Sunday, 21 August 2016 00:00

የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጥር በካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(25 votes)

ክፍል 1
12 ዓመታትን ባስቆጠረው የመሰለ መንግስቱ ‹‹እግር ኳስን በራድዮ ተመልከቱ›› ቀጥታ ስርጭት ላይ የካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ቋሚ ተሰላፊ ናቸው፡፡ በዳኝነት ዙርያ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ከበሬታን ያተረፉ ፡፡ ባለፈው ሰሞን እንኳን በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ላይ የአርሰናልና ሊቨርፑል ጨዋታ ከኮሜንታተሩ መሰለ መንግስቱ ይሰጡ የነበረውን የማጠቃለያ አስተያየቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ግምገማቸውን፤ አነጋጋሪ ክስተቶች እና ውሳኔዎችን በማንሳት አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
‹‹…ሌላው እጅ ኳስ ብለን ትንሽ ተናጋግረን ነበር፡፡ የ2016 17 የጨዋታ ህግ ላይ በደንብ ወጥቷል፡፡ እጅን ናቹራል ተፈጥሯዊ ብሎታል፡፡ ተፈጥሯዊ በሆነ ንቅናቄ ላይ ኳሷ ሄዳ እጁን ብትነካው… በእጅ የተነካ ኳስ ነው ተብሎ ተጨዋቹ ሊቀጣ አይችልም አሁን፡፡ የድሮው አይደለም፡፡ ህጉ ሙሉ ለሙሉ ተለውጧል፡፡ …. ›› በማለት እያብራሩ
ኮሜንታተሩ መሰለ …‹‹ገና ለገና በእጅ ተነካና ፔናሊቲ መስጠት…. ›› በማለት ጥያቄውን ያቀርባል
‹‹አዎ… ኢንስትራክተሩ ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹…ናቹራል ማለት ምንድነው… የሚነቃነቅ እጅን ማለት አይደለም፡፡ የሚነቃነቅ ስትል ከመሮጥ ጋር በተያያዘ የእጅ እንቅስቃሴ አለ፡፡ የእጅ እንቅስቃሴው የግድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እጅን የሚነካ ኳስ በእጅ የተነካ ማለት አትችልም፡፡ በእጅ የተነካ የምትለው በተፈጥሯዊ ሁኔታ የሚንቀሳቀስን እጅ ወደየምትፈልገው አቅጣጫ ስታነቃንቀው፤ ስትለውጥበት ፤ ስትጨምርበት…¸ግን ይሄ በእጅህ ነው የተጫወትከው በሚል መጠየቅ ያፈልጋል፡፡ ኳስ ወደ እጅ እጅ ወደ ኳስ የሚሉት ነገሮች…›› በማለት፡፡ ይህ እንግዲህ የካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ በየሳምንቱ በሬድዮ ሞገድ በትጋት የሚሰሩበት ሁኔታን የሚያሳይ ነው፡፡ የኢንስትራክተሩ የእግር ኳስ ዳኝነት ማብራርያዎች በብዙዎች የእግር ኳስ አፍቃሪ የስፖርት ቤተሰቦች ከፍተኛ ግምት ይሰጠዋል፡፡ በእግር ኳስ ዳኝነት ሙያው ከ46 ዓመታት በላይ ልምድ አካብተዋል፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት በእግር ኳስን በራድዮ ተመልከቱ የጨዋታዎች ቀጥታ ስርጭት ኢንስትራክተሩና ማብራርያቸው ተለምደዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የዳኝነት ሙያን በየጊዜው በሚያሳድጉ የህግ ትርጓሜዎች፤ ስልጠናዎች እንዲሁም ሙያዊ አስተያየቶች ስለዳኝነት ብዙ እውቀት ማስጨበጥ የቻሉ ባለሙያም ናቸው፡፡
ለአመታት በዳኝነት ሙያ ውስጥ በማለፍ ለሙያው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት የካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ለአሰልጣኞች ፣ ለእግር ኳስ አመራሮች፣ ዳኞች እና ለስፖርት ቤተሰቡ የሚሆን የዘመናት ጥንስሳቸው እውን ሆኖ “ የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጥር “ በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሃፍ ዛሬ በኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል ከረፋዱ 4 ስዓት ያስመርቃሉ፡፡ ይህን ምክንያት በማድረግ ከስፖርት አድማስ ጋር ሰፊ ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የህይወት ታሪካቸው፤ የሙያ ተመክሮ እና የስራ ልምዳቸው ላይ በማተኮር ከዚህ በታች የቀረበው የመጀመርያው ክፍል ነው፡፡
******************
የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጢር በሚል ስላዘጋጁት አዲስ መፅሀፍ በስፋት ሊያወጉን በመፈቅድዎ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ እንግዲህ እንደመግቢያ የመፅሃፉ አጠቃላይ ይዘት ምን እንደሚመስል በአጭሩ ገልፀውልን ፤ በተለይ በመፅሀፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ በማተኮር ውይይቱን ብንጀምርስ…
አመሰግናለሁ፡፡ የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጢር በሚል ያዘጋጀሁት መፅሀፍ የተለያዩ ጉዳዮችን አጠቃልሎ የያዘ፤ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ጥያቄዎች፣ አነጋጋሪ በሆኑ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የጨዋታው ህግ ያለውን ምላሽ በማንሳት የሚያብራራ እና የሚያስረዳ ነው፡፡  መፅሃፉ በአጠቃላይ ይዘቱ በ4 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ  የህይወት ታሪኬን፣ ያለፍኩባቸውን የትምህርት ደረጃዎች፣ የሙያ ታሪኬን እና የስራ ልምዴን የሚያካፍል ነው፡፡ በመፅሀፉ መግቢያ  ይህን  ምዕራፍ ማካተት ያስፈለገው በምክንያት ነው፡፡  በማንኛውም የሙያ ሂደት ውስጥ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ብዙ እንቅፋቶችም ይገጥማሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ ያለኝን ተመክሮ ለማካፈል ስለፈለግኩ መነሻ አድርጌዋለሁ፡፡ በየሙያው የሚገጥሙ እንቅፋቶች እና ፈተናዎች  ለመስራትና ለማደግ የሚፈልግን ሁሉ የሚያሰለቹ እና የሚፈታተኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያሰቡትን ለማሳካት እና የፈለጉት ደረጃ አያደርሱም በሚል ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ ለማመላከት የሞከርኩበት ነው፡፡ ከህይወት ታሪኬ እና ካለፍኩበት የስራ ልምድ እና ተመክሮ በማንኛውም ሙያ ውስጥ የሚገኝ ወጣቱ ትውልድ ብዙ ሊማርበት እንደሚችል አስባለሁ፡፡ አሁን በሙያው ላይ ያሉ ዳኞች፣ ኢንስትራክተሮች፣ ታዛቢዎች፣ ኮሚሽነሮች ሙያው የሚጠይቀውን ሂደት እንዲገነዘቡበት እና እንዲነሳሱበትም ነው፡፡ ሙያተኞቹ የዳኝነት ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለስፖርቱ ቤተሰብ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ በማሰብ አስፈላጊ መልዕክቶችን አስፍሬበታለሁ፡፡ በተጨማሪም በዳኝነት ሙያው በየጊዜው እውቀታቸውን እያሳደጉ እና ልምዳቸውን እያዳበሩ እንዲሄዱ ለማነቃቃትም ነው፡፡ በምሰራበት የዳኝነት ሙያ አንዳንድ ገጠመኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚያን አጋጣሚዎች በምን መልኩ እንደተወጣኋቸው ለማሳየት፣ ለሁሉም የበጎ ነገር አካሄድ እንደየእምነቱ የእግዚአብሔር ፍቃድ እንዳለ ሆኖ፣ ከዚያ ባሻገር የግል ጥረት የሚፈለግ ደረጃ ያደርሳል የሚል ዕምነት ስላለኝ ነው፡፡ እኔ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የበቃሁት ብዙ ፈተናዎችን በማለፍ ነው፡፡ እነዚያን ተመሳሳይ ፈተናዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ያሳለፉ ባለሙያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ አሁን በሙያ ውስጥ በማደግ ላይ ያሉት ግን እነዚን እንቅፋቶች የሚፈልጉበት ደረጃ ከመድረስ እንዳያሰናክላቸው ለማሳመን ጥረት አድርጊያለሁ፡፡
በአጠቃላይ በመፅሀፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከላይ ከተጠቀሱ ጉዳዮች ባሻገር በሙያው ላይ ለስንት ጊዜ ስሰራ እንደቆየሁ፣ ምን አገልግሎት ስሰጥ እንደነበር፤ ከመጀመሪያው የ2ኛ ደረጃ ዳኝነት እስከ ኢንተርናሽናል ደረጃ ያለፍኩበትን ሂደት የገለፅኩበት ነው፡፡ በእግር ኳስ ዳኝነቱ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ባስቀመጠው የዕድሜ ጣሪያ ገደብ ስሰራ ቆይቼ ከዚያም በኋላ በሙያው እየሰሩ እንዴት መቀጠል እንደሚቻል የሚያሳይም ነው፡፡
ያለፉባቸውን የትምህርት ደረጃዎች ከዚያም በኋላ የስራ ልምድዎን ይግለፁልን?
ከትምህርቱ ስነሳ እንግዲህ በወሎ ከሚገኘው ከወ/ሮ ስህን ኮፕርሄንሲቭ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የንግድ ስራ ትምህርት በመማር ነው የጀመርኩት ፤ ከዚያም የማህበራዊና ዘመናዊ አስተዳደር መሰረታዊ ትምህርቶችን በሞስኮ የመከታተል እድሉ ነበረኝ፡፡ በ1979 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ዲፕሎማ እንዲሁም በ1991 የእግር ኳስ ዳኝነት ኢንስትራክተር ከአፍሪካ እ/ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF-CAIRO) አግኝቻለሁ፡፡
ከእነዚህ የትምህርት ደረጃዎች በኋላ በበርካታ ሃላፊነቶች ለረጅም ዓመታት እያገለገልኩ ቆይቻለሁ፡፡ የመጀመርያው በደሴ ከተማ በሚገኘው በወ/ሮ ስህን ኮምፕርሄንሲቭ 2ኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ለ4 ዓመት ከ2 ወር በጸሐፊነት እና በረዳት አስተዳዳሪነት ያገለገልኩበት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በወሎ ክ/ሀገር ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ለ6 ዓመት ከ5 ወር በዋና ስራ አስኪያጅ ልዩ ጸሐፊነት፤ እንዲሁም በመምህራንና ሰራተኞች አስተዳደር ምክትል ኃላፊነትና በጎልማሶች ትምህርት ክፍል በፕሮግራም አስተባባሪነት ሰርቻለሁ፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ደግሞ በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መ/ቤት ለ3 ዓመት ከ3 ወር የአስተዳደርና የፋይናንስ መምሪያ የጽ/ቤት ኃላፊነት፣ የሰራተኛ ማሰልጠኛ አስተዳደር ኃላፊነት አገልግዬም ነበር፡፡ የወሎ ባህል አምባ አስተዳዳሪ  እንዲሁም የደሴ የላሊበላ ኪነትና የሲኒማ ቤቱ ኃላፊ በመሆን የሰራሁበትም ልምድ አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ለ10 ዓመት ከ2 ወር በሰራተኛ ማስተዳደሪ አገልግሎት እና በኢንስቲትዩቱ አስተዳዳሪነት ከመስራቴም በላይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ ተ/ኃላፊነት ለ4 ወራት እንዲሁም በጥናት ቡድን አስተባባሪነት ለ10 ወራት አገልግያለሁ፡፡ በአጠቃላይ በመንግሥት ሥራ ውስጥ ከ24 ዓመታት በላይ ሰርቻለሁ ማለት ነው፡፡
ከመንግስት መስርያ ቤቶቹ  በኋላስ?…
በግል የህግ አማካሪነትንና የአስተዳደር ነክ ስራዎችን ለ14 ዓመታት ስሰራ ቆይቼ ወደ ስፖርቱ በደንብ እየገባሁ መጣሁ፡፡ የመጀመርያው ስራዬም በኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን የካፍ ትምህርት ኦፊሰር  በመሆን ለ2 ዓመታት ያገለገልኩበት ነበር፡፡ በመንግስት መስርያ ቤቶች ከዚያም በኋላ በግሌ ስሰራ ዓለም በቆየሁባቸው ጊዜያት የነበሩኝን ትርፍ ሰዓቶች በልዩ ልዩ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ኮሚቴዎች በመሳተፍ ጥቅም ላይ አውያዋለሁ፡፡ በዋናነት የሚጠቀሱት በወሎ  በክ/ሀገር ስፖርት ም/ቤት ም/ሊቀመንበርነት  በልዩ ልዩ ስፖርት ኮሚቴዎች ኃላፊነት የሰራሁባቸው ናቸው፡፡
በእግር ኳስ ዳኝነቱ ላይ ያልዎትን ልምድ በተመለከተስ…
በእግር ኳስ ዳኝነት ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ደረጃ በእድገት የደረስኩበት እና ኢንተርናሽናል አልቢትር በመሆን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ፣ በደቡብና ሰሜን አፍሪካ አገሮች በመዘዋወር አገራችንን የሚያስጠራና የሚያኮራ ዳኝነት ፈፅሚያለሁ፡፡ የእግር ኳስ ዳኝነትን በሚመለከቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጡ ከ15 የሚበልጡ የእግር ኳስ ህግ ኮርሶችን በየጊዜው ተከታትያለሁ፡፡ በዳኝነት መስራት እስከሚቻልበት ይፋዊ የዕድሜ ገደብ ድረስ ማለት ነው፡፡  በመጋቢት ወር 1987 ዓ.ም የጨዋታ ዳኛ ሆኜ  መስራቱን ከማቆሜ በፊት፤ በ2ኛ ደረጃ ዳኝነት ለ5 ዓመታት፤በ1ኛ ደረጃ ዳኝነት ለ3 ዓመታት ፤ በፌደራል (አገር አቀፍ) ዳኝነት ለ14 ዓመታት በኢንተርናሽናል ዳኝነት ለ4 ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ በድምሩ ለ26 ዓመታት እግር ኳስን በማጫወት በዳኝነት ሙያው ሰፊ ልምድ ለማካበት በቅቻለሁ፡፡ ዳኝነትን ካቆምኩ ከ5 ወራት በኋላ በክልል 14 የአርቢትር ኮሚቴ አባል ሆኜ የሰራሁ ሲሆን ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ በመሆን ለ6 ዓመት ከ6 ወር ከማገልገሌም በላይ በኮሚቴው አባልነት የሰራሁባቸው ጊዚያትም ነበሩ፡፡ በተጨማሪም በ1997 እና በ2002 ዓ.ም የኮሚቴው ሰብሳቢ በመሆን አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
 በኢትዮጵያ እግር ኳስ የዳኝነት ትምህርትን በየጊዜው በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳልዎትም ይታወቃል፡፡ በርካታ ዳኞችን እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ደረጃ ማድረስዎም በተደጋጋሚ ይጠቀሳል…
የዳኞች መምህራንን ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በመስጠት ፈርቀዳጅ ነበርኩ ማለይ ይቻላል፡፡ ለዚህም የጨዋታ ህግ መምህራንን በማፍታት ደረጃቸውን የሚለይ ማስረጃ እንዲገኙ ማድረጌን  መጥቀስ ግድ ይሆናል፡፡ በተጨማሪ የታዛቢነት ሙያን በተመለከተ ተከታታይ ስልጠናና ትምህርት እስጥም ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ በርካታ ታዛቢዎችና የዳኞች መምህራን እንዲኖራት አስተዋፅኦ የሚያደርግ ተግባርም ሳከናውን ነበር፡፡ በፊፋና በካፍ ለሀገራችን የዳኝነት ህግ ትምህርት ለመስጠት ለሚመጡ መምህራን የኮርሱ አስተባባሪ በመሆንም አገልግያለሁ፡፡
ከስልጠናው ባሻገር እንግዲህ በተለያዩ የእግር ኳስ ዳኝነት የህግ ትርጓሜዎች፤ ሰነዶችእና ህትመቶችም ላይ ስላከናወኗቸው ተግባራትስ…
ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ከፊፋ የሚመጡ የጨዋታ ህጎች ማሻሻያዎችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዘጋጅለሁ፡፡ በዝርዝር መጥቀስ ካስፈለገም እ.ኤ.አ በ2000 ፊፋ ያወጣውን ባለ 45 ገጾች የጥያቄና መልስ መጽሐፍ፤  የ2006ን የጨዋታ ህግ መጽሐፍ (84 ገጾች)፤የ2006ን የትሳል የጨዋታ ህግ (61 ገጾች) ፤ የ2006ን የጨዋታ ህግ ጥያቄዎችና መልሶች መጽሐፍ፣ (84 ገጾች)፤ የ2007/2008 የጨዋታ ህጎ፣ (81 ገጾች)፤ የ2008/2009 የጨዋታ ህጎች፣ (50 ገጾች)
፤ የ2009/2010 የጨዋታ ህጎች፣ (66 ገጾች) የ2009/2010 ለዳኞች - የጨዋታ ህጎች አተረጓጎም እና ተጨማሪ መመሪያዎች … (84 ገጾች) ፤ የ2010/2011 የፊፋ እግር ኳስ ጨዋታ ህግና ለዳኞች የጨዋታ ህጎች አተረጓጎም እና ተጨማሪ መመሪዎያዎች የሚለውን መጽሐፍ … (84 ገጾች)፣  የ2014/2015 የፊፋን የእግር ኳስ የጨዋታ ህግ መጽሐፍን /150 ገጾች/፣ እና የ2015/2016 ማሻሻያን ጭምር አዘጋጅቻለሁ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን የእግር ኳስ ደንቦች፤ ህጎች፤ መመርያዎች እና ማሻሻያዎች በአማርኛ ተርጉሜ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማቅረብ፣ በስራ ላይ እንዲውልና በመላው አገሪቱ ላሉ ክልሎች ጭምር እንዲሰራጭ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጌያለሁ፡፡  ዳኞች መምህራን፤ ዳኞች፣ ታዛቢዎች፣ የክለብ አሰልጣኞችና ተጨዋቾች፣ የስፖርቱ ሚዲያዎች፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የሚገኙ የእግር ኳስ ባለሙያዎችና ቤተሰቦች መጽሐፍቱን በፌደሬሽኑ ባለቤትነት አግኝተው እስካዛሬ  እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል በ1997 ዓ.ም በፌደሬሽኑ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለማስተካከል፣ በፊፋ የተቋቋመው የኖርማላይዜሽን ኮሚቴ አባል ሆኜ ከፊፋ ታርሞ የተላከውን የፌደሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ ወደ አማርኛ ተርጉሜ በማቅረብ በአወያይነት ተሳትፌበታለሁ፡፡
በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም ሻሸመኔ ከተማ ላይ፣ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ዳኝነትን ላቆሙና ከሁሉም ክልሎች በብሔራዊ ደረጃ ለተውጣጡ ኢንተርናሽናል ፌዴራል ዳኞች ለነበሩ ሠልጣኞች፣ በሀገራችን ለ3ኛ /ሶስተኛ/ ጊዜ የዳኞች የኢንስትራክተርነት ኮርስ በመስጠት የሀገራችን የባለሙያዎች ብዛት እንዲጨምር ማድረጌም የሚጠቀስ ነው፡፡ በ2007 ነሐሴ ወር ከኦሮሚያ ክልል ለተውጣጡ በለሙያዎች በአምቦ ጎል ፕሮጀከት ለ25 ባሙያዎች የውድድርና የዳኝነት ታዛቢነት የብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና /ኮርስ/ በመስጠት የክልሉም ሆነ የአገር አቀፉ የባለሙያዎች ብዛት እንዲያድግ ከማስቻሌም በላይ በዚሁ ዓመት መጨረሻ በስፖርት ዘርፍ ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው ዕጩ›› ሽልማትም መውሰድ ችያለሁ፡፡
ሌላው ከፍተኛ ታዋቂነት ያገኙባቸውን የራድዮ ፕሮግራምልምዶች እዚህ ላይ ብናነሳስ፤ በተለይ ከመሰለ መንግስቱ ጋር በእግር ኳስን በራድዮ ተመልከቱ ማለት ነው፡፡
ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 እና ቀጥሎም በፋና ብሮድካስቲንግ ኤፍ.ኤም 98.1 “እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ መሰለ መንግስቱ” ፕሮግራም ላይ ስለ ዕለቱ የእግር ኳስ ዳኝነት ለፕሮግራሙ ተመልካቾች ትምህርታዊ ማብራሪያ በመስጠት፣ በቡድን ደጋፊዎች መካከል ይፈጠሩ የነበሩት አለመግባባቶች እንዲረግቡ የማድረግ ተግባርንና የእግር ኳስ ጨዋታ ሕግን ለሕዝቡ የማዳረስ ሥራ ለማከናወን የቻልኩበት ነው፡፡  በ2002 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በአ/አበባ መስተዳደር ኤፍ ኤም 96.3 ‹‹ስለአገራችን ስፖት አንጋገር›› ሣምንታዊ የእግር ኳስ የጨዋታ ሕግ ጥያቄና መልስ ፕሮግራም ላይ፣ ከስፖርት አፍቃሪ ሕዝብ ጋር በቀጥታ ሥርጭት እየተገናኘሁ ከጨዋታው ሕግ እንጻር ተገቢውን መልስ በመስጠት ሙያዊ አስተዋጽኦም ነበረኝ፡፡ አሁንም በብሥራት ኤፍ አ6ም 101.1 ሬዲዮ እና በፋና ብሮድካስቲንግ ኮሮፕሬሽን ትብብር በመላው ኢትዮጵያ የሚተላለፈው ‹‹እግር ኳስና በሬዲዮ ተመልከቱ መሰለ መንግስቱ›› ፕሮግራም ላይ በእግር ኳስ ዳኞች የሚሰጡ ውሳኔዎችን በተመለከተ ትምህርታዊ አስተያዬቶችን እያቀረብኩ እገኛለሁ፡፡ በተጨማሪም፣ ከህዳር ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ በብሥራት ኤፍ ኤም 101.1 ሬዲዮ በኦያያ መሴ መልቲ ሚዲያ- ‹‹የዳኝነት ሚስጢር› በሚል አርዕስተ ዘወትር ማክሰኞ ከ 12፡30-2፡00 ሰዓት በእግር ኳስ የጨዋታ ሕግ ሚስጥሮችን የማስተዋወቅና የመማሪያ ፕሮግራም እየሰራሀ ነኝ፡፡ ለእግር ኳስ አፍቃሪው ሕዝብ እና በሙያው ለተሰለፉ ሁሉ በዳኝነት ላይ በማተኮር የቀጥታ ሥርጭት አገልግሎት በመስጠት የመስራት ትጋቱ አለኝ፡፡ የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች በሬዲዮና ቴሌቪዥን በሚያደርጉት ጥሪ ላይ እንግዳ ሆኜ በመገኘት፣ የበርካታ ዓመታት ሙያዊ ልምዴን በተደጋጋሚ ያካፈልኩ ሲሆን፤ በአከራካሪ የእግር ኳስ ዳኝነትና የጨዋታ ሕግ ትርጉሞች ላይ፣ የአገራችንን የእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪ ሕዝብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትምህርቶችና ማብራሪያዎችን በመስጠት ብዙ ሰርቻለሁ፡፡
ከአገር ውጪ ስለወሰዷቸው ኮርሶችና ያከናወኗቸው ተግባራት ቢጠቀሱልን
ፊፋ ባዘጋጀው የእግር ኳስ ህግ ማሻሻያ ኮርስ በናይሮቢ (ኬንያ)፤ የዳኞች ኢንስትራክተርነት ኮርስ በካይሮ (ግብፅ) ላይ በመካፈል እና ፈተናውን በከፍተኛ ውጤት በማለፍ የካፍ ዳኞች ኢንስትራክተር ማዕረግ ለማግኘትም ችያለሁ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ የእግር ኳስ ዳኞች የሰጠውን የግምገማ (Evaluation) ኮርስ በናይጄሪያ (ፖርት ሐርኮርት) በመካፈል የኢንስትራክተርነት ሙያየን ማሳደጌም የሚጠቀስ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2003 ጀምሮ የፊፋ ዳኞች ኢንስፔክተር በመሆን፤ እ.ኤ.አ በ2006 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ካምፓላ ላይ የዑጋንዳንና የሞሪሺስን ብሄራዊ ቡድኖች ያጫወቱ ዳኞችን የሥራ ውጤት በመስራት ፤ እንዲሁም ለ2010 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የጅቡቲ እና የግብፅ ብሄራዊ በድኖችን ያጫወቱ ዳኞችን በመገምገም ተገቢውን ሪፖርት ለፊፋ ማድረጌም ካከናወንኳቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆኑ፤ በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ቡሩንዲ ከሌሴቶ 15/11/2011 ያደረጉን ጨዋታ ቡጁምቡራ በመሄድ ዳኞቹን በመታዘብ ሪፓርቱን እንድልክ በፊፋ ተመድቤ በወቅቱ ሙያዊ ተግባሩን ተወጥቻለሁ፡፡ በ35ኛው የምስራቅ መካከለኛው አፍሪካ ቻሌንጂንግ ካፕ ኢትዮጵያን በመወከል የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው አባል በመሆን ታንዛኒያ- ዳሬሰላም ላይ በጨዋታ ታዛቢነት ከመስራቴም በላይ  ውድድሩ በተዘጋጀለት ደንብ መሰረት መከናወኑን የማረጋገጥ ሥራ አከናውኛለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የካፍ ትምህርት ኦፊሰር ሆኜ ከተመደቡበት እ.ኤ.አ ከሰኔ 24/2010 ጀምሮ፤  በደቡብ አፍሪካ የቴክኒክ ዳሬክተር እና የትምህርት ኦፊሰር ሴሚናር ፤ በ3ኛው የካፍ የክፍለ አህጉሩ የትምህርት ኦፊሰር ሴሚናር ላይ በካይሮ ግብጽ ፤ በደቡብ አፍሪካ- ፕሪቶሪያ ላይ የተዘጋጀውን የፊፋ/ካፍ ቴክኒካል ዳሬክተር እና የትምህረት ኦፊሰር ሴሚናር ተሳትፌያሁ፡፡ በአዲስ አበባ ካፍ ለአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች ያዘጋጀውን የሴቶች አሰልጣኞች ኢንስትራክተሮች ኮርስ በአስተባበሪነት፤ ፊፋ አዲስ አበባ ላይ ለከፍተኛ የእግር ኳስ ዳኞች ያዘጋጀውን ኮርስ በማስተባበርና በኢንስትራክተርነት፤ የአዲስ የሴቶች አሰልጣኞች ኢንስትራክተርነት ኮርስ በአስተባባሪነት ካፍ የጨዋታ ታዛቢነት ማዕረግ በመስጠት፤ ለ9ኛው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማጠሪያ የቻዱ-ሬነሳስ ከኒጀሩ-ሳህል ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ዲነጃሚና ላይ ተገኝቼ የታዛቢነት ሃላፊነት መወጣቴም ይጠቀሳሉ፡፡ ለካፋ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጁን 2/2013 ሊዲያ ሉዲክ /ቡሩንዲ/ ከስታድማሊዮን /ማሊ/ ጋር ቡጁቡራ ላይ ያደረጉትን ጨዋታ ለመሩት የአልጀሬያ ዳኞች ገምጋሚ /Inspector/ በመሆንም ሰርቻለሁ፡፡
……….ይቀጥላል

Read 7148 times