Monday, 08 August 2016 06:20

ግስ አርቢዎቹ

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(6 votes)

  “ፀሐፊዎች መተባበር ሳይሆን መወዳደር ነው ባህሪያቸው” እያለው የራሱ ጭንቅላት ከጓደኛው ሂስ ለመቀበል ቤቱ ድረስ ሄደ፡፡ የሄደው ቀጭኗን የኮረኮንች መንገድ ይዞ ነው፡፡ አሁን ግን መንገዷ ኮብል እስቶን ለብሳለች፡፡ ወደ ጓደኛው ሰፈር ከመጣ ብዙ ወራት አልፎታል፡፡ ጓደኛውም እንደሱ ለፅሁፍ ብሎ ሁሉንም አለም እርግፍ አድርጎ የተወ ነው፡፡ እሱ ፅሁፍን ይፈልጋታል እንጂ እሷ ግን እሱን ብዙም የምትፈልገው አይመስልም፡፡ አዲስ ነገር መፃፍ ትቷል፡፡ ቤቱ ውስጥ ተቆልፎ ከቀናት እስከ ወራት፣ ከወራት እስከ ዓመታት ያሳልፋል፡፡
ቀስ በቀስ “ገጣሚው የት ጠፋ?... አግኝታችሁት ታውቃላችሁ ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎች እየተመናመኑ መጡ፡፡ ከሰዎች መሀል የጠፉት ባልጠፉት ይተካሉ፡፡ ይረሳሉ፡፡ ተረሳ፡፡
ይሄኛው ጓደኛው ብቻ በስምንት ወራትም ቢሆን እየመጣ ይጠይቀዋል፡፡ የሚጠይቀው የጠፋው ሰው ሁኔታ አስጨንቆት ሳይሆን እሱ ራሱ የደረሰበት የእድገት ደረጃ ከእዛኛው ዝቅጠት ጋር በቁስል መለኪያው እየጠለቀ ሊያቆስለው በመፈለጉ ነው፡፡ ሁለቱም የድርሰት ቄሶች ናቸው፡፡ አንዱ በመንደር ገዳም ሌላኛው ከሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ትከሻ ሲተሻሽ ይውላል፡፡ ሲተሻሽ ውሎ አሁን አዲስ መፅሐፍ አውጥቷል፡፡ ይኼኛው የመጀመሪያ መፅሐፉ ነው፡፡ ስለ መጀመሪያ መፅሀፉ ህትመት የሰማውና በራሱ ደግሞ ያዘነውን ጓደኛውን በእሱ ፊት ዝቅ ሲል ለማየት አልሞ ቤቱ ድረስ ሄደ፡፡
የኮብል እስቶኑ መንገድ ወገብ ላይ በስተግራ ሱቋ  አለች፡፡ ሱቋ ውስጥ እናትየው አይጠፉም፡፡ በመንገዱ የሚመጣና የሚሄደውን ሰው ከሩቅ እስከ ቅርብ … ብቅ ብሎ እስኪሰወር … ሲቆጥሩ ይውላሉ፡፡ ሱቋ ለንግድ ስራ እንደሚቋቋሙ የአስፋልት ጎዳና ሱቆች በሸቀጥና ምናምንቴ የተሞላች እደለችም፡፡ የመንደር ሱቅ ናት፡፡ በትንሽ ወጪ፣ ከትንሽ የንግድ እውቀት … እና በግማሽ አላማ የምትከፈት ናት፡፡ የተከፈተችው ለመዋያነት ነው፡፡ በመዋያ ሞያቸውን ለመስራት እናትየትው ከሱቁ አይጠፉም፡፡
ገና ከላይ ሲመጣ አይተውታል፡፡ እሱም ሲያዩት አይቷል፡፡ እስኪደርስ ማየታቸውን ቀጠሉ፤ እሱን መታየቱን፡፡ ግራ ስለገባው ስልኩን የውሸት አውጥቶ መደወል ነበረበት፡፡ ከብዙ ቆይታ በኋላ አጭሯን መንገድ አገባዶ፣ የሱቋ መስኮት ጋር ደረሰ፡፡ የተለመደውን ግን ምንም ትርጉም የሌለውን ሰላምታ በልዋጭ አቀረበ፡፡
ሱቋ በብረት ፍርግር ተማግራለች፡፡ የብረት ሰራተኛና በያጅ ሁሉንም ነገር በሚበይድበት ዘመን የታነፀች መስኮት ናት፡፡ ሁሉም ዜጋ የሌባ ዘረ መል እንዳለው፣ እርስ በራሱ በሚተዋወቅበትና በሚጠረጠርበት ሀገር ላይ ትርፋማ የሚሆነው የብረት ሰራተኛው ብቻ ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን፤ የብረት ሰራተኛውን ግንበኛው መጣና በለጠው፡፡ ረጃጅም አጥሮች በመገንባት እንደዚሁም የቤቶችን ቁመት ወደ ፎቅ በማሳደግ፣ የብረት ሰራተኛውን ብየዳ መቀነስ እንደሚቻል ተደረሰበት፡፡ ድሮ ሌባ በመሰላል ነበር አጥርን ተሻግሮ የሚገባው፡፡ አጥርን ተሻግሮ በመግባት ፎቅን መውጣት የሚያስችል መሰላል ባለመኖሩ፤ ግንበኛ ብረት ሰራተኛን አሸነፈው፡፡ ሌባ ግን መቼም አይሸነፍም፡፡ በፎቅ ቤቶቹ ውስጥ ሌባ ከውጭ፣  ሳይሆን ከውስጥ፣ መፈጠሩ አልቀረም፡፡
ፀሐፊው፣ ከዛሬ ስምንት ወር በፊት ጓደኛውን ሊጠይቀው በአሁኑ መንገድና አኳኋን በመጣበት ጊዜ በብረቱ ፍርግርግ ውስጥ እናትየው “እንደው ይሄንን ልጅ መምከር አቃታችሁ? … … ሌሎች ጓደኞቹ ርቀውታል፡፡ እንግዲህ አንተና መኮንን ብቻ ናችሁ እየመጣችሁ የምትጠይቁት … መኮንንም የት አገር ገባ ነው ያሉት? … በቃ አንተ ብቻ ነው የቀረኸው፡፡ ጓደኛውን የሚያስብ ማንም የለም፡፡ ሁሉም ለራሱ ነው …”
ቤት ውስጥ ራሱ ላይ ዘግቶ የተቀመጠውን ገጣሚ እንደሚመክረው ቃል ገብቶ ነበር፣ ያኔ የተለያቸው፡፡ ያኔ የዛሬ ስምንት ወር ገደማ፡፡ እናትየውና እሱ እያወሩ፣ ገጣሚው ከኋላው ሲመጣና ሰላምታ መለዋወጥ ሲጀምሩ … እናትየው .. አቤቱታውን ከአንሰራፉበት አየር ላይ እያፈሱ ወደ አፋቸው መልሰው ከተው ሹልክ ብለው መሰወራቸው ትዝ ይለዋል፡፡ እናቱ የምትፈራው ልጅ፤ እንደ አባወራ አይነት ባህሪ አለው፡፡ አባ ወራ ብዙውን ጊዜ መአረጉን የሚቀዳጀው፣ ሚስትየዋን በማግባት ብቻ ሳይሆን … ሚስትየዋን በልጆች አማካኝነት ወደ እናት ማሳደግ ስለሚችልም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አባ ወራ … አባባ የሚሉትን ማሳደግና ከእናታቸው ላይ ጣራው እንዳይነሳ ህይወቱን ሙሉ በመፍጨርጨሩ ምክኒያት ነው የአባባነት ማእረግ የሚያገኘው፡፡
ገጣሚው ብር የለውም፡፡ ሱቁ ውስጥ ያሉት ሴትየዋም አምጠው ስለወለዱት፣ ልጅ ነው ማለት ነው፡፡ ግን ያደገው እስከ ሀያ አምስት አመቱ ድረስ ብቻ ነው፡፡ አሁን አርባ ዓመቱ ቢሆንም ከሀያ አምስት መቱ በኋላ ያሉት አመታት አስተሳሰቡን ጨምሮ እተደጋገሙ አሁን ያለበት እድሜ ድረስ ዘልቀዋል፡፡
ብዙ ሰዎች ልጅ ለምን ወደ “አባባዎች›› አለም ሊያድግ እንዳቻለ የራሳቸው መላ ምት ይሰጣሉ፡፡ እናቱ ማሳደግ ማቆም ስላልቻሉ ነው ልጅ ያደገው፤ የሚሉ አሉ፡፡ አገሩ ስላላሳደገው ነው ‹‹ሀገሬ አላደገም›› እያለ ይከራከር የነበረው በማለትም ተወያይተዋል፡፡ የባከነው ትውልድ አባልነቱ ስለሚያናድደው ነው በራሱ እንቢታ ውስጥ ገጣሚ ነኝ ብሎ የተደበቀው የሚሉም ብዙ ናቸው፡፡ ገጣሚነቱን ሁሉም የሰፈሩ ሰዎች ቢያውቁም፣ የግጥም መፅሀፍ እንዳሳተመ ግን መርሳት ነው የሚፈልጉት፡፡ መርሳት የሚፈልጉት በተለይ እሱ ባለበት ቦታ ላይ መሆኑ ይገርማል፡፡
“እሱን ነገር ቢተው እኮ ህይወቱ ይስተካከል ነበር” ብለውታል፤ እናትየው የመጀመሪያ የግጥም  መፅሐፍ ባወጣ ሰሞን፡፡ ደራሲ፣ ግጥሙን ወይንም የግጥም መፅሀፍ መፃፉን ቢረሳ፣ የኑሮ መፅሐፍ መነበብ እንዳለበት ይታወሰው ነበር ማለታቸው ነው፡፡ ግን እናትየው ግጥምን ስለመተው አስፈላጊነት እየተናገሩ፣ የሚነግሩት ሰውም ፀሐፊ መሆኑ ድንገት ሲታወሳቸው እንደ ማፈር ብለው ወደ ሌላ ወሬ ተሻገሩ፡፡ መፅሐፍ ያሳተመ ሰውን መኪና ከገዛ ሰው እኩል እንደማያከብሩ  በነገረ ስራቸው ያስታውቃል፡፡
“ዶሮ ማርባት ለመጀመር … ተመዝግቤ … ቦታ ተከራይቼ ጨርሻለሁ፡፡ … መንገር ግን ፈራሁ፡፡ ሌላ ሰው ዶሮ አርብቶ ስላገኘው ብር ስነግረው … ቅንቅን … ምናምን … ምንድን ነበር ያለው እቴ? … ብሎ አጣጣለብኝ” ይሄንንም ለፀሐፊው የነገሩት የዛሬ ስምንት ወር  በፊት ነበር፡፡ የዛሬ ስምንት ወር፣ ገጣሚው ከፀሐፊው ጀርባ መጥቶ፣ ሰላም ሳይለው በፊት በወፋፍራም ብረት ተጠቅጥቆ፣ እንደወንፊት በተማገረው መስኮት በኩል እናትየው ስለ ልጇ ያወራችው፡-
“እናትህ፤ የዶሮ እርባታ እንድትጀምር ፈልገው እንድነግርህ ለምነውኝ ነበር” አለው ፀሐፊው ያን ቀን፤ የዛሬ ስምንት ወር በፊት፡፡
“እኔ እንደዚህ ህዝብ ዶሮ ላርባ? … ለቅንቅናም ህዝብ ነው የዶሮ እርባታ የሚጠቅመው” ብሎ በንቀት መልሶለት ነበር፡፡ የዶሮውን እርባታ የናቀው የግስ እርባታው ላይ በትጋት ተጠምዶ ቢሆን  አንድ ነገር ነው፡፡ እሱ ዶሮውንም ግሱንም አያረባም፡፡ ወይንም የግስ እርባታውን ተጠቅሞ፣ ለምን ዶሮ ማርባት እንደማይጠቅም አይቀኝም፡፡ ምንም ነገር የማያረባ ሰው አይረባም ይላሉ፡፡ ወይ ልጅ፣ ወይ ብር፣ ወይ ስም፣ ወይ እውቀት .. ሰው እስከሆነ የሆነ ነገር ማርባት አለበት ባይ ናቸው፤ ባዮቹ፡፡ ካልሆነ “አይረባም!”
ወደ መስኮቱ ተጠግቶ የውሸት ሰላምታዎች፣ ምነው ጠፉ(ሆች) … ምን እየሰራህ ነው (ዎች)…? ከእናትየው ጋር፡፡ ፀሐፊው በኋላ … ገጣሚውን እንዲያስጠሩለት ጠየቃቸው፡፡ ፀሐፊውና የድሮ ጓደኞቹ፤ ገጣሚው ቤት ውስጥ ተቆልፎ መቀመጥ ያበዛ ጊዜ “አንተ የቤት ውስጥ ሀምሌት… አትወጣም?!” እያሉ ከተደበቀበት እንዲወጣ ይገፋፉት ነበር፡፡ እሱም ሳይወጣ፣ እነሱም አለመውጣቱ ሳይገባቸው ቀሩ፡፡
እናትየው ጮክ ባለ ድምፅ፤ “ንፁህ” ብለው ልጃቸውን ጠሩት፡፡ ድሮ እንደ ስሙ ንፁህ ነበር፡፡ በልቦናውም ሆነ በልብሱ፡፡ “ኧረ ጠፋህ … ልጄን አንተም ሸሸኸው … እስቲ ምናለ ሌላው ነገር እንኳን ቢቀር ልብሱን አስተካክሎ እንዲለብስ ብትነግረው … ንፁህ ልብስ አልለብስም ብሎ አስቸግሮኛል” አሉ፤ ከመምጣቱ በፊት በፍጥነት፡፡ ፀሐፊውን ሲመለከቱ የሚመጣባቸው የ ልጃቸው ጉዳይ ነው፡፡ ለምን ራሳቸው እንደማይነግሩት ፀሐፊውን አልገባውም፡፡ ምናልባት በእናትየው ዘመን ልጅን የሚቀይረው ጓደኛው ነበር፡፡ ያሁኑ ዘመን እንደዛ መስሏቸው ነው፤ ሲል አሰበ፡፡ ‹‹በእኛ ዘመን ጓደኛን ለመቀወር ነው የምንጎበኘው፡፡ ለመቀየር አይደለም፡፡ ልቀውረው ነው የመጣሁት፤ ልቀይረው አልችልም››
ገጣሚው እየተጎተተ ወጣ፡፡ ጫቱ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ፀሐፊው መልኩን አስተውሉ፣ ግስም ሆነ ዶሮ ሲያረባ እንዳልከረመ አወቀ፡፡ የለበሰው የወጣት ልብስ ነው፡፡ በኮሌታው በኩል ብቅ ያለው፣ አንገቱ የተቋጨበት ጭንቅላቱ ብቻ የትልቅ ሰው ሆኗል፡፡ በኮትና በጨርቅ ሱሪ መታየት የነበረበት ጭንቅላት ነው፡፡ በእስኒከር ጫማ ውስጥ አድርጎ በ Skinny ሱሪ፤ ከዛ በሸሚዝ አንገት ኮሌታ ወጥቶ ሰላም ሊለው ፈገግ አለ፡፡ ገጣሚው ራሱን ብቻ ሳይሆን ፀሐፊውንም ስለመምሰሉ ትዝ አለው፡፡ ሁለቱም በሀያ አምስት አመት ልብስ ነው አርባ አመታቸው ላይ ያሉት፡፡ በራሳችን ዘመን ለሀያ አምስት ይሆነን የነበረውን ብንለብስ ያምርብን ነበር፤ ብሎ ፀሐፊው አሰበ፡፡ ሰላም ተባባልን፡፡
በግራና ቀኝ ጉንጮቹ ላይ ነጭ ፀጉር ጣል ጣል ብለዋል፡፡ አርፎ እንዳይሞት ለምን ምቀኛ እንደምንሆን አላውቅም፡፡ “እሱን ከራሴ መኖር ጋር ካላነዋወርኩ፣ እኔም በመኖር ላይ መሆኔ አያስታውቅማ›› ብሎ ፀሐፊው ከራሱ ጋር በመሀል ይወያያል፡፡  
ከሰላምታው በኋላ ገጣሚው  መንገዱን በረጅሙ ተመለከተው፡፡ ኮብል እስቶን መነጠፉን ያላወቀ ይመስላል፡፡ “ሁሉም ነገር አዲስ ሆኖበታል፡፡ እሱ አዲስ ለሆነበት ነገር ሁሉ፣ እሱ ደግሞ በተቃራኒው አሮጌ መሆኑን ግን አልተገለጠለትም›› መፅሐፍ ማውጣትህን ሰማሁ ይለኛል ብሎ ሲጠብቅ ዝም አለው፡፡ ‹‹አለሁ! አለሁኝ! ጠፋህ አልጠፋሁም! ምን ባክህ ሩጫ በዛ! አበዛሁት! ጤና! ሰላም ነው? ናችሁ? ቤተሰብ?››
ሲሻተቱ ቆዩ፡፡ ፀሐፊው፤ ገጣሚ ምን ሲሰራ እንደቆየ ማወቅ እንደጓጓው፣ ያንኛውም በተቃራኒው… ማወቅ ፈልጓል፡፡ ፀሐፊው ጓደኛው የት እንደቆመ ማወቅ እንደጓጓው  ወይንም የቱ ጋ ሞቶ የቱ ጋ እንደተቀበረ ያሳየኛል በሚል ጠበቀው፡፡
‹‹መፅሐፌን አገኘኸው?››
እንዳልሰማኝ ፂሙን እየደባበሰ ዝም አለ፤ ገጣሚው፡፡ ጥያቄውን አልደገመለትም፤ እንደሰማ አውቋል፡፡ ‹‹ድሮ የጠፉ ጓደኞችን መሞታቸውን አስቀድሞ ሰምቶ፣ ወሬውን እቤታችን ድረስ መጥቶ የሚያረዳን እሱ ነበር፡ ባሌ ሄዶ እየኖረ መሆኑን በማወቃችን፣ ተደንቀን የወሬው እፍታ ሳይወጣልን ባሌ የሄደው ጓደኛችን መሞቱን የነገረንም ይኸው ገጣሚው ነው›› ውልደትን የሚያበስሩ እንዳሉ ሁሉ ሞትን የሚያረዱም አሉ፡፡ ገጣሚ ሞትን ያውቃል፡፡
ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ተወለደ ብሎ ሊናገር የመጣው ፀሐፊ፤ የመጀመሪያው መፅሐፍ የሞተ መሆኑን በአጭር ቃል ነገረው፡፡ ‹‹በሕይወት ያለነው እኔና እሱ ብቻ መሆናችንን ነገረኝ፡፡ በምን ምክኒያት ገና ከመወለዱ መፅሐፌ እንደሞተ ስጠይቀውም ዝም አለኝ፡፡ የሁሉም ምክኒያትና ውጤት ሞት ነው ማለት ነው››  ‹‹ሌሎች ሰዎች ግን ህያው ነው ብለውኛል›› አለው ፀሐፊው፤ ግን ቁመቱ እያጠረ ሲመጣ ይሰማዋል፡፡ ገጣሚው ሞትን በደንብ ያውቃል፡፡ የራሱ የግጥም መፅሐፍ ሲሞት አይቷል፡፡ መሞቱን አምኖ ቀብሮታል፡፡
ጭራሽ ገጣሚው ፀሐፊውን ተቆጣው፡፡ ለምን የተሞተ መፅሐፍ ወለድክ እንደ ማለት ‹‹ሊያስተዛዝነኝ? ይገባ ነበር፡፡ ግን እኔ የሱ የበኩር መፅሐፍና የገጣሚነቱ ፃረ ሞት በመንፈስ ውስጥ ሲመላለስ መች አስተዛዘንኩት? ስለ ዶሮ ርቢም ሆነ ስለ ግስ ርቢ ሳልጠይቀው… በውሸት ተስፋዎች  ተገናኝተን እንደምንጨዋወት ነው በቅርቡ ሳገኘው አወራለት የነበረው››
ወደ ቤቱ ተመልሶ መፅሐፉን ‹‹ሰልሳዊን›› አንስቶ እያገለበጠ አየው፡ እንደ በፊቱ በአይኔ ስር እንደ እንቦቃቅላ አይቦርቅም፤ በድን ሆኗል፡፡ ‹‹መልአኩ የመስከረውን  አመንኩ፡፡ መሞቱን ላረጋግጥ የሄድኩበት ሰው፤ ልጄ መሞቱን አረዳኝ፡፡ ማንም ደፍሮ ያልነገረኝን እሱ ነግሮ ጨከነብኝ››
ልጅ የሞተበት ሰው ሀዘኑ በቀላሉ አይወጣም፡፡ ማንም ወላጅ ልጁን መቅበር አይፈልግም፡፡ ልጅ፤ እሱ በመአረግ ቀብሮ እንዲያስከብረው ነው አባት የሚፈልገው፡፡ አባትነት ልጆች እስከኖሩ ብቻ ነው፡፡ ወይንም የልጅ ልጆች፡፡ገጣሚው የገጠመው መከራ፤ ለፀሐፊው የገባው፣ የሆነው ነገር በእሱም ሲደርስ ነበር፡፡ ሞትን ከልደት አስበልጦ ይፈልግ ጀመረ፡፡ ማንም ቀብር ላይ ይገኛል፡፡ መርዶ ለመንገርም የማይሳሳ ሆነ …. ከነገረው መርዶ በኋላ በስምንት ወር ሳይሆን በየቀኑ ከገጣሚው ጋር መገናኘት ጀመሩ፡፡ አንድ ላይ የሞቱ ልጆቻቸውን እያነሱ… ቢኖሩ ኖሮ ምን ሊሆን ይችሉ እንደነበር እየተመኙ… ልጆቻቸውን የገደሉ እነማን እንደሆኑ በምሬት እየገለፁ፣ ቶሎ ቶሎ መገናኘት ቀጠሉ፡፡ የገጣሚው እናት የሚያረቧቸው ዶሮዎች፤ በቁጥር ሲጨምሩ ልብ አላሉም፡፡ የቁጥራቸውን መጠን በደቂቃዎች አካፍሎ ከተፍ የሚል ፈንግል፣ ዶሮዎቻቸውን ሲፈጅባቸው፣ ልናፅናናቸው እንሄዳለን፡፡ ከምናፅናናቸው ዶሮ በማርባቱ ብናግዛቸው እንደሚሻላቸው እየተማረሩ ይነግሩናል፡፡ ግስ ማርባት እንደ ዶሮ ማርባት ቀላል አይደለም፡፡ የረባ ዶሮን እንደሚገድለውም ፈንግል  አይደለም፡፡ የድርሰት ሞት፤ ተመልሶ ጫጩት ተገዝቶ ወደ እርባታ ለመግባት ያስፈራል፡፡ ቅስም ይሰብራል፡፡  እንደ ፀሐፊውና ገጣሚው ያደርጋል፡፡ ሀዘንን አሸንፎ ለመውጣት ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ምናልባትም እድሜ ልክ፡፡

Read 3998 times