Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 05 March 2012 14:39

የቤት ውስጥ ጥቃት ምንድነው?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጾታዊ ጥቃት ማለት ማንኛውም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የስርዓተ ጾታ ያልተማከለ (የኃይል/የስልጣን) ግንኙነት በመመርኮዝ በሌላው ላይ የሚደርስ ጉዳት/ጥቃት ወይም ማስፈራራት ነው፡፡ በርካታ አዋቂ ሴቶችና ሴት ሕጻናት የጸታ መድልዎ በሚደረግባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ከመሆናቸው የተነሳ በአብዛኛው በእነሱ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ወይም የሃይል ተግባራትን ጾታን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ጾታዊ ጥቃት በተለይ በአዋቂ ሴቶችና ሴት ሕጻናት ላይ በጣም የከፋ ጉዳት፣ የመብት መጣስ የሚያደርሱና የተለያዩ እድሎችን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርግላቸዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃት ሲባል በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ቢሆኑም ወንዶችም ተጠቂ ሊሆኑባቸው የሚችሉባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡

የተለያዩ የሃይል ጥቃቶች/ተግባራት በአገራችን እንዲሁም በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በሴቶች ላይ ሲፈጸሙ ኖረዋል፡፡ ለነዚህም ጥቃቶች አንዳንድ ጊዜ መነሻ የሚሆኑት የህብረተሰቡ ባህልና ልማድ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የድርጊቱ ፈጻሚዎች አስተዳደግ፣ አመል እና የአእምሮ ጤንነት ሁኔታም ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጥቃቶችም በሴቶች ላይ ሲፈጸሙ አካላዊ ጉዳት፣ ማህበራዊ ጉዳት፣ ስነልቦናዊ ጉዳት፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና የሰብአዊ መብቶች መጣስን ያስከትላሉ፡፡ እነዚህ ጥቃቶች በአብዛኛው የሚፈጸመት የቤተሰብ አባላት፣ በጎረቤት/ጓደኛ፣ በቅርብ የማህበረሰብ አባላት ሲሆን፣ ልማዳዊ በሆኑና ባልሆኑ (የባህል፣ የሃይማኖት፣ የመንግስትና የግል) ተቋማት ሊፈጸም ይችላል፡፡ (Gender Based Violence Tools Manual, for Assessment, Program Design, Monitoring & Evaluation in conflict – affected settings, RHRC Consortium, 2004, USA)

የቤት ውስጥ ጥቃት ከሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የራሱ የሆነም ዓይነተኛ ባህሪያት አሉት፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቃት አድራሹ ለተጠቂው ያለው ቅርበት፤ በሁለቱ መካከል ያለው እምነት በጥቃቱ ምክንያት መሸርሸር፤ ያልተመጣጠነ የኃይል/የስልጣን ግንኙነት፤ የድርጊቱ ተደጋጋሚነት፤ ተጠቂው በጥቃት አድራሹ ላይ ያለው ጥገኝነት እና ጥቃት አድራሹ ተጠቂውን ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት ይጠቀሳሉ፡፡

የቤት ውስጥ ጥቃት በተለያየ መልኩ በጠባቡም ሆነ በሰፊው ሊተረጎም የሚችል ሲሆን እነዚህ የተለያዩ ትርጉሞች ስርዐተ ጾታን፤ ተጠቂያችን፤ ጥቃት አድራሾችንና የችግሩን ስፋት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ፡፡ የተጠቂዎችንና ጥቃት አድራሾችን ማንነት ተንተርሶ በሰፊው ሲተረጎም በቤተሰብ እና በቤተዘመድ አባላት መካከል (ህጻናትን ጨምሮ) የሚፈጸም ጥቃትን ሊያመለክት ይችላል፡፡ እንደገናም የቤት ውስጥ ጥቃት በሰፊው ሲተረጎም በባልና ሚስት ወይም እንደ ባል ሚስት አብረው በሚኖሩ ሰዎች መካከል፤ በቀድሞ ባለትዳሮች፤ የፍቅር ወይም የወሲብ ግንኙነት ባላቸው ወይም በነበራቸው ሰዎች፤ አብረው ልጅ በአፈሩ ሰዎች፤ የፍቅር ጥያቄ ባቀረቡ ሰዎችና እንዲሁም አንደኛው ወገን የፍቅር ግንኙነት አለ ብሎ በሚያስብበት ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጥቃት ሊሆን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል የቤት ውስጥ በጠባቡ እንዲተረጎም ስናደርግና ትርጓሜው የሚያካትተው በተጋቡ ወይም በቀድሞ ባለትዳሮች፤ ወይም አብረው ልጅ በአፈሩ ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጥቃት ላይ ሊወሰን ይችላል፡፡ በዚህ የአተረጓጎም የቤት ውስጥ ጥቃት የተለየ ግንኙነት (intimate relationship) ባላቸውና አብረው በሚኖሩ ወይም የኖሩ ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጥቃት ሲሆን ትርጉሙ ከዚህም ከጠበበ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጸም ጥቃትን (wife abuse/wife battering) ሊያመለክት ይችላል፡፡

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቤት ውስጥ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ሰዎች ውስጥ ሴቶች (አዋቂና ህጻናት ሴቶች) አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆን ወንዶች ደግሞ ከጥቃት አድራሾች ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በተወሰነ ሁኔታ ወንዶችም የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች ሊሆኑ ሲችሉ ሴቶችም ጥቃት አድራሽ ሊሆኑ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሆኖም ለብዙ ሴቶች ቤት ወይም ቤተሰብ ብለው የሚጠሩት ቦታ/መዋቅር ደህንነታቸውና መብቶቻቸው በእጅጉ የሚጣሱባቸው ቦታዎች ይሆናሉ፡፡ ይህም እውነታ የቤት ውስጥ ጥቃትን ከጾታዊ ጥቃት ውስጥ እንዲመደብ ያደርገዋል፡፡

የቤት ውስጥ ጥቃት በተለያየ መልኩ ሊፈፀም ሲችል አካላዊ፤ ስነልቦናዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ወሲባዊ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ አካላዊ ጥቃት ሥር የሚካተቱ ድርጊቶች እንደ ድብደባ፤ ጥፊ፤ ቡጢ፤ መምታት፤ እርግጫ፤ ቁንጥጫ፤ ማነቅ፤ መወርወር፤ መጐተት፤ መነቅነቅ፤ እጅ መጠምዘዝ፤ እጅ/እግር መስበር፤ በተለያዩ ነገሮች የሰውነት ክፍሎችን ማቃጠል፤ የሚጐዱ ፈሳሽን በሰውነት ማፍሰስ፤ በተለያዩ ስለታማ ነገሮች መውጋት ወይም የሰውነት ክፍሎችን መቁረጥ፤ በጦር መሳሪያ መተኮስ፤ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሌላው ሰው ላይ መወርወር የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሌላኛው ወገን ፈቃደኛ ያልሆነበትን ዓይነት ወሲባዊ ወይም ወሲብ ነክ ድርጊቶችን እንዲፈጽም ወይም እንዲመለከት ማስገደድን ይጨምራል፡፡ በአብዛኛው ወሲባዊ ጥቃት ከአካላዊ ጥቃት ጋር በጥምረት ሊደርስ የሚችል ሲሆን፤ በተወሰነ መልኩ ደግሞ ከአካል ጋር ሳይያያዝ ሊፈፀም ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ኢኮኖሚያዊ ጥቃት በተለይ ሴቶች ለተለያዩ የሃብት ምንጮች እንዲሁም የዕለት ተዕለት መሰረታዊ ቁሶችን እንዳያገኙ ማድረግን፤ ከቤት ውጪ ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ እንዳይሳተፉ ጫና ማሳደር፤ ምግብ መከልከል፤ የቤት ወጪ መከልከልን የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡

ስነልቦዊ  ጥቃትም በተለይ በንግግር ሌላውን መዝለፍን፤ ለብቻ ወይም በሰዎች መሃል (ወይም የቤተሰብ አባላት፤ ጓደኞች…ባሉበት) ሌላውን የሚያዋርድ ንግግር መናገርን፤ ማስፈራራት (ለግድያ፤ ለአካላዊ፤ ጥቃት፤ ለፍቺ፤ ተጨማሪ ሚስት ለማግባት ወዘተ)፤ ከቤተሰብና ጓደኛ እንዳይገናኙ መከልከል፤ እንቅስቃሴን መቆጣጠርን ይጨምራል፡፡በተለይ ሴቶች በትዳር አጋራቸው ወይም በተሳሳይ ሁኔታ ውስጥ አብረው በሚኖሩት ሰው ድብደባ እና ሌሎች አካላዊ ጥቃቶች ይፈፀምባቸዋል፡፡ ይህም ጥቃት በአብዛኛው በህብረተሰቡ ዘንድ በልማድ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ ለማስወገድ ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ የተለያዩ የመስኩ ባለሙያዎች በቤት ውስጥ ጥቃት ላይ ዓለምአቀፍ የሆኑ ጥናቶች ያካሄዱ ሲሆን ዴቪድ ሌቪንሰን የተባሉት ባለሙያ በFamily Violence in Cross – cultural Perspectives 1989 በተሰኘ መጽሐፋቸው ባሎች በሚስቶች ላይ ለሚያደርሱት አካላዊ ጥቃት እንደ በቂ ምክንያት በተለያዩ ማህበረሰቦች የተጠቀሱ ምክንያቶችን በቅደም ተከትል እንዲህ ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመሪያው ተቀባይነት ያገኘው ምክንያት ሚስቶች ታማኝ አይደሉም የሚል ጥርጣሬ መኖር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚስቶች “ግዴታቸውን” ባግባቡ አለመወጣት (ምግብ ማብሰል፤ ሌሎች የቤት ውስጥ ስራዎች፤ ወሲብ መፈፀም) የተቀመጠ ሲሆን በሶስተኛ ደረጃ በማናቸውም ሌላ ምክንያት ወይም ያለምንም ምክንያት መፈፀሙ እንደ በቂ ምክንያት እንደሚታይ ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ይህ ጥቃት በሚደርስባቸው ሰዎች (በተለይ ሴቶች) ላይ አካላዊ ተጽእኖ (ለምሳሌ የአካል መጉደል፤ ለተለያዩ የጤና እክሎች መጋለጥ) በተጠቂዎች ላይ ያደርሳል፡፡ ይህም በጤናቸው ወይም በህይወታቸው ላይ ችግር ይፈጥርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ስነልቦናዊ ተጽእኖዎች ማለትም ጥቃቱ የደረሰባት/የደረሰበት ሰው በሌላ ሰው ላይ እምነት ማጣትን፣ ፍርሃትን፤ ቁጡ መሆንን የሚያካትት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ አካባቢን መጠራጠርንና መፍራትን፣ እና የረዳት አልባነትን ስሜት ይፈጥራል፡፡ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣትን፣ የራስ ምታት ህመምን፣ የድካም ስሜትን፣ ማልቀስ፣ ድብርትን (depression)፣ እራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረግን ያጠቃልላል፡፡ እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ የልብ ህመምና ከባድ የጤና መታወክ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ማህበራዊ ተጽእኖዎች በተለይ ከሌሎች ሰዎች እና ማህበራዊ ግንኘነቶች መገለልን፤ በአንዳንድ ሁኔታም የሰው መጠቋቆሚያ መሆንን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ጥቃት ምክንያት ጥቃቱ የደረሰባቸው ሰዎች በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ የመሳተፍ አቅማቸው በጥቃቱ ምክንያት ሊቀንስ/ሊጠፋ፤ እንዲሁም በጥቃቱ በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት ራሳቸውን ለማስተዳደር ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡ እነዚህ ተጽእኖዎች በአንድ ጥቃት ምክንያት በተደራራቢነት ሊደርሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ማህበሩ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ሁሉም ከጐኑ እንዲቆሙ ይጠይቃል፡፡

ጥቃትን ለማስቆም እንረባረብ!

ሳምንት ይቀጥላል!

=============================================================
ጥቂት ስለ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እ.ኤ.አ በ1987 ዓ.ም ተቋቁሞ ሴቶች የአሏቸው መብቶች በህጐች ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ፤ የሥልጠናና የትምህርት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሴቶችና ህብረተሰቡ እንዲሁም የሕግ አስፈፃሚ አካላት በሕግ የታወቁ መብቶችን እንዲያውቋቸው ለማድረግ፤ ሴቶች መብቶቻቸው ተጥሰውባቸው የህግ መፍትሔ በሚፈልጉበት ጊዜ ነጻ የህግ ምክር አገልግሎት ለመስጠት ይሠራል፡፡ በዚህ መልኩም ከ85,000 በላይ የሚሆኑ ሴቶችን አገልግሏል፡፡ ከ2,000,000 (ሁለት ሚሊዮን) በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች (ሕብረተሰቡ፤ የሕግ አስፈፃሚ አካላት፤ ሴቶች፤ ወዘተ) ደግሞ በሴቶች መብቶችና በሕጐቻችን ዙሪያ እንደሥልጠና፤ ወርክሾፕ፤ የሚዲያ ፕሮግራሞች በመሳሰሉ መንገዶች በተካሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሳተፍ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡

 

 

Read 5279 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:45