፡፡


Read 4817 times