Saturday, 30 July 2016 11:54

ዕዳ ከሜዳ

Written by 
Rate this item
(30 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ ጠዋት ማለዳ ተነስቶ ለሚስቱ፡-
“ዛሬ ከቤት ውጣ ውጣ ብሎኛል” ይላታል፡፡
ሚስቲቱም፤
“ወዴት ነው ውጣ ውጣ ያለህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
“ወደ ሆነ ጫካ ሄጄ መዝፈን ፈልጌያለሁ”
ሚስቲቱም፤
“እኔ አልታየኝም፡፡ ደግሞስ ከመቼ ወዲያ ያመጣኸው ፀባይ ነው? እኔ ቀፎኛል፡፡ መዝፈንም ከሆነ ያማረህ እዚሁ ቁጭ ብለህ እንደልብህ እየጮህክ ዝፈን ምን ጫካ ለጫካ ያንከራትትሃል?” አዝማሪውም፤
“በገዛ አገሬ ጫካ ብሄድ፣ ሜዳውን ብጋልብ፣ ያሰኘኝን ባረግ ምን እንዳልሆን ብለሽ? እባክሽ ፍቀጂልኝና ዱር ሄጄ ዘፍኜ ይውጣልኝ” ሲል ለመናት፡፡
“እንግዲህ ይሄን ያህል ተንገብግቤለታለሁ ብለህ ልብህ ከተነሳ እዚህ ቁጭ ብለህም ምንም አትፈይድልኝ፤ ይሁን ሂድና ያሰብከው ይሙላልህ” አለችው፡፡
አዝማሪው ደስ ብሎት ወደ ዱር ሄዶ አንድ ትልቅ የዋርካ ዛፍ ስር ተቀምጦ ክራሩን ቃኝቶ፤ በሚያምር ድምፅ፤ ጮክ ብሎ፣ መዝፈን ይጀምራል፡፡
“ኧረ ፋኖ ፋኖ፣ አንት አሞተ መረራ የልብህ ሳይሞላ፣ ተኝተህ አትደር፡፡
ሜዳላይ አይድከም፣ ለዳገት የጫንከው የልቡን አርጎ ነው፤ ጀግና እፎይ የሚለው፡፡”
ይህን እየዘፈነ ፍንድቅድቅ እያለ አርፍዶ በድንገት ወደሱ የሚመጣ የእግር ኮቴ ሰማ፡፡ በርካታ ሰዎች መጥተው ከበቡት፡፡
እነዚህ ሰዎች በሬያቸው ተሰርቆባቸው ፍለጋ ላይ ናቸው፡፡
“የበሬያችን ሌባ ተገኘ፡፡ ያዙት! ያዙት!” እያሉ ይቀጠቅጡት ጀመር፡፡
አዝማሪው
“እረ ጌቶች፤ እኔ በሬ እሚባል አላየሁም፡፡”
“አንተ ነህ እንጂ የሰረቅኸው! ይሄው ከጀርባህ ያለውን አታይም፡፡ ሥጋውን በልተህ በልተህ ስትጠግብ የተረፈህን ሰቅለህ፤ በጥጋብ ትዘፍናለህ፡፡ ቆዳውም ያው የኛ በሬ መልክ ነው ያለው፡፡ መስረቅህ አንሶ ልታታልለን ትፈልጋለህ?” እያሉ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ቀጥቅጠው፣ እጅ እግሩን አስረው፤ ጥለውት ሄዱ፡፡ የተረፈውን ስጋ ይዘው ሄዱ፡፡ ሚስቱ ወደ አመሻሹ ላይ ቤት ሳይመለስ በመቅረቱ ሰው ይዛ በጫካው ስታስፈልገው ዋርካው ስር ተኮራምቶ ተኝቶ ተገኘ፡፡
“ምነው ምን ሆንክ?” ብትለው፤
“እረ ተይኝ፡፡ ዕዳ ከሜዳ ነው የገጠመኝ!”
*   *   *
በል በል አለኝ፣ እንዲህ አርግ አሰኘኝ ብለን በዘፈቀደ የምናደርገው ነገር ዕዳ ከሜዳ ያመጣል፡፡ አካባቢን፣ ግራ ቀኙን በቅጡ አለማየትና አለመመርር ዕዳ ከሜዳ ያመጣል። የሌሎች ግንዛቤና የእኛ ግንዛቤ ላይጣጣም ይችላልና የሀሳብ ርቀትን ልብ እንበል። ደምቦች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆች የድንገቴ ሲሆኑ ህዝብ ላይ ዕዳ ከሜዳ ይሆናሉ፡፡ ዕዳ ከሜዳ መሆናቸው ሳያንስ የአፈፃፀም ችግር ካለ ደግሞ ይብሱን ከድጡ ወደማጡ ይሆናል፡፡
ስለአፈፃፀም ችግር ሌት-ተቀን ቢወተወትም ‹‹ወይ›› ያለ የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹እሺ እናርማን› የሚል፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ባለሥልጣን ወይም አለቃ አልተገኘም፡፡ ችግሮች የማያባራ ዝናብ የሆኑ አንድም በምንግዴ ነው፤ አንድም ሠንሠለታዊ ባህሪ ስላላቸው ማን ማንን ይነካል ነው፤ አሊያም እከክልኝ ልከክልህ ነው፤ ወይም ደግሞ የአቅም ማነስ ነው፡፡ የችግሮች ባለቤት ማጣትም ሌላው ችግር ነው፡፡ የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታም ዓይነተኛ አባዜችን ነው፡፡ አንድ ነገር የተሸከመው ችግር ሳያንስ፤ ቆሻሻ ማንሳት ችግር ሆኖ ሲያነጋግር ማየትና መስማት እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ ዛሬ እንደ ዘበት ‹‹ቆሻሻ ውስጤ ነው!›› እየተባለ ሲቀለድ መስማት ይዘገንናል፡፡ ስለለውጥ ማውራት ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬም ውሃ የለም፡፡ ሆኖም ስለአተት እናትታለን። ዛሬም መብራት የለም፡፡ አገር እየተሰጠነች ስትሄድ መብራት የኃይል ምንጭነቱ የህልውና ጉዳይ ይሆናል እንጂ ዛራና ቻንድራን ለመመልከቻ አሊያም ስፖርት መከታተያ አይደለም ዋናው ጭንቅ ስለምጣድና የእለት እንጀራ ማሰብ ግዴታ ነው። ስለኢንዱስትሪ መፈጠር ነጋ-ጠባ የምንወተውተው ካለኤሌትሪክ ግባት ከሆነ የታሪክ ምፀት ይሆናል! የትራንስፖት እጥረት፣ ያውም በክረምት፣ እሰቃቂ ሆኗል፡፡ ከጫፍ እስከጫፍ አንዳንዴም ሰልፍ ዞሮ የት ገባ እስከሚባል ድረስ እየተምዘገዘገ የሚሄደው ሰልፍ ከዕለት ዕለት እየረዘመ መምጣቱን ለማንም አለቃ መነገር ያለበት ጉዳይ አልሆነም፡፡ ፀሀይ የሞቀው ጉዳዳ ነውና፡፡ ይልቁንም ህዝብ ትዕግሥቱንና ልቦናውን ሰጥቶት በሥነ-ስርዓት ሰልፍ ገብቶ ራሱን ማስተናገዱና ቅጥ ስለ መፍጠሩ ሊመሰገን ይገባል ያም ሆኖ በየተቋማቱ ዘንድ አሁንም የአፈፃፀም ችግር የማይዘለል ችግር ነውና። የዘፈቀደ አሰራር ሥር ከሰደደ አድሮ ዕዳ ከሜዳ መሆኑ አይቀሬ ነው! ግምገማ ውሃ ወቀጣ እንዳይሆን እናስብበት!

Read 7602 times