Monday, 08 August 2016 05:55

‹‹አይ ሱፐር ማን - የኔ ጀግና!!››

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(8 votes)

 መምህሩ ለሰባተኛ ክፍሉ ለናቲና ለክፍል ጓደኞቹ ‹ስለሚያደንቁት ጀግና› ባለ ሁለት ገጽ ድርሰት እንዲጽፉ አዟቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ የናቲ ጓደኞች ‹ስለማን እንጽፋለን› እያሉ ሲነጋገሩ ናቲ ግን ነገሩ ለርሱ ቀላል መሆኑን እየገለጠ ነበር ከጓደኞቹ የተለያየው፡፡
ቤቱ ሲገባ እናቱ አስቀድማ ገብታ አገኛት፡፡ መምህሩ ያዘዛቸውን ነገራትና ‹ማንን ልጻፈው› አላት፡፡ ወይ ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ፣ ወይም ስለ ዐፄ ዮሐንስ ወይም ደግሞ ስለ አበበ ቢቂላ አለያም ደግሞ ስለ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጻፍ› አለቺው፡፡ አንገቱን እየነቀነቀ ወደ ምድር ቤቱ በሩጫ ወረደና መክሰሱን ጠየቀ፡፡ መክሰሱን ሲበላ ስለ ማን መጻፍ እንዳለበት እየወሰነ ነበር፡፡ ለርሱ ከዚህ ሰው የተሻለ የሚያደንቀው ሰው የለም፡፡ ስለ እርሱ ማወቅ፣ ማየትና መናገር ይወዳል፡፡ ጓደኞቹም በዚህ ምክንያት በሰውዬው ስም ናቲን መጥራት ጀመሩ፡፡
መክሰሱን ጨርሶ ወደ ማጥኛው ክፍል ገባና መጻፍ ጀመረ፡፡
‹ለእኔ የማደንቀው ሰው ሱፐር ማንን ነው፡፡ አቤት ሱፐር ማን፤ ማንም አይችለውም‘ኮ፡፡ ሁሉን ሰው ፒው፣ ፒው፣ ፒው እያደረገ ይረፈርፋቸዋል፡፡ አቤት ተራራውን ሲዘለው፤ አቤት ፎቁን ሲሻገረው፤ አቤት ሰማዩን ሲደረምሰው፡፡ ደግሞ‘ኮ ሱፐር ማን ምን ያክላል? ዳዲ ራሱ አይችለውም፡፡ እዚህ ግዮን ሆቴል አጠገብ ካለው ፎቅ ራሱ ይበልጣል፡፡ ባለፈው ግዮን ከዳዲ ጋር ስንሄድ አወዳድሬያቸዋለሁ፡፡ ሱፐር ማን እጥፍጥፍ አርጎ ፎቁን ይበልጠዋል፡፡ ከእጁ ደግሞ ‹ፓወር› ያወጣል፡፡ ብረት ነው ደግሞ የለበሰው፡፡ እኛ ሠፈር ያለውን ብረት ሠሪ ሄጄ ‹የሱፐር ማን ልብስ ሥራልኝ ብለው›፤ ‹አልጋ ነው እንጂ ልብስ አልሠራም አለኝ፡፡ እኔ አሜሪካ መሄድ የምፈልገው ይህንን የሱፐር ማን ልብስ ለማስገዛት ነው፡፡
ከፈለገ ደግሞ ወደ ሰማይ ይሄድና ሰማዩን ሰብሮት ይገባል፡፡ ደግሞ ሲፈልግ ት-ል-ቅ ድንጋይ ያነሣና ይወረውራል፡፡ ባለፈው እናቴ ገጠር የወሰደችኝ ጊዜ አንድ የድሮ ቤተ ክርስቲያን ስታሳየኝ ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ት-ል-ቅ-ዬ ድንጋይ ተተክሎ አይቻለሁ፡፡ እናቴ ግን ‹ግራኝ ወርውሮት ነው› አለችኝ፡፡ እማዬ ተሸውዳ ነው እንጂ ያንን ድንጋይ የወረወረው ሱፐር ማን ነው፡፡ ፊልሙን ስላላየቺው ነው፡፡ እርሱ‘ኮ ከዚህ የሚበልጥ ‹ሮክ› ይወረውራል፡፡ አሁን ሲገባኝ እኛም አገር በድሮ ጊዜ ‹ሱፐር ማን ነበረ› ማለት ነው፡፡ አሁን ይህንን ለአጎቴ ብነግረው ‹ፈረንጆች‘ኮ ከኛ ሀገር ያልወሰዱት ነገር የለም፡፡ ሱፐር ማንንም ከኢትዮጵያ ነው የወሰዱት ማለት ነው› ይለኛል፡፡ እርሱ ሁሉን ነገር ከኢትዮጵያ ነው የሄደው ነው የሚለው፡፡
እናቴን ስለማን ልጻፍ ስላት፤ ‹ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ ጻፍ› አለቺኝ፡፡ አይ እማዬ! ሱፐር ማንን ስለማታውቀውኮ ነው፡፡ አሁን ዐፄ ቴዎድሮስ ከሱፐር ማን ይበልጣል? ራሷ እናቴ ምንድን ነው ያለቺኝ፡፡ ‹ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ የሚባል ተራራ ላይ ወጥቶ እንግሊዞች ከበቡት› ብላኝ ነበር፡፡ ሱፐር ማን ቢሆን ኖሮ ምን እንደሚያደርግ ታውቃላችሁ? ልክ እንግሊዞች ሲመጡበት ትልቅ ሮክ(ዐለት) ያነሣና ፒ-ው አርጎ ይወረውርባቸዋል፡፡ እንግሊዞቹ ፈርተው ሺው - ሺው እያሉ በፎቁ ላይ ወጥተው ይደበቃሉ፡፡ እንደገና ሲወረውርባቸው ፎቁ ይደረመሳል፡፡ በፓወራቸው ድንጋዩን ሲሰባብሩበት ሱፐር ማን ደግሞ ከእጁ ላይ ባለው ፓወር ወደ ሰማዩ ገመድ ይዘረጋና በዚያ ተንጠልጥሎ ወደ ፎቁ ይሄዳል፡፡ እንግሊዞቹ ደግሞ ዐለቱን ልክ እንደ ሄሊኮፕተር አስነሥተው ሲበሩ፣ሱፐር ማን ይከተላቸውና በፓወሩ ይከሰክሳቸዋል፡፡
እማዬ ግን ይህንን ስለማታውቅ ነው እንጂ መቅደላ ላይ የነበረው ሱፐር ማን ቢሆን ኖሮ እንግሊዞች መጽሐፍ አይሰርቁንም ነበር፡፡ እማዬ ሁልጊዜ ትናደዳለች፡፡ ‹ብዙ መጽሐፍ ሰርቀው ወሰዱ› ትላለች፡፡ ሱፐር ማን ቢሆን ኖሮ አይወስዱትም ነበር፡፡ በፓወሩ ፊ--ው ሲያደርገው መጽሐፉ ማግኔት እንደነካው ብረት እየተሳበ ወደ መቅደላ ይሰበሰብ ነበር፡፡ ካልሆነም ደግሞ እንግሊዝ ሄዶ በሁለት እጁ ታቅፎ ያመጣው ነበር፡፡ ሱፐር ማንʻኮ እንኳን መጽሐፍ መሬትን ራሷን ያቅፋታል፡፡  
እኛ ትምህርት ቤት የተሳለው የዐፄ ቴዎድሮስ ሥዕል፣ አንድ ተራራ ላይ ቆመው በሽጉጥ ራሳቸው ሲገድሉ ያሳያል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሱፐር ማን ስላልሆኑ ነው እንጂ እንደዚያ አያደርጉም ነበር፡፡ ሱፐርማንʻኮ ሽጉጥ አይዝም፡፡ እጁ ላይ ፓወር አለው፡፡ መክፈቻውን ኪ-ው ሲያደርገው የብረት ልብስ ያለብሰዋል፡፡ ከዚያ እጁን ሲሰነዝረው እሳት ይተፋል፡፡ ሱፐር ማን ቢሆን ኖሮ መቅደላ ከሚባለው ተራራ ፒ-ው ብሎ ዘሎ ይወርድ ነበር እንጂ ለምን ራሱን ይገድላል፡፡
እማዬኮ ዐፄ ምኒሊክ ከሱፐር ማን የሚበልጥ ነው የሚመስላት፡፡ ሁልጊዜ ትነግረኛለች፡፡ ‹ጣልያን ሀገራችንን ሊወር ሲመጣ፣ ሕዝቡን ሁሉ አነሳሥተው፣ እየሸለሉና እየፎከሩ፣ አድዋ ዘምተው ጣልያንን ድል አድርገዋል› ትለኛለች፡፡ ሱፐር ማንኮ ያንን ሁሉ ጦር ይዞ አይዘምትም ነበር፡፡ ሱፐር ማን አይሸልልም፣ አይፎክርም፡፡ ደግሞ እማዬ ቆሎ ተቆልቶ፣ ስንቅ ተዘጋጅቶ ነው የሄዱት ትላለች፡፡ እና እነዚህን ነው ከሱፐር ማን ይበልጣሉ የምትለኝ? ሱፐር ማን ቆሎ አይፈልግም፡፡ እንዲያውም ሲበላ አይቼው አላውቅም፡፡ ስንቅ ምናምን አይዝም፡፡ ፒ--ው ብሎ ይበርና አድዋ ይደርሳል፡፡ ጣልያን እዚያ ሲጠብቀው አድዋ ተራራ ላይ ቂ-ብ ይላል፡፡ ፓወሩን ኪ-ው ሲያደርገው ብረት ይለብሳል፡፡ እንደገና ኪ--ው ሲያደርገው እሳት ይተፋለታል፡፡ ከዚያ ጣልያንን ፒ-ው፣ ፒው እያደረገ መግደል፡፡
ጣልያን ሱፐርማንን አይቶ ሲሮጥ የአድዋን ተራራ ይቆርጠውና ይወረውርባቸዋል፡፡ አሁን እማዬ ስለ ምኒሊክ ስትነግረኝ የተዋጉት ተራራው ሥር ነው ብላኛለች፡፡ እና ምኒሊክ እንዴት ነው ሱፐር ማንን የሚበልጠው? ምኒሊክ ጎበዝ ከሆነ ጎራዴ፣ መድፍ፣ ጦር፣ ጋሻ ምን ያደርግለታል፡፡ ደግሞ ፊልሙን ሳየው ብዙ ሰው ሞቷል፡፡ ተራራውን ቆርጠው ጣልያን ላይ መጣል ነው፡፡ ጦር፣ ጎራዴ ምን ያደርጋል?
እኔ ሱፐር ማን እንጂ ቴዎድሮስና ምኒሊክ መሆን አልፈልግም፡፡ እሷ እንዲያውም አበበ ቢቂላና ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጀግኖች ናቸው ትላለች፡፡ እነርሱ ሮጠው፣ ሮጠው፣ ሮጠው በመከራ ነው ወርቅ ያገኙት፡፡ ሱፐር ማንኮ ቢሆን ‹ሩጡ› ሲባል ፓወሩን ኪ-ው ያደርግና ብረቱን ለብሶ ፒ-ው ብሎ ማሸነፍ፤ በቃ፡፡ መሮጥ፣ መድከም አያውቅም፡፡ ያንን ሁሉ ዙር ስታዲየሙን ሲዞሩ፣ ሲዞሩ፣ ሲዞሩ ከሚውሉ ፒ-ው ብለው አይሻገሩትም? ሱፐር ማን‘ኮ ቢሆን በአንድ ጊዜ ስታድየሙን ይሻገረውና ሽ-ው ብሎ መጨረስ፤ በቃ፡፡
ለኔ ጀግና ማለት ሱፐር ማን ነው፡፡ ቴዎድሮስ፣ ምኒሊክ፣ ዮሐንስ፣ ዐሉላ፣ አበበ ቢቂላ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ እያለች እናቴ የነገረችኝ ሱፐር ማንን ስለማታውቅ ነው፡፡ እርሷ የምታውቀው ፊልም ፍቀጅልን ስንላት ‹ተው እናንተ ልጆች፣ ይሄ ወይ ተረት ወይ ታሪክ ያልሆነ ነገር እያያችሁ› ትለናለች፡፡ ሱፐር ማን ያለ አይመስላትም፡፡ አምና ከአሜሪካ የመጣው የአክስታችን ልጅ አሌክስ ሱፐርማንን ሊያክል ምንም አልቀረውምኮ፡፡ በርገሩን ምናምኑን ጭው እያደረገ ነው አለች አክስቴ፡፡ እኔ መቼም ይህንን እንጀራ እየበላሁ ሱፐር ማንን የማክል አይመስለኝም፡፡ አሜሪካ ብሄድ ግን በርገር ምናምን ልፌ ሱፐር ማንን አክል ነበር፡፡
አይ ሱፐር ማን - የኔ ጀግና!!፡፡

Read 6380 times