Monday, 08 August 2016 05:57

መርሳት፤ አንዱ ጥበብ፣ ሌላው ጀሃነብ!

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ)
Rate this item
(3 votes)

 ስለመርሳት ሳስብ ሁለት ሰዎች አስታውሳለሁ፤ አንዱ… በመርሳት የታወቀ፣ ወይም የመርሳት ተሰጥኦ ያለው አለበለዚያም የመርሳት ችግር ያለበት አንድ ልጅ አለ፡፡ ለመርሳት ፣ የሚያሳየው ፍጥነት ከዕለት ወደ ዕለት ጨምሮ ወደ መጨረሻ ገደማ እያወራም መዘንጋት ጀመረ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡-
አንድ የጎረቤት ሰው መጥቶ ‹‹ቹቹ፤ እናትህ አለች?›› ሲለው
‹‹የለችም›› ብሎ ይመልሳል
‹‹የት ሄደች?›› የሚል ጥያቄ ሲደገምለት እረስቶ
‹‹ማን?›› ብሎ መልሶ ይጠይቃል
‹‹እናትህ?›› ሲሉት
‹‹በእናት›› ሲሉት
‹‹እራስህ እናትን›› ሲል ለፀብ ይጋበዛል፡፡
…ሌላኛውን የተዋወቅሁት ነፍሱን ይማርና በአያሻረው (አስማማው ኃይሉ) ወግ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ ለሠላሳ አምስት አመታት የኖረ የኢህአሠ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ሠራዊት) ታጋይ ነው፡፡ በመጨረሻ ዕድሜው ላይ ሁሉን በመርሳት የአእምሮ ህመም (Alzheimer) ተያዘ፡፡ ዘመድ፣ አዝማድ ብቻ ሳይሆን ቋንቋ ሁሉ ጠፋው የአፍ መፍቺያ ቋንቋ ተራ ቱማታ በሆነበት ወቅት አንድ ቃል ብቻ አልጠፋውም ነበር፤ ያም ቃል የትግል ሥሙ የነበረ ነው፡፡ ‹‹በትግል ስሙ ሲጠሩት ይዞራል›› ብሎ አያሻረው አለቀሰ፡-
በእርግጥም ያስለቅሳል፡፡ ያ የትግል ሥም ምን ትኩረት ቢሰጠው፣ እየትኛው የአንገሉ ጥግ ቢወሽቀው ትውስታን ሁሉ ከሚያጠፋው የአእምሮ ወረርሽኝ ተረፈ? ከበሽታው በላይ የትግል ሥሙ ተአምር አይሆንም? ከበሽታው ባሻገር በዓመታት መግፋት በራሱ ጊዜ ሊጠፋ አይገባውም ነበር?
….. ሰው እራሱ ተአምር ነው፡፡ ትኩረት የማይሠጠው በሰከንዶች ሽራፊ ከአእምሮው ሲያስወግድ፤ አክብዶ ያየውን ደግሞ እንደ መክሊት ላያተርፍበት አእምሮው ውስጥ ቀብሮት ይኖራል፡፡ ከማስታወስ ይልቅ መርሳት እንደ ጉድለት ስለሚታይ፣ የሰው ልጅ የመሳትን ምንጭ ለማግኘት ብዙ ዳክሯል፡፡ የሥነ ልቡና ምሁራን፤ ለምን እንረሳለን? ለተሰኘው አውራ ጥያቄ መንታ ምላሾችን ያቀርባሉ፡፡ አንዱ ሊታወስ የሚባው መረጃ፣ ከቦታው ሲጠፋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ መረጃው ቢኖርም አንቅቶ ለመጠቀም ሲያዳግት ነው ይለሉ፡፡ ነገርየው የቀበሌ መዝገብ ቤት መሰለ እንዴ? ‹‹ፋይልህ ጠፍቷል›› ለካ ተፈጥሯዊ ነው? ስንቀጥል….
….. ስለመርሳት ሳስብ ሌሎች ሁለት ሰዎች ትዝ ይሉኛል፡፡ አንዱ እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ በርናንዶ ሾ ነው፡፡ በባቡር ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ እየተጓዘ ነው፡፡ ፊርማታ ላይ ትኬት ተቆጣጣሪው፤ ሾ  ወዳለበት ፋርጎ ገብቶ፡-
    ‹‹ትኬት አውጡ፣ ትኬት›› ሲል ጮኸ፡፡
ሾ ከተመሰጠበት ተናጥቦ ትኬቱን መፈለግ ይጀምራል፡፡ የደረት ኪስ፣ የጎን ኪስ፣ የኋላ ኪስ፣ የውስጥ ኪስ፣ የቦርሳ ኪስ፣ የምስጢር ኪስ፣ የፓንት ኪስ…. ትኬት የለም፡፡ ተበሳጨ፡፡ የፈተሻቸውን ኪሶች መልሶ ፈተሸ፤ አጣው፡፡
ትኬት ተቆጣጣሪው ትኬቱን እንዳጣው ስለገባው፤
‹‹ሚስተር ሾ፣ እርስዎን የማያውቅ ሰው የለም፡፡ ቀስ ብለው ይፈልጉት፤ ካጡትም ግዴለም፤ እርስዎ ያጭበረብራሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ይጥፋ!›› አለ፡፡
ሾ ቱግ ብሎ፤ ‹‹ትኬቱን ላንተ የምፈልገው መስሎሃል? ለእኔ ነው፤ የምሄድበት‘ኮ የተፃፈው ትኬቱ ላይ ነው›› ለካ መሄጃው ጠፍቶታል፡፡ ይሄ መርሳት የጭንቀትላት ጉድለት አይሆን እንዴ? የሾን የመርሳት ልክፍት በሁለተኛው በአይዛክ ኒውተን እናፅናው፡፡
የሒሳብ ሊቅ ሰር አይዛክ ኒውተን፤ በሥራ ከሚጠመድበት ክፍል ፊት ለፊት ጠረጴዛ ላይ የሚመገበው ይቀመጥለት ነበር፡፡ እንዳይረበሽ ነው፡፡ በሆነ ሰዓት ወጥቶ ይመገብና ተመልሶ ይገባል፡፡ አንድ ቀን ግን አንድ ወዳጁ በቀጠሮ መጥቶ ሲጠብቀው፣ የምግቡን ጥሪ መቋቋም  ተሳነው፡፡ በዚህ ላይ ርቦታል፡፡ ቀርቦ መመገብ ጀመረ እስኪጨርስ ድረስ ኒውተን አልወጣም፡፡ በኋላ ብቅ ሲል ሰሃኑ ባዶ ነው፡፡ እንዲህ አለ፡-
‹‹አይ የኛ ፈላስፎች ነገር! እራት ያልበላሁ መስሎኝ ልበላ መውጣቴ ነበር፡፡ ለካ አቀላጥፌው ኖሯል፡፡ (How absent we philosophers are, I realy thought that I had not dined)
አለማስታወስ የበሽተኞች ወይም የደደቦች አለበለዚያም የልበ-ቢሶች ብቻ እንዳልሆነ በበርናርድ ሾ እና በኒውተን ያረጋገጥነው ጉዳይ ይመስላል፡፡ ታዲያ መርሳት ምንድነው? የማነው? ጉዳት አለው? ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ ጥቅምስ? እያልን በጥያቄ መታጠር የሰው ልጅ ሁሉ ባህርይ ነው፡፡ የቼኩ ደራሲ ሚላን ኩንዴራ (Milan Kundera) መርሳት ላይ ያተኮረ አንድ ልቦለድ አለው፡፡ “The book of Laughter and Forgetting” የሚል፡፡ ገፀ-ባህሪዎቹ እንደ ደሴት የተከፋፈሉ ታሪኮችን የሚያስተዳድሩ (እንደ አዳም ረታ) ናቸው፡፡ የአንዱ አንባ ታሪክ ገዢ ሚርክ (Mirek) ማስታወስን የሥልጣንና የበላይነት ምንጭ አድርጎ የሚናገርበት ጥቅስ አለው፡፡ (The struggle of man against power is the struggle of memory against forgetting) ይላል፡፡ ትውስታውን የሚያነቃ የኃይል ባለቤት ከሆነ፣ የማያነቃው የደካማነት ድልድል ውስጥ ይገባል ማለት ነው? እንዲህ ከሆነ በዝንጋኤ ታሪክ የተጥለቀለቀ የህይወት ታሪክ ያላቸው ደራሲዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የሂሳብ ሊቆች … እንዴት ማስደግደግ ቻሉ?
ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬዲሪክ ኒች (Friedrich Nietzsche) በመርሳት ላይ የኩንዴራ ተቃራኒ አቋም ያለው ይመስላል፡፡ ነገሮችን ለመርሳት አለመቻል፤ ለመኖር አለመቻል ነው በሚል፡፡ ታሪክን (ታሪክ ማስታወስ አይደል?) የሚያብጠለጥል አንድ መፅሐፍ አዘጋጅቷል- “Disadvantage of History for life” የሚል እዚህ መፅሀፍ ውስጥ እንዲህ የሚል አባባል አለ፡-
“መርሳት ባይኖር መኖር ጨርሶ አዳጋች ይሆን በነበር” (without forgetting it is quite impossible to live at all)
ለሰው ልጅ የማስታወስ ጥበብ ብቻ ሳይሆን የመርሳት ክህሎትም ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ነገሮችን በመርሳት የሚቸገሩ እንዳሉ ሁሉ ለመርሳት ባለመቻልም የሚሰቃዩ ሞልተዋል፡፡ በቀላሉ የጦርነት፣ የግርግር የሽብር ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ማሰብ ይበቃል፡፡ በቀይ ሽብር ዘመን ልጆቸውን ያጡ አንዲት እናት ታሪካቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ልጃቸው ከተገደለ ከአርባ ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም እናቲቱ አሁንም የልጁን አልጋ እያነጠፉ፣ ቤቱን እየጠረጉና ውኃ በጠርሙስ እየሞሉ ‹‹አትንጫጩ፣ ይተኛበት” ይላሉ አሉ፡፡ ይሄ መርሳት አለመቻል፣ ከእውነታ ሲያቆራርጥ አይደለም? ታዲ ኒች… ይሄን እንጂ ሌላ ምን አለ?
ስቲፈን ካርፔንተር (Stephen Carpenter) የኒቼን ሀሳብ የሚደግፍና የሚያስደግፍ አቋም ያለው ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ካርፔንተር መዘንጋት ያለባቸውን በብዛት ይመጥናቸዋል እንጂ እንደ ኒቼ በጅምላ አይፈርጅም፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“መኖርን ለማስቀጠል ካሻህ መረሳት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡” (There are things that have to be forgotten if you want to go on living) እዚህም ላይ የማስታወስ ብቻ ሳይሆን የመርሳት ጥበብን መማር ሊጠበቅብን ነው ማለት ነው፡፡ የሥነ ልቦና ኮርስ 101 (መተዋወቂያ) የማስታወስ ብቃትን እንዴት ማዳበር እንደሚቻልና እራሱ የማስታወስ ባህርይ ምን እንደሚመስል የሚተነትን ምዕራፍ አለው፡፡ አእምሮ መረጃዎችን የሚደረድረውና ሲያስፈልግ የሚያቀርበው ነገሮችን ዘርፍ፣ ባህሪና አዝማሚያ እያለ በመደልደል ነው አሉ፡፡ መቅደስ አና ቅድስት የተባሉ ስሞችን በባህሪና በድምፅ ዘርፍ ስለሚመሳሰሉ አእምሯችን መመዝገብና ሲያስፈልግ ፋይሉን አውጥቶ ማቅረብ የሚቸገረው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ የነገሮችን አምታቺ ባህሪያት አራግፎ ለአእምሮ ማቅረብ ለማስታወስ አይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡
ለምሳሌ ስልክ ቁጥሮችን በጥሬው ለመያዝ ከመሞከር፣ ከሁነቶች ጋር አዛምዶ ማጥናት ከተወለድንበት ቀን ጋር፣ ከአውቶቡስ ቁጥር ጋር ከፔሬዲክ ቴብል ንጥረ ነገሮች  ቁጥር ጋር … የስልክ ቁጥሩን ማዳበል፡፡
ማስታወስ መቻል ለመርሳት ከመቻል በላይ ቀላል ነገር ይመስላል፡፡ ከባድ ጉዳት ያላቸውን መጥፎ ገጠመኞች መርሳት እንጂ የሚያስፈልገንን መዘንጋት አይደለም፡፡ ውጥንቅጡ የአእምሮ ጉዳይ ውስጥ ገብተን ጨዋታችንን ውጥንቅጥ ውስጥ ከማስገባታችን በፊት ወደ ታላላቆቹ ዝንጋዜ ነገር እናምራ፡፡ አንድ እንጥቀስ፡፡ አሜሪካዊው ተመራማሪ ቶማስ አልኤዲሰን፤
ኤዲሰን እረጅም ጊዜውን የሚያሳልፈው የምርምር ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ግድ ካልሆነት አይወጣም፡፡ ማርጋሬት ካውሲን የፃፈችው የህይወት ታሪክ መፅሐፍ (The man who heighted )ውስጥ አንድ ጊዜ የረሳውን ነገር ትተርካለች፡-
ለሚሰራቸው ስራዎች የመንግስት ግብር ለመክፈል ወደ ከተማው ማዘጋጃ ቤት ሄዶ ነው አሉ፡፡ የግብር መክፈያ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ቀን ብቻ ቀርቶታልና ወረፋው ረጅም ነበር፡፡ ኤዲሰን ተሰለፈ፡፡ ቢሰለፍም የሚያውጠነጥነው ስለ ሳይንስ ምርምሩ ነውና ከቀልቡ አልነበረም፡፡ ወረፋው ደርሶት ግብር ተቀባዩ መስኮት ጋ ሲደርስ አንድ ጥያቄ ቀረበለት፡-
‹‹ሥም የሚል?››
‹‹የፈጣሪ ያለህ ዘንግቼዋለሁ፡፡ ኧረ ስሜን እረስቼዋለሁ›› አለ፡፡ አሰብ፡፡ አውጠነጠነ፡፡ ስሙ ጠፋው፡፡
‹‹ሥምም ከጠፋዎ ምንም ማድረግ አልችልም፤ ዘወር ይበሉ›› ብሎ ቀጣዩን ግብር ከፋይ ተካ፡፡
ኤዲሰን ግብር ሳይከፍል ዛሬን ካሳለፈ ለነገ ቅጣቱ ብዙ ብር ነውና ጨነቀው፡፡ ከግቢው በመውጣት ሰዎች እያስቆመ፤ ‹‹ታውቁኛላችሁ? ሥሜ ማው?›› እያለ መጠየቅ ጀመረ፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ አንድ የሚያውቀው ሰው አግኝቶ ስሙን ነገረው፡፡ እ-ፎ-ይ!!
ለመሆኑ እናንተ ሥሙ የጠፋው ሰው መንገድ ላይ ቢያጋጥማችሁ ምን ይሰማችኋል? ቂል፣ የአእምሮ ህመምተኛ? አጭበርባሪ?... ወይስ ምን? መጠርጠር ደግ ነው፤ እርሱ የአምፖልን መብራት ጨምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ሳይንሳዊ በረከት ጀባ ያለን ቶማስ አልቫ ኤዲሰን ሊሆን ይችላልና፡፡

Read 4654 times