Saturday, 30 July 2016 12:36

“የባልና ሚስት አለመግባባት እና የፍቺ ምክኒያቶች”- አበበ አሳመረ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(9 votes)

በአገራችን ብሎም በከተማችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ ካሉ ማህበራዊ ጉዳዮች አንዱ የወጣቶች ጋብቻ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ወደ ትዳር የማምራታቸው ጉዳይ ይበል የሚያሰኝ ማህበራሰባዊ ባህሪ ቢሆንም ቀደም ብለው የመሰረቱትን ትዳር የሚያፈርሱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ወደ ማዘጋጃ ቤት ቢሮዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በክፍለ ከተማ ደረጃ ወደ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቢሮዎች ለመፈራረም ጎራ የሚሉ ጥንዶች የመብዛታቸውን ያክል ፊርማችንን ቅደዱልን እያሉ የፍትህ አካላትን የሚማጸኑ ጥንዶችም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ያስረዳሉ፡፡
ይህንን ጉዳይ ያስተዋሉ የተለያዩ አካላትና ግለሰቦችም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ገሚሶቹ የሬዲዮ እና የተሌቪዥን ፕሮግራም መወያያ ርዕሳቸው ካደረጉት ሰነባብተዋል፡፡ ከነዚህ ለፍቺ ችግሮች መፍትሄ መስጠትን ጉዳያቸው ካደረጉ ግለሰቦች መካከል አንዱ አቶ አበበ አሳመረ ነው። አቶ አበበ የኢትዮጲያ ጽንስና ማህጸን ሃኪሞች ማህበር (ኢሶግ) የህግ አማካሪ ሲሆን- የባልና የሚስት አለመግባባት እና የፍቺ ምክኒያቶች- በሚል በ2007 አ/ም ባሳተመው መጽሃፉ የፍቺን ምክኒያቶች በዝርዝር ለማስቀመጥና እና መፍትሄ ያለውንም ለመጠቆም ሞክሯል፡፡
133 ገጾች ባሉት በዚህ መጽሃፍ አቶ አበበ በሶስት ክፍሎች ስለርዕሰ ጉዳዩ በዝርዝር አውስቷል። መጽኃፉ እንደጸሃፊው በተግባር ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ጸሃፊው ካነሳቸው ችግሮች መካከል ከወሲብ፤ ከድንግልና፤ ከአካላዊ ጥቃት እና ከልጆች ጋር የተገናኙትን መራርጠን በሁለት ክፍል ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡
ጸሃፊው ለፍች ምክኒያቶች ካላቸው ተግባራዊ ልምዶች መካከል አንዱ በወሲብ አለመጣጣም ነው፡፡ መጽኃፉ በዚህ ረገድ በወሲብ አለመጣጣም ትልቁ የፍቺ ምክኒያት ሊሆን እንደሚችል ያወሳል። እንደጸሃፊው ይህ ችግር ከመቶ ፍቺዎች መካከል ለ80ዎቹ ምክኒያት ሊሆን እንደሚችል ሌሎች ጽሁፎችን ዋቢ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡
የሃይማኖት ጽሁፎችም የወሲብ አለመጣጣምን እንደ ትልቅ ችግር እንደሚዩትና ይህም “ወሲብን ታላቅ የፈጣሪ ጸጋ አድርጎ ከማሰብ የሚመነጭ ነው” ይለናል፡፡ በዚህም ብቻ ሳይገደቡ ብዙ የሃይማት ጽሁፎች ለወሲብ አለመጣጣም መፍትሄ ናቸው የሚሏቸውን ሳይንሳዊ መንገዶች እስከመጠቆም እንደሚደርሱም ይገልጻል፡፡
የወሲብ አለመጣጣም የሚከሰትባቸው ምክኒያቶች እንደጸሃፊው ከሆነ የተለያዩ ናቸው፡፡“የወሲብ ፍላጎት ማጣት ወይ መቀዝቀዝ፤ የወሲብ ብቃት ማነስ፤ ቀድሞ መርካት፤ ለወሲብ በበቂ ሁኔታ አለመዘጋጀትና ሌላውንም አለማዘጋጀት፤ በወሲብ ባህሪ ምክኒያት አለመግባባት፤ በጾም ምክኒያት በሚጣል ገደብ አለመግባባት፤ የአመጋገብ ስርዐት ችግር፤ ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት፤ የብልት አለመመጣጠን፤ ወሲብን እንደመደራደሪያ በማድረግ የሆነ ነገር ካደረክ ወይም ካላደረክ በሚል ድርድር ወሲብ መፈጸም መፈለግ፤ የስራ ብዛትና የኑሮ ውጥረት፤ በተለያየ ፖዚሽን ወሲብ መፈጸም ፈቃደኛ አለመሆን” መሆናቸውን ጽሁፉ ጥናቶችን ጠቅሶ ያስረዳል፡፡
“ባለቤቴ ግብረሰዶማዊ ሳይሆን አይቀርም የወሲብ ባህሪው ተቀይሯል ያለቺም ሴት ትዝ ትለኛች፤” ይላል ጸሃፊው ተግባራዊ ልምዶችን ለመሰብሰብ ካነጋገራቸው ግለሰቦች መካከል ከአንዱ ያገኘውን ልምድ ሲያካፍል፡፡
በጥንዶች መካከል የሚኖር ጭቅጭቅ የወሲብ ፍላጎት መቀነስን እንደሚያስከትል፤ የወሲብ መቀነሱ ደግሞ እራሱን የቻለ ምክኒያቱ የማይታወቅ ጭቅጭቅ እንደሚያስከትልና በዚህ ዑደት ውስት ስለሚኖሩ ጥንዶችም እጣ ፋንታ የሚከተለውን ልምድ በማካፈል ጽሁፉ ያስረዳል፤
“… ቁጣዋና ንዝንዟ ወደ አዕምሮዬ ይመጣና እንኳን ስለወሲብ ላስብ አይኗንም ማየት ያስጠላኝ ጀመር፡፡ ከዚያም ከአንዲት የመስሪያ ቤት ባልደረባዬ ጋር ግንኙነት ጀመርኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ይበልጥ ለሚስቴ ያለኝ ስሜት ሞተ” ይላል፡፡
በወሲብ አለመጣጣም ችግር እጅግ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩን ሆድ ይፍጀው ብለው የሚኖሩ ጥንዶች እነዳሉ ሁሉ፤ ፍቺን የሚመርጡም ብዙ ናቸው፡፡ የወሲብ አለመጣጣምን በግልጽ ወደአደባባይ ይዞ ወጥቶ ፍቺ መፈጸምን በማፈር አላስፈላጊ ምክኒያቶችን ፈጥረው የሚለያዩም አልጣጡም፡፡ ጸሃፊው በዚህ ረገድ የሚከተለውን ግለሰብ ልምድ አካፍሏል፤
 “… ሰራተኛዋን ደፈርክ የተባልኩት ሀሰት ነው። ሚስቴ ከውጪ አገር ስትመጣ እኔ ምክኒያቱን በማላውቀው ሁኔታ ወሲብ መፈጸም የማልችል ሆኜ በሽተኛ ሆንኩ፡፡ ሃኪምም ይህንኑ አረጋግጦልኛል፤ ሚስቴ ግን ስላላመነችኝ እሰራልሃለው ብላ ተመካክረው ደፈረ ብለው በሃሰት ከሰሱኝ፡፡” ይላል ጸሃፊው ፍርድ ቤት ሲናገር ሰማሁት ያለውን ግላሰብ ታሪክ ሲያካፍል፡፡
በወሲብ አለመጣጣም ችግር መኖሩ ብቻም ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ለፍቺ ምክኒያት መሆኑ የመታወቁን ያክል በጥንዶች መካከል ስለጉዳዩ በግልጽ የመወያየት ልምድ እንደሌለ ጸሃፊው ያወሳል። በዚህ ረገድ ወጣቱ ትውልድ በተሻለ መልኩ ስለወሲብ የመያየት ፍላጎትና ድፍረቱን ቢያሳይም የተፈለገውን ለውጥ እስኪያመጣ በባህል ምክኒያት የሚደርስበት ተጽእኖ እንደሚኖር ይገልጻል፡፡
የአመጋገብ ስርዐትን ማስተካከልና በጥንዶች መሃል የሚኖር ጭቅጭቅን መቀነስ ችግሩን ለመፍታት አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚነራቸውም ጽሁፉ ያስረዳል፡፡ ጥንዶች በግላቸው ጊዜን ለማሳለፍ ማቀድ እንዳለባቸውም ይመክራል፡፡
ጸሃፊው ለፍቺ ምክኒያቶች መሆናቸውን ደርሼበታለው ካላቸው ምክኒቶች ሌሎቹ በሚስት/ በሴቷና በልጆች ላይ የሚደርስ አካላዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች ናቸው፡፡ በሚስት ላይ የሚደርስ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት እጅግ በርካታ እንደሆነ የሚያወሳው ጸሃፊው አካላዊ ጥቃቱ እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችልና ስነልቦናዊ ጥቃቱ ደግሞ ስድብ እና ሰብዐዊ ክብርን የሚነኩ ንግግሮችን እንደሚያካትት ያብራራል፡፡
በሚገርም ሁኔታ ጸሃፊው በተወሰኑ የአፍሪካ ሃገራት ላይ የተደረገ ጥናትን ጠቅሶ እንደሚያብራራው፤ ሁሉም ሴቶች የሚደርስባቸውን ጥቃቶች እንደ መጥፎ እንደማያዩትና እንደውም አብዛኛዎቹ (87 በመቶ የሚሆኑት) ባሎቻቸው የሚደበድቧቸው ስለሚቀኑባቸው መሆኑንና ይህም በባሎቻቸው ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት እንደሚያሳይ እንደሚያምኑ ያስረዳል፡፡
በርግጥ ሁሉም ሴቶች የሚደርስባቸውን ጥቃት ወደህግ ፊትም ሆነ ወደ ማህበረሰቡ የማያመጡበት ምክኒያት ይህ ብቻ እንዳልሆነ ጸሃፊው አልሸሸገም፡፡ የገቢ ማጣትና ሚስት ብቻም ሳትሆን ቤተሰቦቿም ጭምር በባል ላይ ጥገኛ የሆኑበት ሁኔታ ሲኖር፤ ቤተሰብ ተበትኖ ልጆች እንዳይጎዱ በማሰብ፤ የሴት ቤተሰብ ቢሰማ ባሌን ያጠቁብኛል በሚል እና በሌሎች ምክኒያቶች ብዙ ሴቶች ከአካላዊ እና ስነልቦናዊ ጠባሳዎቻቸው ጋር ለመኖር እንደሚመርጡ ጸሃፊው ያስረዳል፡፡
በልጆች ላይ የሚፈጸም የአካልና የወሲብ ጥቃት ሌላኛው የፍቺ ምክኒያት ሊሆን እንደሚችል ጸሃፊው ይናገራል፡፡ በባል ወይም በአባት ሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ሌላኛው የፍቺ ምክኒያት ነው፡፡ ለዚህም እንደማስረጃነት ያቀረበው በልደታ ምድብ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወነጀል ችሎት ውስጥ ተቀምጬ ሰማሁት ያለውን ሚስት ለአቃቤ ህግ የሰጠችውን ቃል ነው፤
ሚስት፡ “ልጄን ደፍሮ እኔ እነዴት ነው ከሱ ጋር የምረው” ስትል እድምጫለው ይላል ጸሃፊው፡፡
የአባት ሴት ልጁን መድፈር እጅግ እየተበራከተ መምጣቱን ጸሃፊው አውስቶ እንዲህ አይነቶቹን የፍርድ ሂደቶች ሲከታተል ለቆየ ሰው “ሴት ልጁን ለማንም አምኖ ትቶ ሊሄድ አይችልም” ይላል፡፡
ከጥንዶች መካከል በአንድኛው የሚፈጸም እና ልጆች ላይ የተቃጣ አካላዊ ጉዳት የፍቺ ሌላኛው ምክኒያት ነው፡፡ ምንም እንኳን ሁል ጊዜ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች በክፉ ልቦና ተነሳሽነት ባይሆንም የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በሆነ ጊዜ ለፍቺ ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ ጸሃፊው ለዚህ እማኝ እንዲሆን አንድ ታሪክ አካፍሏል፤
ሚስት፡ “እኔ ግን የገዛ ልጁን በሽተኛ ካደረገ አረመኔ ጋር አልታረቅም ብያለው፤ አሁንም አልታረቅም፤ ህግ እንዳደረገ ያድርገው” ትላለች ይላል፡፡
እንዲህ ያሉ ብዙ ታሪኮች ወደ ፍርድ ከመቅረብ ይልቅ በቤት ውስጥ ተደበስብሰው ስለሚቀሩ እንጂ በዚህ ብቻ የተገደቡ አይደሉም፡፡ ብዙዎቻችን በባህል ምክኒያት የቤተሰብን ገመና ወደ አደባባይ ማውጣትን እንደነውር የምናይ ከመሆናችን ጋር ተያይዞ ልጆች ላይ የሚደርሱ ብዙ ጥቃቶች ተደበስብሰው የመቅረት እድል አላቸው፤ እንደ ጸሃፊው፡፡
ከልጆች ጉዳይ ብዙ ሳንርቅ ልጆች መውለድ ያመፈለግ ጉዳይ ሌላኛው የፍቺ ምክኒያት ነው ይለናል ጸሃፊው፡፡ ከጥንዶች መካከል አንድኛው አካል (በአብዛኛው ጊዜ ወንዶች ቢሆኑም) ከትዳር በኋላ መውለድ የማይፈልጉባቸው ምክያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤
“ነጻነቴን ያሳጣኛል፤ መዝናናት እፈልጋለው፤ ከወለድኩ ገንዘቤን ለምፈልገው አላማ ብቻ ማዋል አልችልም፤ የማሳደግና የመንከባከብ ሃላፊነትን ለመሸከም ፍቃደኛ አይደለሁም፤ መውለዴ የወሲብ ሰሜቴን ሊቀንስብኝ ይችላል፤ በፈለግነው ጊዜና ሁኔታ ወሲብ ለመፈጸም አንችልም፤ ከወሊድ በኋላ ቅርጼ ይበላሽብኛል፤ አሁን ላይ መውለድ አልፈልግም” የሚሉትና ሌሎችም ምክኒያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በተግባር የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጸሃፊው አስነብቧል፡፡
ሌላው ልጅ ላለመውለድ ፍላጎት ማጣት የሚከሰተው ደግሞ ንበረትን ላለማካፈል ከሚመነጭ ስጋት ሊሆን እንደሚችልም ጽሁፉ ያትታል፡፡ ምክኒያቱ ምንም ይሁን ምን ግን የትዳር ዋንኛ ትርጉሙ ልጅ መውለድና ዘርን ማስቀጠል ነው ብለው በሚያኑ እንደ ኢትዮጲያውያን ባሉ ህዝቦች መካከል ልጅ መውለድ አለመፈለግ ለፍቺ ትልቁን ድርሻ ሊይዝ እንደሚችል ጸሃፊው ያስረዳል፡፡
ጥንዶች ልጅ የመውለድ ፍላጎት እና የሚወለድበትን ጊዜ አስመልክቶ ከትዳር በፊት የሚደረግ ግልጽ መግባባት ሊኖር እንደሚገባና ይህ በሆነበትም ሁኔታ ትዳር ውስጥ ከተገባ በኋላ ሃሳብን መቀየር እና ባልተስማሙበት መዋል ግን ስምምነቱን ባላከበረው አካል ላይ የከሃዲነት ባህሪ እንዳለው ተደርጎ መወሰዱና ይህም በተቀረው አካልና ቤተሰብ ላይ የስሜት መጎዳት እንደሚፈጥር ጸሃፊው ያብራራል፡፡
ውድ አንባቢያን ለዛሬ የፍቺ ምክያቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ባተኮረው የአቶ አበበ መጽሃፍ ላይ ተመስርቶ የቀረበው ጽሁፋችን በዚሁ ያበቃል። ሳምንት ከተመሳሳይ መጽሃፍ ያገኘናቸውን ተጨማሪ የፍቺ ምክኒያቶች እና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ ሌላ ጽሁፍ ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ መልካም ሳምንት፡፡    

Read 8197 times