Sunday, 21 August 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by 
Rate this item
(6 votes)

· ሳንፈራረጅ በውይይት ችግሮቻችንን መፍታት አለብን
· ጥያቄዎች ሳይወሳሰቡ በጊዜ መፈታት አለባቸው
· ህዝብ መተንፈሻ ሲያጣ አደባባይ ይወጣል

“ኢትዮጵያዊነት ላይ ስራ አልተሰራም”
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የኢኮኖሚ ባለሙያ)

ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት የህዝብ ድምፅ    መሰማት አለበት፡፡ የህዝብ ድምፅ በሚሰማበት ጊዜ በተለይ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲፈልግ ለመንግስት ማሳወቅ ያስፈልጋል። ይሄ በሰለጠኑ ሀገራትም የሚደረግ ነው፡፡ መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ነው ይህ የሚሆነው፡፡ እኛ ሀገር አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ራሱ እንደሚናገረው የሙስና መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በተለይ ወጣቱ የስራ እድል አለማግኘቱ፣ መንግስት ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ለሚወጣው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የተማረ ኃይል የስራ እድል አለመፍጠሩ ----- በሀገሪቱ ካሉ ወቅታዊ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በዋናነት በህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ የተጠቀሰው የማንነት ጉዳይ እየተስፋፋ ሄዶ የት ነው የሚደርሰው የሚለው አሳሳቢ ነው። ህገ መንግስቱ የማንነት ጥያቄን እስከፈቀደ ድረስ መንግስትም ማክበር አለበት፡፡ ግን እኔ እንደማስበው ከሆነ፣ እኛም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሆነን ካነሳናቸው ጥያቄዎች መካከል የመሬትና የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸው ባህላቸው ተከብሮላቸዋል፡፡ ግን ይሄ ከተረጋገጠ በኋላ “ኢትዮጵያዊነት” የሚለው ላይ ስራ አልተሰራም፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን የሚለውን በተለይ አዲሱ ትውልድ እንዲያወቀው የማድረጉ ጉዳይ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ሌላው የሰብአዊ መብት አከባበር ጉዳይ ነው፡፡ ትልቁ የመንግስት ስራ ያለው ወረዳዎች አካባቢ ነው፡፡ የመሬት፣ የፍትህ፣ የፀጥታ የመሳሰሉ ጉዳዮች በቀጥታ ከህዝቡ ጋር በሚገናኙት በነዚህ የወረዳ አመራሮች እጅ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ሰዎች ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ መንግስት ልማቱን የሚያቀነባብሩትና ከህዝቡ ጋር በቀጥታ የሚገናኙት ወረዳዎችና ዞኖች መሆናቸውን በመገንዘብ፣ በከፍተኛ ደረጃ ብቃት ያላቸው ሰዎች መመደብ አለበት፡፡ ከማንም በላይ እነዚህ ሰዎች ህዝቡን አዳምጠው ምላሽ የሚሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ በክልል ወረዳ ድንበሮች አካባቢ ያለ ግንኙነትና የልማት ሁኔታዎችን ብቃት ያላቸው ሰዎችን በመመደብ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም፤ በኦሮሚያ በደረሰው ጉዳይና ባጋጠመው ችግር ይቅርታ መጠየቃቸው በራሱ መንግስት ህዝቡን እያዳመጠ ነው እንድል ያደርገኛል፡፡ ከዚያም አልፎ በመግለጫዎች የህዝብን ጥያቄ እያዳመጠ መሆኑን ለመገንዘብ ያስችላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ፊንፊኔ ዙሪያ ማስተር ፕላን እንዲቆም ማድረጉ ሌላው ትልቁ ነገር ነው፡፡
ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ብዙ አይነት ናቸው፡፡ አንዳንዱ የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ቅማንት፣ ወልቃይት የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ በቀላሉ መፈታት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ በመንግስት ደረጃ ደግሞ በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉት ጥያቄው ቢገባቸውም፣ በቀዬው ያሉት ባለስልጣናት ግንዛቤው ይኖራቸው ይሆን የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደርና በሙስና ጉዳይ ላይ ዋና ተዋናይ ሊሆኑ የሚችሉት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ነፃ ፕሬስ ናቸው፡፡ ነፃ ፕሬስ በተለይ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ተግባራዊ አድርጎ፣ እንዲህ ያሉ ንቅዘቶችን መርምሮ ማውጣት አለበት። በተለይ ሙስና ላይ ብዙ ሊሰሩ ይገባል፡፡ ግን ይሄን ለማድረግ አሁን ያሉት ነፃ ሚዲያዎች አቅም ተፈጥሮላቸዋል ወይ የሚለው የኔም ጥያቄ ነው፡፡ በሽግግሩ ጊዜ ወደ 90 ጋዜጦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ጋዜጦች ሁሉንም ነገር በድፍረት ያወጡ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እያነሱ መጥተው አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ አሁን እንደምናየው ቅዳሜና እሁድ የሚወጡ ጋዜጦች፤ በማተሚያ ቤት ችግር ለረቡዕ ነው እየደረሱ ያሉት። መንግስት ይሄን የሚዲያ ዘርፍ ማነቆዎች መፍታት ይገባዋል፡፡
ህዝብ የታመቀ ችግር ሲመጣ ነው ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው፡፡ መተንፈሻ ሲያጣ አደባባይ ይወጣል። እነዚህ ነገሮች ወደ ንብረት ውድመትና የህይወት ጥፋት እንዳይሄዱ ጥንቃቄ ይሻል፡፡ ምናልባትም እንደ ደቡብ ሱዳን፣ በአራት ወገን ጦርነት ውስጥ እንዳለችው ሱዳን (ኮርዶፋን፣ ዳርፉር፣ አቢዬ፣ ብሉ ናይል-----ጦርነት ላይ ናቸው)፣ ሶማሊያ ወዘተ-- እንዳንሆን ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ተቃውዎችም ሲነሱ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ሳይፈታተኑ መንግስት ማስተካከል ያለበትን ነገር ቢያስተካክል፤ መቀየር ያለበት ነገር ቢቀይር፤ የተቃውሞ ኃይሎችም ራሳቸውን አደራጅተው፣ ህዝቡን አሳምነው የመንግስትን ስልጣን በሰላማዊ ምርጫ የሚይዙበት አካሄድ ነው መከተል ያለባቸው፡፡ አሁን በሀገሪቱ ያሉት ፓርቲዎች 90 ቦታ የተከፋፈሉ፣ አንድ አጀንዳ ይዘው መውጣት ያልቻሉ ናቸው፡፡  የ97 ምርጫ ጊዜ የቅንጅት ኃይሎች፣ በፓርላማው 172 ያህል ወንበር ነበር ያገኙት። የእነሱ ወደ ፓርላማ አለመግባት የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ክፉኛ የጎዳው ይመስለኛል፡፡ ያኔ ህዝቡ መርጧቸው ፓርላማ አለመግባታቸው፣ብዙዎችን ተስፋ አስቆርጧል፡፡ አሁን ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ የሚናገረው ስለከፋውና ስለቸገረው ነው፡፡
በአረብ ሀገራት በእነ ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ በመሳሰሉት ሲካሄድ የነበረው አመፅ በሶሻል ሚዲያ ብቻ አልነበረም የተመራው፡፡ እርግጥ ነው ሶሻል ሚዲያ አገልግሎት ነበረው፡፡ ዋናው ግን የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት የሚባሉ ከ50 ዓመታት በላይ ሲደራጁ የቆዩ ኃይላት ነበሩ አመፁን በባለቤትነት የመሩት፡፡ እኛ ሀገር ዋናው ችግር ሀገር ሳይፈርስ ፀጥታ ሳይደፈርስ፣ የህዝብ ህይወት ሳያልፍ፣ ንብረት ሳይጠፋ ሰላማዊ የመንግስት ስልጣን ሽግግር ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለው ነው። ተቃዋሚዎች ይሄን ለመፍጠር አስበው መደራጀት ያስፈልጋቸዋል። ምናልባት የቅንጅት ምሳሌ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ህዝቡ ብቻ የሚንቀሳቀስ ከሆነ የትም አያደርስም፤ ሀገር ነው የሚያፈርሰው። መንግስት ደግሞ የሀገሪቱንና የህዝቡን ፀጥታ ማስከበር አለበት፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ከመደረጉ በፊት ለመንግስት ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ መንግስትም እንዲህ ያሉ ሰልፎችን መፍቀድ አለበት። ምክንያቱም በሌላ መድረክ ሊሰማ የማይችለውን የህዝብ ቅሬታዎች የሚሰማበት መድረክ ይሆናል፡፡
እነ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን የሚያወጡት በስልክና በመሳሰሉት በሚያገኙት መረጃ ላይ ተመስርተው ነው፡፡
ምናልባት እነዚህ ድርጅቶች ሀገር ውስጥ ገብተው የሚከናወኑ ነገሮችን ተመልክተው፣ የሰብአዊ መብቶች መጓደልን ሪፖርት ቢያደርጉ መንግስትን ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ አሁን በውጭ ሆነው የሚያቀርቡት ሪፖርት ችግሩን እያባባሰው ያለ ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ቅሬታ እንዳላቸው ያስታውቃሉ፡፡
መንግስት እነዚህ ሰዎችን በመቅረብ ሀገራቸውን የሚያገለግሉበትን ነገር ማመቻቸት አለበት፡፡ ጥያቄያቸው ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በዜግነታቸው የሚገባውን ክብር ሰጥቶ መንግስት ማነጋገር አለበት፡፡   

==================================

“በውይይት ችግሮቻችንን መፍታት አለብን”
ፕ/ር አህመድ ዘካሪያ (የዓለም እርቀ ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት አመራር)

እኛ እንደ ሀገር ሽማግሌዎች የማረጋጋት ስራ ነው በዋናነት መስራት ያለብን፡፡ መፍትሄውን የሚያወያዩ አካላት ናቸው የሚያስቀምጡት፡፡ እንደ ሀገር ሽማግሌ፣ የህግም የፖለቲካም ስልጣን ስለሌለን የሞራል ጫና የማሳረፍ ሚና ነው የሚኖረን። እኛ ሰላም እንዲሰፍን፣ የተጋጩ እንዲታረቁ ነው የምንጠይቀው፡፡
ጦርነትን አንፈልግም፡፡ የሀሳብ ግጭት ከሆነ በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታል፡፡ ደም መፋሰስ ለዚህች ሀገር አይበጅም፡፡ ህገ መንግስቱን አይቶ እንደገና ማስተካከል የሚያስፈልገው ነገር ካለም ማስተካከል ይገባል፡፡  
አሁን ያለው ጥያቄ ከአስተዳደር ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ይመስላል፡፡ ጥያቄውን ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ መፍታት ያሻል፡፡ የሰለጠኑት ሀገራትም የራሳቸው ችግር አለባቸው፤የመፍትሄ አሰጣጣቸው ነው ከኛ የሚለየው፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ከፈጣሪ ያገኘው ችሮታ የማስተዋል፣ የማመዛዘንና የመፍረድ ኃይልን ነው፡፡ ፈጣሪ እኒህን ከሰጠን የመፍትሄ ምንጮች መሆን አለብን፡፡ ህዝቡን በነዚህ ባህሪዎች ውስጥ እንዲገባ ማድረግ አለብን። ያለበለዚያ እቺ ሀገር ለማንም የማትሆን አገር ትሆናለች፡፡
አሁን ትልቁ ጦርነታችን ረሀብ ነው፤በየጊዜው እየመጣ የሚፈታተነን፡፡ ግን እሱንም ማሸነፍ ያቃተን ይመስላል፡፡ አንዳንዴ ረሀብን ማሸነፍ ስላቃተን ይሆን የምንጣላው ብዬ አስባለሁ። እንደ ኢትዮጵያዊነታችን አንድ የሆንን ህዝቦች፣ እርስ በእርስ የምንናቆርበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ ለኢኮኖሚ በሽታው መድኃኒት ብንፈልግለትና ትንሽ ችግር ባያጣላን ጥሩ ነው፡፡ እኔ መንግስት፤ ህዝብ ለማለት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም መንግስትም ህዝብ ነው፡፡ ከኛው ነው የመጡት፡፡ ሳንፈራረጅ በውይይት፣ በንግግር ችግሮቻችንን መፍታት አለብን፡፡

======================================

“ህገ መንግስቱ ለህዝብ እንጂ፣ህዝብ ለህገ መንግስቱ አይደለም የተሰራው”

አቶ ክቡር ገና

ጥያቄውን ያነሳው አካል በግልፅ ባይወጣም ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ጥያቄዎቹ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆኑ በብዙ ሰዎች የሚንሸራሸሩም ሆነዋል። ስለዚህ መልስ አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ አንደኛ በህዝቡ የተነሱትን ችግሮች መሰረታዊ ምክንያት ሳይሆን ከላይ የሚታዩትን ብቻ ለመቅረፍ ከተጣረ ችግሩ ለጊዜው ጋብ ይላል እንጂ አይጠፋም። በአጠቃላይ አሁን የተነሱ ጥያቄዎች ከጊዜ በኋላ ሊነሱ እንደሚችሉ ይታወቁ የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በሁለት አይነት መንገድ መመለስ ይቻላል፡- በኃይልና  በፖለቲካዊ መፍትሄ፡፡ የኃይል አማራጭ ምን ያህል ምላሽ ይሰጣል የሚለው አጠያያቂ ነው። ፖለቲካዊ መፍትሄ ይሰጥ ከተባለ ግን ረጅም ጊዜ ቢወስድም፣ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መደራደር ያስፈልጋል፡፡ ለአንድ ጥያቄ አንድ መልስ በሚል ብቻ ሊታለፍ የሚችል ችግር አይደለም፡፡ መጀመሪያ መሰረታዊ ችግሩን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄው ከጠያቂዎች ሲመጣ በትክክለኛ መንገድ ስላልመጣ፣በትክክል ላልመጣ ጥያቄ በትክክል ምላሽ ላይሰጥበት ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ መንግስትም ጥያቄው ባይመጣም፣ጥያቄውን ራሱ ፈጥሮ መመለስ አለበት።
ጥያቄዎቹን በአጠቃላይ ስናያቸው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ የአመራር ሁኔታ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊነት፣የሙስና ችግርን በሙሉ የሚያካትቱ ነው የሚመስሉት፡፡ ጎንደር የተነሳውን ጥያቄ ስንመለከት፣ ከግዛት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በጊዜ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ሳይወሳሰቡ በጊዜ መፈታት አለባቸው፡፡ ትክክለኛ ምላሽም ማግኘት አለባቸው፡፡ እንደኔ እነዚህ ብቻ አይመስሉኝም ምክንያቶቹ፡፡ ህዝቡ የመተንፈሻ መድረክ ማጣቱ አንዱ ምክንያት ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ በየ5 ዓመቱ አንዴ ድምፁን እንዲሰጥ ብቻ ነው በምርጫ የሚጠየቀው፡፡ ከዚያ በኋላ መነጋገሪያ መድረክ የለም፡፡ ለምሳሌ አሁን ፓርላማውን ስናይ፣መቶ በመቶ አንድ አካል ሆኖ ሃሳብ እንደተፈለገው እንዳይንሸራሸር አድርጓል። ምላሽ የማያገኙ ነገር ግን በየጊዜው የሚነሱ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ግን ብዙ ጊዜ የሚደረገው መልዕክቱን ትቶ መልዕክተኛውን መደብደብ ነው። እነዚህ ነገሮች ሲደማመሩ ነው ህዝቡ እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስደው፡፡
እንዲህ ያለውን ችግር ያስተናገዱ በርካታ የዓለም ሀገራት አሉ፡፡ በእንዲህ ያለው ችግርም የጠፉ ሀገራት አሉ፡፡ ዩጎዝላቪያ የምትባለው ሀገር ልክ እንዲሁ በዘር በብሄር ተለያይታ፣ኋላ ላይ በ1980 ከሀገራት ዝርዝር ጠፍታለች፡፡ ከዚህ እኛም መማር አለብን፡፡ ህገ-መንግስቱ ለህዝብ እንጂ ህዝብ ለህገ-መንግስቱ አይደለም የተሰራው፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎቹ በሙሉ በፍርሃት ሳይሆን በግልፅ መውጣት አለባቸው፡፡ የችግሩ ፈቺ የተባለው አካልም ከህዝቡ ሳይጠብቅ ራሱ ጥያቄዎቹን ፈጥሮ ለመፍታት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው ሁሉም በእኩል ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት ሲረባረብ ብቻ ነው፡፡

Read 6816 times