Sunday, 21 August 2016 00:00

‹የህክምና ሥህተት›

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(11 votes)

    አያሌው ጤነኛ ይሁን ወፈፌነቱን ያለየለት አወዛጋቢ ሰብእና ነበረው፡፡ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባት ባለቤቱ ትዝታ፣ ጥለው ከሄደች አመታት ተቆጠሩ። ‹‹መሄድዋ ሳይሆን እስካሁን መቆየትዋ ነው የሚገርመው!” “በልጇ ህሩይ ላይ እንዴት ጨከነች›› ያሉም ነበሩ - አዛኝ ቅቤ አንጓች ጎረቤቶቿ፡፡
ህሩይ ለእናቱ ያለው ጥልቅ ፍቅር በአያሌው ዘንድ የጥላቻ ጥንስስ ጠንስሶበታል፡፡ ጥንስሱም እየፈላ ነበር፡፡ በተለይ አያሌው መጠጥ ሲጠጣ አብሾው ይነሳበትና የነገር መአቱን ልጁ ላይ እንደ ዶፍ ያወርደዋል…… “ዘረ እብድ ነኝ! የማወርስህ ሀብቴን ሳይሆን እብደቴን ነው›› ይለዋል፡፡  
…. ህሩይ 15 ዓመት ሲሞላው እብደት መሰል ጭላንጭሎች ታዩበት፡፡ ጥልቅ የሆነ ድብርት …. ራስን የማጥፋት ሀሳብ ቦግና ብልጭ! ይሉበት ጀመር። ‹ራስን ማጥፋት- ጊዜያዊ ለሆነ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሄ!› የሚል ሀሳብ፣ ከአንደኛው የአእምሮው ጥግ ብቅ እያለበት ተቸገረ፡፡ ራሱን ፈራው፡፡ ከአባቱና ከፊቱ ከተደቀነበት እብደት ሽሽት ከደሴ ወደ አዲስ አበባ ጠፋ - አጎቱ ዘንድ፡፡ ዘብጥያ እንደ መውረድ የሚቆጠር ነበር፡፡ ከአእምሮአዊ ስቃዩ ፋታ ቢያገኝም በርሃብ አሳሩን አይቶአል። አብዛኛውን ጊዜ የሚላስ የሚቀመስ ቤቱ ውስጥ አይኖርም፡፡ የምግብ ዘር ቤቱ ሲኖር፣ ቀላዋጭ ጎረቤቶቹ ከየት መጡ ሳይባል እንደ ተምች መአዱ ላይ ይሰፍሩበታል፡፡ ቀላዋጭነት በሰፈሩ አያሳፍርም - እንደ ማህበራዊ ሕይወት የሚታይ ነው፡፡ አጎቱም ቢሆን ጎረቤት እንቁላል ተሰብሮ ሲመታ፤ የእንቁላሉን የመጠበስ ሂደት በንቃት ተከታትሎ፣ ደቂቃዎችን አስልቶ፣በሽርፍራፊ ሰከንድ እንቁላሉ ትሪው ላይ ሲቀርብ ከች! የሚል ሴረኛ ቀላዋጭ ነው፡፡
ህሩይ የአጎቱ ነገር የማይፈታ እንቆቅልሽ ሆኖበታል፡፡ ምን እንደሚሰራ እንኳን አያውቅም፡፡ አያሌ ሱሶች የተጠናወቱት…. ሱሶቹን ድል ለመንሳት ደፋ ቀና የሚል የሰው ልቃሞ!! ……. አንዳንዴ ተራ የመንደር ጅራሬ ሴት በውድቅት ይዞ ይገባል፡፡ ያኔ ህሩይ ከጎረቤት የማደር ግዴታ አለበት፡፡ ምቾት ፍፁም የማይታሰብበት አሰቃቂ የቅዠት አዳሮች፡፡ አባቱ ከዚህ መሰሉ ቅዠት ብቅ ይልና፤‹‹ዘረ እብድ! አይቀርልህም!›› እያለ በቃጭል ድምጹ ሲዝትበት ህሩይ ብንን ብሎ ይነቃል፡፡ ከዚያ በኋላ እንቅልፍ እሺ አይለውም፡፡ እንዲሁ እንዳፈጠጠ ይነጋለታል፡፡  
ጠዋት አጎቱ ያስመለሰውን የአረቄ ትፋትና ምናምንቴ እጣቢ መድፋት ማፅዳት ይጠበቅበታል። ከዚህ የዘቀጠ ህይወት… የኑሮ አተላ የሚወጣበትን መንገድ ዘወትር ቢያልምም ህይወቱ መውጫው የማይታወቅ ዋሻ ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሰካራም አጎቱ በውድቅት ይዟቸው ከሚመጣው ጭራቅ መሳይ የሴት ፍጡራን አንዷን በሚስትነት አገባ፡፡ የቤቱን ሙያ በደረሰበት አትደርስበትም፡፡ እንደ ባሏ አደገኛ ቀምቃሚ፡፡ ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳሉ - ያውም ከመጠጥ ባህር፡፡ የሴትዋ ወደ ቤት መግባት ለህሩይ እንደ መቅሰፍት የሚቆጠር ነበር፡፡
የአጎቱ ሚስት፤ሲላት የትም ውላ የምታድርበት ጊዜ ነበር፡፡ ዛሬም እንደ ልማድዋ አልመጣችም - ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ቢያልፍም፡፡ አጎቱ አረቄውን እያወራረደ…
‹‹ይቺ ዘልዛላ ዛሬም ማደሯ ነው…. አይ ሴቶች ከነሱ ጋር መኖር ችግር! ያለ እነርሱ መኖር አይቻል! ሴቶች ማለት ልዩ ፍጡራን ናቸው… ከምን አይነቷ ዋልጌ! አለሌ… ጋር ትዳር ብዬ ቤቴን ሲኦል አደረግሁት!?… ›› ሚስቱን እንደ ጥጥ ቦጭቆ ጨረሳት-በሃሜት፡፡ አጎቱ ውሎው ነገር ከበሉ ጠበቃዎች… ከመሰሪ ደላላዎች… ከአሽሙረኛ የመንደር አሮጊቶች ጋር በመሆኑ የእርሱን መርዛማ ምላስ ማንም አይችለውም፡፡
አረቄውን ጎንጨት አደረገና፤ ‹‹ያንተም እናት ብትሆን እህቴ…›› ሲል ጀመረ፡፡ ህሩይ ስለ እናቱ ምን ሊያወራ ይሆን በሚል ነቃ ብሎ ማዳመጥ ጀመረ …
‹‹እናትህም ከሀገር ሀገር የሚያዞር አባዜ ነበረባት … እንዲሁ ብድግ ብላ አንዴ ጅማ፣ ሌላ ጊዜ ድሬደዋ ስትንጦለጦል፣ እሷን ፍለጋ ስንቱን ስቃይ አሳለፍኩት… ደሴ ላይ አያሌውን አግኝታ አንተ እስክትወለድ ድረስ … ይኽው የያዛት አባዜ አለቅ ብሎ ቤቷን ጥላ… ጉድ እኮ ነው…..›› ሲል የእህቱን ትዳር አቆራቆር ከተረከ በኋላ… አረቄውን ጨለጠና፤ ‹‹ህይወት…. ትዳር----አልቃናልህ ያለኝ ምስኪን ፍጡር…. ብዙም ጤንነት አይሰማኝም… እያንዳንዷ የምጠጣት የአረቄ ጠብታ ለእኔ እንደ መርዝ ወደ ሞቴ…››
ህሩይ ነቃ ብሎ፤‹‹ጋሼ መጠጡ ቢቀርብህስ›› አለው፡፡
‹‹አረቄ ማቆም የማይታሰብ ነው፡፡ እንኳን በ40 ዓመቴ በ400 ዓመቴም መጠጥ ስለማቆሜ እርግጠኛ አይደለሁም…. ለዚህ አለም የተፈጠርኩ አይመስለኝም…. ምድር ላይ ምን ጉድ እንደሚገጥመው ሳያውቅ፣ከሰማይ እንደወረደ መላእክት ቅጥአንባሩ የጠፋብኝ! ወይኔ መይሳው - የፒያሳ ልጅ !››
አጎቱ አረቄውን እየጨለጠ መዘላበዱን ቀጥሏል - እኩለ ለሊት ቢያልፍም……  ህሩይ ከወሰደው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ…. ‹‹ዘረ እብድ!!›› የሚለው የአባቱ ቃጭል ድምፅ  አባነነው፡፡ ዳግም መተኛት አልቻለም፡፡ ሊነጋጋ ሲል ሸለብ አደረገው….
በህልሙ እናቱ ከተሸሸገችበት ድብቅ አለም ብቅ ብላ፤‹‹ህሩይ… መጣሁልህ… በል ተነስ ወደ ቤታችን…›› የሚል ድምጽዋን ሰምቶ ብንን አለ። እናቱን የሚያገኝበት ጊዜ ስለመቃረቡ እርግጠኛ ሆነ፡፡ በተስፋ ጢም አለ፡፡ ከዚህ የኑሮ ትቢያ----ኦና ሙት ቤት ነፃ የሚወጣበት.. ሲያውጠነጥን በሩ በሀይል ተንኳኳ፡፡
‹‹ ቤቶች ኧረ ክፈቱ ዘመድ! … ››
እናቱን ሊያገኛት የተቃረበበት ቅፅበት - በሩን ከፈተው፡፡ ክው ብሎ ደነገጠ፡፡ ብርክ ያዘው። በህልሙ ይሁን በእውኑ በመደናበር አባቱ ላይ አፈጠጠ፡፡ በዚህ ማለዳ ከደሴ ይመጣል ብሎ በፍፁም አልጠበቀም፡፡ አያሌው እጅና እግሩ ታስሯል፡፡………     ለይቶለታል፡፡ ከደሴ ይዘውት የመጡት ጎረቤቱ አቶ ነጋሽ ነበሩ፡፡….
አያሌው አዲስ አበባ በመጣ በማግስቱ አማኑኤል ገባ፡፡ ህሩይ አባቱ አይሆኑ ሆኖ፣ አማኑኤል መግባት ቅስሙን ሰብሮታል፡፡ አይኖቹን አባቱ ላይ ተክሎ፣ ከንቱ ቤተሰባዊ ህይወቱን እያውጠነጠነ ነበር……
በድንገት አያሌው ከእንቅልፉ እንደነቃ ብንን ብሎ፤ ‹‹ህሩይ ወደ ቤት ሂድ … እየመሸ እኮ ነው››…. በግርምት አባቱን እንደ አዲስ እያስተዋለ ክፍሏን ለቆ ወጣ፡፡ ለአይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል፡፡…… ወደ ውጪ ለመውጣት ዋናው በር ጋር ሲደርስ ዘበኛው ‹‹ተመለስ!›› ሲል አምባረቀበት፡፡ ህሩይ ግራ ተጋብቶ ሊያስረዳው ሲጠጋው፣ በያዘው አለንጋ ጀርባው ላይ አሳረፈበት፡፡ የአለንጋው ግርፊያ እንደ ኤሌክትሪክ ሰውነቱን ነዘረው፡፡ ‹‹ፈጠን ወደ ክፍልህ!›› ዳግም ላለመመታት ወደ ህሙማኑ ዋርድ ሸሸ፡፡…
ዳጎስ ያለ ፋይል ይዞ በእርጋታ የሚራመድ.. በሙሉ ሱፍ የተሰተረ ወጣት አየና ጠጋ ብሎ በዘበኛው በኩል የገጠመውን ዘርዝሮ ነገረው ….
‹‹ማንም የአእምሮ ህመምተኛ፤ ህመሙን አምኖ ያለመቀበል ችግር ! የፈጠራ ታሪክ ማነብነብ….›› እያለ በምሬት አጉረመረመና ጥሎት ሄደ …..
ታጥቦ የተተኮሱ አንሶላዎችን በጋሪ እየገፋች የምታልፍ ሴት ወይዘሮን አስቆማትና በትህትና ሰላምታውን አስቀድሞ፣ ከአባቱ አእምሮ ህመምተኝነት በመነሳት፣ ዘበኛው የፈጠረበትን መሰናክል አጫወታት፡፡ ሴትየዋ በጥሞና አንገትዋን እየነቀነቀች አዳመጠችው፡፡ ከመሄድዋ በፊት የጠየቀችው ጥያቄ፤‹‹ልጄ! ዋርድ ስንት ነህ?››
ህሩይ በተረት አለም ውስጥ ያለ መሰለው፡፡ አባቱ ወደሚገኝበት ዋርድ ለመሄድ ከመራመዱ በፊት …. ‹‹አዲስ ገቢ ነህ ?›› የሚል ጥያቄ ጆሮ ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡
‹‹ለወጪ ለወራጁ የህይወት ታሪክህን እየተረክ ነው ልበል… በዚህች ደቂቃዎች ውስጥ እንኳን ለሁለት ሰው !.... እያየሁህ ነበር›› አለው ጎልማሳውም የአእምሮ ህመምተኛ፡፡
ህሩይ ለጎልማሳው የገጠመውን ዱብዕዳ አሳጥሮ አጫወተው፡፡
ሰውየው ረጋ ብሎ፤‹‹የለበስከው ፒጃማ ከኛ ጋር ይመሳሰላል…..›› ፒጃማውን ልብ ብሎ አየው - ሰውየው ካደረገው ጋር ተመሳሳይ ነበር….
‹‹በይበልጥ ዘበኛውን ያሳሳተው አንተን የሚመስል ከጅማ የመጣ ቀዥቃዣ ልጅ እግር የአእምሮ ህመምተኛ ጋር ተመሳስለህበት ሊሆን ይችላል - ይህ ግምቴ ነው›› ሰውየው ደንቀፍ ሳይለው ኩልል ባለ ጥርት ያለ ድምፅ ነበር የሚያወራው፡፡ አንዳችም እእምሮአዊ እንከን አይስተዋልበትም፡፡ ሰውየው ቀጠል በማድረግ፤‹‹አጋጣሚ ነው፤ግጥምጥሞሽ.. በቅርቡ ለእንቅርቷ ህክምና ሄዳ ለሀሞት ጠጠር ኦፕሬሽን ስለተደረገች ሴት አልሰማህምን? የህክምና ስህተት ያለ ነው….. ያንተው ግን የህክምና ስህተቱ በዘበኛ መፈጸሙ የህይወትህ ምጸትን ያሳያል›› ብሎ ተንከትክቶ ሳቀ፡፡ ሰውየው ፍፁም ጤነኛ ይመስላል። አሳሳቁ ግን ከጤነኛ ሰው ለየት ይላል - የእብደት ጠረን ይዟል፡፡  
ጨለማ ነግሷል፡፡ አባቱ ወደሚገኝበት ዋርድ አቀና፡፡ ልክ በሩ ጋ ሲደርስ የሆነ ነገር ትዝ ብሎት ሽምቅቅ አለ፡፡ ‹‹ዘረ እብድ !›› የሚለው የአባቱ ድምጽ በእዝነ ህሊናው አቃጨለበት፡፡ ‹‹ቃልህ ተፈጸመ !›› ብሎ ከት እያለ ሳቀ፡፡ ቦግ እና ብልጭ! ድርግም ! ግም ! ….. የእብደት ዋዜማ!!
የበሩን እጄታ ጠምዝዞ ከፈተው፡፡ ወደ ውስጥ ዘለቀ - ወደ አባቱ፡፡         

Read 2689 times