Monday, 29 August 2016 10:40

ንጉሱን ፍለጋ

Written by  በተክለ ኪዳን አምባዬ
Rate this item
(7 votes)

    በሃያ ዓመት የጋዜጠኝነት ህይወታቸው እንደዚህ ዜና አስደንግጧቸው አያውቅም፡፡ ከዓመታት በፊት ሀገር ምድሩ አልቅሶ የቀበራቸው የሀገሪቱ ንጉሥ በህይወት ስለመኖራቸው የሚናፈሰው ወሬ በራቸውን አንኳኩቶ ቢሮ ድረስ የገባው ቀጣዩን የጋዜጣቸውን ዕትም የተመለከቱ ጉዳዮችን ከጋዜጠኞቻቸው ጋር ለመነጋገር ስብሰባ በተቀመጡበት ወቅት ነው፡፡ በከተማው ውስጥ እየተወራ ያለውን ወሬ ያልሰሙ በመምሰል በስብሰባው ላይ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሲናገሩ አንዷ ሪፖርተር በመሀል እጇን አውጥታ፤ ‹የንጉሱስ ነገር?› አለች፡፡
ጉዳዩ ያልገባቸው ለመምሰል ጥረት ቢያደርጉም መላ የከተማው ህዝብ እየተቀባበለ ስለሚወራው የንጉሱ በህይወት መኖር ጉዳይ ‹እንደ ጋዜጠኛ አንድ ነገር ማድረግ አለብን› አሉ፤ ሁሉም ጋዜጠኞች እየተቀባበሉ፡፡ ሁኔታው ዋና አዘጋጁን ግራ አጋባቸው፡፡
‹የዛሬ 10 ዓመት ሀገሪቱን ለረዥም ዓመታት የመሩት ንጉስ ታመው መሞታቸውና ህዝባዊ የሀዘን ሥነ ሥርዓት ተዘጋጅቶ፣ የተለያዩ ሀገር መሪዎች ተገኝተው መቀበራቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱ በዚህ ስብሰባ ላይ ያላችሁ ጋዜጠኞች ሁሉ ለዚህ ጉዳይ ምስክሮች ናችሁ። አንዳንዶቻችሁ ገና ከተቀጠራችው አንድ ሁለት ዓመት የሆናችሁና ቀደም ሲል ገና በዩኒቨርሲቲ ትምህርታችሁን እየተከታተላችሁ የነበራችሁ ቢሆንም ሌሎቻችሁ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኛችሁና ቀደም ሲል ጋዜጣችን ባዘጋጀው የልዩ ዕትም ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ሪፖርቶችን ያዘጋጃችሁ ናችሁ፡፡ እና ይሄ ሁሉ ነገር ላይ የተሳተፋችሁና ቀብሩ ላይ የተገኛችሁ ሆናችሁ ሳለ፣ ዛሬ የከተማው ህዝብ የሚያወራውን ወሬ ይዘን ጋዜጣ ላይ እንፃፍ ማለታችሁ አልገባኝም› አሉ በንዴት ጦፈው፡፡
መጀመሪያ ላይ እጇን ያወጣችው ሪፖርተር ሃሳብ አለኝ አለች፡፡ እውነቱን ለመናገር ዋና አዘጋጁ ዕድሉን ሊሰጧት አልፈለጉም ነበር፡፡ ግን በጋዜጣው የኤዲቶሪያል ስብሰባ ህግ መሰረት፣ አንድ ጉዳይ ተነስቶ ከተከራከሩበት በኋላ የማይሆን ከሆነ ብቻ ነው በክርክሩ የሀሳብ ብልጫ ውድቅ የሚሆነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሪፖርተሯ ዕድሉን መከልከል የማይቻል ነው፡፡ ስለዚህ እንድትናገር ፈቀዱላት፡፡ ሪፖርተሯ ከዚህ በፊት ዋና አዘጋጁ ያላሰቡትንና እርግጠኛም የነበሩበትን ሀሳብ ብትንትኑን አወጣችው፡፡ ‹እንደ ጋዜጠኛ ንጉሱ ሞቱ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ሰዎች ሲያለቅሱም በቴሌቪዥን ቤቴ ሆኜ ተመልክቻለሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ ስለ ንጉሡ ሞት የማላውቃቸውና እንደ ጋዜጠኛ ብጠየቅ አስረግጬ ልናገራቸው የማልችላቸው ነገሮች አሉ› አለች፡፡
‹ምንድናቸው እነሱ?› አሉ በንግግሯ ያልተሳቡ ለመምሰል እየጣሩ፡፡
‹ለምሳሌ ንጉሱ ሞቱ ተብሎ የዛሬ ስምንት ዓመት ሲለቀስ እኔ ጋዜጠኛ አልነበርኩም፡፡ ጋዜጠኛ ብሆን ግን መጠየቅና ማጣራት ያሉብኝን ነገሮች ሳላጣራ ምንም አይነት ዘገባ አልዘግብም ነበር› በማለት በወቅቱ መረጋገጥ የነበረባቸውን ነገሮች አንድ ሁለት ብላ በዝርዝር ተናገረች። ሁሉም ግራ ተጋባ፡፡ በከተማው እየተወራ ባለው ወሬ ላይ እምነት ያላት ይመስላል፡፡ ‹አንድ ጋዜጠኛ በአንድ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ ማሳደሩ ትክክለኛና እውነተኛ ዘገባ ለህዝቡ ለማቅረብ እንደሚያግዘው ግልፅ ነው፡፡ እንኳን ፍንጭ ባለበት ጊዜ ይቅርና ፍንጭ በሌለበት ጊዜ እንኳ አንድ ጋዜጠኛ ከመሬት ተነስቶ ሁኔታዎችን በመመርመርና በማጣራት ወደ እውነታው የሚደርስበት መንገድ አለ። ከዚህ አንፃር ንጉሱ ሞቱ በተባለበት ጊዜ መጠየቅ ያለባቸውና ጋዜጠኛው አጣርቶ ያላረጋገጣቸው ነገሮች ስላለ ነው አሁን ይህ ወሬ ከዓመታት በኋላ የመጣው። በመሆኑም ወሬው እውነት ይሁንም አይሁን የንጉሱን የአሟሟት ሁኔታ እንደገና በማጣራት እውነታውን ለህዝቡ ማቅረብ ያለብን ይመስለኛል፡፡› አለች ፡፡
ዋና አዘጋጁ በሁኔታው ላይ መጀመሪያ አስተያየት ለመስጠት አልፈለጉም፡፡ ሌሎቹ ጋዜጠኞች የሚሉትን ለመስማት ተራ በተራ ዕድል ሰጧቸው፡፡ የተማከሩ ይመስል ሁሉም በየተራ የሪፖርተሯን ሃሳብ በማጠናቀር ተናገሩ፡፡
ዋና አዘጋጁ የሪፖርተሯን ሀሳብ አሳማኝ በመሆኑ ተቀበሉትና አንድ የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን በማቋቋም ሪፖርተሯ እንድትመራውና ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላትን በግንባር በመሄድ እንድታነጋግር ፈቃድ ሰጡ፡፡
ፍሬህይወት ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት /Journalism and communication/ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪዋን ይዛ ሥራ የጀመረችው በዚህ ጋዜጣ ላይ ነው፡፡ በትምህርቷ ውስጥ የተማረቻቸውን መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ትምህርቶች በመያዝ የምትሰራቸው ዘገባዎች፤ትክክለኛ ሚዛናዊና ግልፅ በመሆናቸው በርካታ አንባቢያን በስሟ ብቻ ሳይሆን በፅሑፎቿ ይለዩታል፡፡ ሙያዋን ስለምትወደው በድፍረትና በልበ ሙሉነት ነው ማናቸውንም ዘገባዎች የምትሰራው፡፡ ይህንን የሀገሪቱ ንጉስ ሞት ተከትሎ እየተወራ ያለውን ወሬ ከሥረ መሰረቱ አጣርቶ የማቅረብ ሃላፊነት ሲሰጣትም በደስታ ነው ተቀብላ ከስብሰባ ቢሮው የወጣችው ፡፡
ንጉሱ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ‹ሞቱ› ተብሎ ከተነገረ በኋላም የተለያዩ ወሬዎች ይወሩ ነበር፡፡ ሞቱ ከተባለ በኋላም ለህዝብ ግልፅ ያልነበሩና ያልተብራሩ ሁኔታዎች በመኖራቸው ፍሬህይወት ሁኔታውን ማጣራት የፈለገችው ከሥረ መሠረቱ ነው። በመሆኑም ጥያቄዎቿን ይመለከታቸዋል ወዳለቻቸው ተቋማትና የሥራ ሃላፊዎች ይዛ ሄደች፡፡
በመጀመሪያ የሄደችው የንጉሱን የሞት ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጀው የሀገሪቱ ብሔራዊ የሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ ቀጠሮ አስይዛ ሥራ አስኪያጁ ዘንድ ገባች፡፡ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ በከተማው ውስጥ እየተወራ ያለውን ወሬ የሰማው ቢሆንም ‹አሉባልታ› ብሎ አልፎት ስለነበር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ብዙ ፍላጎት አልነበረውም፡፡ እንደውም ከጉዳዩ ቀላልነት አንፃር ምክትሉን እንድታነጋግር ሁሉ ጠቁሟት ነበር፡፡ ግን የግድ ከእርሱ ጋር መነጋገር እንደምትፈልግ አሳምናው በቢሮው ተገኘች፡፡
‹የንጉሱን የዜና እረፍት በጣቢያችሁ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገራችሁት እናንተ ናችሁ አይደል?› አለች ለመንደርደር፡፡ ሥራ አስኪያጁ በተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ወደ ኋላ ለጠጥ ብሎ ‹አዎ› አለ። ‹የንጉሱን ዜና እረፍት በዕለቱ ስትናገሩ ስለመሞታቸው እርግጠኞች ነበራችሁ?› አለችው፤ አልገባውም፡፡ ለአፍታ ዝም ካለ በኋላ ‹አዎ› አለ፡፡
‹በምን እርግጠኛ ሆናችሁ?› አለችው፤ጠረጴዛው ላይ የተቀመጠውን የንጉሱን ምስል የያዘ ፖስት ካርድ እየነካካች፡፡
‹መግለጫው የመጣው እኮ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው›
‹መግለጫው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት መምጣቱ እንጂ እናንተ በራሳችሁ መንገድ እውነተኛነቱን ሳታረጋግጡ ነው ያስተላለፋችሁት ማለት ነው፡፡›
ፍሬህይወት ይዛ የመጣችው ጉዳይ ‹አሉባልታ› ብቻ እንዳልሆነ ሥራ አስኪያጁ  አሁን እየተገለፀለት ሳይመጣ አልቀረም፡፡ ‹ምን ለማለት ፈልገሽ ነው? ሀገሪቱን የሚያስተዳድረውና በህዝብ የተመረጠ መንግስት እኮ ነው መግለጫውን የላከው፡፡ መንግስት ይዋሻል እያልሽ ነው?›
‹ለምን አይዋሽም? በዓለም ላይ የሚዋሹ መንግስታትን ማየት አዲስ ነገር አይመስለኝም፡፡ የዛሬው ቀጠሮአችን ዓላማ ግን በመንግስት ማንነት ዙሪያ ለመነጋገር ስላልሆነ ይህንን ብንተወው ጥሩ ነው፡፡ የኔ ጥያቄ መንግስት መግለጫውን ሲልክላችሁ እንደ አንድ የሚዲያ ተቋም  በመግለጫው ላይ የተጠቀሰው ነገር እውነት ስለመሆኑ ማጣራት አልነበረባችሁም ወይ?›
‹ምን እንድናጣራ ነው የምትፈልጊው? ንጉሱ ታመው ነበር ብሏል መንግስት፤ ከዛ ሞቱ አለ፡፡ በቃ፤ ከዚህ በላይ ምን እንድናጣራ ነው የሚፈለገው?›
‹‹ለምሳሌ ታመው እንደነበር በዕለቱ ለህዝብ ያስተላለፋችሁት ዜና  ላይ ተገልጿል፡፡ ህመማቸው ምን እንደሆነ ግን ለህዝቡ አልገለፃችሁም፡፡››
‹ህመማቸው ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ማወቅም አያስፈልገኝም፡፡ ዋናው ነገር የንጉሱ መሞትን ለህዝቡ እንድናስተላልፍ መንግስት መግለጫውን አዘጋጅቶ ልኮልናል፡፡ ከዚህ በፊት እንደምናደርገው ይህን  ሳንጨምር ሳንቀንስ አስተላልፈናል፡፡ አሉባልታ እየያዛችሁ እየመጣችሁ በሰላም ያረፉትን የንጉሳችንን ነፍስ አትረብሹ፤ ጨርሻለሁ› አለ ዋና ሥራ አስኪያጁ ፊቱን እንዳኮሳተረ፡፡
ፍሬህይወት አመስግና ወጣች፡፡ ከሬዲዮ ጣቢያ እንደወጣች በቀጥታ ያመራችው  ንጉሱ ሞቱ በተባለ ማግስት አስከሬኑን ይዘው ከውጪ ሀገር ካመጡት ከፖሊስ፣ከምድር ጦርና ብሔራዊ ደህንነት ከተውጣጡ ኮሚቴ አባላት ሰብሳቢ ጋር ነበር፡፡ ሰብሳቢው ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ የሚዲያ ሽፋን አግኝተው ስለማያውቁ፣ ይህንን አጋጣሚ እንደ ልዩ ነገር ነው የተመለከቱት። ፍሬህይወት በሰፊው ቢሮአቸው ገብታ ከተቀመጠች በኋላ ‹ሻለቃ የዛን እለት አስከሬን ለማምጣት የሄዳችሁት ወደ የት ሀገር ነው?› አለቻቸው በሰፊው ቢሮአቸው ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን የንጉሱን ፎቶ እየተመለከተች፤ ሻለቃ ግር አላቸው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ማንም ጠይቋቸው የማያውቀው ጥያቄ አሁን መጣ፡፡ ምን ብለው ይመልሱ። ‹ወደ የት ሀገር እንደበረርን አላውቅም፤ ግን ማታ ላይ አውሮፕላን ስለተዘጋጀ ቶሎ ግቡ ተብለን መሄዳችንን አስታውሳለሁ፡፡ ወደ የት ሀገር እንደበረርን ግን አላውቅም›
‹የንጉሱን አስከሬን ለማምጣት ስትሄዱ የአስከሬን ሳጥን ይዛችሁ ነበር?›
‹አልያዝንም፤ እዛው ተዘጋጅቶ ይጠብቃችኋል ስለተባለ ባዶ እጃችንን ነው የሄድነው›
‹እዛ እንደ ደረሳችሁ ምን አደረጋችሁ›?›
‹በቃ ትንሽ አለቃቀስንና አስከሬኑን ቶሎ ተሸክመን፣ ወደ አውሮፕላኑ አስገብተን መጣን›
‹የአስከሬን ሳጥኑን ከፍታችሁ የንጉሱን አስከሬን ተመልክታችኋል?›
‹እኔ እንኳን ንጉሱ ሞተው ይቅርና በህይወት እያሉም ለአንድም ቀን ቀና ብዬ አይቻቸው አላውቅም›
‹ከመካከላችሁስ አስከሬናቸውን ያየ ሰው ነበር?›
‹እኔ አላውቅም፤ ግን ምን ማየት ያስፈልጋል? የሞቱት እኮ ንጉሳችን ናቸው፤ በሀዘን እንባ እየተራጨ ወዳለውና አስከሬናቸውን ለሚጠብቀው ህዝብ ቶሎ ማድረስ ነበር የሁላችንም ሀሳብ፤ በዚህ መሠረት ያንን አድርገናል›
‹የአስከሬን ሳጥኑ ውስጥ የንጉሱ አስከሬን ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ይቻላል?› ሻለቃ ድንገት ቱግ አሉ፡፡ በንጉሱ ሞት ሳቢያ ደጋግመው በቴሌቪዥን የመታየትና መጠነኛ ታዋቂነት ያገኙበትን አጋጣሚ ጥላሸት ለመቀባት የመጣች መልዕክተኛ አድርገው ሳሏት፡፡ ‹ምን እያልሽ ነው? ይህንን አሉባልታሽን ይዘሽ ከቢሮዬ ውጪልኝ› አሉ በቁጣ ነደው፡፡ ጊዜ ሳታጠፋ መቅረፀ ድምጽዋን ይዛ ወጣች፡፡
ጉዞ ወደ ቤተ ክህነት፡፡
ቤተ ክህነት ንጉሱ ሞቱ ከተባለበት ዕለት አንስቶ ግብዓተ መሬታቸው እስከ ተከናወነበት ቀን ድረስ በቤተ-መንግስት ፀሎተ ፍትሀትና ቃለ ምዕዳን ስታደርግ ነበር። በወቅቱ  ፓትርያርኩ ታመው ስለነበር በብፅእነታቸው ታዘው ይህንን የፀሎተ ፍትሐት ከሌሎች ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሲደርጉ የነበሩት የባሌና ጊኒር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ብፁእ አቡነ ዜና ማርቆስ ነበሩ፡፡ ፍሬህይወት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቢሮአቸው ከተገኘች በኋላ መስቀላቸውን ተሳልማ ጥያቄዋን ማቅረብ ጀመረች፡፡ ‹ብፁእ አባታችን፤ ለንጉሱ የተደረገው ፀሎተ ፍትሀት ለስንት ቀን ነው?›
‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አህዱ አምላክ አሜን! እንግዲህ የአባታችንና የመካሪያችን ንጉሰ ነገስት ግርማዊ ዜና እረፍት ከተሰማበት ዕለት አንስቶ በፀሎት ላይ ነበርን፡፡ ፍትሀቱም እስከ ቀብራቸው ዕለት ዘልቋል፡፡›
‹ብፁእ አባታችን፤ በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት አንድ ሰው በህይወት እያለ ፀሎተ ፍትሀት ይደረግለታል እንዴ?›
‹እንዴት ሆኖ?›
‹ታዲያ እናንተ ለአስራ አምስት ቀናት ያህል ፀሎተ ፍትሐት ታደርጉ የነበረው ለማነው?›
‹አልገባኝም ልጄ፤ ምን እየጠየቅሽ ነው? ፀሎተ ፍትሐቱማ ያው ለንጉሱ ነበር የምናደርገው፡፡ ለዚያውም የክርስትና ስማቸው ሀይለገብርኤል መባል ሲገባው ተክለ ኪዳን እያልን ነበር የምንጠራው፡፡ በኋላ ግን ከቤተሰቦቻቸው መሀል ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ከትውልድ መንደራቸው ከሰሜን መጥተው እንድናስተካክልና ፀሎተ ፍትሐቱ እንዲቀጥል ሆኖአል፡፡ ስለዚህ ፀሎተ ፍትሐቱን ስናደርግ የነበረው ለንጉሱ ነው፡፡ አስከሬናቸውንም ከበን ስንፀልይ ነው የከረምነው›
‹አባቴ በጣም ይቅርታ ፤ለመሆኑ ከባችሁ ፀሎተ ፍትሐት ስታደርጉለት የነበረው አስከሬን ሳጥን ውስጥ የንጉሱ አካል እንደነበረ አረጋግጣችሁ ነበር?›
‹እመ ብርሃን ድረሽ! ምንድነው ነገሩ? ›
‹አሁንም በድጋሚ ይቅርታ ለመጠየቅ እወዳለሁ አባቴ፤ በቤተክርስቲያን ህግ መሠረት ፀሎተ ፍትሐት የሚደረገው ከግንዛት በፊት ነው በኋላ?›
‹ከግንዛት በኋላ ነው እንጂ፤›
‹ንጉሱን የገነዘው ማነው?›
‹እመቤቴ ድረሽ! እኔ የማውቀው ነገር የለም፤ ንጉሱ አርፈዋል ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን ከተነገረ በኋላ ለፀሎተ ፍትሐቱ ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ ሂዱና ፀሎተ ፍትሐቱን አድርጉ፤ ብለው ብፅእ አባታችን ስላዘዙኝ ነው የሄድኩት እንጂ ስለ ግንዛቱ የማውቅ ነገር የለም፡፡ እንደሰማሁት የንጉሱ አስከሬን የመጣው ከውጪ ሀገር ነው፤ግንዛቱ እዛው ስለተደረገ በቀጥታ እኛ የተጠራነው ለፀሎተ ፍትሐቱ  ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ የንጉሱ አስከሬን ምን ሆነ? ለሌላ ሰው ኖሯል እንዴ ያን ያህል ቀን የእግዚአብሔርን ደጅ ለማስከፈት ስንደክም የከረምነው?›
ብፁእ አቡነ ዜና ማርቆስ በከተማው ውስጥ እየተወራ ስላለው ወሬ ጆሮአቸውን የሰጡ አይመስሉም። በመሆኑም ፍሬህይወት ከዚህ በላይ ከእሳቸው ጋር መቆየት ስላልስፈለጋት አመስግና በድጋሚ መስቀላቸውን ተሳልማ ወጣች፡፡
ፍሬህይወት ከቤተ ክህነት ቀጥሎ ያመራችው የንጉሱን የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማስፈፀም ከመንግስት ጋር ውል ገብቶ ሂደቱን ወደ አስፈፀመው ‹ትንሳኤ የቀብር አስፈፃሚ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር› ፅ/ቤት ነበር፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን በከተማው ስለ ንጉሱ እየተወራ ያለውን ነገር የሰሙ ቢሆንም የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የሳቸው ድርጅት ስለማስፈፀሙ በወቅቱ አንድም መገናኛ ብዙሃን ስላልዘገበ ይህንን አጋጣሚ ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ እንደ መልካም አጋጣሚ ሳይቆጥሩት አልቀረም፡፡ በየጊዜው በሀዘን የተሞሉና በእንባ በሚታጠቡ ሰዎች የአስከሬን ሳጥን፤ አበባና መኪና ፍለጋ የሚጨናነቀው ቢሮአቸው የዛን ዕለት ብቻ በማያለቅስና የሃዘን ፊት በሌለው ሰው መጎብኘቱ አስደስቷቸዋል፡፡
‹አቶ ሳምሶን የንጉሱን የቀብር ሥነ ሥርዓት ያስፈፀመው የእርስዎ ድርጅት ነውና፤ እስኪ እንዴት ይህንን ዕድል ልታገኙ ቻላችሁ በሚለው እንጀምር?›
‹እንግዲህ› አሉ አቶ ሳምሶን የድርጅታቸውን አመሰራረትና ቀብር በማስፈፀም በኩል ያለውን ልምድ ከሥረ መሠረቱ ለማስረዳት እየተንደረደሩ፡፡ ‹እንግዲህ …› ብለው ሲቀጥሉ ፍሬህይወት ጥቂት ታግሳ ቆይታ፣ ‹ስለዚህ መንግስት ነው ይህንን ስራ እንድትሰሩ የመረጣችሁ ማለት ነው?› አለቻቸው፡፡ አቶ ሳምሶን በመንግስት አመኔታ ተጥሎባቸው መመረጣቸውን ጋዜጠኛዋ ማረጋገጣ አስደስቷቸው፣ ‹ትክክል ነሽ፤ የኛ ድርጅት ደንበኞች ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፤ መንግስትም ጭምር ነው› አሉ በኩራት፡፡
‹ግን መንግስት ከዚህ ሁሉ ቀብር አስፈፃሚ ድርጅት መሀል የእርስዎን ድርጅት እንዴት መረጠ?›
‹መልካም ስማችን ነዋ! ስማችን፤ስራችን፤አፈፃፀማችን ሁሉ ይህንን ትልቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንድናስፈፅም አብቅቶናል፡፡ መንግስትም እኮ ቢሆን ሰው ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ሁሉን ነገር ይሰማል፤ ያያል፡፡ ስለዚህ ስራችንን ያይ ስለነበር መርጦናል›
‹ከቀብሩ በፊት የነበረው ቅድመ ዝግጅት ምን ይመስል ነበር?›
‹በጣም ጥሩ፤ ያው እንደማንኛው ጊዜ እንደምናደርገው ሳይሆን እኔ ራሴ ነኝ ሥራውን በዋናነት ስመራ የነበርኩት፡፡ ንጉሱ እኮ ባለውለታዬ ናቸው፤ ይህንን ያለሁበትን ኮንዶሚኒየም እኮ ያሰጡኝ እሳቸው ናቸው፡፡ እና በመጀመሪያ ውሉን ከተፈራረምኩ በኋላ የቀብር ቦታቸው የት ይሁን በሚለው ላይ በእርግጥ በመንግስት ሰዎች መሀከል ስምምነት አልነበረም፡፡ ይህም የኛን የመቃብር ቦታ ቁፋሮ ስራ በአንድ ሳምንት አዘግይቶብናል፡፡
‹ማለት?››
‹ማለቴ አንዳንድ ሰዎች መቀበር ያለባቸው እዛው የትውልድ ሀገራቸው መሆን አለበት ሲሉ ሌሎች ግን እዚሁ ነው መሆን ያለበት ይሉ ነበር መሰለኝ፡፡ በዚህ የተነሳ ጥቂት ቀናት ከተጉላላን በኋላ ቤተክህነት እንድትፈቅድ ተደርጎ ጉድጓዳቸውን ቆፈርን፡፡›
‹ጉድጓዱን ግን በምን ልክ አውቃችሁ ቆፈራችሁ?›
‹አስከሬናቸውን ሄደን ለካና፡፡ እንደውም እኔ ራሴ ነኝ ቤተመንግስት ድረስ ገብቼ አስከሬናቸውን ለክቼ የመጣሁት›
‹አስከሬናቸውን እርስዎ አይተውታል ማለት ነው?›
‹አረ በፍፁም! የአስከሬን ሳጥናቸውን ማለቴ ነው። አስከሬናቸውማ ያው ከውጪ ሀገር አይደል  ተገንዞ የመጣው? አይ ሳጥን! በህይወቴ የእሳቸውን አይነት ሳጥን አይቼ አላውቅም፡፡ መቼም ያንን የመሰለ ሳጥን እንደ ተራ ሳጥን አፈር ውስጥ ከተትነው፤ ምን ያደርጋል? ለነገሩ እንኳን ሳጥኑ እኛን የመሰሉ ባለ ራዕይ ንጉስ አፈር ውስጥ ገብተው የለ?› አሉ አይናቸው እንባ እያቀረረ፡፡
‹ግን ግብዓተ መሬታቸው ሲፈፀም ወደ ጉድጓዱ የከተታችሁት አስከሬናቸውን ነው ወይስ ሳጥኑን ነው?›
‹አልገባኝም›
‹ማለቴ ሳጥኑ ውስጥ አስከሬናቸው ነበረ ወይ ማለቴ ነው›
‹እኔ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የንጉሱን የቀብር ሥነ ሥርዓት በአግባቡ ፈፅመን ክፍያችንን ከመንግስት ካዝና ወስደናል፡፡ ለዚሁም መንግስት የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ውጪ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ጥያቄሽ ራሱ ግራ ነው፡፡ እኔ በ35 ዓመታት የቀብር ማስፈፀም ልምዴ ስቀብር የኖርኩት አስከሬን እንጂ ሳጥን  አይደለም። ቤተሰብም ገንዘብ የሚከፍለን የሞተ ዘመዱን አስከሬን በአግባቡ እንድንቀብርለት እንጂ ሳጥኑን እንድንቀብርለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ሳጥን የሌለው አስከሬን በኬሻ ጠቅልለን ቀብሬ ባውቅም አስከሬን የሌለው ሳጥን ግን ቀብሬ አላውቅም፡፡›
‹ያ የንጉሱ አስከሬን አለበት የተባለው ሳጥን ውስጥ ግን የንጉሱ አካል ስለመኖሩ እርግጠኛ ነዎት?›
‹በይ ቢሮዬን ለቀሽ ውጪ፤ ከመንግስት ጋር እኔን በማጋጨት እንዲያስረኝ ነው እንዴ ለጥቆማ የመጣሽው? ነው ወይስ ደንበኞቼ እንዲሸሹኝ ተልከሽ ነው?› አቶ ሳምሶን ትዕግስታቸው ያለቀ ይመስል ከወዲያ ወዲህ እየተወራጩ ማውራት ሲጀምሩ ፍሬህይወት  ተንደርድራ ወጣች፡፡
ከዚህ በኋላ አንድ የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ ወደ  ህክምና ባለሙያዎች ማህበር በመሄድ ፕሬዚዳንቱን ለማነጋገር ወሰነች፡፡ የማህበሩ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር እንደውም የንጉሱ የግል ሀኪም ከመሆናቸው አንፃር ትንሽ ፍንጭ ቢገኝ በማለት ቢሮአቸው ተገኘች፡፡ ዶክተሩ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ ሊገቡ በመሆኑ ፍሬህይወት ቃለ ምልልሷን የጀመረችው በፍጥነት ነበር፡፡ ‹ዶክተር፤ ንጉሱ በህመም ሳቢያ መሞታቸው በወቅቱ ተገልፆ ነበርና ህመማቸው ምንድነው?›
‹እንግዲህ አሁን ላይ ህመማቸው እንዲህ ነበር ብዬ ለመናገር ቢከብደኝም በአብዛኛውን ከስራ ውጥረት ጋር የተያያዘ የአእምሮ እረፍት ማጣት ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ›
‹እርስዎ በሚያክሟቸው ጊዜ የዚህ አይነት ችግር እንዳለባቸውና ማስተካከል እንዳለባቸው ነግረዋቸው ያውቃሉ?›
‹አዎ፤ እነግራቸዋለሁ፤ሁኔታውን አስተካክለውም ከጭንቀት ነፃ መሆናቸውን ነው የማውቀው›
‹ታዲያ ለሞት ያበቃቸው ህመም  ምንድነው?›
‹እንግዲህ በመጨረሻ ላይ ህይወታቸው ከማለፉ በፊት እኔ ስላላከምኳቸው ህመማቸው ይሄ ነበር ለማለት እቸገራለሁ›
‹አንድ ሰው በህክምና ሙያ ሞተ የሚባለው እንዴት ነው?›
‹እንግዲህ የተለያዩ የሞት ደረጃዎች ቢኖሩም የልብ ለተወሰነ ደቂቃ ሥራ ማቆም በዋናነት ሞትን ያስከትላል፡፡ ያን ጊዜ ያ ሰው ሞተ እንላለን፡፡›
‹ከዚህ አንፃር ንጉሱ ሞቱ ሲባል በዚህ ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው በህክምና ተረጋግጧል?›
‹እኔ ንጉሱ ሞቱ ሲባል በቦታው አልነበርኩም ብያለሁ፡፡ የሞቱትም ከሀገር ውጪ ነው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ በሥፍራው የነበሩ ሀኪሞች ናቸው ይህንን ሊያረጋግጡ የሚችሉት ብዬ ነው የማስበው፡፡›
‹የንጉሱ አስከሬን ወደ ሀገር ቤት ከመጣ በኋላ በህክምና ሙያ በትክክል መሞታቸውን ለማረጋገጥ ሞክራችኋል?›
‹እኛ አልሞከርንም፤ ምክንያቱም ውጪ ሀገር ይሄ ሁኔታ ተረጋግጧል ብለውን ስለነበር ድጋሚ ለማረጋገጥ አላስፈለገንም፡፡›
‹የንጉሱ የህክምና ማስረጃ ዶክመንቶችንስ ተመልክተውታል?›
‹እኔም ጠይቄ ይላካል ተብሎ ነበር፤ ግን የሰጠኝ የለም ›
‹የንጉሱ የሞት ሰርተፍኬትስ በምን የተነሳ ሞቱ ይላል?›
‹እየነገርኩሽ እኮ ነው፤ ሁሉም ዶክመንቶች ገና አልተላኩም፤ አልደረሰንም፡፡›
‹ንጉሱ ግን ህክምናቸውን ሲከታተሉ የነበረው የት ሀገር ነው?›
‹ውጪ ሀገር መሆኑን እንጂ የት ሀገር እንደሆነ እኔ አላውቅም›
‹ሆስፒታሉስ?›
‹ሆስፒታል ውስጥ ህክምናቸውን ሲከታተል እንደነበር እንጂ የት ሆስፒታል እንደሆነ መረጃው የለኝም›
ፍሬህይወት ሁሉምን ወገኖች ካነጋገረች በኋላ  የተለያዩ የከተማ ነዋሪዎችን ስለ ንጉሱ አሟሟት የሚያውቁትን እንዲነግሯት እየተዘዋወረች ጠየቀች፡፡ ሁሉም የከተማው አስተያየት ሰጪዎች ንጉሱ ታመው ስለመሞታቸው በሬዲዮ ሲነገር መስማታቸውንና የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መከታተላቸውን እንጂ በምን ህመም እንደሞቱና በትክክል ስለመሞታቸው እርግጠኛ ሆነው መናገር እንደማይችሉ ነገሯት፡፡
ዘገባዋን አጠናቅራ ወደ ህትመት ጋዜጣው ከመላኩ በፊት ግን ዋና አዘጋጁ አንድ ሀሳብ አቀረቡ፡፡ ንጉሱ በአሁኑ ወቅት በካሪቢያን ደሴት ላይ ባለ አንድ ገዳም ውስጥ እንደሚኖሩ እየተወራ በመሆኑ ፍሬህይወት ዘገባውን ለህዝብ ከማቅረቧ በፊት ወደ ተባለው ደሴት በመሄድ ሁኔታውን ተመልክታ ለአንባቢ የአይን ምስክርነቷን እንድትሰጥ አሳሰብዋት፡፡
ፍሬህይወት ዘገባውን የተሟላ የሚያደርገው ሁኔታውን ያውቃሉ የተባሉ ሰዎችን ሃሳብ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ተፈፅሞበታል የተባለውን ቦታ ወይም ግለሰብ በማግኘት ጭምር በመሆኑ ንጉሱን ፍለጋ ወደተባለችው የካሪቢያን ደሴት ከአንድ ቀን በኋላ በረረች… 

Read 4486 times