Print this page
Monday, 29 August 2016 10:21

ዳግማዊ ኦሮማይ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ኢህአዴግ ሕገ መንግሥት አርቅቆ ቢነሣም ሕገ መንግሥታዊነትን አላሰፈነም
          የሕዝብ ብሶት ሲያይል ሽንገላና ጊዜያዊ መፍትሔዎች ቀልቡን አይስቡትም
          በሥርዓቱ በመሾምና ንብረት በማግበስበስ መካከል እምብዛም ልዩነት የለም
                    ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
   ለበዓሉ ግርማ ሞት ምክንያት የኾነው፣ ‹‹ኦሮማይ›› በሚል ርእስ የጻፈው መጽሐፍ እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ እንደ እርሱ አተረጓጎም፣ ኦሮማይ ማለት አለቀ፣ ተፈጸመ፣ ሰዓቱ ደረሰ የሚል አንድምታ ያለው ቃል ነው፡፡ የበዓሉ ትረካ የደርግን ሥርዓተ መንግሥት ማብቂያ የሚጠቁም ሲኾን፣ ኒኮሎ ማኪያቬሊ የዛሬ አምስት መቶ ዓመት፣ ‹‹ስለ ልዑላኑ ማውራት ከአንገት ያሳጥራል›› እንዳለው የበዓሉም መጨረሻ በዚኹ መንገድ ተጠናቋል፡፡
የዚህ መጣጥፍ ዋና ዓላማ፣ በዓሉ፣ ‹‹ኦሮማይ›› በሚለው መጽሐፉ የደርግ ሥርዓት እያበቃለት መኾኑን እንደጠቆመው፣ እኔም በአኹኑ ወቅት በአገራችን እየተከሠተ ያለው ቀውስ፣ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ማብቂያው እየተጓዘ መኾኑን እንደሚያመለክት ለማሳየት ነው፡፡ ለመጣጥፌ ‹‹ኦሮማይ›› የሚለውን የበዓሉን ቃል በመዋስና የእርሱን ትረካ እንደ ‹‹ቀዳማዊ ኦሮማይ›› በመውሰድ፣ አኹን ኢሕአዴግ ያለበትን የፖለቲካና የሥርዓት ቀውስ ‹‹ዳግማዊ ኦሮማይ›› ብዬዋለኹ፡፡ እዚኽ ላይ ቀዳማዊም ኾነ ዳግማዊ ኦሮማይ የአንድን ሥርዓት የፍጻሜ ደውል የሚያስተጋቡ መኾናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ኢሕአዴግ የሚመራውን ሥርዓት ከኦሮማይ ኹኔታ ጋር አዛምዶ ለማየት የሚያስችሉ በርካታ መገለጫዎች ቢኖሩም፣ ለዚኽ ጽሑፌ የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች እንደ ማሳያ አቀርባለኹ፡፡  
አገር በጄ
በዚኽ ነጥብ የማነሣው ዋነኛ ርእሰ ጉዳይ፣ ከኢሕአዴግ በፊት የነበሩት የፖለቲካ ሥርዓቶች የነበረባቸውን ግድፈቶች በማስወገድ፣ ለሕዝቦች ነጻነት እና ለጠንካራ አገራዊ አንድነት ዋስትና በሚል መርሕ የተመሠረተው ፌዴራላዊ የፖለቲካ ሥርዓት መከተል የሚገባውን ፈር ለቆ፤ ከዚኽ በፊት ‹‹አገር በጄ›› ብለው እንደተነሡት ነገሥታት ኢሕአዴግም፣ ያንኑ የጠቅላይነት ሥርዓት በፓርቲ የበላይነት እንደተካው ለማሳየት ነው፡፡
ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ አሰባስበው በአሰናዱትና፣ ‹‹Kasa and Kasa›› በሚል ርእስ በታተመው መጽሐፋቸው፣ ስለ ዘመነ መሳፍንት አስደናቂና ፈር ቀዳጅ የታሪክ እይታ ያላቸውን ነጥቦች አቅርበዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ አቀራረብ፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ቀደም ሲል ከነበረው የአገዛዝ ሥርዓት የተለየና አዲስ ሥርዓት መሥርተዋል። ይህንኑም አዲስ ሥርዓት፣ ‹‹አገር በጄ›› የሚል ስያሜ ሰጥተው ካብራሩት ሦስት ምሁራን (ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴና ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል) መነሻ ሐሳብ በመውሰድ የራሳቸውን ትንተና አቅርበዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በዚኹ ትንታኔአቸው፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ‹‹አገር በጄ›› ብለው መሳፍንቱንና መኳንንቱን እንዲኹም ከፍተኛ ማዕርግ ያላቸውን ባላባቶች ወደ ጎን በመገፍተር በምትካቸው ራሳቸው በመረጧቸውና ዝቅተኛ የሹመት ደረጃ ባላቸው ምስለኔዎች ማስተዳደር እንደ ጀመሩ አብራርተዋል፡፡ እንግዲኽ ይህ በዐፄ ቴዎድሮስ የተወጠነው የ‹‹አገር በጄ›› መርሕ ነው፣ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ ተጠናክሮ የቀጠለው፡፡ ይህ መርሕ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ይበልጥ ተጠናክሮ፣ ‹‹ጠቅል›› የሚል ስያሜ በመያዝ ሙሉ ለሙሉ ጠቅላይ አሐዳዊ ሥርዓት ኾነ፤ ደርግም ቢኾን ይህን አሐዳዊ ሥርዓት በሶሻሊስት ሥርዓት መርሕ አስቀጠለው፡፡
በደርግ ውድቀት ዋዜማ የኢሕአዴግ አዲስ ሕገ መንግሥት ተረቆ አገሪቷ፣ ወደ አገር በጃችን (ፌደራላዊ) ሥርዓት መሸጋገሯን ይደነግጋል፡፡ ይህንንም የፌደራል ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አገሪቱ በተለያዩ የክልል መንግሥታት ተዋቀረች፡፡ ይኸው፣ ሕዝቦችን የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት የሚያደርግ ነው በሚል መርሕ የተመሠረተው አዲሱ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጥቂት መንገድ ከተጓዘ በኋላ በሒደት፣ አገር በጃችን ቀርቶ አገር በፓርቲዬ መኾን ጀመረ፡፡
በዚኽ የ‹‹አገር በጄ›› መርሕ፣ አንድ ገዢ ፓርቲ ፍጹም የበላይነት ከተቀናጀ በኋላ የፈለገውንና የተመቸውን የክልሎች ግዛትና ሀብት፣ ‘የፓርቲዬና እኔ ወክዬዋለኹ የሚለው ሕዝብ ንብረት ነው’ ብሎ በተስፋፊነት ቢራመድ የሚያስገርም አይኾንም፡፡ የገዢው ፓርቲ የበላይነት ሥር ከሰደደ በኋላ የሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በእጅጉ እየተገደበ ሔዷል፡፡ በየክልሉ የሚነሡ የማንነት ጥያቄዎች፣ በኢንቨስትመንት ስም የሚካሔደው የመሬት ወረራ፣ ‘ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም የላቸውም’ በሚል ሰበብ የሕዝቦችን ሉዓላዊነትና የራሳቸውን ክልል በራሳቸው የማስተዳደር መብት የመጣስ ችግሮች፤ በአኹኑ ወቅት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
አገር በጄ በሚለው ፅንሰ ሐሳብ፣ ነገሥታቱ በተበታተነ መልኩ በተለያዩ መሳፍንት ይተዳደሩ የነበሩ ግዛቶችን አዋሕደው አገራዊ አንድነትን አጠናክረዋል። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ግን፣ ለአገር አንድነት የነበራቸውን ትልቅ ግምትና ቦታ ያኽል፤ ለሕዝቦች ነጻነት፣ ማንነትና መብት መጠበቅም ተገቢውን ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በበኩሉ፣ ሕገ መንግሥት ቀርፆ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሲመሠርት፣ የግዛት አንድነት ብቻ ሳይኾን የሕዝቦች ነጻነትም ለአንድ አገር ህልውና አስፈላጊ ነው፤ በሚል መርሕ ከአሐዳዊ አገዛዝ ወደ ፌዴራላዊ አገዛዝ ማለትም ከ‹‹አገር በጄ›› ወደ ‹‹አገር በጃችን›› ለማሸጋገር በማለም ነበር፡፡
የዚኽም ሽግግር ዓላማ፣ የአገሪቱን አንድነት አስጠብቆ ለዜጎች መብትንና ነጻነትን የሚያጎናጽፍ የፌደራል ሥርዓትን በሕገ መንግሥት ለመመሥረትና ሕገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን ነበር፡፡ ይህ ዓላማም ኢትዮጵያ፣ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር መኾኗን በመገንዘብ የአገሪቷን አንድነት ለማስጠበቅና የሕዝቦችን መብት ለማስከበር ነበር፡፡
ነገር ግን፣ የኢሕአዴግን አገዛዝ ስንመለከት፣ አገር በጄ ወይም አገር በፓርቲዬ የሚለው አካሔድ፣ የአገሪቱን የአንድነት ጉዞም ኾነ የሕዝቦችን የነጻነትና የመብት ፈለግ አልተከተለም፡፡ ይልቁንም የተወሰኑ ወገኖችን ጥቅምና የበላይነት ማእከል በማድረግ፣ ነገሥታቱ ያስጠበቁትን የአገር አንድነት በማፋለስና በፌዴራሊዝሙ አስከብረዋለሁ ያለውን የአገር አንድነትም ኾነ የሕዝቦች መብትና ነጻነት በመጋፋትና በመፈታተን አዝማሪው እንዳለው ‹‹...ኹለተኛ ጥፋት›› ኾኗል፡፡
ኢ-ዴሞክራሲያዊነት
የኢሕአዴግ የፖለቲካ ሥርዓት ሲጀምር፣ ሕገ መንግሥት በወረቀት ላይ አርቅቆ በአንድ በኩል፣ ከአሐዳዊ ወደ ፌደራላዊ ሥርዓት ሽግግር ሲደነግግ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ከግለሰባዊ አገዛዝ፤ የሥልጣን ክፍፍልን መሠረት ወደ አደረገ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ለመግባት የሚያስችል መንገድ ከፍቶ ነበር፡፡ እዚኽ ላይ ቁልፍ ጉዳይ የሚኾነው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ ሠናይ ትልሞች አኹን ባለንበት የፖለቲካ ምዕራፍ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ስንጠይቅ ነው፡፡
ይህን ጥያቄ ይዘን፣ የኢሕአዴግን የ21 ዓመት የሕገ መንግሥት ጉዞ ስንገመግመው፣ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥት አርቅቆ ቢነሣም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓተ ወግን ሊጎናጸፍ ግን አልቻለም፡፡ ይኸውም ኢሕአዴግ፣ ሕዝቦችን ለሉዓላዊ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ከማብቃት ይልቅ በጥቂት ሰዎች እንዲከማች ያደረገ፤ ሕገ መንግሥትን ማጽደቅ እንጂ ሕገ መንግሥታዊነትን ያላሰፈነና በኹሉም መልኩ የበላይነት የተጎናጸፈ ሥርዓት መኾኑ ነው፡፡ ለዚኽም እውነታ የሚከተሉትን ነጥቦች በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡
አንደኛ፣ ማንኛውም ዴሞክራሲ በመሠረቱ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያስገድዳል፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር በምናይበት ጊዜ፣ ሥርዓቱ፣ ‹‹የፖለቲካ ሥልጣንን ለሕግ አውጭው፣ ለሕግ አስፈጻሚውና ለሕግ ተርጓሚው ያከፋፈለና የመንግሥት ሥልጣንን የገደበ ነው፤›› ቢባልም፤ የሕግ አስፈጻሚው ክፍል በአንድ በኩል ፌዴራሊዝሙን በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሕግ አውጪውና በሕግ ተርጓሚው ላይ ትልቅ ጫና በማሳረፍ ሥልጣናቸውን በእጅጉ ገድቦታል፡፡ በመኾኑም የሕግ አስፈጻሚው ተቋም ራሱን እያፋፋና እያጠናከረ በአንፃሩ ሌሎቹን የመንግሥት ተቋማት እያሽመደመደ ሔዷል፡፡
ኹለተኛ፣ ከአገራችንም ኾነ ከሌላው አገር ታሪክ እንደምንረዳው፣ ሕግ ለነጻነት ትልቅ ዋልታ ነው፡፡ በመኾኑም የአንድን አገር ፍትሕም ኾነ ነጻነት ለማስከበር የፍትሕ ተቋማት በነጻነትና በገለልተኛነት መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው፡፡ ኾኖም በአገራችን የፍትሕ ተቋማት የራሳቸው ልዕልና ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም፡፡ የራሳቸውን ልዕልና ያላስከበሩ ተቋማት ደግሞ የዜጎችን ነጻነት ያስከብራሉ ለማለት አይቻልም፡፡ በዚኽም የተነሳ የሕግ የበላይነት ሳይኾን የፖለቲካ ፍላጎት የበላይነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሕግ ባለሥልጣናትን መቆጣጠር ሲገባው በተቃራኒው ባለሥልጣናት ሕግን እንዳሻቸው ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል፡፡ በመኾኑም አገሪቱን የሚያስተዳድሩ መሪዎች የሕግ ማህቀፍ ሳይጣልባቸው በዘፈቀደ ሕግ እያወጡ ለፖለቲካ መሣርያነት እንዲጠቀሙበት ኾኗል፡፡
ሦስተኛ፣ ማንኛውም ሕገ መንግሥት በዜጎችና በመንግሥት መካከል የሚገኝ የውል ሰነድ ነው፡፡ ይኹንና የውል ፍጥጥሙን፣ በብሔርና በመንግሥት መካከል ያደረገው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን፣ ለዜግነት ተገቢውን ቦታና ዋጋ አልሰጠም፡፡ በመኾኑም ብሔር የሚለው እሳቤ ጎልቶ ሲቀርብ፣ ዜጋ የሚለውን እሳቤ አኮስሶታል፡፡ ይህን የዜጋ እሳቤ ማኮሰሱ ሦስት ዐበይት ችግሮችን ፈጥሯል፡፡
አንደኛው፣ ዜጎች በብሔራቸው ከተመደበላቸው ክልል ውጭ ተንቀሳቅሰው መኖር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ኹለተኛው፣ ከተለያዩ ብሔሮች የሚወለዱትንና ራሳቸውን ከብሔር ማህቀፍ ያወጡ ዜጎችን ብሔር አልባ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል፡፡ ሦስተኛው፣ መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤሎችን፣ ‹‹የተመረጡ ሕዝቦች›› እንደሚላቸው ኹሉ፣ በእኛ አገር የፖለቲካ ሒደትም በአገሪቷ ውስጥ ካሉ ብሔሮች መካከል ‘የተመረጠ ብሔርና ሕዝብ’ በሚል መድልዎ ይካሔዳል፡፡
ሥርዓቱ ፍጹም የበላይነትን ያሰፈነ ለመኾኑ አራተኛው ማሳያ፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የዴሞክራሲ ግብ የሚሠምረው፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚተገበሩ ፖሊሲዎችን ከማርቀቅ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ያለው ሒደት፣ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሲከናወን ነው፡፡ በዚኽ ረገድ ኢሕአዴግ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፥ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ፣ የሕዝቡን አስተያየት ያካተቱና የሕዝቡን ይኹንታ አግኝተው የሚተገበሩ አይደሉም፡፡ ይልቁንም የምናወጣቸው ፖሊሲዎችና የምናስፈጽማቸው ተግባራት፣ ትክክለኛውን አቅጣጫ የተከተሉ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ የተለያዩ ሐሳቦችና አመለካከቶች በግልጽና በሐቅ እንዲንሸራሸሩ ቦታ አይሰጡም፡፡ ይህ ፍጹም ርግጠኝነት ለዴሞክራሲ ማበብ ትልቅ መሰናክል እንደሚኾን መረዳት ተስኗቸዋል። ይህም ሕዝቦች በነጻነት ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክና የሚደመጡበት ተቋም (የብዙኃን መገናኛ) በአገሪቷ ውስጥ እንዳይኖር ምክንያት ኾኗል፡፡
ሙሰኝነት
በአማርኛ፣ ‹‹ሙስና›› በእንግሊዝኛ፣ ‹‹Corruption›› የሚባለው ስያሜ በጣም ሰፊና በተለያዩ የታሪክ ዘመናት የራሱ የኾነ ይዘት፣ ቅርፅና ትርጉም እየያዘ የመጣ ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ‹‹ሙስና›› ለሚለው ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የሚከተለውን ፍች ሰጥተዋል፡፡ ሙስና ማለት ‹ጥፉነት›፣ ‹ጥፋት›፣ ‹መፍረስ›፣ ‹መበስበስ›፣ ‹መከራ›፣ ‹መቅሠፍት›… ወዘተ ማለት ነው፡፡ እንዲኹም ‹‹ሙሱን (Agent)›› ‹የማሰነ›፣ ‹ጥፉ›፣ ‹መጥፎ›፣ ‹ብልሹ›፣ ‹ግም›፣ ‹ድፍር› …ወዘተ. ማለት ነው፡፡ እንደ እንግሊዝኛው ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ፍች ደግሞ፣ ‹‹Corruption›› ማለት በዋናነት ‹መበስበስ›፣ ‹መቆርቆዝ›፣ ‹መበታተን›፣ ‹መዝቀጥ›… ወዘተ ሲኾን፣ ከእነዚህ ገለጻዎች የምናገኘው ምስል፥ ‹‹መበከል›› እና ‹‹ከተፈጥሯዊ ማንነት መውጣትን›› ነው፡፡
ልብ ብለን መገንዘብ የሚኖርብን ነገር ቢኖር፣ የአማርኛውም ኾነ የእንግሊዝኛው ትርጓሜ በሐሳብ ደረጃ ተቀራራቢነትና ተያያዥነት እንዳላቸው ነው። በተጨማሪም የአማርኛውም ኾነ የእንግሊዝኛው ፍቺ፣ አኹን በዘመናችን ካለው እሳቤ ጥልቀትና ስፋት ያለው ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህንንም የምንልበት ዐቢይ ምክንያት፣ ዘመናዊው አተያይ ሙስናን፣ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውጭ የማያይ፤ በግለሰብና በማኅበረሰብ ጥቅም መካከል የሚገኝ ሽኩቻ ብቻ አድርጎ ስለሚያቀርብ ነው፡፡
በአገራችን ያለውን የሙስና ደረጃና ኹኔታ በሚገባ ለማየት ግን የጥንቱንና ዘመናዊውን አተረጓጎምና አተያይ በድምር መውሰድ ይኖርብናል፡፡ እኔም ከፈላስፎች ጥቂት ብሂላትን በመውሰድ፣ ኹለቱንም አተያዮችና አተረጓጎሞች በጥቂቱም ቢኾን ማየቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ እላለኹ፡፡ የአራት ፈላስፎችን ሐሳብ አጠር አድርገን እንመልከት፡-
አርስቶትል፡-
እንደ ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ አርስቶትል አስተምህሮ፣ የአንድን የፖለቲካ ማኅበር እንደ ሰንሰለት የሚያያይዘው ተቀዳሚ ዕሴት ፍትሕ ነው፡፡ ያለ ፍትሕ ማንኛውም ማኅበረሰብ በሰላምና በጸጋ ሊኖር አይችልም። ሙስና፣ ይህን ወሳኝ የሞራልና የሕግ ዕሴትና አውታር ስለሚያበትከውና ስለሚያመክነው ለማኅበረሰቡ ህልውና ትልቅ አደጋ ነው፡፡
ሲሰሮ፡-
ለሲሰሮ፣ የሙስና ተቀዳሚ መሠረቱ፣ ማኅበረሰቡን ለማስተዳደር ሓላፊነት የተቀበሉ ሰዎች በፍቅረ ንዋይ እየተነዱ ከዋናው ተግባራቸው መውጣታቸው ነው። ለዚኽ ፈላስፋ፣ ሙስና፣ ሰፋ ያለ የሞራል፣ የሕግና የፖለቲካ ብልሹነትን የሚጠቁም ጉዳይ ነው፡፡
ቅዱስ ኦገስቲን፡-
እንደ ቅዱስ ኦገስቲን አባባል፣ የሰውነት ክፍሎቻችን የየራሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳላቸው ኹሉ፤ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ተቋማትም የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ እንደ እርሳቸውም እሳቤ፣ የሰው ልጅ አንድ አካሉ ሲታመም መላው ሰውነቱ እንደሚታወክ ኹሉ፤ ሙስናም፣ በአንደኛው የማኅበረሰብ አካል ከታየ ሌሎቹንም ክፍሎች እንደሚበክል ይናገራሉ፡፡
ኒኮሎ ማኪያቬሊ፡-   
እንደ ማኪያቬሊ አገላለጽ፣ የጥንት ሮማውያን ወታደራዊ ድል ከተጎናጸፉ በኋላ ግዙፍ ግዛተ ዐፄ/ኢምፓየር/ ገነቡ፡፡ በዚኽም ብዙ ሀብት እና ትልቅ የፖለቲካ ኃይል ማግኘት ቻሉ፡፡ ኾኖም ግን ያገኙት ሀብት እና ምቾት የተንደላቀቀ አኗኗር እንዲያገኙ ቢያስችላቸውም፣ ከንዋይ ጋር ተያይዞ ከሚመጣው የሞራል ዝቅጠት ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ማኪያቬሊ፣ ይህን የታሪክ እውነታ ዋቢ በማድረግ ስለ ሙስና የጻፈውን በኹለት ነጥቦች አሳጥሬ ላቅርብ፡፡
ሀ/ ሙስና፣ ከምቾት እና ከቅምጥል ኑሮ የሚነሣ የሥነ ምግባር እና የዲስፕሊን ጉድለት ነው፡፡
ለ/ የግል ጥቅም ከማኅበረሰብ ጥቅም የበላይነት ይዞ ሲገኝ፣ ‹‹የእኔ…›› የሚለው የራስ ወዳድነት መንፈስ ከሪፐብሊኩ ፍላጎት እና መንፈስ ጋር ሲጋጭ ነው፡፡
በአገራችን ያለው የኢሕአዴግ ሥርዓት በሙስና የተዘፈቀ በመኾኑ ሳቢያ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከተሟሉ መገለጫዎቻቸው ጋር ተሸክሞ እንደሚገኝ አምናለኹ፡፡ የኢሕአዴግ ሥርዓት በአስከፊ ሙስና ውስጥ እንዲዘፈቅ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
አንደኛው ምክንያት፣ መንግሥቱም ኾነ ዜጎች፣ በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅሮች የየራሳቸው ሓላፊነትና ድርሻ ሊኖራቸው ሲገባ፣ ይህ ካለመኾኑ የመነጨ ነው፡፡ ሥርዓቱ፣ እኒኽ ዜጎች በመንግሥት የተለያዩ መዋቅሮች ተገቢው ሓላፊነትና ድርሻ እንዳይኖራቸው በማድረግ ራሱ የፖሊሲ አውጪ፣ ራሱ አስፈጻሚና ራሱ ዋነኛ የኢኮኖሚው ተዋናይ ኾኗል፡፡
ከዚኽ ጎን ለጎን ሳይጠየቅ የማይታለፈው ደግሞ፣ ሥርዓቱ በሕዝብና በግለሰብ መብት መካከል ያለውን ልዩነት ማየት የተሳነው መኾኑ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ፣ ፍትሕ ላይ የተመሠረተ፣ የማይሻርና የማይገሰስ መብት አለው፡፡ በመኾኑም ብዙኃኑን ይጠቅማል በሚል እሳቤ የግለሰቡን የማይገሰስ መብት መጣስ ፍትሐዊ አይደለም። በዚኽ ሥርዓት ግን የማኅበረሰቡን ወይም የብዙኃኑን ጥቅም ለማስከበር በሚል ሰበብ የግለሰቡ መብትና ህልውና ሲጨፈልቅ ይታያል፡፡ ይህም በዋነኛነት የግለሰቡ ጉዳት ፖለቲካዊ ኪሳራ አያመጣብኝም ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው፡፡
ይህም መንግሥት ለግለሰቡና ለሲቪል ማኅበረሰቡ መላወሻ የማይሰጥ፣ አንድ ወጥ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኾን አድርጎታል፡፡ እነዚኽ የሥርዓቱ ባሕርያትም፣ መንግሥት በኹሉም የአገሪቱ ሀብትና ንብረት ላይ እጁን እንዲዘረጋ፣ የመንግሥት የአስተዳደር ሕጎች በትክክል እንዳይተገበሩ፣ የአሠራር ብልሹነት እንዲስፋፋ፤ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት በማባከን ሥርዓቱ የሙስና መናኸሪያ እንዲኾን አድርጎታል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸውን ፈላስፎች ሐሳብ አጠቃለን ስናየው፣ ሙስና የሚከተሉትን አሉታዊ ተጽዕኖዎች እና ውጤቶች ያስከትላል፡፡ እነርሱም፡- ኢፍትሐዊነት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅነት፣ ሥርዓተ ብልሹነት፣ አድልዎና የሞራል ዝቅጠት ናቸው፡፡
በአገራችንም ያለው የኢሕአዴግ ሥርዓት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከተሟሉ መገለጫዎቻቸው ጋር የተሸከመ እንደኾነ ስለምናምን፣ ሥርዓቱ ደግሞ እንዴት ወደ እነዚኽ አስከፊ የሙስና ኹኔታዎች እንደገባ በሚከተሉት ነጥቦች ማሳየት ይቻላል፡፡
አንደኛ፡- የኢሕአዴግን የፖለቲካ ሥርዓት ስንመለከት፣ በይዘቱ በጣም ሰፊና ትልቅ መንግሥት ነው፡፡ ይህም አንዱ፣ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ልዩነት እና ወሰን መኖሩን የማይቀበል ሲኾን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሕዝብና በግለሰብ መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት በመናድ አንድ ወጥ የኾነ የጠቅላይ አገዛዝ መንግሥት የዘረጋ ኃይል ነው፡፡ ይህ ደግሞ፣ በኹሉም የአገሪቷ ንብረት ላይ በበላይነት እጁን እንዲከትና የብክነት እክሎችና የትግበራ እንከኖች ብሎም የሙስና መናኸሪያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡     
ለሥርዓቱ በሙስና መዘፈቅ ኹለተኛው ምክንያት፣ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ በብቃት ላይ የተመሠረተ ውድድር፣ ከጤናማ የኢኮኖሚ ፉክክር፣ ከሕጋዊ የሀብት ምንጭ… ወዘተ አኳያ ትልቅ ክፍተት ያለበት ሥርዓት መኾኑ ነው፡፡ በእኔ ግምት ይህ ክፍተት ካለማወቅ የመነጨ ሳይኾን፣ ኾነ ተብሎ የፖለቲካ ሥልጣን ከጨበጡት ሹመኞች ጋር የብሔር ትስስር ያላቸውንና የእኛ የሚሏቸውን ወገኖች ለመጥቀም በማሰብ የተደረገ ነው፡፡ በዚኽ መልኩ ፍትሐዊነት በጎደለው በአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ፣ እነዚህ ዕሴቶች በሚጓደሉበት ወቅት ደግሞ፣ አኹን በአገራችን እንደምናስተውለው፣ የአገሪቷ ሀብት የጥቂት ቡድኖች መጠቀሚያና ችሎታን መሠረት ያላደረገ ኢፍትሐዊ ውድድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ አስችሏቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በኢሕአዴግ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የሙስና ደረጃ ስናየው፣ ሌቪ የተባለው የጥንታዊ ሮማ የታሪክ ምሁር ስለ ሙስና ያለውን ያስታውሰናል። ሌቪ እንደሚለው፣ ‹‹ሙስና የተንሰራፋበት ሥርዓት ዝም ብለው ቢተዉት ሥርዓቱን ማፍረሱ አይቀርም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ፣ የተስፋፋውን ሙስና ለመግታት ሙከራ ቢደረግም እንኳ ሥርዓቱ መፍረሱ አይቀርም፡፡››
ከላይ ያነሣናቸው የአገር በጄ፣ የኢ-ዴሞክራሲና የሙስና መንሰራፋት ችግሮች፣ አኹን ሥርዓቱ ለአጋጠመው ሕዝባዊ ተቃውሞና ዐመፅ መንሥኤዎች ናቸው፡፡
ወደ ኦሮማይ ጎዳና
ሌኒን፣ በ1920 (እ.ኤ.አ)፣ አንድ አገር ዐብዮታዊ ኹኔታ ውስጥ ስትገባ የሚከተሉትን አራት ክሥተቶች እንደ ምልክት እናያለን ብሎ ነበር፡፡ እኔም ሥርዓቱ ወደ ዳግማዊ ኦሮማይ ድባብ እየገባ ነው፣ ብዬ ስለማምን የሌኒንን አራት መገለጫዎች አንሥቼ የራሴን አተያይ ለማቅረብ እሞክራለኹ።
1ኛ/ ለዐብዮቱ ጠላት የኾኑ መደቦች በመካከላቸው ባለው ውስጣዊ ትግል ምክንያት ወደ ውዥምብርና ክፍፍል ያመራሉ፡፡ ይህ ውስጣዊ ውዥምብር ደግሞ ለድክመት ይዳርጋቸዋል፡፡ በመኾኑም ድሮ በሚተገብሩት መንገድ ሥርዓታቸውን ማስቀጠል አይችሉም፡፡  
2ኛ/ ከሥርዓቱ ተጠቃሚነት አልፎ ተቀባይነትና አመኔታ ያለው የንኡስ ከበርቴ መደብ፣ በሕዝቡ ዘንድ ማንነቱ በሚገባ ታውቆና በሕዝቡ ፊት ተጋልጦ፣ በጥቂቱም ቢኾን የነበረውን ሕዝባዊ ቅቡልነት ሙሉ ለሙሉ ያጣል፡፡
3ኛ/ ዐብዮተኞቹ ከቡርዣው መደብ ጋር የሚያደርጉትን ቁርጠኛ ትንቅንቅ ሰፊው የሠራተኛው መደብ መደገፍ ይጀምራል፡፡
4ኛ/ የገዢው መደብ ሠራዊት እርስ በርስ መከፋፈል፣ መፈረካከስና ማመፅ ይጀምራል፡፡
እንደሚታወቀው እነዚህ ነጥቦች፣ የሩስያ ዐብዮት መሪ የዛሬ መቶ ዓመት ለዐብዮት መፈጠር አመልካች ክሥተቶች ናቸው በሚል የጠቀሳቸው ናቸው፡፡ በመኾኑም ሌኒን ያለውን በንባቡ ( ቃል በቃል) በመውሰድ፣ ዛሬ አገሪቷ ያለችበትን ኹኔታ ለመግለጽ ሳይኾን፣ ከእነዚህ ነጥቦች መካከል የተወሰኑት አኹን ባለው የአገራችን የፖለቲካ ኹኔታ ላይ እንዴት እንደሚስተዋሉ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡
ሀ/ ‹‹በድሮው መንገድ ሥርዓቱ መቀጠል ሲሳነው››
በፍትሕ፣ በዴሞክራሲና በመብት ዙሪያ የተነሡ ጥያቄዎች፣ ሥርዓቱ እስከ ዛሬ በሚያስተዳደረው መንገድ ሊፈቱ እንደማይችሉ ሕዝቡ ርግጠኛ ኾኗል፡፡ በመኾኑም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚቻለው የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ ብቻ እንደ ኾነ ሕዝቡ ተገንዝቧል፡፡ ሌኒንም፣ እንደ ድሮው ሥርዓቱ መቀጠል አይችልም፤ በሚልበት ጊዜ፣ በሕዝቡ ለተነሡት ኹለንተናዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው፣ በድሮው መንገድ ሳይኾን አዲስ የሥርዓት መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ ሕዝቡ ሲያምን እንደኾነ መናገሩ ነው፡፡  
ለ/ ‹‹የሕዝብ ቅቡልነት ማጣት››
ለአንድ ሥርዓት የቅቡልነት ጥያቄ ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ ቅቡልነቱም በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል፤ መንገዶቹም፡- ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ… ወዘተ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ የአንድ ሥርዓት ዕድሜ፣ ቀጣይነት ወይም ዘላቂነት የሚወሰነው፣ ከሕዝብ ከሚያገኘው ቅቡልነት የተነሣ ነው፡፡
አገዛዙ የሕዝብ ቅቡልነትን ሲያጣ በመሣሪያ ኃይል ሥርዓቱን ማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ አኹንም በአገራችን እያየን ያለነው የሕዝብን ጥያቄ በመሣሪያ ለመግታት የሚደረግን ጥረት ነው፡፡ ነገር ግን፣ ይህ የኃይል አካሔድ እንደማያዛልቅ የታወቀ ነው፡፡ በዚኽ ረገድ ፈረንሳዮች አንድ ትምህርታዊ  አባባል አላቸው፡፡ ይህም ‹‹መሣሪያን ብዙ ነገር ያደርጉበታል፤ ኾኖም ለብዙ ጊዜ አይቀመጡበትም›› የሚል ነው፡፡
ሐ/ ‹‹የሕዝብ ቁርጠኝነት››  
የሕዝብ ብሶት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰ ጊዜ ሽንገላና ጊዜያዊ መፍትሔዎች ቀልቡን አይስቡትም፡፡ ቀደም ሲል፣ ሕዝቡ፣ መንግሥት ወይም የአስፈጻሚ አካላት ሕገ መንግሥቱን ቢያስከብሩ ችግራችን በሒደት ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ አኹን ግን ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የሕዝቡን ጥያቄ ለማስተናገድም ኾነ መፍትሔ ለመስጠት ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ከመረዳት አልፎ፣ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥቱን ለመተግበር የሚያስችል ባሕርይና ፈቃድ እንደሌለው ተገንዝቧል፡፡ በዚኽ ምክንያት በተነሣሣው ሕዝባዊ ዐመፅ፣ መንግሥት በብቸኛነት በሚቆጣጠረው የብዙኃን መገናኛ የተለያየ ምክንያት ቢያቀርብም ሕዝቡ ልቡንም ጆሮውንም ሳይሰጠው የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡
ማጠቃለያ  
እንደ ኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ባሉበት አገር፣ የሚዘረጋው የፌዴራል ሥርዓት ቢያንስ የሚከተሉትን ኹለት ወሳኝ ጉዳዮች ማሟላት እንደሚገባቸው በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ጥናትና ምርምር ያደረገው አረንድ ሊፕሐርት ይገልጻል፡፡ እነርሱም፡-
አንደኛ፡- በአገሪቷ ውስጥ ባሉት ማኅበረሰቦች መካከል ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ፡- በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ማኅበረሰቦች፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት መጎናጸፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ሊፕሐርት፣ የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያስፈልጋል፣ ሲል ኹሉም ማኅበረሰቦች ውሳኔ በመስጠት ሒደት ላይ ቀጥተኛና ተገቢውን የተሳትፎ ሚና ሊኖራቸው ይገባል ማለቱ ነው፡፡
ኹሉም ማኅበረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ ማለትም፣ የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሃይማኖት… ወዘተ እንዲያሳድጉና በአገሪቷ ላይ የሚኖራቸውን የጋራ የባለቤትነት ስሜት እንዲያጎለብቱ እንዲያስችላቸው ነው። ከእነዚኽ ኹለት ነጥቦች አኳያ የኢሕአዴግን መንግሥት አመራር ስናየው፣ ፌዴራላዊ ሥርዓትን በመተግበር በባህልና በትምህርት መስኮች ማኅበረሰቦች ያላቸውን ማንነት እንዲያስጠብቁ ቢሞክርም፣ ጅማሮው እየዋለ ሲያድር መልሶ የማኅበረሰቦችን ማንነት ወደ መጨፍለቅ፣ እኔ የሰየምኩኽን ማንነት መላበስ አለብኽ፣ ወደሚል ዓምባገነናዊ አካሔድ ተለውጧል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፣ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የሕዝቦችን ዴሞክራሲ መብት በጉልበት በመገደብ ፍትሐዊ የሥልጣን ውክልና እንዳይኖራቸው እስከ ማድረግም ደርሷል። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲ፣ ለኹሉም እኩል የኾነ መንገድ ትከፍታለች፡፡ ኾኖም በአንድ ጉዳይ ላይ ‹‹የመድልዎ›› ስሜት ይታይበታል፡፡ ይህም ዴሞክራሲ በተፈጥሮዋ ግቧን ለማሳካት በዋናነት የቁጥርን መርሕ መከተሏ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ሥርዓት ግን፣ ዴሞክራሲ፣ ይህን መርሕ ተከትላ ለሕዝቦች የሥልጣን ውክልናና ትክክለኛውን ምላሽ እንዳትሰጥ በጉልበት ተገድባለች፡፡ ለዚኽም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ የመቀመጫ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ወደ ኋላ ተገፍተው፣ ከእነርሱ በእጅጉ ያነሰ የመቀመጫ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ይዘዋል፡፡ ይህን ሕዝቦች ባላቸው የመቀመጫ ቁጥር ውክልና መሠረት ተገቢውን ሥልጣን አለማግኘታቸው እንደ ማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡
በእነዚህ ኹለት መሠረታዊ ችግሮች ሳቢያ፣ በአኹኑ ወቅት የኢሕአዴግ ሥርዓት ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍልን ለመተግበርም ኾነ ሙሉ ለሙሉ አስጠብቄዋለኹ በሚለው የሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ለሚነሡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ተስኖታል፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው፣ ትላንት የነበሩት ሥርዓቶች የሕዝቦችን ማንነት አላከበሩም፤ እያለ ሲወነጅል የነበረው መንግሥት፣ አኹን ካለፈው በከፋ መልኩ ለማኅበረሰቡ ባይተዋር የኾነ ማንነት እየለጠፈ ባለኽበት እርጋ ማለቱ ነው፡፡
አኹን የተነሣው ጥያቄ፣ በዴሞክራሲ ዕጦት አካባቢና አብረው የሚሔዱት የሕግ የበላይነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኹም፣ በሰብአዊ መብት ረገጣ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን፣ ከአኹን በኋላ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን ማክበር ቢጀምር ነገሮች ይስተካከላሉ፤ የሚል አቋም ይዘው እየተሟገቱ ነው፡፡ እንደ እኔ አስተሳሰብ፣ በአንድ በኩል፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ባለው ፍላጎትና ዴሞክራሲ ራሷ እንዲተገበርላት በምትፈልገው መካከል ትልቅ ቅራኔ ስላለ፣ ሥርዓቱ፣ ሕገ መንግሥቱን በሥራ ላይ ያውላል ብሎ መመኘቱ ትልቅ ስሕተት ነው የሚኾነው። በሌላ በኩል፣ ዴሞክራሲ በሌለበት ቦታ የመናገርና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ብሎም ኹሉም ወገኖች የሚደመጡበትና ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ ሊኖር አይችልም፡፡
አንዳንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በብዙኃን መገናኛ እየቀረቡ፣ ‹‹አኹን የተፈጠረው ችግር በውይይት ይፈታ፤ ሕዝቡም ሐሳቡን በግልጽ ተወያይቶ መፍታት ይኖርበታል›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡
የእኒኽን ምሁራን ሐሳብ ስሰማ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተነሣውን ችግር ቀርቶ፣ የሐሳብ መፈተሻና የነጻ ውይይት መዲና ሊኾን በሚገባውና ዛሬ የዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ በኾነው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ እንደማይቻል እየታወቀ፣ ምሁራኑ ራሳቸውም ሐሳባቸውን በነጻነት የማንሸራሸር መብታቸውን ተገፈው ባሉበት ወቅት፣ ‹‹ሕዝቡ በነጻ ውይይት ችግሩን ይፍታ›› ማለታቸው ነው፡፡
ሙስና ለአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ኢፍትሐዊነት ማሳያ ነው፡፡ የመንግሥት የአስተዳደርና የአገልግሎት ተቋማት በሕጉ መሠረት ለዜጎች ፍትሐዊ አገልግሎት የሚሰጡና ኹሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተናግዱ አይደሉም፡፡ የአገሪቱን የልማትና የንግድ ሥራዎች በበላይነት የሚመሩት የመንግሥት ተቋማትም በአገሪቱ ሕግ መሠረት በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎችም ኾነ የግል ድርጅቶች ከአድልዎ የጸዳ ፍትሐዊ አገልግሎት የሚሰጡ አይደሉም፡፡ በዚኽም ምክንያት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኮንስትራክሽንና መሰል የአገሪቱ ወሳኝ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ጥቂቶች ብቸኛ ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡
ይህም በሥርዓቱ ውስጥ የሕግና የፖለቲካ አይነኬ ሕዋሶችን ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ሕዋሶች ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን በመጣስ የፈጠራቸው ከመኾኑ አኳያ፣ የእነዚኽ ሕዋሶች ህልውና እስከ ቀጠለ ድረስ ሙስናን ለመቆጣጠር የሚያስችል ርምጃ ለመውሰድ አይቻልም፡፡ በኢሕአዴግ ሥርዓት በመሾምና ንብረት በማግበስበስ መካከል እምብዛም ልዩነት የለም፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ተሾመ ማለት ከበረ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ችግር በአገሪቷ ውስጥ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ነጻ የኢኮኖሚ ውድድር እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ አገሪቷን ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ጨምሯታል፡፡
በመሆኑም ከላይ ያነሣናቸው የፌዴራሊዝም፣ የዴሞክራሲና የሙስና ችግሮች ባለው የኢሕአዴግ ሥርዓት መፍትሔ የሚያገኙት፣ ቀደም ብሎ እንደዚኽ ዓይነት ጥያቄዎችን የሚያስተናግድና የሚፈታ አሠራርና ተቋም ቢኖር ነበር፡፡ ኾኖም ይህ በሌለበትና ሕዝቡ ውስብስብና አስቸጋሪ ጥያቄ ባነሣበት በዚኽ ወቅት፣ አገዛዙ ሥርዓቱን ለማዳን የሚያስችል መፍትሔ ይዞ ይቀርባል ብሎ ማመን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ከእነዚኽ መፍትሔ አልባ ችግሮች ተነሥቼ፣ ኢሕአዴግ ወደ ‹‹ኦሮማይ ቀጣና›› እየገባ ነው ብዬ አምናለኹ፡፡
መጣጥፌን የምደመድመው፣ ከደበበ ሰይፉ፣ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› ግጥም፣ በአኹኑ ወቅት እየተከሠተ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ያሳያል ብዬ ያመንኩበትን ስንኞች በማቅረብ ነው፡፡
---- በእሱ ውድቀት እናንተ እርካብ ብትመቱ
በብሶቱ ብትፈይዱ
በመክሊቱ ብትነግዱ፤…
ይህ ፍጹም ባድማ፣ ይህ ፍጹም ድቅድቅ ጨለማ
እሚበራ እንዳይመስላችሁ በእናንተ የይስሙላ ቁራጭ ሻማ፡፡
ግን መጋረጃው ያልተነሣ ተውኔት፣
ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ፣ አለውና ጨለማ
           ነፋስ - እሳት ገሞራን፣ ሊታቀፍ ይችላልና ጠፍ ባድማ
ዐይን ያለው ይይ!
ልብ ያለው ያስተውል!
ጆሮ ያለው ይስማ!
********   **********
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ  መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

Read 10533 times
Administrator

Latest from Administrator