Monday, 05 March 2012 14:17

“ዐይን ከጽዮን” አንዲት ታዳጊ ታደገ “ሦስተኛው የጤና ምሽት” ረቡዕ ይቀርባል

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

“ዐይን ከጽዮን (Eye from zion)” የተባለ የእስራኤል በጐ አድራጊ ሀኪሞች ቡድን ለአንዲት ኢትዮጵያዊት ታዳጊ ሕፃን ነፃ የህክምና አገልግሎት በማድረግ ህይወቷን  ታደገ፡፡ አዲስ አበባ ከሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ መግለጫ እንደሚጠቁመው ዶክተሮቹ በጊዜ ባይደርሱላት ህመሙ ይገድላት ነበር፡፡በእስራኤሉ የቴልሃሾሜር ሆስፒታል በሚገኘው የቻይም ሳባ ሕክምና ማዕከል ቀዶ ሕክምና ቡድን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ 160 የዓይን ካተራክት ሕክምና መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ወቅት የ10 ዓመቷን ሕፃን የምስራች ከበደ ዐይኗ ውስጥ ባለ ትልቅ ኪንታሮት ቢኖርም ሕክምናው ኢትዮጵያ ውስጥ ባመኖሩ በዶ/ር ናሂም ሮዘን የሚመራ ቡድን የመጀመርያ ዙር ቀዶ ሕክምና ኪንታሮቱ ወደ ነቀርሳ መለወጥ አለመለወጡን ካየ በኋላ ወደ እስራኤል ሊወስዷት እንደወሰኑ ከኤምባሲው መግለጫ ማወቅ ተችሏል፡፡“የመዳን ተስፋዋ ጠባብ ነበር” ያሉት የ’ዐይን ከፅዮን’ መስራችና ልጅቱ አስራኤል ሄዳ ትታከም ዘንድ የጐተጐቱት ሚስተር ናቲ ማርቆስ “እንዳየሁት እድሉን ተቀበልኩ” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አስራኤል እንድትሄድ ከተወሰነ በኋላ የእስራኤል ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር መስርያ ቤት፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ ይሁዳውያን የጋራ ኮሚቴ እና የሀገሪቱን እጅግ ምርጥ ዶክተሮች ቀዶ ሕክምናውን በነፃ ለማከናወን ቃል ገብተዋል፡፡ ከዶክተሮቹ ውስጥ ውስብስቡን ቀዶ ህክምና ለማድረግ የጠየቁ እጅግ ምርጥ የእስራኤል ዶክተሮች አሉበት፡፡

ከእህቷ ጋር ወደ እስራኤሉ ማዕከል የተጓዘችው የምስራች ከጥልቅ ምርመራ በኋላ የተሳካ የዐይን ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በዶ/ር ጋይ ቤን ስምኦን እና ዶ/ር ናሆም ሮዘን ተደርጐላታል፡፡ በጥቂት ቀናትም ውስጥ ወደ ወደብ ከተማዋ ሃይፋ በመጓዝ ዶ/ር ዮቭ ቫርዲዘር የፕሮስቴቲክ አይን ከተገጠመላት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳለች ብሏል መግለጫው፡፡“ይሄ የተለመደ ቀዶ ሕክምና ስላልሆነ በአንድ ሰው ብቻ አይከናወንም” ያሉት ዶ/ር ቤን ስምኦን በዓለም ዙርያ ካሉ ሌሎች ባለሙያዎች ጋር እንደተወያዩበት ተናግረዋል፡፡ ኪንታሮቱ በትንሽ ቦታ የወጣ ቢሆንም ለዐይነ ሥውርነት የመዳረግና ህይወት የማጥፋት አቅም እንደነበረው ማወቅ ተችሏል፡፡“ዐይን ከፅዮን” በኢትዮጵያ፣ በቪትናም፣ ማይኒማር፣ አዘርባጃን እና ሌሎች ሀገሮች ይሰራል፡፡

በሌላም በኩል ውዴ ፕሮሞሽን እና ኢቨንት ኦርጋናይዚንግ ሃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር መጪው ረቡዕ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በሚያካሄደው ሦስተኛው የጤና ምሽት ስለ ኦቲዝም እንደሚወያይ አስታወቀ፡፡ በቦሌ ሮክ በተዘጋጀው የጤና ምሽት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶር. ዮናስ ባህረጥበብ እንዲሁም ሌሎች የህጻናትና ወጣቶች አዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች በምሽቱ ሙያዊ ማብራርያ ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ የኦቲዝም ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

 

 

Read 26638 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:30