Monday, 15 August 2016 09:04

‘አንዳንድ ቀን አለ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ክፈት በለው ተነሳ፣ ያንን አንበሳ
ክፈት በለው በሩን፣ የጌታዬን
ይባል ነበር፡፡ “ክፈት በለው…” አሪፍ አባባል ነች፡፡ ብዙ የተዘጉብን በሮች ስላሉ ይከፈቱልንማ! በየቦታው ‘በር ከርቻሚዎች’ እየበዙብን ስለሆነ ወይ “አትከርችሙባቸው…” ይባሉ  (‘ማለት የሚችል’ ካለ)  ወይ ‘ማስተር ኪይ’ ይሰጠን!
እኔ የምለው…ይቺ “የጌታዬን…” የምትል ነገር…ድሮ አይደለም የእኛን የምስኪኖችን… ‘የጌታን’ በር ሳይቀር ማስከፈት ትችል ነበር ማለት ነው! ልክ ነዋ…አሁን፣ አሁን እንኳን ‘የጌታን’ በር ልናስከፍት ይቅርና ‘በጌቶች’ ሰፈር በኩል ስናልፍ… አለ አይደል… በዓይን እያነሳ የሚያፈርጠን በፀጉር ልክ ሆኗል፡፡ የምር…‘የምጣዱ ሳለ የዕንቅቡ ተንጣጣ’ አይነት ታማኝነት አስቸግሮናል፡፡
እናላችሁ…“ክፈት በለው በሩን፣ የጌታዬን” ሲባል ተኖረና ‘ሪቮሉሲዮን’ ይምጣ፣ ምን ይምጣ…ብቻ ‘ጌታዬ’ ‘እመቤቴ’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር ኋላ ቀር ነው ምናምን ተባለ፤ ልክ… “እንኳን አደረሰህ አይባልም፣ በራስህ ስለደረስክ እንኳን ደረስክ ነው የሚባለው…” ሲባል እንደነበረው ማለት ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ያኔ እኮ በዓመት አንድ ጊዜ ቡሄ ሲመጣ ነበር ‘የጌታዬ’ ቤት፣ ‘የእመቤቴ’ ቤት ይባል የነበረው፡፡ ዘንድሮ ቡሄ የለ፣ ምን የለ…በየቀኑ “የጌታዬ ቤት…” “የእመቤቴ ቤት…” የምንል መአት አይደለን እንዴ!  ልክ ነዋ! (“ባለ መኪና ዝም ብሎ አይደለም የበዛው…” ያልከው ወዳጃችን፣ “የጌታዬ ቤት…” ስለማለት ነበር እንዴ ስታወራ የነበረው!)
ደግሞላችሁ…አለ አይደል…በ‘ቦተሊካው’ በሉት፣ በማህበራዊውም በሉት፣ በምንም በሉት “ጌታዬ ካላላችሁኝ መቅሰፍት ይወርድባችኋል…”፣ “እመቤቴ ካላላችሁኝ ውርድ ከራሴ…” ምናምን አይነት የሚሉ ‘ቪ.አይ.ፒ.’ዎች  (ቂ….ቂ….ቂ…) በዝተውብናል፡፡
እኔ የምለው… ለእኛም ይታዘንልና! ለእነዚህ ሁሉ ‘ጌቶች’ እና ‘እመቤቶች’…አለ አይደል… ‘ብጥስ፣ ቅንጥስ’ ስንል ወገብስ መቀጨቱ ይቀራል! ባለ ፈራንካ በሉት፣ ባለ ትልቅ ወንበር በሉት…ባለ ትልቅ ዘመድ በሉት… ‘ጌታ’ በዛብን እኮ፡፡ ‘ጉልበተኛነት’ በሽ የሆነበት ዘመን!
ስሙኝማ…ያው ዳያስፖራዎች ወደ አገር ብቅ በሚሉበት ጊዜ፣ “ምን ይዤልህ ልምጣ…” ሲሉን…
“ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ሰቨን…”
“ሌተስት አፕል ላፕቶፕ…”
“ፕሮፌሽናል ዲጂታል ካሜራ…”
ምናምን ስንል ኖረናል፡፡ አሁን ልጄ ጊዜ እየተለወጠ ነው፡፡ ሆድ ባዶ ሆኖ፣ ‘ጋላከሲ ኤስ ሰቨን’ ምናምን ምን ያደርጋል! እናላችሁ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ ጥያቄያችን ይለወጣል፡፡
ዳያስፖራ ወዳጅ፡— ስማ… ለኒው ይር ስለምመጣ ምን ይዤልህ ልምጣ?
ምስኪኖቹ እኛ፡— ካላስቸገርኩህ ሰባት ኪሎ ቲማቲምና ስምንት ኪሎ ሽንኩርት አምጣልኝ፡፡
ልክ ነዋ… እኛ ስንት ዘመን ሽሮና በርበሬ ስንልክ ኖረን የለም እንዴ!
እናማ…ቲማቲም እንኳን ‘ጉልበተኛ’ ሆነችብና! የደላቸው የበዓል ቀን ሰይመውላት ይደባደቡባታል፣ እኛን ደግሞ ይኸው አናት አናታችንን እየደበደበችን ነው፡፡
ይኸው ሽንኩርትም ‘ከአቅሟ’ ‘ጉልበተኛ’ ሆና…አለ አይደል…አንዴ አልበቃ ብሏት ሁለቴ እያስለቀሰችን ነው፡፡ በፊት የምታስለቅሰን ገዝተን ስንልጣት ነበር፣ አሁን ደግሞ ገና ስንገዛትም እዬዬ እያስባለችን ነው፡፡
የምንይዛት ገንዘብ ‘ትልቅ’ መስላ በአይነት ስትለወጥ የምትኮስስበትን ዘመን ያሳጥርልንማ! ስለ ገንዘብ ካነሳን ይቺን ስሙኝ…አንድ ትንሽ ልጅ 100 ዶላር በጣም አስፈልጎታል፡፡ ከዛም 100 ዶላር በመጠየቅ ለእግዚአብሔር ደብዳቤ ለመጻፍ ወሰነ፡፡ ደብዳቤውን ጽፎም መላኪያ ሳጥን ውስጥ ይከተዋል፡፡ በነገሩ የተገረሙ የፖስታ ቤቱ ሠራተኞች፣ ደብዳቤውን ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ላኩት፡፡ ፕሬዝዳንቱ በመገረማቸው የተነሳ፣ “ልጅ ስለሆነ አምስት ዶላር ክተቱና ላኩለት…” ይሉና ለረዳቶቻቸው ይናገራሉ፡፡
ልጁ አምስት ዶላር በማግኘቱ ደስ ይለዋል። ስለሆነም ለእግዚአብሔር የምስጋና ደብዳቤ ይጽፍለታል፡፡
“እግዚአብሔር ሆይ፤ ገንዘቡን ስለላክልኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ግን ደብዳቤውን የላከው በዋሺንግተን ዲሲ በኩል ነው፡፡ እየውልህ እግዚአብሔርዬ፤ እንደለመዱት ዘጠና አምስት ዶላር ግብር ቆርጠውብኛል፡፡”
እኛም ገንዘባችንን እነማን ምን እያደረጉብን እንደሆነ ለአንድዬ የሚነግርልን ‘ማሙሽ’ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ህጻናቱ ገና ሰብአዊነታቸውን አልተነጠቁም፡፡
ሊጠቅም የሚችል ሀሳብ አለን…እንግዲህ ‘የምክር አገልግሎት’ ዘመን አይደል…እናማ ‘ሽንኩርትና ቲማቲም ለመግዛት ገበያ ወጥተው ለሚመለሱ ሰዎች የምክር አገልግሎት እንሰጣለን’ የሚል ተቋም በአነስተኛና ጥቃቅንም ሆነ፣ በደረጃ ‘ሀ’ ይቋቋምልን።
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እዚህ ምስራቅ አዲስ አካባቢ በዛ ሰሞን የተደረገ ነገር ነው። እናላችሁ… የዕድር ለፋፊው እሁድ ዕለት ክፍያ እንዳለ እየለፈፈ ነበር፡፡ ምን ብሎ ቢለፍፍ ጥሩ ነው…
“የ…ዕድርተኞች፣ እሁድ ክፍያ ስለሆነ በተለመደው ሰዓት ተገኝታችሁ ክፍያችሁን እንድትፈጽሙ፡፡ ደግሞ ዛራና ቻንድራን እያየን ስለነበር አልሰማንም እንዳትሉ!”  አሪፍ አይደል!
ደግሞላችሁ…አንድ የኃይማኖት አባት፤ “ዛራና ቻንድራ የሚሏቸውን እንዳታዩ…” እያሉ ሲሰብኩ ነበር አሉ፡፡ እነኚህ ህንዶች አባሉንሳ!
እናማ… ገና የእነቲማቲምን ነገር ሳንወጣው ‘ዛራና ቻንድራ’ የሚባሉ ‘ጉልበተኞች’ ይምጡብን! ዘንደሩ መቼመ በእኛ ያልበረታ የለ!  ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…በቡሄ ጭፈራ ‘ክበር በስንዴ፣ ክበር በጤፍ ምቀኛህ ይርገፍ’ የሚሏት ነገር አሪፍ ነች። የምር ግን ልክ ለዚህ ዘመን ተለክታ የተሠራች አትመሰልም! “ምቀኛህ ይርገፍ” ቢባልልን በአደባባይም ባይሆን በልባችን ደስ የሚለን መአት ነን፡፡ ለነገሩ “ምቀኛ ይርገፍ የሚሉት የባላባታዊ ስርአት ናፋቂዎች ናቸው…” ምናምን ሊባል ይችላል፡ እዚህ አገር ምን ሊባል የማይችል ነገር አለ!
እንደ እውነቱ…አለ አይደል…
ቀጥ ያለ ነው ያልነው ነገር ሁሉ የእንግድድ ሲሄድብን፣
አእምሮ የጡንቻን ቦታ ለመተካት ሲያቅተው…
አይደለም ያየነው፣ ያላየነው ዘመን ቢናፍቀን ምን ይገርማል! ልክ ነዋ…
ቢያንስ፣ ቢያንስ የአህያ ምናምን ሥጋ የከብት ነው ብለው ስለሚሸጡ አንሰማም ነበር…
ቢያንስ፣ ቢያንስ ሸክላ ከበርበሬ ጋር ቀላቅለው ስለሚሸጡ አንሰማም ነበር…
ቢያንስ፣ ቢያንስ ጤፍ ከጄሶ ጋር ቀላቅለው ስለሚሸጡ አንስማም ነበር…
ከጤፍ ጋር ጄሶ ማለት እኮ ልክ መርዝ እንደመስጠት ማለት ነው፡፡ እናማ… እንዲህ ሲሆን ምንስ ነገር አይናፈቅም! የመርዝ ነገር ካነሳን ይቺን ስሙልኝማ…
ሰውየው ይቺን ዓለም ሊሰናበት ተቃርቧል፡፡ ሚስቱ አጠገቡ ተቀምጣለች፡፡ በደከመ ድምጹም “የምናዘዘው ነገር አለ” ይላታል፡፡ እሷም፤
“ውዴ እባክህ ትንፋሽህን አትጨርስ” ትለዋለች። እሱም፤
“ፍቅሬ እባክሽ ይቅር በዪኝ፡ በትዳሬ ላይ ስማግጥ ኖሬያለሁ…” ይላታል፡ ይሄኔ እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“እሱንማ አውቃለሁ፡ ለዚህ እኮ ነው መርዝ ያበላሁህ!” አለችውና አረፈች፡፡
ይሄኔ ላዛኛው ውስጥ ጄሶ ከታበት ይሆናል!
ሺ ቀጠሮ ኖሮህ አንዱም ሳይሳካ
ሺ ኢላማ አልመህ አንዱንም ሳትመታ
ሺ መንገድ አቅደህ ባንዱ እማትሄድበት
አንዳንድ ቀን አለ እንከን የሞላበት
----ብሏል ነቢይ መኮንን፡፡ እናማ…ይሄ አንዳንድ ቀን…አለ አይደል… በየቀኑ እየሆነብን ግራ ገብቶናል። ቀጠሮው አይሳካ፣ ኢላማው ግቡን አይመታ፣ አንድም መንገድ አይኬደበት…ኑሯችን ሁሉ በእርግጥም በእንከን የተሞላ ሆኗል፡፡
በዚህ የጾመ ፍልሰታ ሰሞን…‘አንዳንድ ቀን አለ እንከን የሞላበት’ እያሰኘን ካለው ኑሮ፣ አንድዬ ምህረቱን እንዲያወርድልን የልባችንን እንንገረውማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3392 times