Sunday, 21 August 2016 00:00

ኢዴፓ የመንግስት ሚዲያዎችንና የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤትን አስጠነቀቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

የጋራ ም/ቤቱን ሊለቅ እንደሚችል ፓርቲው ገልጿል

በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶችን አስመልክቶ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች የመንግስት ሚዲያዎች አዛብተው ለህዝብ እያቀረቡ ነው ሲል የተቸው ኢዴፓ፤ የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤትም ከፓርቲው እውቅና ውጪ አቋሞችን በማንፀባረቅ ደንብ እየጣሰ ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው ለአዲስ አድማስ በላከው ደብዳቤ እንዳመለከተው፤ ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 6 በሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን የሰጠውን መግለጫ ኢዜአ፣ ፋና፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና የአማራ ብሄራዊ ክልል ቴሌቪዥን ይዘቱን አዛብተው በማቅረብ፣ ህዝብ ስለ ፓርቲው ያለው አቋም እንዲናጋ ማድረጋቸውን ጠቁሞ፤ የሚዲያ ተቋማቱ አሰራራቸውን እንዲፈትሹና እንዲያስተካክሉ አሳስቧል፡፡
በእለቱ ኢዴፓ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶች፣ በውይይት ሰላማዊ መፍትሄ ማግኘት አለባቸው የሚል አቋም ማንፀባረቁን የጠቆሙት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ፤ የተጠቀሱት የመገናኛ ብዙኃን ግን “ፓርቲው ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት የለውም” ብሏል በማለት በመግለጫው ላይ ፈፅሞ ያልተጠቀሰ ዘገባ አስተላልፈዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ሰንደቅ አላማን በተመለከተም ኢዴፓ ሰልፈኞቹ የያዙትን ሰንደቅ አላማ እንዳወገዘ ተደርጎ በዘገባዎቹ ቀርቧል ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ ፓርቲያችን የሰንደቅ አላማ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በህገ መንግስቱም መሻሻል ያለባቸው አንቀፆች አሉ ብሎ ያምናል፤ ሰንደቅ አላማውም ለህዝብ ምርጫ መተው ነው ያለበት በማለት የኢዴፓን አቋም ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲው አባል የሆነበት የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 10 በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፤ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የወሰደው አቋም ኢዴፓ ልዩነት ያንፀባረቀበት እንደነበር ተመሳሳይ አቋም እንደያዘ ተደርጎ መዘገቡ የም/ቤቱን ደንብ የጣሰ ነው ብሏል። ም/ቤቱ ይህን በ3 ወር ጊዜ ውስጥ የማያስተካክል ከሆነ ኢዴፓ ከም/ቤቱ እንደሚወጣ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Read 5624 times