Monday, 15 August 2016 08:52

በሰሞኑ ተቃውሞና ግጭት 142 ሰዎች መሞታቸውን መኢአድ አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(55 votes)

ቅዳሜና እሁድ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተደረገ ህዝባዊ ተቃውሞና ግጭት 142 ሰዎች መገደላቸውን መኢአድ አስታወቀ፡፡
“መንግስት በሀገራችን ዜጎች ላይ የሚፈፅመውን ግድያ በአስቸኳይ ያቁም” በሚል ርዕስ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው የመላ ኢትዮጵያውን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ በአማራ ክልል አርብ ሐምሌ 29 እና እሁድ ነሐሴ 1 በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ 82 ሰዎች መሞታቸውንና 67 ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሐምሌ 30 በአንድ ቀን ብቻ ከ60 በላይ ዜጎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሁለቱ ክልሎች በተፈጠሩ ተቃውሞዎችና ግጭቶች በኦሮሚያ 67 ሰዎች፤ በአማራ ክልል 30 ሰዎች በድምሩ 97 ሰዎች በቀጥታ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት፤ ቢቢሲ እና አልጀዚራን ጨምሮ የዓለም ዋና ዋና ሚዲያዎች ሲዘግቡ ሰንብተዋል፡፡
መኢአድ በበኩሉ ትላንትና በሰጠው መግለጫ የ142 ሰዎችን ህልፈት ያረጋገጥኩት በየዞኑና ወረዳው ባሉ መዋቅሮቼ ከተሰበሰበና ከተጠናከረ መረጃ መሆኑን ጠቅሶ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም ብሏል፡፡
መንግስት ያልተመጣጠነ ሃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብና የመከላከያ ሃይል ከግጭት አካባቢዎች እንዲወጣ ፓርቲው ጠይቋል፡፡

Read 6285 times