Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 05 March 2012 14:36

ሴባስቶፖል ሲኒማ በ4 ሚሊዮን ብር እንደገና ተገነባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የመታሻ አገልግሎት የሚሰጡ ወንበሮች ተገጥመውለታል

ሴባስቶፖል ሲኒማ ቤትን በተመለከተ በየጊዜው ከተመልካች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ያስጨንቁት እንደነበር የገለፀው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ ምንም እንኳን በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚገኘው ሲኒማ ቤት በኪራይ የተገኘ ቢሆንም ለፊልም ተመልካቹ ምቾት ለመስጠት ሲል በ4 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደገና ማደሱን ለአዲስ አድማስ ተናገረ፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ሲኒማ ቤት ለሲኒማ ቤት ምቹ ያልሆኑ ወንበሮች የታጨቁበት፣ የሰው ትንፋሽ እና የአዳራሹ ሙቀት የሚፈጥረው ወበቅ ተመልካቹን ሰላም የሚነሳ ነበር፡፡

እንዲያም ሆኖ በሌሎች ሲኒማ ቤቶች አዳዲስ ፊልሞች ሲወጡ ያለውን የተመልካች ሰልፍ በሴቫስቶፓል ሲኒማ ቤትም የሚኖር ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ተመልካቹ ቦታ ባለማግኘቱ ሲመለስ ማየት የተለመደ ክስተት ነው፡፡

ላለፉት ስድስት ዓመታት ለፊልም አፍቃሪዎች ፊልም ማሳየት እና ለሌሎች የስብሰባ አዳራሽ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ይኸው ሲኒማ ቤት፤ ለሁለት ወራት ያህል በዝግ ሲያደርግ የነበረውን እድሳት አጠናቆ በዛሬው ዕለት ለተመልካች ክፍት እንደሚያደርግ አርቲስት ቴዎድሮስ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

ሲኒማ ቤቱ ከዚህ ቀደም “መቅደላ”፣ “ቋራ” እና “የተዋበች እልፍኝ” የተሰኙት አዳራሾችን በመጠቀም አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር የገለፀው አርቲስት ቴዎድሮስ፤  የ”መቅደላ” እና የ”ቋራ”ን አዳራሽ እድሳት ቢያጠናቅቅም የ”ተዋበች እልፍኝ” የተባለው አዳራሽ ግን ገና በግንባታ ላይ እያለ የግንባታ ፈቃድ የለውም በሚል ለአምስት ወራት ያህል ግንባታው ተቋርጦ መቆየቱን ይናገራል፡፡

የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ላይ ለ10 ዓመት ተከራይቶት ለሴባስቶፖል እንዳከራየው ገልፆ በውሉ መሰረትም መንግሥት አፍርስ ባለው ጊዜ ሊያፈርስ፤ እስከዚያው ግን ሊሠራበት ተስማምቶ እንደያዘው ገልጿል፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረትም መነሳት ሲፈለግ በቀላሉ በሚነሱ ቁሳቁሶች ለመገንባት መሰረቱን ካወጣ በኋላ ክልከላ ስለተደረገበት ግንባታውን አቁሞ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሁለቱ አዳራሾች ከሁለት ወር በላይ ቢዘጉ አሁን ካደረሱት ኪሣራ የበለጠ ኪሳራ ሊያደርሱ እንደሚችሉ የተናገረው አርቲስት ቴዎድሮስ፤ ሌሎቹ ግን ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ስለተጠናቀቀ በዛሬው ዕለት ሥራ እንደሚጀምሩ ተናግሯል፡፡

መቅደላ የተባለው አዳራሽ፤ የመደበኛ ተመልካች ወንበሮች ከአሜሪካ የተገዛ ሲሆን ቀደም ሲል የነበረው የመግቢያ ዋጋ ላይ አምስት ብር ተጨምሮባት 30 ብር ሆኗል፡፡

በተጨማሪም ከሌላ ቦታ የሚመጣውን እና ከእራሱ ክፍል የሚያወጣውን ድምጽ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር የድምጽ ማስወገጃ የተገጠመለት ሲሆን ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገባን ሙቀት የሚያስቀር እና ውስጥ ያለውንም ሙቀት የሚያቀዘቅዝ መሣሪያ ተገጥሞለታል፡፡

መደበኛውን ወንበር ለማይፈልጉ ተመልካቾች በ50 ብር በልዩ ወንበር ከፍ ብለው የሚቀመጡበት መቀመጫ በተለመደው አጠራር (VIP) የተዘጋጀላቸው ሲሆን፣ “ክላውድ ናይን” የተባለ በአንድ ጊዜ 15 ሰዎች ብቻ የሚቀመጡበት ክፍልም በአዳራሹ ተካቷል፡፡ 200 ብር በመክፈል በዚህ ክፍል ተቀምጠው ፊልም ለማየት ወደ አዳራሹ የሚሄዱ ተመልካቾች መቀመጫዎቻቸው የመታሻ (Massage) አገልግሎት የሚሰጡ ወንበሮች እና “ምን ልታዘዝ?” የሚሉ አስተናጋጆች እንደሚኖሩት ባለቤቱ ተናግሯል፡፡

“በዚህ ክፍል የሚቀመጡ ተመልካቾች እነሱ ሌሎችን ያያሉ እንጂ ማንም ሰው እነሱን አያያቸውም” ብሎናል - ቴዎድሮስ ተሾመ፡፡ እነዚህ 15 ወንበሮች እያንዳንዳቸው ከ11ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ መገዛታቸውንም አርቲስቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ከእድሳቱ በፊት 400 ወንበር ብቻ የነበረው መቅደላ አዳራሽ የቪ.አይ.ፒ እና ክላውድ ናይንን ጨምሮ 500 ወንበሮች ሆነዋል፡፡ ቀደም ሲል 330 መቀመጫ የነበረው ቋራ አዳራሽ ደግሞ 400 ወንበሮች እንደተገጠመለት አርቲስት ቴዎድሮስ ተናግሯል፡፡

በስፍራው ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች ከሞያው የተገኘውን ገቢ መልሶ ለሞያው አገልግሎት ማዋሉ ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

 

 

Read 2906 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:37