Monday, 08 August 2016 05:55

“ህሊና የለህም…!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ግርም አይላችሁም፣ እንዴት ነው እንዲህ ‘ሰለጠነ’ በተባለበት ዘመን የሰዋችን ባህሪይ ወደ ‘ድንጋይ ዘመን’ ምናምን ወደሚባለው እያሽቆለቆለ የሚሄደው! ልክ ነዋ…ዝም ብሎ “ገጽታ ግንባታ ምናምን… እያሉ ዲስኩር ማሳመሪያ ከማድረግ እውነቱን ማየት ነዋ! ገጽታ ማለት ባህርይ ማለት ነው! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ገጽታችን ራይትና ኤክስ የሚሰጠው ሳጥን የመሳሰሉ ህንጻዎች ስለበዙ ሳይሆን ባህሪያችን…. የምር እኮ…ህንጻው ወደ ላይ እየወጣ፣ ባህርይ ወደ ታች እየወረደባት ያለች ከተማ ነች እኮ! የስልጣኔ አንዱ ምልክት እኮ መከባበር ነው፡፡ መከባበር እልም ብሎ እየጠፋባት ያለባት አገር ሆናለች ፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ የህዝብ መገልገያዎች ምናምን ለጥቂት ደቂቃ ቆም ብላችሁ እዩማ…እንዴት ነው ሰዉ እንዲህ እርስ በእርሱ የተናናቀው! መሀል ከተማ አካባቢ ነው፡፡ እናላችሁ…ሰዉ ያው የፈረደበት ታከሲ ጥበቃ ላይ ነው፡፡ በሆነ ምክንያት ሰልፉ ተተራማምሶ ሰዉ እየተገፋፋ ነው የሚሳፈረው፡ እናላችሁ…እኚህ አዛውንት ሴትዮ እየገቡ ሳለ የሆነ ወደል ቢጤ (ባለ ‘ታቱ’) ገፍትሯቸው ይገባል፡፡ ሴትየዋ ተንገዳግደው ነው የቆሙት፡፡ እና አንዷ ደፍተሀቸው ነበር እኮ… ብላ ቆጣ ትላለች፡፡ ዘወር ብሎ ዝም በይ፣ አፍሽን…አት…!” ምናምን አላት፡፡
ህሊና የሚሉት ነገር የት ጠፋ!
እናላችሁ…ሁሉም ሰው ‘ቡራ ከረዩ’ ባይ ሲሆን፡ ሁሉም ‘ከእኔ በላይ ላሳር ባይ ሲሆን፣ ሁሉም “እኔ ናፖሊዮን ነኝ፣ ሌሎቻችሁ አገልጋዮቼ ናችሁ…” ምናምን አይነት ነገር ባይ ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡ እናማ…ባህሪይ እየተበላሸ ሲሄድና… “ዋ አንተን አያድርገኝ!” በሚል ‘ጌታውን ተማምኖ ላቱን ውጪ የሚያሳድር’ ሲበዛ የሆነ ነገር ተበላሽቷል ማለት ነው፡፡
በዛ ሰሞን አንድ ወዳጄ ይዝናናበት የነበረበት ቡና ቤት ውስጥ አንዱ የሆነ ቢራ አዞ ይከፈትለታል፡፡ ግማሽ ድረስ ከጨለጠ በኋላ “ጣዕሙ ሌላ ነው፣ ፎርጅድ ነው የሰጣችሁኝ…” ምናምን ብሎ ቤቱን ቀውጢ አድርጎት ነበር አለኝ፡፡  “ፎርጅድ ቢራ ነው የሰጣችሁኝ…” ብሎ ጠብ የሚያነሳ ሰው ስታዩ፤ “እውነት ምን እየሆንን ነው!” አያሰኛችሁም?  ኮሚኩ ነገር ሰውየው…አንደኛ ነገር እየተሳደበ ባለበት ሰዓት ሁሉ እኮ መጠጣቱን አልተወም!  ሰውየው… በሆነ ባልሆነው የረጋ ማደፍረስ የምንወድ፣ ‘ፈረንጅ’ እንደሚለው በቡና ስኒ ውስጥ ቅልጥ ያ ማዕበል ለማስነሳት የምንሞክር አይነት ሰው ነዋ! እንዲህ አይነቱ ሰው…ሆቴል ገብቶ… አለ አይደል… ወጥ ውስጥ ያለው ድንች ፎርጅድ ነው ብሎ ምናምነኛውን የዓለም ጦርነትን ለመጀመር ከመሞከር ወደ ኋላ አይልም፡፡
ህሊና የሚሉት ነገር የት ጠፋ!
ስሙኝማ…የድንች ነገር ካነሳን አይቀር የሆነ ምግብ ቤት ወይም ሌላ ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ስንመገብ ዓመልን በጉያ አይነት ነገር አያስፈልግም! አንዳንዶቻችን እኮ አበላላችን በአምስት ኪሎሜትር ክልል፣ አጠገባችን አንድም ሰው የሌለ ነው የምናስመስለው፡፡ ልክ ነዋ…አንዳንዶቻችን ስንጎርስ እኮ ምግብ አፋችን የምንከት ሳይሆን አሸዋ የሆነ ሲኖትራክ ላይ የምንጭን ነው የሚመስለው! ስሙኝማ…የእኔ ቢጤው ደግሞ ጉርሻ ‘በኪኒን መልክ’ የታዘዘለት ይመስል በሁለት ጣቱ ነገር እያነሳ ሲጎርስ…አለ አይደል…“ጉርሻም ሳምፕል አለው እንዴ!” ያሰኛል፡፡  ቂ…ቂ…ቂ…፡፡
ስለ ምግብ ካወራን…ሰውየው ቬጄቴርያን ነኝ ምናምን እያለ ይፎክር ነበር፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ቅልጥሙን እንዳጋደመ ሰው ይደርስበታል፡፡
“አትክልት ብቻ ነው የምበላው ብለህ አልነበር እነዴ!” ሲል ያፋጥጠዋል፡፡
“አዎ፣ቬጄቴርያን ነኝ፡ አትክልት ብቻ ነው የምበላው፣” ሲለ ይመልሳል፡፡
“ታዲያ ፊትህ ያለው ጥብስ ምን ይሠራል?” ብሎ ሲጠይቀው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“አትክልት ብቻ ለመመገብ የወሰንኩት ጥንካሬዬ፣ምን ያህል እንደሆነ ራሴን ለመፈተን ነው…” ብሎት አረፈ፡፡
እናላችሁ… “ይሄ ነገር እየባሰበት ሲሄድ ምን ያመጣ ይሆን!” የሚያሰኝ የባህሪይ ምስቅልቅል ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ለሁሉም ይጠቅማሉ ተብለው የወጡ ህጎች ከምንም የማይቆጠሩበት ዘመን ላይ ደርስናል፡፡  ከወራት በፊት አንድ ‘ሬስቱራንት’ ውስጥ አንዱ ሲጋራ ይለኩሳል፡፡ ሠራተኞቹ “እዚህ ሲጋራ ማጨስ ክልክል ነው፣” ይሉታል፡፡ እሱም ምን ቢል ጥሩ ነው… “ወንድ የሆነ ሲያስቆመኝ አያለሁ…”  ምናምን ሲል ይፎክራል፡፡  ግንዲላ የሚያካክል ሰው በሞላው ሬስቱራንት፣ የሚያስቆም ወንድ ጠፋና እሱዬው እግሩን አጣምሮ ማንቦለቦሉን ቀጠለ፡፡
ህሊና የሚሉት ነገር የት ጠፋ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… መኪናን በተከለከለበት ስፍራ ማቆም የትራፊክ ህግ መጣስ ብቻ ሳይሆን የባህሪይ ችግርም ነው፡፡ ልክ ነዋ… የትራፊከ ህግን የጣሰ ሰው ሌሎቹንም ለህብረተሰብ ጥቅም ተብለው የወጡ ህጎችን የማይጥስበት ምክንያት የለማ! ትንሽ ትልቁ መሀል ጣትን በመስኮት ሲቀስር በሚውልባት ከተማ ለምሳሌነት የሚበቃ እየጠፋ ነው፡፡ (እግረ መንገዴን..እንትናዬዎች ኸረ እናንተ እንኳን ይቺን መሀል ጣት እዛው መሪው ላይ አስቀሯት፡ የእናንተ የጣቷን ግማሽ የሚሆን ጥፍር ስላለበት ያስፈራላ! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ ደግሞ አንድ ያስቸገረን ነገር ታክሲ ውስጥ ጮክ ብለው በሞባይል የሚያወሩ ሰዎች ድምጽ፡፡ የምር እኮ…ሞንታርቦ ነው ምናምን የሚሉትን ድምጽ ማጉያ የዋጡ ነው የሚመስለው! ደግሞ ወሬያቸው መላቅጥ የሌለው ነው፡፡ (‘ቁጩ’ የሚባለው ‘የአራዶቹ ቋንቋ’ በቃ ጠፋ እንዴ!
“አንድ ሺህ ብሩን ለሰውየው ልኬልሀለሁ… ካልበቃሀ አንድ፣ ሁለት ሺህ እጨምርልሀለሁ…አንድ መኪና ስንዴ አስመጥቼ እሱን ለማውረድ እህል በረንዳ እየሄድኩ ነው… (ቂ…ቂ…ቂ… አንድ መኪና ስንዴ የሚያስወርድ ሰው ከእኛ ጋር ሁለት ብር ተሀምሳ ታክሲ ውስጥ ምን ይሠራል!) …እሷማ አማሪካን ገባች እኮ…ወር ሆናት…ጋበዛኛለች፣ ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንት በኋላ እሄዳለሁ…(ኸረ እኛም ታክሲ ውስጥ አለን! አማሪካን በገባች በወር ውስጥ የግብዣ ወረቀት የምትልክ…የሚሼል ኦባማ የእህት ልጅ ነች እንዴ!)… እባክህ እዚህ ሲኤምሲ ቤት እገዛለሁ ብዬ አስወደዱብኝ…ዘጠኝ ሚለዮን ነው የሚሉት..እኔማ አንድ አምስት መቶ ሺዋን ቀንሱልኝ እያልኩ ነው… (“ረዳት ወራጅ!” ምን በወጣን ነው በሁለት ብር ተሀምሳ የሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር ‘ቡፋ’ የምንጫነው!)
ህሊና የሚሉት ነገር የት ጠፋ!
እናላችሁ…ነገሮችን እንድናመዛዝን፣ ህብረተሰቡን የሚስቀይም ነገር እንዳናደርግ እንደ መከላከያ የሚያገለግለን ህሊና የሚሉት ነገር በየትኛው አውሮፕላን ተሳፈሮ ከአገር እንደወጣ ሳይገባን ይኸው ስንት ዘመን ከረምን፡፡
ሰውየው አይደለም “እንዴት ነህ… እንዴት ነሽ” የተባባለችውን፣ በአጠገቡ ያለፈች እንትናዬ አታልፈውም (ወይም ‘አታመልጠውም’) ይባላል፡፡ እናላችሁ አንድ ቀን የስነ አእምሮ ሀኪም ዘንድ ይሄድና ምክር ይጠይቃል፡፡ ሀኪሙ “ችግርህ ምንድነው?” ይለዋል፡፡
“ዶክተር ጥሩ ባህሪይ እያሳየሁ አይደለም፡፡ በቃ ያለፈች ያገደመችውን ሁሉ ማሳደድ ነው፡፡ ይሄ ነገር ህሊናዬን በጣም እየረበሸኝ ነው…” ይለዋል፡፡ ሀኪሙም፡
“ገባኝ፣ ህሊናህን እየረበሸህ መሆኑ ለጊዜውም ቢሆን ክፋት የለውም፡፡ እና አሁን ይህን ጠባይህን ሙሉ ለሙሉ እንድትተው አእምሮህን የሚያጠናክርልህ ህክምና እንዳደርግልህ ነው የምትፈልገው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
“ዶክተር፤እንደ እሱ እንድታደርግልኝ አይደለም የምፈልገው፡፡” ዶክተሩም ግራ ይገባዋል፡፡
“ታዲያ ምን እንዳደርግልህ ነው የምትፈልገው?” ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“ዶክተር፣ በሆነ ዘዴ ይሄ ህሊና ህሊና የሚሉትን ነገር አስወግድልኝ…”  ብሎት አረፈ፡
የምር ግን ሰውየው ወደ ሀኪሙ ከሚሄድ እኛ ዘንድ ቢመጣ እንፈውሰው ነበር፡፡ ልክ ነዋ…እኛ ዘንድ እኮ ያለ አእምሮ ሀኪም፣ ያለ ጠበል ምናምን እርዳታ ህሊና ራሱ ‘ለደህንነቱ’ ሰግቶ ደብዛው ከጠፋ ስንት ዘመኑ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እና ህሊና የሚሉትን ነገር አንድዬ ከተሰወረበት ቦታ ይመለስልን፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በሆነ ነገር ሳንግባባ ስንቀር… “ህሊና የለህም እንዴ!” መባባልም ጸጋ ነው፡፡ ደብዛው በጠፋ ነገር “…የለህም እንዴ!” መባባሉ ግራ ገብቶን እየተቸገርን ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2401 times