Monday, 29 August 2016 10:17

ሰማያዊ ፓርቲ ህዝባዊ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

 ፓርቲው በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቷል
                        
   ሰማያዊ ፓርቲ በወቅቱ የሀገሪቱ ችግር ላይ መንግሥት፣ ተቃዋሚዎች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት በጋራ ህዝባዊ ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ፡፡ በሌላ በኩል በፓርቲ የውስጥ ችግር ሲናጥ የቆየው ሰማያዊ፤ የፓርቲውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለመስከረም 14 ቀን 2009 ዓ.ም መጥራቱን አስታውቋል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤውን የጠራው ከፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ባገኘው ይሁንታ መሰረት፣ የፓርቲው የኦዲት ምርመራ ኮሚሽን መሆኑን የሰማያዊ  ም/ፕሬዚዳንት አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው የኦዲትና ኢንስፔክሽን እንዲሁም ብሄራዊ ም/ቤቱ ሪፖርት የሚያቀርቡ ሲሆን ከሪፖርቱ በመነሳት ውይይቶች እንደሚደረጉ ያስረዱት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ተጠሪ አቶ አበራ፤ የፓርቲው የወደፊት አቅጣጫ በጉባኤው  የሚወሰን ይሆናል ብለዋል፡፡ የአመራር ምርጫ ይካሄድ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ አበራ ገብሩ፤ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚለው በጠቅላላ ጉባኤው እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣በአሁኑ ወቅት  የሚገኙት በአሜሪካ ሲሆን ለጉባኤው ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ አበራ፤ ሆኖም እሳቸው ቢገኙም ባይገኙም ጠቅላላ ጉባኤው መደረጉ አይቀርም ብለዋል፡፡

Read 3370 times