Sunday, 21 August 2016 00:00

የድሬዳዋ 10ኛ ዓመት የጎርፍ አደጋ መታሰቢያ ስነ- ስርዓትን አስመልክቶ ከድሬደዋ አስተዳደር የተሰጠ ምላሽ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም በወጣው የጋዜጣችሁ እትም ላይ ‹‹የድሬዳዋ 10ኛ ዓመት የጎርፍ አደጋ አከባበር ከፍተኛ ቅሬታ አስነሳ›› በሚል ርዕስ በትክክለኛ መረጃ ላይ ሳይመሰረት ለቀረበው ዘገባ እንደሚከተለው ምላሽ ለመስጠት እንወዳለን፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ሌሊት በከተማው ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ የበርካታ ሰዎች ህይወት የቀጠፈና በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች መጠለያ ማጣትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነበትን ቀን ከዚህ በፊት በሐይማኖት ተቋማት፣ በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ማህበራት በየዓመቱ ሲከበር መቆየቱ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ የዘንድሮውም የአደጋውን 10ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ፤ አስተዳደሩ ለተጎጂዎች ያለውን አጋርነት  በልዩ ሁኔታ እንዲታሰብ ለማድረግና የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ለመፍታት በአስተዳደሩ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው በማድረግ፣ከአደጋው ስጋት ተላቆ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ ማድረግን ያለመ ተግባር በመሆኑ፣ ይህን ቅዱስ ዓላማ ከሚደግፉ ድርጅቶች ጋር በመሆን አክብሯል፡፡
በዚሁ የተቀደሰ አላማ መሰረት ነው፤‹‹በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችን ሁሌም እናስባለን፤ስጋቱንም ለመቀነስ ተግተን እንሰራለን›› በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንዲከበር የተደረገው፡፡ በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይም በድሬደዋ የጎርፍ አደጋና ጎርፉንም ለመቀነስ ባለፉት አስር ዓመታት በተሰሩት ስራዎች ዙርያ፤ ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ሰራ አመራር ኮሚሽን የተዘጋጀ ጽሁፍ እንዲሁም በስነ ልቦና ባለሙያ የቀረበ  ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርቦ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ተጋባዥ እንግዶችና የአስተዳደሩ ኃላፊዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በሌላ በኩል የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ሊቀንሱ ከሚችሉ ተግባራት አንዱ በሆነው የችግኝ ተከላ ላይ የአስተዳደራችን ነዋሪዎች፣ የሰራዊት አባላት፣ ታዋቂ የሀገራችን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ከ4ሺህ በላይ ችግኞችን የተከሉ ሲሆን በጎርፉ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ግለሰቦች ያሉበት ሁኔታ የተጎበኘና በአስተዳደሩ በወቅቱ የነበረውን አደጋ የሚያስታውሱና የሚዘክር ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች የተሳተፉበት የፊልም ምርቃትና የኪነ-ጥበብ ስራዎች በማቅረብ እንዲታሰብም ተደርጓል፡፡ በዚህም የአስተዳደሩ ኃላፊዎችና የአገሪቱ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በየዝግጅቱ ላይ በመገኘት ለአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች አጋርነታቸውን ማሳየት ችለዋል፡፡ በዚህም የተሳካ የአብሮነትና ፍቅር የተንፀባረቀበት የማይረሳ ቀን ሆኖ ተጠናቋል፡፡
እውነታውና አላማው ይሄ ሆኖ ሳለ ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃዎች ባልቀረቡበት የአስተዳደሩን የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የፍቅርና ማንንም አግላይ ያልሆነ እንዲሁም የህዝቡን ባህልና እሴት የሚሸረሽርና መልካም ስማችንንና ገፅታችንን የሚያበላሽ ፅሁፍ በጋዜጣችሁ ላይ ወጥቷል፡፡ በፅሁፉ ለወጡት ለእያንዳንዱ ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ ባይሆንም ለዋና ዋናዎቹ በመረጃ ላይ ላልተመሰረቱት ሃሳቦች መረጃ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ጋዜጠኛዋ የጎርፍ አደጋውን 10ኛ ዓመት አስመልክቶ 13 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መታሰቢያ ተደርጓል በማለት ፅፋለች፡፡ የጠቀሰችው የቁጥር አሃዝ ከየት የመረጃ ምንጭ እንደተገኘ ያልገለጸች ሲሆን መረጃው የግለሰቦች ጥያቄና ቅሬታ ምንጭም ከሆነም በግልጸኝነት ከሚመለከተው አካል ተጠይቆ መረጃው መሰረተ ቢስ መሆኑ ምላሽ የተሰጣት ቢሆንም፣ ይህን መግለጽ ለምን አልተፈለገም? በተጨማሪም አስተዳደሩ ከህዝቡ የሚነሱትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ለሁለት ቀን ፕሮግራም 13 ሚሊዮን ብር ያወጣል ብሎ ማሰቡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሌላው አደጋው ከፍተኛና ሰፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን የነካካ ከመሆኑ አንፃር ምን አልባትም ሁሉም ተጎጂዎች በመታሰቢያ ቀኑ ተካትተው ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን 3 ተጎጂዎችን ብቻ አናግሮ፣ ከፍተኛ ቅሬታ አስነሳ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በ10 ሺዎች ባፈናቀለና ከመቶዎች በላይ የሚቆጠር ሕይወት ለቀጠፈ አደጋ የ3 ሰዎች ሀሳብ ብቻ ተወስዶ የአብዛኛውን ተጎጂ ባልወከለ ሁኔታ ከፍተኛ ቅሬታ አስነሳ በሚል ርዕስ ሰጥቶ መፃፍ፣ ከጋዜጠኝነት ፅንሰ ሃሳብ ጋር የሚጣረስና ስነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው ብለን እናምናለን፡፡
ሌላው አርቲስቶችን በባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሰብስቦ በማስጨፈር መከበሩ ተጎጂዎችን ማሳዘኑን ገልጻለች። ነገር ግን በየሆቴሉ ጭፈራ መካሄድ አለመካሄዱን ከአዘጋጆቹ ማጣራት ተገቢ ነበር፡፡ ታዋቂ የሀገራችን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በፕሮግራሙ የተገኙበት ዋና ዓላማ፣ አደጋው በደረሰ ጊዜ ተጎጂዎችን በመልሶ ማቋቋም ወቅት በአካል ተገኝተው ማጽናናታቸውና ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን አሁንም  አስተዳደሩ በዘላቂነት የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ባላቸው አቅም ሁሉ ለመደገፍና ለድሬደዋ ህዝብ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽና ለማገዝ እንጂ ዘጋቢዋ  እንዳሉት ለመጨፈር አይደለም፡፡
በሌላ በኩል የጎርፍ ተጎጂዎችን በማቋቋም ረገድ በርካታ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን አስተዳደሩ ከጎርፍ አደጋ በኋላ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፎች አድርጓል፤ ዋና ዋናዎቹም 14 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 699 የአጣዳፊ ቤቶች ተገንብተው ለተጎጂዎች ተላልፈዋል፤ቀሪዎቹን በካምፕ የነበሩ ለእያንዳንዳቸው የ6 ወራት የቤት ኪራይ በመስጠት ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። የግል መኖሪያ ቤታቸው በከፊል ለወደመባቸውና ጠግነው ሊኖሩበት ለሚችሉት በመሀንዲስ ግምት መሠረት የጥገና ወጪ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ተደርጓል። አደጋውን በዘላቂነት ለመቀነስ ከ10 ኪ.ሜ በላይ ሪቴይንግ ዎል ማሰራት የተቻለ ሲሆን ዘንድሮ  በድጋሚ በመጣ ጎርፍ በተወሰነ አካባቢዎች በግድቡ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት በድጋሚ ጥገና ተደርጎለታል፡፡ የጎርፍ መሄጃ የሆኑትን የደቻቱና ጎሮ ወንዞች ግራና ቀኝ ተከትሎ  የጎርፍ መከላከያ ተሰርቷል፤ በተጨማሪም  የመልካጀብዱ መሄጃ ድልድይም በቅርቡ በጣለው ከባድ ዝናብ በጎርፍ ጉዳት የደረሰበት እውነት ቢሆንም፣ ከድሬዳዋ መልካጀብዱ የ8 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን በ2009 በጀት ዓመት ከሚሰሩ አራት መንገዶች አንዱ ሲሆን  በአስፓልት ደረጃ በአዲስ የሚሰራና ቅድመ ሁኔታው ተጠናቆ ስራው ሊጀመር ያለበት ሁኔታ እንጂ የአስተዳደሩ ቸልተኝነት ተደርጎ መቅረቡ ትክክል አይደለም፡፡  
አስተዳደሩ የጎርፉን አደጋ ለመቀነስ ባሰራው ጥናት ላይ ተመስርቶ ከከተማዋ አጎራባች ወረዳዎች የሚመጣውን የጎርፍ ጉልበት ለመቀነስ ባለፉት 5 ዓመታት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት፣ ከ75 በመቶ በላይ የነበረው የአካባቢ መራቆት ወደ 33 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የተቻለ ሲሆን በቅርቡ በኢሊኖ ሳቢያ የተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ጎርፍ በከተማዋ ላይ ያስከትል የነበረውን ከፍተኛ አደጋ መቀነስ ተችሏል፡፡ ዘጋቢዋ ይህን የአስተዳደሩን ተግባር ለማወቅ የፈለገች አትመስልም፡፡
ለእያንዳንዱ ሀቅን መሰረት ያላደረገ ፅሑፍ ምላሽ እየሰጡ መሄድ አስፈላጊ ነው ባንልም በድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪው ዘንድ ያለውን የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልና እሴት ካለማወቅና ካለመረዳት እንዲሁም ተቆርቋሪና አሳቢ መስሎ የምንታወቅበትን አብሮ የመኖር ባህል ለመጉዳት መነሳሳት በቀላሉ የሚሳካ አይሆንም፡፡ ዘጋቢዋ ለጽሁፉ በቂ ትኩረት ያለመስጠቷን የሚያሳየው የአስተዳደሩን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ስም እንኳን በትክክል አጥርታ ያለመፃፏ ነው፡፡
በመጨረሻም ጎርፍን በዘላቂነት መከላከልና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የአስተዳደራችን ትኩረት ከመሆኑ ባሻገር፤ ከተማችን ድሬደዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣መልካም አስተዳደር የሰፈነባት በንግድ፣ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስቀመጠችውን ራእይ እናም የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ኮሪደር እንድትሆን በፌደራል መንግስት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት፣ በቀጣይ ግዙፍና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚገነቡባት፣ ለሀገራችን ህዝቦች ሰፊ የስራ እድል የምትፈጥር ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም ከዚህ አኳያ ያለተጨባጭ ማስረጃ የሚቀርቡ ፅሁፎች የአስተዳደሩን በጎ ገፅታ ከማጉደፍ በተጨማሪ የአስተዳደሩን ህዝብ ካለማክበር የሚመነጭ እንዲሁም የአዘጋጆቹን ልፋትና ድካም ሞራል መንካት እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡  
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር

Read 2446 times