Saturday, 30 July 2016 12:48

የገነት መግቢያ ፈተና

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(20 votes)

እነሆ የባቢሌ የመሞቻ ቀን ደረሰ፡፡ ደረሰና ተገነዘ፡፡ ወደ ጉድጓድ ተወረወረ፡፡ ከጉድጓድ በስቲያ ምስጥና ጉንዳን በልቶ የተረፈው ነፍሱ ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ ተሰደደ፡፡ የሚቀጥለው ምዕራፍ የሚወሰነው እንደ ሟቹ እምነት ነው፡፡
ባቢሌ ከሞት በኋላ መንግስተ ሰማይ ወይንም መንግስተ ሰይጣን ይኖራል ብሎ የሚያምን በመሆኑ ወደ አመነበት ደረሰ፡፡ ወይንም የደረሰ መሰለው፡፡ መምሰልና መሆን እንደ ህልምና እውነታ የተነጣጠሉ የመሆናቸው ጉዳይ እዛው ከጉድጓድ ቀደም ብሎ የከረመበት አለም ላይ አክትሟል፡፡
ሟቹ ምድር ላይ ህይወቱን በሚገፋበት ጊዜ ራሱን አንባቢ ወይንም ፀሐፊ ነኝ ብሎ ያስብ ነበረ አሉ፤ እናም መጀመሪያ የቀረበለት ጥያቄ፣ “ሽማግሌው እና ባህሩ” የማን ድርሰት ነው የሚል ነበር፡፡ ጥያቄውም የቀረበለት እንዲመልስም የተጠበቀው በፅሁፍ ነው። የተጠየቀው ጥያቄ በሁለት ቃላት የሚመለስ መሆኑን እርግጠኛ ቢሆንም ለመልስ የተተወለት ባዶ ቦታ ግን የኑዛዜ ያህል የረዘመ በመሆኑ ጥርጣሬ ገባው፡፡ ጭራሽ የክፍት ቦታው መስመሮች በሂሳብ ምልክቶችና ሰንሰለታማ እንቆቅልሻዊ ሳጥኖች የተሞላ ነው፡፡
የመጀመሪያውን ጥያቄ ለበኋላ ይሁነኝ ብሎ ዘለለው፡፡ እስኪመረቅን እንደሚጠብቅ ሰው ወይንም ያዘዘው ቡና የተለየ ንቃት እንዲፈጥርለት የተማመነ ይመስል ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ሄደ፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ ቀላል ነው፤የእንግሊዝኛ ሆሄያትን እንዲዘረዝር የሚጠይቅ ነው፡፡ እስኪርቢቶውን አንስቶ ለመፃፍ ሲጀምር ቀለሙ ከአማርኛ ሆሄያት በስተቀር አልተፋ አለው፡፡ ከሀ-እስከ ፐ በመፃፍ እንግሊዝኛ የማስመሰል እልሁ የትም እንደማያደርስ ሲያውቅ ሁለተኛውንም ጥያቄ ለይደር አቆየው፡፡
ሶስተኛው ጥያቄ ግን ሁለተኛው ላይ የተቋረጠ በመሆኑ አንዱን ሳይፈታ ሌላኛውን ማሰር እንደማይችል በቀይ ቀለም የአደጋ ምልክት ሰፍሮበት የተጋደመ መግለጫ ነገረው፡፡ ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማይን ትልቅ የሰረገላ ቁልፍ መቀነቱ ላይ አስሮ እንደ አስተማሪ በእሱ አናት ዙሪያ ይሽከረከራል፡፡ አልሮ አልፎ እሱ ከፈተናው ወረቀት ጋር የሚያደርገውን ትግል እየተመለከተ እንደ መሳቅ ይላል፡፡
“In examination the fools ask questions the wise could not answer” የሚለው አባባል ለባቢሌ ድንገት ትዝ አለው፡፡ ገና ትዝ ከማለቱ አራተኛው ጥያቄ በእሱ ትዝታ ላይ ተመርኩዞ በወረቀቱ ላይ ተፈጠረ፡፡ አራተኛው ጥያቄ፡- “አሁን ትዝ ያለህን አባባል የተናገረው ማነው?” የሚል ነው። ማን እንደተናገረው ሳይሞት በፊት ያውቅ እንደነበር ባቢሌ እርግጠኛ ነው፡፡ ግን ሳይሞት በፊትና በኋላ እውቀቶቹ ቀኝ ኋላ ተዟዙረውበታል፡፡ ደግነቱ ለጥያቄው ቀላል መፍትሄ የሚያመለክቱ የምርጫ ዝርዝሮች ቀርበውለታል፡፡
ዝርዝሮቹ ግን የጥቅሱ ደራሲ ስም ከመምሰል ይልቅ … ከባድ የመጠጥ ጉስቁልና ካሳለፈባቸው ምሽቶች በኋላ ጠዋት ቁርስ ላይ የሚቀርብለት የምግብ ዝርዝሮች ስም የመምሰል አዝማሚያ አላቸው፡፡ በፊት የቁርስ አይነቶቹን ዝርዝር በአይኑ ቁልቁል እየተንደረደረ ሲማትር የሚቀሰቀስበት የማቅለሽለሽ ስሜት አሁንም እየተሰማው መሆኑ፣ የጥቅሱ ደራሲ ስም ዝርዝርና የሚያውክ የቁርስ ዝርዝር ያላቸውን ተመሳሳይነት ከማመልከት ውጭ ለአራተኛው ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ አላገዘውም፡፡
 ማንኛውም ተፈታኝ የመጀመሪያዎቹ አራት ጥያቄዎች ግራ ሲያጋቡት እንደሚያደርገው፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ገፆችን ገልጦ የተሻለ ወይንም ቀለል ያለ ጥያቄ ማግኘት ይችል እንደሆን መመርመር ጀመረ፡፡
ገፆቹ መጀመሪያ ከሁለት የሚበልጡ እንዳልሆኑ ከፈታኙ እጅ ሲቀበል አውቆት ነበር፡፡ እውቀቱ ደግሞ ከአያሌ አመታት የስራ ልምድ የመነጨ በመሆኑ ስህተት አልነበረውም፡፡ የወረቀትን ብዛትና የብርን ብዛት በመዳሰስ ማወቅ ይችል ነበር፡፡ በምድር ላይ ድንጋዩን እንደ ሲሲፈስ በእድሜው ኮረብታ ላይ እያንከባለለ ይውል በነበረበት ወቅት፡፡
ያ የቀድሞ እውቀቱ ግን አላገላገለውም፣ ገፆቹን በገለጣቸው ቁጥር እንደ ኑሮ እየተመነዘሩ መብዛት ያዙ፡፡ ከብርና ወረቀት ባህሪይ ይልቅ የመከራን ባህርይ የተላበሱ ወረቀቶች ሆነው አታከቱት፡፡ ፈተናው ምንም አይነት የመገላገያ አማራጭ ዘዴ የለውም፡፡ ወደ ኋላ መመለሻ በር የለም፡፡ “ይቅርብኝ” ብሎ መተው አይታሰብም፡፡ እንደማይታሰብ ያወቀው ማሰብ ስላልቻለ ነው፡፡
“ዘነዘና የሚያክለውን እስክሪብቶ የመርፌ ቀዳዳ ባከለው የጥያቄ አይኖች ውስጥ መስደድ መቻል” ብሎ የገጠመውን መከራ ለመግለፅ ፈለገ። ስለሚቀለው ግን መግለፅ ይፈቀድለታል ማለት አይደለም፡፡ የተፈቀደለት ጥያቄውን መመለስ ነው፡፡
አምስተኛው ጥያቄ ደግሞ ግራ የሚገባ ነው፡፡ “በግራ እጅህ ቀኙን ቁጠር” የሚል ነው፡፡ በጣም ግልፅ ነገር ነው፡፡ ቸኩሎ “አምስት/አምስት” ብሎ ከሞላው በኋላ ጥያቄና መልሱ ህጋዊ ጋብቻ መፈፀማቸውን ሊያረጋግጥ ሲል አንዲት ህፀፅ አገኘ፡፡ ላብ በላብ ሆነ። ላብና እንባ መውጫ ቀዳዳቸው በዚህኛው ዓለም እንጂ በወዲያኛው እንደማይቀላቀል እርግጠኛ ነው ወይንም ነበር፡፡ “በግራ እጅህ ቀኙን ቁጠር” በሚለው ጥያቄ የመጨረሻዋ ቃል ላይ ያለችው የመጀመሪያዋ ፊደል “ከታይፕ ኤረር” ምክኒያት ወገብ ላይ መሆን የነበረባት ጭረት አናት ላይ ውላ “ቁጠር” የሚለው ንባብ፣ “ቅጠር” ወደሚል ትርጉም አልባ አቅጣጫ ሰድዳዋለች፡፡
የፈተናው ወረቀት አናት ላይ የሰፈረው የመጀመሪያው ሀሌታ መመሪያ፤ “የቃላት ግድፈት በመንግስተ ሰማይ ታይፒስቶች ዘንድ ስለሚፈጠር በአግባቡ አንብበህ ለተጠየቅኸው ጥያቄ መልስ ነው ብለህ የምታስበውን አስፍር” የሚል ነው፡፡
በ“ቁጠር” እና “ቅጠር” መሀል ሊኖሩ የሚችሉ የትርጉም ልዩነትና ተመሳሳይነቶችን መዘርዘር ጀመረ፡፡ የፈተናው ጊዜ በሰዓት የተገደበ ስላልሆነ … ምንም አላሰጋውም፡፡ ይኼንን ጥያቄማ መፍታት አለብኝ ብሎ በወኔ መፈላሰፍ ቀጠለ፡፡
በረጅም ማሰቢያ ወረቀት ላይ፡-
በመሰረቱ “ቀጣሪ … ቆጣሪ ነው” ብሎ ጀመረ። ቀጣሪ አትራፊ ስለሚሆን ነው የሚቀጥረው። ከቀጠረ በኋላ … ወር ቆጥሮ … ለቀጠራቸው ይከፍላል። ቋጣሪም ነው፡፡ እንደ መንግስት የቀጠራቸውን ይቆጣጠራል … ቀጣሪ፣ ቋጣሪ፣ ተቆጣጣሪ … ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ወር ቆጥሮ ስለሚከፍል … ቀጠሮ አክባሪም መሆን አለበት፡፡ … ስለዚህ በቃላቱ መሀል ያን ያህል ልዩነት የለም። … በቀጣሪና ተቀጣሪ መሀል አቋጣሪም ታኮ ሊገባ ይችላል፡፡ … በ“ቀ” ላይ የተጨመረችው ቅጣይ … አናት… ወገብ ወይንም ግርጌ ላይ ብትሰፍር ያን ያህል የፖለቲካ ልዩነት አታስነሳም። ችግሩ ያለው ከእኔ እጅ ጋር ስትገናኝ ነው፡፡ “በግራ እጅህ ቀኙን ቅጠር” ከሆነ የተባልኩት … መልሴ የሚሆነው “የት ቦታ” የሚል ነው፡፡ “ቋጥር” ከሆነ … “እጄን ቋጥሬ በምን ፈተናውን እሰራለሁ” ነው መልሱ፡፡ ደግሞ ግራ እጅ ከመቼ ወዲያ ነው ቀኝን ቆጥሮትም ሆነ ተቆጣጥሮት የሚያውቀው፡፡ “ግራ አይንህ ብታሰናክልህ”… ብሎ ሰንካላነትን ለመመሰል የተፈጠረ አቅጣጫ አይደል እንዴ ግራኝነት … ግራኝነት እኮ የወረራ ጊዜን ማስታወሻ ቃል  ነው፡፡ የተጨቆነ አቅጣጫን የሚያመለክት ቃል፡፡ “ከግራ ጎኑ ተወስዳ ደካማ ሚስቱ ተፈጠረችለት” አይደል እንዴ የራሳቸው የፈተና አውጭዎቹ ታሪክ፡፡
ግን የሚቆጥረው ነው ወይንስ የሚቆጠረው---በስልጣን መለኪያ ብልጫ ያለው? … “ከሰው አትቆጠርም” ብሎ በስልጣኑ ወደ ሰውነት እርከን የሚያወጣና የሚያወርደውን መሰላል የሚቆጣጠረው ቆጣሪው አይደል እንዴ? … ስለዚህ ግራ እጅ ቀኙን እንዲቆጥር ከታዘዘ … እውነትም መንግስተ ሰማይ ገብቻለሁ ማለት ነው ሲል አሰበ። ግራ እጅ ቀኙን (ከእጅነት) ሊቆጥረው የሚችለው ይቅርታ ካደረገለት ብቻ ነው፡፡
ይህንን ሲወስን መልስ መስጫው ላይ፤ “ይቅር ብዬሀለሁ” የሚል መልስ ፃፈ፡፡ “በግራ እጅህ ቀኙን ቁጠር” ለሚል ጥያቄ “ይቅር ብዬሀለሁ” የሚል መልስ በምድር እያለ ተጠይቆ የሚመልስ፣ የሃይማኖት ሰባኪ ብቻ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ እንደ ጠዋት ትንባሆ መጀመሪያ ላይ አዙረውት ነበር፡፡ እየቆየ በጥያቄዎቹ አወለጋገድ ልክ የሚሆኑ ወልጋዳ መልሶች በቀላሉ ይመጡለት ጀመር፡፡ ግን ያሰጋው ጥያቄዎቹ በሙሉ የሀይማኖት ጭብጥ ያላቸው አለመሆናቸው ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ራሱ ከሚያውቀው ነገር የሚነሱ ጥያቄዎች ስለመሆናቸው ማስጠንቀቂያው ላይ ተገልጿል፡፡ “እና እኔ ስለ ሀይማኖት ለመናገር የሚበቃ ምንም ዕውቀት የለኝም ማለት ነው?” ብሎ “ሂድ ከዚህ!” እንደተባለ ልጅ ከፋው፡፡
ልክ መከፋቱን ሲያይ ጴጥሮስ ወገቡ ላይ ያሰረውን አንድ ቁልፍ እያንቃጨለ፣ ወደ እሱ መጥቶ ስድስተኛውን ጥያቄ ከተደፋበት ቀና አደረገው። ጠማማው ጥያቄ ቀና መልስ መሰለ … “ስድስት” ከተደፋበት ሲቃና “ዘጠኝ” ሆነ፡፡ ዘጠነኛው ጥያቄ ቀና ሳይሆን፣ “ቀና ሲታጣ …” የተመለመሉትን ጎባጦችም ቀና ማድረግ ሲቸግር … በችኮላ ተጠርቦ የገባ ሸክላ ነገር ነው፡፡
“የማንን ጎፈሬ ታበጥራለህ?” ይላል ጥያቄው፡፡ ተግሳፅ ነው ጥያቄ? … ደግሞስ ከመንግስተ ሰማይ መግቢያ ክህሎቱ ጋር ምን ተያያዥነት አለው? … ሀይማኖታዊ ጥያቄ ለማድረግ ነበር ጴጥሮስ ስድስቷን ወደ ዘጠኝ ያቀናት፡፡ ሀይማኖታዊ ጥያቄ ብሎ በቅንፍ ከጥያቄው አጠገብ ፅፎበታል፡፡
“LOL” ልበለው እንዴ ብሎ ከጀለ፡፡ ጴጥሮስ ያሰበውን ሰምቷል መሰል ፊቱን አኮፋተረበት። ወገቡ ላይ ያለው አንድ የሰረገላ ቁልፍ ነው፡፡ አንድ ቁልፍ ከምን ጋር እየተጋጨ እንደሚያቃጭል ተፈታኙ ምትሀት ሆነበት፡፡ የሰረገላ ቁልፍ ማለት ራሱ ምን አይነቱ ቁልፍ ነው?
“Concentrate” ብሎ ጮኸ ጴጥሮስ … እንግሊዝኛ ስለሚናገር፤ “ፒተር-- am trying bro … is just the questions are awful and confusing…?” ምናምን ብላ ባቢሌ ፌስቡክ ላይ በለመደችው የኮመንት አድፋጭ ቋንቋዋ… በፍኔውኔው አክሰንቷ ተጥመለመለች፡፡ ጴጥሮስ አልመለሰለትም፡፡ ባቢሌ ወደ ሌላ አቅጣጫ እየነጎደ ያለውን የሀሳቡን ሰረገላ በጥሞና ልጓም ገታውና ጥያቄው ላይ አተኮረ፡፡
እሺ…አለ----ሀይማኖታዊ ጥያቄ ነው ተብሏል፡፡ ጎፈሬ የጉልበተኝነት መገለጫ ነው፡፡… ጉልበተኝነት ወይንም ጀግንነት፡፡… ጉልበተኛን አውጋዥ… ጀግናን ጉልበተኛ ብሎ አሉታዊ ፅልመት ያለብሰዋል፤ ጉልበትን አሞጋሹ፤ ጀግና ብሎ ያበራዋል፡፡ የማብራትና የማጥፋት አንፃራዊ አመለካከት እንጂ ሌላው እዳው ገብስ ነው፡፡
… የማንን ጎፈሬ ታበጥራለህ? ማለትና የማንን እግር ታጥባለህ---ማለት ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ… ሀይማኖተኛው የባልንጀሮቹን እግር አጠበ… ጉልበት አምላኪው ደግሞ የወጋሪውን ጎፈሬ አበጠረ…፡፡ ሐይማኖተኛውም እኮ የፈጣሪን ጉልበት አምልኮ ነው የባልንጀሮቹን እግር ያጠበው፡፡ እርግጥ ያመለከው ግን ሰውን አይደለም፤ፈጣሪውን ነው። ወይንም የፈጣሪን ጉልበት፡፡ ፈጣሪው ጉልበቱን በሀይል ሳይሆን በፍቅር ነው የሚያሳየው፡፡… የፍቅር ጉልበት፤ የፍቅር ሀይል ነው ያለው፡፡ አሉታዊና አዎንታዊ ሀይል ላይ ነው ጥሉ እንጂ… ሃይማኖትና ፖለቲካ በመሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ጎፈሬን በማበጠርና እግርን በማጠብ መሀል አይደለም ግጭቱ ያለው፡፡…
መልሱን አገኘው፡፡ በክፍት ቦታ ላይ ሞላው፡፡
‹‹የባልንጀራን እግር ማጠብ የፈጣሪን ጎፈሬ እንደ ማበጠር ነው››
መልሱን አስፍሮ… የጴጥሮስን ፊት ቀና ብሎ አጠና፡፡ አልተደሰተበትም ወይም አላዘነበትም። በሥራ ገበታው ላይ ያተኮረ፣ ቀልድ የማያውቅ ፊት ነው የተላበሰው፡፡ ቁልፉ በመቀነቱ ላይ ሆኖ ይንቃጨላል፡፡ ምናልባት ‹‹የህሊና ደውል›› አዘውትሮ ሲባል መረዳት ያቅተው የነበረው ድምፅ ይህ ይሆናል ብሎ አሰበ፤ ሱሰኛው ተፈታኝ፡፡
በጥያቄዎቹ መርቅኗል፡ ብዙ የሚቀረው መስሎት ነበር፡፡ አስረኛው ጥያቄ የመጨረሻው ብቻ ሳይሆን…. ብቸኛውም ነው ይላል መግለጫው፡፡ እስካሁን እያነከሰና እየዘለለ የመጣቸው ጥያቄዎች… አስረኛውን መፍታት ይችል ዘንድ ልቦናውን  እንዲያፍታታባቸው ተብለው የተቀረፁ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ከመግለጫው ስር በአስረኛው ተራ ቁጥር ትይዩ የጥያቄ ምልክት ተቀምጧል፡፡ ጥያቄው ግን የለም፡፡ … ወረቀቶቹን እያገላበጠ አሰሰ፡፡ ልብስ መስቀያ የሚያክል የጥያቄ ምልክት ብቻ ነው ያለው።
ጴጥሮስ አዲስ  ለመጣ ተፈታኝ፣ የፈተና ወረቀት ካስቀመጠበት አውጥቶ እየሰጠው ነው፡፡ አዲሱ ተፈታኝና ጴጥሮስ ባቢሌ ላይ አትኩረዋል፡፡ አዲስ ተፈታኝ ጥያቄዎቹን መስራት እንዲጀምር… አሮጌው ተፈታኝ ጨርሶ መነሳት አለበት፡፡ ወረቀቱ ላይ ያለው ጥያቄ ምልክት በጴጥሮስም ፊት ላይ ያለ መሰለው። ሱሰኛው የሆነ የረሳው የድሮ ነገር ያማረው መሰለው፡፡ ግን ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻለም፡፡
ወደ ጥያቄው አተኮረ… ጥያቄው የጥያቄ ምልክት ነው… ጥያቄው ግን ምን እንደሆነ አይታወቅም። አልሰፈረም፡፡ ጥያቄውን በማስፈር ነው መልስ የሚሰጠው፡፡ ማሰብ ጀመረ፡፡
… ጥያቄ እና መልስ የሙሉነት ግማሽ ስባሪ ናቸው… ጥያቄ… እና መልስ በእኩል ሁኔታ መፈላለግ ይኖርባቸዋል… እንደ ባል እና ሚስት …. እንደ ሰው እና ፈጣሪ… ሰው ጥያቄ ነው፤ፈጣሪ የጥያቄው ባለቤትና የመልስ ምንጭ…. ባል እና ሚስት በአንድ ጊዜ ጥያቄም መልስም ናቸው፡፡ ለባሏ ጉድለት፤ ሚስት ሙሌት ታዋጣለች፡፡ ሙሌት የምታዋጣው ሙሉ ስለሆነች ሳይሆን የባሏን ጥያቄ በመሙላት ነው፤ ለራሷም ጥያቄ መልስ ለማግኘት የምትበቃው።… እያለ አሰበ፡፡
… ስለዚህ ጥያቄና መልሱን በአንድ ላይ የሆነው ሙሉው ነው፡፡ ሙሉነትም ደረጃ አለው፡፡ ጠብታም በራሷ ሙሉ ናት፡፡ ከባህር አንፃር ቁንፅል ነች፡፡ ሰው በራሱ ሙሉ ነው፡፡ ግን ከትዳር ህይወት አንፃር ጉድለት ነው፡፡… ሁሉም ጥያቄ ናቸው፡፡ በተናጠልም ሆነ በጋራ ለጥያቄነታቸው መልስ ይፈልጋሉ፡፡ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚያገኙት የጥያቄአቸው መልስ ግን… ሙሉ አይደለም፡፡ ጉድለት አለው። ጉድለቱ በአንፃራዊ ሙላት ቢደፈንም… በፈጣሪ ሙሉነት አንፃር ሲታይ ግን ጉድለት ነው… ጥያቄ ነው። ጥያቄ ምልክቷ… ለትንንሽ ጥያቄዎች መልስ አግኝታ የተረጋጋች ብትመስልም፣ ከፍ ላሉ ጥያቄዎች ግን መረጋጋቷ የወገኛ መረጋጋት ነው፡፡ ጥያቄ ምልክቱ ሰው ነው፡፡… ከፈጣሪው ጋር እስኪዋሀድ ድረስ…
መልሱን ስለማግኘቱ እርግጠኛ ሆነ፡፡ መልሱን አግኝቶታል፡፡… ግን ለመፃፍ ፈራ፡፡ ለራሱ የሚመች መልስ ለፈጣሪ ላይመቸው ይችላል፡፡… ሰው ብሎ በድፍረት መልሱን ሊሞላ ሲል ሰይጣን ትዝ ይለዋል፡፡ ሰይጣንም የጥያቄ ምልክት ነው፡፡ የጥያቄ ምልክትን የፈታው ሰውን በማሳት ለጉድለቱ መልስ ለመስጠት ወስኖ ነው፡፡
… መልሱን ያውቀዋል ግን መፃፍ ፈራ፡፡… ከፍርሀት ቀጥሎ ተጠራጠረ… ፈተናውን የሚፈትነኝ ራሱ ማነው?.... ሁሉም ነገር ተደበላለቀበት… ከጥያቄ ምልክቷ ጎን “በቃ ለጥያቄና መልስ ብቁ አይደለሁም ---- ወደ ምድር ተመልሼ በመቃብር መቆየት ይሻለኛል…›› ብሎ ፃፈና አረፈ፡፡

Read 6104 times