Saturday, 30 July 2016 12:00

እውቀት ሲሞት ያሳዝናል!

Written by  በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)
Rate this item
(11 votes)

ሰው ሟች ነው፡፡ በመሀል ያለውን ግሳንግስ ብንተወው ሰው የሚወለደው ለመሞት ነው፡፡ የተወለድን እለት ለመሞት እጣ እናወጣለን፤ መወለድ ለሞት መታጨት ነው፡፡ የእውቀት እጣ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እውቀት እየጠነከረ፣ እየታደሰ እየተጨመረበት . . . . ይጎመራ ዘንድ ነው - እጣው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ እውቀትም እንደ ሰው፣ በአጭር ሲቀጭ . . . ሲሞት. . . ያሳዝናል፡፡
አንዳንድ እውቀት አለ፤ ለአንድ ሀገር፣ የአንድ ዘመን ትውልድ ብርቅ የሚሆን፡፡ አንዳንድ ማህበረሰብ ደግሞ አለ፤ እውቀት የማይደንቀው፤ በባህልና ልማድ ተለጉሞ የሚንፏቀቅ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሲገጣጠሙ እውቀት እንደ ሰው ሞቶ ይቀበራል፡፡ የጋሽ አባተ መኩሪያ ብርቅ እውቀትና ያለንበት ለእውቀት የታወረ ማህበረሰብ በመገጣጠሙ፣ አባተ ሰውዬውንና የትያትርና የስነጽሑፍን እውቀት አንድ ላይ ቀበርን፡፡ ብዙ ሰው ለጋሽ አባተ . . . ለሰውዬው አለቀሰ፤ እኔ ስለተቀበረው እውቀት አነባሁ፡፡ ሰውዬው ሰባ ስድስት ዓመት ኖሯል፤ አርባና ሃምሳ አመት ብርቅ በሆነበት ሀገር፡፡ በዚያ ላይ የነብሱን መንፈስ ሳያስቀይም፡፡ ለጋሽ አባተ፣ ለሰውዬው ያለቀሱት ሰውዬውንና ስራውን ብቻ የሚያውቁ ናቸው፡፡
ጋሽ አባተ የትያትር ሰው ብቻ የሚመስላቸው የእነ ኤድጋር አላንፓ፣ ዊልያም ዎርድስ ዎርዝ፣ ኢሚሊ ብሮንቴ … ወዘተን ግጥም በቃሉ እያነበነበ ሲተነትን የማያውቁት ናቸው፤ እኔ ግን አውቀዋለሁ፡፡ ጋሽ አባተ ከክላሲካል እስከ ዘመነኛ የስነ ጥበብ ትውርቶችን፣ ከመገለጫ ታላላቅ ሥራዎች (ሲያሻው በጠራና በማይጠገብ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፍሰት) ሲያብራራ እያዳመጡ ውሎ ለማደር አያሰለችም፡፡
ጋሽ አባተ ጥበብን ተምሯታል፤ ኖሯታል፤ ሰርቷታል፡፡ መማሩ በጥልቅ ንባብ፣ ኑሮው በሚያስደንቅ አለማቀፋዊ ተግባራዊ ልምድ፤ ሥራው ከ‹‹ሀሁ በስድስት ወር›› እስከ ‹‹አፋጀሽኝ››፣ የተረጋገጠ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን እኒህን አሰናስሎ የያዘ የጥበብ ባለሙያ (በተለይ በትያትር) ሀገሬ የላትም፡፡ ከዚህ ሁሉ የተገኘ እውቀትን ነው ከሰውዬው ጋር የቀበርነው፡፡ መጽሐፍ አልፃፈምና የተለየ የአዘገጃጀት ፍልስፍናውና ጥበቡ አልተቀረሰም፡፡ በእርግጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ት/ቤት ከተረሳበት ፈልጎ፣ በአማካሪነት ከቀጠረው በኋላ፣ ያዘጋጃቸው ሥራዎች በምስል መቅረጫ ተቀድተው አሉ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ግን ያለቀለትን ዝግጅት እንጂ ቅደም ተከተላዊ ሂደቱን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ነቢባዊ እውቀቱና ልምዱንም በመጽሐፍ አላስተላለፈልንም፡፡ ሁሉንም ይዞት ሄደ፡፡ ያሳዝናል፡፡
አንዳንዶች ለዚህ ክፍተት (ላለመፃፉ) ወደ ራሱ ወደ ጋሽ አባተ ጣታቸውን ይቀስራሉ፡፡ ‹‹ሊጽፍና እውቀቱን ሊያስተላልፍ የሚችልባቸው የመጨረሻዎቹን አመታት እየጠጣ፣ እያጨሰ… በቁዘማ አሳልፏል›› ይሉታል፡፡ ይህ አይገርምም! የማህበረሰባችን አይን የሚያየው ይህንን ነው፡፡ እየጠጣህ፣ እያጨስክ፣ የነብስያህን መሻት እየኖርክ፣ አሰልቺ ኑሮውን የሚያጣፍጥ፣ ድህነቱን የሚታደግ፣ መንፈሱን የሚያለመልም እውቀት ከምታበረክትለት፣ ጋቢ ደርበህ ሰንበትን እየተሳለምክ፣ ጀለቢያ አጥልቀህ ሶላት እየሰገድክ ለማህበረሰቡ ምንም ሳትሰራ ብታልፍ ያከብርሃል፡፡ ‹‹ታላቅ ሰው ነበር!›› ብሎ ውሎህን ይተርክልሀል፡፡ ድሮስ ከማያነብ ማህበረሰብ ምን ይጠበቃል! ይህ እኮ የታወቁና አንባቢ ያላቸው ደራሲዎቻችን አምስት ሺ ኮፒ መጽሐፍ ለመሸጥ አመት የሚጠብቁበት የመቶ ሚሊየን ዜጎች ሀገር ነው፡፡
‹‹ጋሽ አባተ የመጨረሻዎቹን አመታት በማማረር ከማሳለፍ ቢጽፍ ይሻል ነበር›› የሚሉ ሰዎች ሰውዬውን አያውቁትም፡፡ ሰውዬው ከምሬት ለደስታ፣ ለሳቅና ለቀልድ ቅርብ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን አጥንት ድረስ የሚሰማ ምሬት ውስጥ ይገባል፡፡
ለምን አይማረር! ያ ለሀገሩ የመጀመሪያውን የትያትር ማዕከል ያቋቋመ ሰው ያዘጋጀውን ትያትር /ለምሳሌ አፋጀሽኝ/ የሚያሳይበት መድረክ ሲነፈገው መቆዘም … ማጨስ … ይብዛበት! ለጊዜውም ቢሆን ሲጋራውን እያጨሰ - ቆሽቱን ጨሶ ከማለቅ አሰንብቷታል፡፡
በለንደን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በስኮትላንድ፣ በኖርዌይ፣ በአሜሪካ፣ በምስራቅ አፍሪካ፣ በሀንጋሪ … አንቱ የተባለው አዘጋጅ፣ ከነፒተር ብሩክ ጋር ረዳት ሆኖ ያዘጋጀው አዘጋጅ - አብዛኞቹ የሀገሩ መድረኮች የደፋር አዘጋጆች ‹‹ቅርሻት›› ሲያስተናግዱ እያየ ማጨስ … መጠጣት … መቆዘም ይብዛበት!
ፈረንጆች ሳይቀሩ ያደነቁት፣ ዶክመንተሪ ፊልም /Under the African Sky/ የሰሩለት ታላቅ ሰው፣ ወገኑ ረስቶት፣ ‹‹በዚህ አለፈ›› ይባል የነበረው ሰው! የገዛ ወገኑ ሸረሪት ሆኖ ሲያደራበት ማጨስ፣ መጠጣት ይብዛበት!
ጋሽ አባተ የመጨረሻ ዓመታት ተረጋግቶ እንዲጽፍባቸው መንግስትና ማህበረሰቡ አልፈቀዱለትም፡፡ ከመሸም ቢሆን ጓደኞቹ ሞክረዋል፤ እንደታሰበው አልተሳካም፡፡ ‹‹መኩሪያ ስቱዲዮን››፣ ‹‹የምስራቅ አፍሪካ ትያትር ኢንስቲትዩት›› አቋቁሞ ሊሰራ ሞከረ፡፡ ከውጭ ድጋፍ እየፈለገ በሚሰራው ስራ፣ የቢራና የአረቄ ፋብሪካ የተከለ ይመስል፣ መንግስት በሚሊዮን ብሮች ግብር ይጭንበት ገባ፡፡ ከረቸመው፡፡ እና መቆዘም ይነሰው!
በዚህ ዓለም ላይ፣ የጥበብ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ፣ መድረክ እንደማጣት ያለ ስቃይ የለም፡፡ ‹‹አፋጀሽኝ››ን ያህል ፕሮዳክሽን ይዞ መድረክ የተነፈገው ጋሽ አባተ፤ በስትሮክ ያልተመታው፣ ልቡ ቀጥ ያላለችው፣ ብሶቱን በአረቄ አለቅልቆ፣ ከጭስ ጋር ስለሚያስወጣው ይመስለኛል፡፡
ጋሽ አባተ የዋህና ቀጥተኛ ሰው ነው፡፡ በሚቀያይራቸው ሜርሴዴስ መኪናዎች የሚታወቀው አባተ፣ ከርካሳ ባለ አንድ በር ላንድ ክሩዘር ውስጥ ተቀምጦ፣ የወሰንን የጀበና ቡና እየጠጣ፣ በአብዮቱ ዘመን ‹‹ኪነት ለአብዮትን›› በሚዘምሩ ካድሬዎች ያደረሱበትን ስቃይ፣ በዘመነ ኢህአዴግ የተነፈገውን መድረክ ሲያወራ፣ ማሳረጊያው ‹‹አቦ ይመቻቸው!›› ብቻ ነው፡፡
በየዘመናቱ፣ እያሰለሰም ቢሆን አንዳንድ ሰዎች ይፈጠራሉ፤ እንደ ጋሽ አባተ መኩሪያና ዮናስ አድማሱ አይነት፤ ገና በወጣትነታቸው ስለማህበረሰባቸው መበደል የሚያለቅሱ፣ ስለመሻሻሉና እድገቱ የሚዘምሩ፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ ነፍሳቸውን የሚያዳምጡ፣ ጥሪያቸውን የሚኖሩ፡፡ ማህበረሰባዊ ልማድ ግን በቀላሉ አይቀበላቸውም፡፡ ከስርዓቱና ከአገዛዙ ጋር ይሰለፍባቸዋል፤ ወይም በአርምሞው ይኮንናቸዋል፡፡ ተስፋ ያስቆርጣቸዋል፡፡ አደባባይ ነፍጎ ወደ ባንኮኒ ይገፋቸዋል፡፡ ለማህበረሰባቸው እድገትና ስልጣኔ ሽተው የቋጠሩትን እውቀት እንደያዙት ይሞታሉ፡፡ አልቅሰን እንቀብራቸዋለን፡፡ ሲቆዝሙ ለማጽናናት፣ ሲታመሙ ለመጠየቅ አንድ ሰዓት ያልነበረው ዜጋ፤ ሊቀብራቸው ግማሽ ቀን ያጠፋል፡፡ መንግስት ሲጠላህ፣ ሲያገልህ፣ ሲያስርህ ‹‹ምነው?›› ብሎ ያላማለደህ አቡን ፍታት ያደርግልሀል፤ ገነትን ያማልድሀል፡፡ ሲበድልህ የኖረ የመንግስት ባለስልጣን፣ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጥልሀል (የበታቹንም ልኮ ቢሆን)፡፡ ዜጋው ደግሞ በእውቀትና በሥራህ የፈነጠካትን ፀሐይ፣ ‹‹በምን ዋጋ አለው፣ ባይጠጣ፣ ባያጨስ…›› የስስት ተረብ ያደበዝዝብሀል፡፡
    የተማረና የሰለጠነ ማህበረሰብ ለእውቀትና ለሥራ ዋጋ ስለሚሰጥ፣ እንደ ሔሚንግዌይ ከመለኪያ ጋር ብትቆርብ፣ እንደ ዶስቶቭስኪ በቁማር ብትለከፍ ግድ የለውም፤ ስለ መልካም ስራህና ስላበለፀግከው እውቀት ሀውልት ያቆምልሀል፤ ይዘምርልሀል፡፡ የሀገሬ ሰው ያልተማረ ‹‹ጨዋ›› እና ያልሰለጠነ ነው፤ አንተ ተፈጥሮአዊውን ሞት ስትሞት፤ እውቀትህንም ገድሎ ይቀብረዋል፤ እንደነ ጋሽ አባተ፡፡ እውቀት ሲሞት ያሳዝናል፡፡

Read 9172 times