Saturday, 20 August 2016 12:34

የማህጸን በር ካንሰር ሴል አመላካች ... ቁጥር እየጨመረ ነው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  “...ከማህጸን ካንሰር ጋር በተያያዘ እናን በህይወ አልረሳትም። በቤታችን ትልቅ ልጅ እኔ ስለነበርኩ እናን የማስታመም ኃላፊነቱ የወደቀው እኔ ላይ ነበር። እኔም እናን ማስታመም ግዴታዬ ነው ብዬ ስለአሰብኩ ከአጠገብዋ አልተለየሁም። እናም በዚህ ሕመም ምክንያት የነበራት ስቃይ ምንጊዜም ከፊ አይሄድም። እጅግ በጣም መጥፎ በሽታ ነው። እሱዋን ካጣናት ወደ ሰባት አመት ይሆናል። እኔም እናን ከቀበርኩ በሁዋላ ወደሐኪም ቤት ነበር የሄድኩት። ሐኪሞቹም የካንሰር በሽታው በቅርብ ቤተሰብሽ ስለታየ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሻል። በየሁለት ወይንም ሶስት አመት ብትታዪ ጥሩ ነው ስላሉኝ ይኼው አሁን ለሶስተኛ ጊዜ እየታየሁ ነው...”
 ገነት ይልማ - በቤተሰብ መምሪያ አዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ ለምርመራ የመጣች
የማህጸን በር ካንሰር ሴቶችን በእጅጉ የሚጎዳ እና ሕመሙ ሲጀምር ምንም ምልክት የማያሳይ መሆኑ ለብዙዎች ሕልፈት ምክንያት ሲሆን ቆይቶእል። ሕመሙን በመከላከል ረገድ በተለያዩ ጊዜያት መረጃዎች ለህብረተሰቡ ለማድረስ ቢሞክረም በተከታታይነትና በስፋት ባለመዘገቡ ዛሬም ሰዎች ዘንድ ግንዛቤው ብዙም የሰፋ አይደለም። በኢትዮጵያ ያለው አሰራር ምን ይመስላል ስንል ወደቤ ተሰብ መምሪያ አዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ ነበር ያመራነው። ዶ/ር አሸናፊ ምትኩ በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የአዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ ሜዲካል ዳይሬክተር እና ሲ/ር ዘውዴ አበበ በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የአዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ አስተባባሪ ባለፈው ሳምንት እትም ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ተከታዩን ክፍል ዛሬም ያወጉናል።
ጥያቄ፡ የቅድመ ካንሰር ምርመራው የሚደረገው በምን ደረጃ ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡ ከዚህ በፊት ለምርመራ እንጠቀምበት የነበረው ፓፕስሚር የሚባለው ነበር። እሱም ማንኛዋም በመውለድ ክልል ውስጥ ያለች ሴትን የምንመረምርበት የህክምና አሰራር ነበር። አሰራሩም ከማህጸን በር ላይ የፈሳሽ ናሙና ተወስዶ ምርመራውን ለሚያደርገው አካል በመላክ ውጤቱን በሶስት ቀን ውስጥ ማወቅ የሚቻልበት አሰራር ነው። ያንን ውጤት ተንተርሰንም ክትትል ማድረግ ብቻ ነበር የምንሰራው። ምናልባትም ሕክምና የምንሰጠው ከዚያ ጋር ተያያዥነት የሌለው ችግር ከተገኘ ብቻ ነው። የቅድመ ካንሰር ምልክት ከታየ በፊት በነበረው አሰራር ከመከታተል ውጪ የምንሰጠው ሕክምና የለም። አሁን የምንጠቀምበት ግን ቀደም ካለው ምርመራ የተሻለ ሲሆን ይህም የአንድ ቀን ምርመራና የአንድ ቀን ሕክምና ነው። አንዲት ሴት መመላለስ ሳያስፈልጋት ምርመራው በተደረገላት ቀን በዚያው ሕክምናውንም አግኝታ ትሔዳለች። ችግሩ የሌለባት ከሆነም ለዚህ አይነት ምርመራ የምትመጣው ከአምስት አመት በሁዋላ ነው። ይህ እንግዲህ ከጊዜም ከኢኮኖሚም አንጻር እና ሴቶቹም ያላቸውን የጤና ሁኔታ ለቀናት ሳይጠብቁ ምላሽ የሚያገኙበት ስለሆነ በጣም የተሻለ ነው።
ጥያቄ፡ አዲስ የተሸሻለው አሰራር ለሁሉም የእድሜ ክልል ነው? ወይንስ?
ዶ/ር አሸናፊ፡ ማንኛዋም እድሜዋ ከ30-49 አመት የሆናት ሴት አሁን በተጀመረው አዲስ የምርመራ ዘዴ ተመርምራ ችግር እንኩዋን ቢገኝ እንደበፊቱ ወደሌላ የምትተላለፍ ሳይሆን በክሊኒኩ ሕክምናውም መሰጠት ተጀምሮአል። ምናልባትም ይህ በቅርብ የተጀመረውን ምርመራና ሕክምና ለመጠቀም በሶስት ቀን ጊዜ ውስጥ እንኩዋን ወደ ሰማንያ ሴቶችን መርምረን ካንሰር ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሕዋሶችን ክራዮራፒ በሚባለው የህክምና ዘዴ አስተናግደናቸዋል። የህክምናው ዋና አለማ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚባሉ ሕዋሶችን መግደል ነው። ከአንድ አመት በሁዋላ እንደገና ሲታይ በሞቱት ሕዋሳት ቦታ ላይ ሌሎች አዳዲስ ሕዋሳት ተተክተው ስለሚገኙ ያ ካንሰር ሊያስከትል የነበረው ሕዋስ በዚህ መንገድ እንዲጠፋ ይደረጋል። ይህ እንግዲህ አስተማማኝ የህክምና ዘዴ ሲሆን ሴቶቹን ማዳን የሚቻለው ግን የካንሰር ቫይረሱ ብዙ ሳይስፋፋ ቀድመን ከደረስንበት ነው። የማህጸኑን በር ቢያንስ ከ75% በላይ የካንሰር ቫይረሱ ካልያዘው ሕክምናውን መስጠት ይቻላል።
ጥያቄ፡ እድሜያቸው ከ30/አመት በታችእና ከ49/አመት በላይ ለሆኑት ሴቶችስ?
ዶ/ር አሸናፊ፡ የእድሜው ገደብ ሲነሳ ሳይንሳዊ በሆነ መሰረት ነው። አንዲት ሴት ከወንድ ጋር ግንኙነት የምትጀምረው በ18/አመት ወይንም ከዚያም በታች ሊሆን ይችላል። ካንሰር ደግሞ በድንገት ተነስቶ ወዲያውኑ ለሕልፈት የሚዳርግ ስላልሆነ ጊዜ ይሰጣል። ችግር የሚሆነው ሕመሙ ሲጀምር ምልክቱ ስለማይታወቅ በጊዜ ሂደት አስከፊ መሆኑ ነው። ከ49 አመታ በሁዋላ ደግሞ የወር አበባ መቋረጥ ወይንም ማረጥ ወደሚባለው ክልል የሚገባበት ነው። ይህ እድሜ በወሲብ እንቅስቃሴም ረገብ የሚባልበትና ኢስትሮጂን የሚባለው ተፈጥሮአዊ ንጥረ ነገርም የሚጠፋበት በመሆኑ ተጋላጭነታ ቸውን በእጅጉ ይቀንሰዋል ተብሎ ይታሰባል። ካንሰርን ሊያመጣ የሚችለው Human papillomavirus (HPV) የሚባለው የቫይረስ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሁለት ዘሮች 16/እና 18 የተባሉት በተለይ 70% የሚሆነውን የማህጸን በር ካንሰር የሚያመጡ ናቸው። ይህ እንደማንኛውም የአባላዘር በሽታ በወሲብ ግንኙነት የሚተላለፍ ስለሆነ በማንኛውም እድሜ ክልል ያሉት ሁሉ መመርመርና መታከም ይችላሉ።
ሴቶች Human papillomavirus (HPV) በሚባለው የቫይረስ እንዲያዙና ለማህጸን በር ካንሰር እንዲጋለጡ ከሚያደርጉዋቸው ምክንያቶች ውስጥ፡-
ለአቅመ አዳም ወይንም ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱ የግብረ ስጋ ግንኘነት መጀመር
ከብዙ ሰዎች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ
ቶባኮ መጠቀም ሲጋራን ማጨስ
ደካማ የሆነ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም...በኢችአይቪ ቫይረስ መያዝ...ወዘተ
ጥያቄ፡ ለመሆኑ አስቀድሞ ምርመራ የማድረግ ሁኔታ ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ሲ/ በአሁኑ ጊዜ በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ነው ባይባልም የግንዛቤው ደረጃ ግን ከፍ ማለቱን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ይህንንም ለመለካት የሚቻለው ቅድመ ካንሰር ምርመራ የሚያደርጉ ሴቶች ቁጥር በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ነው።
በቤተሰብ መምሪያ አዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ በ2008/ዓ/ም የታዩት ወደ 3854/የሚሆኑ ሴቶች ናቸው።
በ2015/ዓ/ም ወደ 8973 /የሚሆኑ ሴቶች ተመርምረዋል።
የዚህ ቁጥር ልዩነት የሚያሳየን ተመርማሪው ምን ያህል በየአመቱ እየጨመረ እንደመጣ ነው። በዚህም ልክ የካንሰር ሴል አመላካች ውጤት የሚታይባቸው ሴቶች ቁጥርም እየጨመረ መጥቶአል።
በ2010/ዓ/ም ከ1632/ታካሚዎች ውስጥ 38/ሴቶች የካንሰር አመላካች ሴል ታይቶባቸዋል።
በ2015 ዓ/ም ግን ከ8973/ የተመረመሩ ሴቶች ውስጥ 2150/ የካንሰር አመላካች ሴል ተገኝቶባቸዋል።
በዚህ አመት በተጀመረው አዲስ የምርመራ ሂደት በግማሽ አመት ውስት 76/ ሴቶች ተመርምረው 6/የካንሰር ሴል ተገኝቶባቸው ህክምናውን አግኝተዋል።
ስለዚህ በየጊዜው የሚገኘው የተመርማሪዎች ቁጥር እንደመጨመሩም የካንሰር ሴል አመላካች ሕዋስ የሚገኝባቸውም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን መረጃው ያሳያል።
ጥያቄ፡ የማህጸን በር ካንሰር ሕመም ከሚባል ደረጃ ወይንም ከፍተኛ ደረጃ ደርሶአል የሚባለው መቼ ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡ አንዳንድ እናቶች ለምርመራ ሲመጡ የሚናገሩዋቸው ሕመሞች ለካንሰሩ ሴል መስፋፋት ምልክት ናቸው። ለምሳሌም ፡-
የወር አበባ ወቅትን ሳይጠብቅ የደም መፍሰስ ወይንም ወር አበባ ከተቋረጠ ብዙ ቆይቶ ዝም ብሎ የደም መፍሰስ
የጀርባ የእግር ወይንም የማህጸን አካባቢ ሕመም
የክብደት መቀነስ ወይንም የምግብ መውሰድ ፍላጎት ማጣት
መጥፎ ሽታ ያለው ጠረን በብልት በኩል መውጣት
አንድ እግርን ለይቶ ማንቀሳቀስ አለመቻል ወይንም እብጠት ማሳየት የመሳሰሉት ነገሮች ከተከሰቱ ሕክምናውም ከበድ ያለ ሊሆን ይችላል።
ዶ/ር አሸናፊ ምትኩ በስተመጨረሻውም የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል።
“...እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ምልክቶች የሚታዩት ካንሰር ሴሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በሁዋላ ሊሆን ስለሚችል በአጠቃላይ የሚመከረው ማንኛዋም ሴት የግብረስጋ ግንኙነት ከጀመረች በተወሰነ አመት አስቀድማ መመርመር ያስፈልጋታል። በተለይም ከ30-40 ዓመት እድሜ ያላቸው ሴቶች ይህንን በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉትን ህመም አስቀድመው መከላከል እንዲችሉ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቤተሰባቸውም ማለትም በተለይም ባሎች ወንድሞች እንዲሁም አባቶች ጭምር ለዚህ እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ሕመሙ ከከፋ ደረጃ ላይ ሲደርስ የታማሚዎቹ ስቃይ እንዳለ ሆኖ ማስታመምና ምናልባትም በሞት ከተለዩ ቤተሰቡ ምንያህል እንደሚጎዳ አስቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል።”

Read 3233 times