Monday, 15 August 2016 08:51

ኢትዮጵያ በአልማዝ ወርቅ የድል ጉዞዋን ጀምራለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(15 votes)

    ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና ትናንት በሪዮ ዲ ጄኔሮ ማራካኛ ስታዲዬም በተካሄደው የ31ኛው ኦሎምፒያድ በሴቶች የ10ሺህ ሜትር የዓለምና የኦሎምፒክ ሪኮርዶችን በማስመዝገብ የወርቅ ሜደልያ ተጎናፅፋለች፡፡ አልማዝ በ10 ሺ ሜትር ውድድሩ ተፎካካሪዎቿን በሰፊ ርቀት ቀድማ ስታሸንፍ የተደነቀው የውድድሩ ኮሜንታተር “በጣም ጎበዝ” ሲል አድንቋታል፡፡ አዲስ የዓለምና የኦሎምፒክ ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበው ሰዓት 29 ደቂቃዎች ከ17.45 ሰከንዶች ነው፡፡
37 የተለያዩ የአለማችን አገራት አትሌቶች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር፣ ብዙ ዙር ሲቀራት ቀድማ የወጣችው አልማዝ አያና፣ ተፎካካሪዎቿን እስከ መጨረሻው ድረስ በሰፊ ርቀት በመምራት የወርቅ ሜዳልያውን አጥልቃለች፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ በ5 ሺ ሜትር ማጣሪያ ቋሚ ተሰላፊ ስትሆን ስኬታማ ሆና አስቀድሞ እንደተሰጣት ግምት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ከቻለች በ2008 በቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ እንዲሁም በ1980 በሞስኮ ኦሎምፒክ ምሩፅ ይፍጠር ድርብ የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ የሰሩትን ታሪክ ትጋራለች፡፡
ዘንድሮ በ5ሺህ ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችው አልማዝ፣ በ2015 በርቀቱ የአለም ሻምፒዮን ለመሆን በቅታለች፡፡ በ10 ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኗ ኬንያዊቷ አትሌት ቪቪያን ቺሮይት፣ በውድድሩ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳልያ ሲሆን ለ4ኛ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈችው ታላቋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፤ 3ኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ወስዳለች፡፡ ጥሩነሽ በ4 ኦሎምፒኮች በ10 ሺ ሜትር ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ፤ እንዲሁም በ5 ሺ ሜትር አንድ የወርቅና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች በመጎናፀፍ ከፍተኛ ውጤት ያላት ድንቅ አትሌት ናት።  በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጥሩነሽ ዲባባ፤ ውድድሩን በድል እንደማታጠናቅቅና በተከታታይ ሶስት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ትሆናለች የሚል ግምት ነበራቸው፡፡
በ10 ሺህ ሜትር የዓለምን ክብረወሰን የያዘቺው ቻይናዊቷ ዋንግ ጁንሺያ ስትሆን፣ በ1993 በተካሄደ ውድድር 29፡31.78 በመግባት ነው ለድል የበቃችው። ትናንት አልማዝ አያና፤ የወርቅ ሜዳሊያዋን ስትጎናፀፍ፤ ይህን ለ23 ዓመታት ሳይሰበር የቆየ ክብረወሰን በ14 ሰኮንዶች አሻሽላዋለች፡፡
ትናንት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በተከናወነው የወንዶች 800 ሜትር የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው መሃመድ አማን፤ ከምድቡ 2ኛ ሆኖ በመጨረስ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል፡፡
ትናንት ሌሊት 8 ሰዓት ከ30 ላይ የሴቶች የ1ሺህ 500 ሜትር ማጣሪያ ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን፣ ዛሬ ተሲያት ላይ ደግሞ የሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ እንዲሁም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ25  ላይ  የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜና፣ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ደግሞ የወንዶች የ800 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 31ኛው የሪዮ ኦሎምፒክ ከ200 የዓለማችን አገራት የተውጣጡ 11 ሺህ አትሌቶች በ42 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኦሎምፒክ ሪከርድ በ2008 ቤጂንግ ላይ በጥሩነሽ ዲባባ በ29 ደቂቃዎች ከ54.66 ሰከንዶች የተመዘገበ ሲሆን ይህንንም ክብረወሰን በትናንትናው ዕለት አልማዝ አያና ሰብራዋለች፡፡
በ10ሺ ሜትር ሴቶች የኦሎምፒክ ውድድር ከ1988 እኤአ በሲኦል ኦሎምፒክ የተጀመረ ሲሆን ከአልማዝ አያና የወርቅ እና ከጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ ሜዳሊያዎች በኋላ ኢትዮጵያ በ8 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ 5 የወርቅና 2 የብር 3  የነሐስ ሜዳልያዎች ያስመዘገበች ሆናለች፡፡ የመጀመርያን የሜዳልያ ክብር በወርቅ ሜዳልያ ያሳካችው በ1992 እኤአ በባርሴሎና ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ ነበረች። በ1996 እኤአ በአትላንታ ኦሎምፒክ ጌጤ ዋሚ የነሐስ፤ በ2000 እኤአ በሲድኒ ኦሎምፒክ ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ እና ጌጤ ዋሚ የብር፤ በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ እጅጋየሁዲባባ የብር እና ደራርቱ ቱሉ የነሐስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡
አልማዝ አያና በ2016 ዳይመንድ ሊግ የሮም ከተማ ውድድር ላይ በ5ሺ ሜትር የምንጊዜም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት 14:12.59 ማስመዝገቧ የሚታወስ ሲሆን ጥሩነሽ ዲባባ የ5ሺ ሜትርን የዓለም ሪከርድ ካስመዘገበች 8 ዓመታት ቢያልፉም፤ አልማዝ በሮሙ ውድድር በ1.44 ሰከንዶች በመዘግየቷ ሪከርዱ ለጥቂት ነበር ያመለጣት፡፡
በ3ሺ ሜትርና በ5ሺ ሜትር ሯጭነት፣ በአስደናቂ አሯሯጥና ታክቲክ፣ እንደሮኬት በምትወነጨፍበት አጨራረስ የምትታወቀው አልማዝ ትናንት በ10 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ የተጎናፀፈችው ገና በሦስተኛ ውድድሯ ነው፡፡
በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቤጂንግ ላይ በ5ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ በሻምፒዮናው ከፍተኛ ብቃት ያሳዮ ምርጥ አትሌቶችን በልጣ በተመልካች ከተሰጠው ድምጽ 23.84 በመቶ የሆነውን ድምጽ በማግኘት የአዲዳስ የወርቅ ጫማ ሽልማት ወስዳ ነበር፡፡ በ2013 ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ የብር፣ በዓለም የአትሌቲክስ ዋንጫ የወርቅ ፣ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችም የሰበሰበችና ለሁለት ጊዜያት የኢትዮጵያ ሻምፒዮንም ለመሆን የበቃች ምርጥ አትሌት ነች፡፡
በ2015 የአመቱ ምርጥ የአፍሪካ ሴት ስፖርተኛ ተብላ ልዮ ሽልማት የተቀበለችው አልማዝ፤ የመከላከያ ስፖርት ክለብ አትሌቲክስ ቡድን አባል ስትሆን ተወልዳ ያደገችው በቤንሻንጉል-ጉሙዝ መተከል ዞን ወንበራ ወረዳ አዲስዓለም ቀበሌ ነው። ባለቤቷ እና የግል አሰልጣኟ አትሌት ሶሬሳ ፊዳ ይባላል፡፡



Read 6743 times