Print this page
Monday, 29 August 2016 10:23

ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከአንድ የተረት ስብስብ መጽሀፍ የተገኘ ተረት የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በጣም ቁጠኛ የሆነ ልጅ ነበር፡፡ አባቱ የልጁን አመል ለመግራት አንድ ካርቶን ሙሉ ሚስማር ሰጠውና፤ “ቁጠኝነት ሲሰማህ አንድ አንድ ሚስማር እያወጣህ ከጣውላ በተሰራው ግድግዳ ላይ በመዶሻ ምታ” አለው፡፡
ልጁ የአባቱን ትዕዛዝ አክብሮ በመጀመሪው ቀን ሃያ አምስት ሚሥማር ግድግዳው ላይ ሲመታ ዋለ፡፡ ሃያ አምስት ጊዜ ተናዶ ነበር ማለት ነው፡፡ በሚቀጥለው ቀናት ግን ቁጣው እየቀነሰ ሄደ፡፡ ግድግዳ ላይ የሚመታቸው ሚስማሮች ቁጥር ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፡፡
በዚህም አንድ ግንዛቤ አገኘ፡፡ “ቁጣን መቆጣጠር ከመዶሻ ሥራ የቀለለኮ ነው” አለ፡፡ በመጨረሻው፤ ቁጣውን ሙሉ በሙሉ ተገላገለው፡፡ ወደ አባቱ ሄዶ፤ “አባዬ ቁጣ አቁሜያለሁ” አለው፡፡
አባትዬውም፤ “ለያንዳንዱ ሳትቆጣ ለዋልክበት ቀን አንድ አንድ ሚስማር ከግድግዳው ንቀል” አለው፡፡ ቀስ በቀስ ልጁ ሚስማሮቹን እየነቀለ ጨረሰና፤ “አባዬ ትዕዛዝህን ፈፅሜያለሁ፡፡ አንድም ሚስማር ግድግዳው ላይ የለም” አለው፡፡
አባት ልጁን ወደ ግድግዳው ወስዶ፤ ‹‹ጥሩ አድርገሃል ልጄ! ግን እስቲ ግድግዳው ላይ የቀሩትን ቀዳዳዎቹን ተመልከታቸው፡፡ ቀዳዳዎቹ አይጠፉም። በተቆጣህ ቁጥር አካባቢህ ላይ ቁስል ትተዋለህ፡፡ አንድን ሰው በጩቤ ወግተህ ጩቤውን ልትነቅልለት ትችላለህ፡፡ ቁስሉ ግን እዛው ነው። ጠበሳው አለ፡፡
ለቁጣህ ሺ ጊዜ ይቅርታ ልትጠይቅ ትችላለህ፡፡ ቁስሉ ግን እዚያው አለ። የቃልህ ቁጣ በአካል ላይ ጠባሳ እንደመተው ሁሌ ይኖራል፡፡ አስከፊነቱን ተገንዝበህ ከእንግዲህ አትድገመው!›› አለው፡፡
*   *   *
ንዴት፣ ቁጣ፣ ስሜታዊነትና ኃይል መጠቀም የሁልጊዜ ማሽነፍ ምልክቶች አይደሉም፡፡ ይልቁንም ጉጂነታቸው ያመዝናል፡፡ ኃይል ሚዛናዊ የአዕምሮ ቁጥጥርን ያዛባል፡፡ የድንገቴ ሁኔታን በቁጣና በኃይል ለመፍታት መሞክር ብዙ ሚስማር ግድግዳችን ላይ በመዶሻ እንድንመታ ያደርገናል፡፡ ሲበርድልን ደግሞ የሚተወው ጠባሳ አይጣል ነው! ጊዜያዊ መፍትሔ የዘላቂ ጠባሳ ወላጅ ነው፡፡ ሰላማዊ ውይይትን ከሁሉም ነገር አስቀድመን እንደ ጥሞና ገበታ መቁጠር ብልህነት ነው፡፡ ችግር መኖሩን ከመካድ፤ አምኖ መፍትሔ መሻት፣ የቀና አመራር ብርቱ እጅ ነው፡፡ የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል! ርኩቻ ለሀገርም፣ ለህዝብም ጤና አይደለም፡፡ ቸኩሎ እርምጃ መውሰድም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡ ‹‹ቁጣና ስሜታዊነት ከሩቅ ግብ አንፃር ሲታዩ ፀረ-ምርታማነት ናቸው፡፡ ሁልጊዜ ረጋ- ያልክና እሙናዊ ሁን፡፡ አንተ የረጋህ ሆነህ ባላንጣህ እንዲቆጣ ካደረግኸው፣ ጠቀሜታው ያንተ ነው! ባላንጣዎችህን ሚዛን አሳጣቸው፡፡ እነሱ ይሯሯጡ-ገመዱን ግን አንተ ያዝ!›› ይለናል ሮበርት ግሪን። ልብ ያለው ልብ ይበል ነው ነገሩ፡፡ ከተሳሳትን ማስተካከያውን እናብጅ- እንጂ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› አንበል፡፡ ‹‹አንጋጠው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ›› ነው መጨረሻው!
“አትጣደፍ፡፡ ጥድፊያ  ራስህን ለመቆጣጠር እንዳትችል ያደርግሃል፡፡ ጊዜንም በቅጡ እንዳትጨብጥ ያስገድዱሃል፡፡ ሁሌ ታጋሽ ሁን፡፡ የመጨረሻው ቀን ያንተ ይሆናል፡፡ ትክክለኛዋን ቅፅበት ሰልላት፡፡ ወደ አሸናፊ ኃይል ትቀየር ዘንድ ጊዜን የማሽተት አቅምህ ወሳኝ ነው፡፡ ጊዜህ ካልበሰለ አፈግፍግ፡፡ ከበሰለ ግን አትዘግይ፤ ጥርቅም አድርገህ ምታ” ይለናል ከላይ የጠቀስነው ደራሲ፡፡
በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉና በውይይት የሚያምኑ፣ ችግሮችን ለመፍታት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ሀገራችን ልበ - ብሩሃን ሰዎችን ትሻለች፡፡ ሆደ - ሰፊና ከስሜታዊነት ለመታቀብ ብቃቱ ያላቸውን ብልህ ሰዎች ትፈልጋለች። ችግሮቻችን በርካታና ሥር የሰደዱ እንደመሆናቸው  ሁሉ፣ የአንድ ሰው ሳይሆን የብዙዎችን ትከሻ፣ የብዙዎቹን ርብርቦሽ፣ የብዙዎችን አዕምሮ - ለአዕምሮ መናበብ የግድ ይሻሉ፡፡ አንድ ድርጅት፣ አንድ ማህበር፣ አንድ ተቋም ብቻ የሚፈታቸው አይደሉም፡፡ ‹‹ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፣ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ›› የሚለው ተረት፤ ሌሎችን የማያሳትፍ አመራር ፋይዳው ትንሽ መሆኑን ነው የሚጠቁመን!!

Read 7127 times
Administrator

Latest from Administrator