Saturday, 30 July 2016 11:53

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ገድል - ክፍል 2

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(9 votes)

የመጀመርያው ምእራፍ 6 ኦሎምፒያዶች ከ1956 እስከ 1980 እኤአ
ፈረንሳዊው  ፒዬር ደኩበርቲን ባመነጩት ሃሳብ የመጀመርያው ኦሎምፒያድ በ1896 እኤአ ላይ በግሪኳ ከተማ አቴንስ ሲጀመር፤ ፋሽስት ጣሊያን በቅኝ አገዛዝ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ጦርነት አውጆ ነበር፡፡ በአድዋ መራሩን ሽንፈት ቀመሰ ፡፡ የአድዋ ድል  ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቁም በላይ ለመላው የጥቁር ህዝብ  ተምሳሌት ለመሆን የበቃ የታሪክ ክስተት ሆነ፡፡  በአብዛኛው በቅኝ ገዢዎች ስር ለነበረችው አፍሪካ የመጀመርያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ምንም አይነት ተጽእኖ ሊፈጥር ግን አልቻለም፡፡ የአድዋ ድል ከተመዘገበ 37 ዓመታት በኋላም በየአራት ዓመቱ ከ9 በላይ ኦሎምፒያዶች በተለያዩ የዓለም አገራት ሲካሄዱ  የአፍሪካ ተሳትፎ አልነበረም፡፡ የኦሎምፒክ ፈርቀዳጅ  ፒዬር ደኩበርቲን  በታላቁ የስፖርት መድረክ ሁሉንም  አህጉራት ለማሳተፍ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ  በሮም በተካሄደ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጉባኤ በቅኝ ገዢዎች ስር ለነበረችው የአፍሪካ ተሳትፎ በድጋሚ ሃሳብ ቢያቀርቡም ከአባል አገራት በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ በወቅቱ ይህንኑ የፒየር ደኩበርቲን ሃሳብ በመደገፍ በግብፅ አሌክሳንድሪያ የሚኖሩ ግሪካዊ ባለሃብት የኦሎምፒክ ስታድዬም ማሰርያ የገንዘብ ድጋፍ ቃል በመግባት ያደረጉት ጥረት ነበር፡፡  ግብፅ በሚገነባው ስታድዬም ኦሎምፒክን ለማስተናገድ ዝግጁነቷን ብታሳውቅም አውሮፓውያን በመቃወማቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡ ፒየር ደ ኩበርቲን ከግብፅ በኋላ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው አልጄርያም በተመሳሳይ ውድድሩን እንድታስተናግድ ሃሳብ አቅርበው  ሳይሆንላቸው ቀረ፡፡ አፍሪካን በኦሎምፒክ መድረክ ለማሳተፍ ከተጠቀሱት ሁለት ሙከራዎች አንድ ዓመት ካለፋቸው  በኋላ በወቅቱ ልዑል አልጋ ወራሽ የነበሩት ተፈሪ መኮንን በአውሮፓ  የስድስት ወራት ጉብኝት ነበራቸው፡፡ በ8ኛው ኦሎምፒያድ አዘጋጅ የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በፒየር ደኩበርቲን ግብዣ በእንግድነት ተገኝተው ነበር፡፡ ልዑል ተፈሪ በተፈጠረው አጋጣሚ የኢትዮጵያን ተሳትፎ በተመለከተ ውይይትም አድርገዋል፡፡ ያኔ አልጋ ወራሽ የነበሩት ተፈሪ መኮንን ከአውሮፓ ጉብኝታቸው ሲመለሱ የመጀመርያው ተግባራቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል እንድትሆንና በ1928 እኤአ በሆላንድ አምስተርዳም በሚካሄደው 9ኛው ኦሎምፒያድ እንድትሳተፍ ጥያቄ ነበር፡፡ በወቅቱ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የነበሩት  ቤልጅማዊው ሄነሪ ደባይላቱር ሲሆኑ፤ በዘውድ ስርዓት ትመራ የነበረችው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን እንኳንስ ለማስተናገድና ይቅርና ተሳትፎ ለማድረግ ብቃት የላቸውም በሚል አቋማቸው በመፅናት ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ከ13 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የስፖርት ኮንፌደሬሽን ቢመሰረትም በቀጣይ ስምንት ዓመታት በአገሪቱ ዘመናዊ   ስፖርት ያን ያህል ሳይስፋፋ በመቆየቱ በኦሎምፒክ ለመሳተፍ የሚደረጉ ጥረቶች አልነበሩም፡፡ በ1956 እኤአ ላይ የኦሎምፒክ ጨዋታዎቹን የምታስተናግደው የአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ስትሆን ኢትዮጵያ በዚህ ኦሎምፒክ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ በመወሰን መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ለመሆንና በኦሎምፒክ ለመሳተፍ በአምስት አለም አቀፍ የስፖርት ፌደሬሽኖች አባል መሆኗ በማረጋገጥ መስራት ያስፈልግ ነበር። ስለሆነም በስፖርት ኮንፌደሬሽኑ አማካኝነት የእግር ኳስ፤ የአትሌቲክስ፤ የቦክስ፤ የብስክሌት፤ እና የቅርጫት ኳስ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች አባል ለመሆን ማመልከቻ ገባ፡፡  ለኦሎምፒክ ተሳትፎ የተቀመጠውን መስፈርቶች ባታሟላም ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባልነቱን አፅድቆላት ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ1956 እኤአ ሜልቦርን ከተማ ባዘጋጀችው ኦሎምፒክ የመሳተፍ እድል አገኘች፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው የኦሎምፒክ ታሪክ ሃተታ ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ኦሎምፒክ ከተሳተፈችበት 17ኛው ኦሎምፒያድ  በሜልቦርን 1956 እኤአ  እስከ  22ኛው ኦሎምፒያድ በሞስኮ 1980 እኤአ ድረስ በዝርዝር የሚያወሳ ነው፡፡  ከ1956 እስከ 1980 እኤአ በተከታታይ በተካፈለችባቸው  6 ኦሎምፒያዶች በርካታ ፈርቀዳጅ ታሪኮች ተመዝግበዋል፡፡
በአምስቱ ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት ወንድ ኦሎምፒያኖች ብቻ ነበሩ፡፡ ሴት ኦሎምፒያኖች ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ የበቁት በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በ6ቱ ኦሎምፒያዶች የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡ ከአትሌቲክስ የረጅም ርቀት ውድድሮች ባሻገር በአጭር እና በመካከለኛ ርቀት አበረታች ተሳትፎ ነበር፣ በዝላይ፤ በጦር ውርወራ እና በርምጃ ውድድሮች ፈርቀዳጅ ተሳትፎዎችም ተደርገዋል፡፡  በብስክሌትና የቦክስ ስፖርት ውድድሮችም  ተከታታይ ተሳትፎዎች ነበሩ፡፡

-------------------------------------------------------------

                   የኢትዮጵያ የመጀመርያ ተሳትፎ በ17ኛው ኦሎምፒያድ

         አውስትራሊያ ፤ ሜልቦርን (1956 እኤአ)
በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን በሚገኘው ግዙፍ የክሪኬት ስታድዬም በተካሄደው 17ኛው ኦሎምፒያድ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ተሳትፋበታለች።   በሁለት የስፖርት ዓይነቶች አትሌቲክስ እና ብስክሌት 12 ኦሎምፒያኖች ተካፍለዋል፡፡ በአትሌቲክስ  በተለይ በአጭር እና መካከለኛ ርቀት ያተኮሩ ሲሆን ጠንካራው ተሳትፎ በማራቶንም ነበር፡፡
በ100 ሜትር፤ 200 ሜትር፤ በ4  በ100 ሜትር ፤ በ4 በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል እና በ800 ሜትር የተሳተፉት ኃይሉ አበበ፤ ለገሰ በየነ  ፤ ንጉሴ ሮባ ፤ ሃይሌ በቀለ እና በየነ አየነው፤ ነበሩ፡፡
 ሁሉም በማጣርያ ውድድሮች ተወዳድረው ለፍፃሜ ያልደረሱ ናቸው፡፡ በመካከለኛ ርቀት 1500 ሜትር  የመጀመርያ ኦሎምፒኩን የተካፈለው ወርቃማው ኦሎምፒያን ደግሞ ማሞ ወልዴ ሲሆን በማጣርያው 3 ደቂቃ ከ51.0 ሰከንዶች የሆነ ሰዓት ቢያስመዘግብም ለፍፃሜ ውድድር አልደረሰም፡፡ በማራቶን  የተሳተፉት  ሁለት ኦሎምፒያኖች   በ29ኛ ደረጃ የጨረሱት ባሻዬ ፈለቀ እና በ32ኛ ደረጃ የጨረሱት ገብሬ ብርቄ ናቸው፡፡
በኦሎምፒክ ብስክሌት ውድድሮች ደግሞ 4 ኦሎምፒያኖች በቡድን እና በግል ተሳትፈዋል፡፡  
ገረመው ደንቦባ፤ መስፍን ታዬ እና ዘሃዬ ባህታ በቡድን በነበራቸው ተሳትፎ በ99 ነጥብ በ9ኛ ደረጃ ለመጨረስ መቻላቸው  ከፍተኛ ውጤት ነበር፡፡  በግል ውድድር ገረመው ደንቦባ በ25ኛ ደረጃ፤ መስፍን ታዬ በ36ኛ ደረጃ፤ ዘሃዬ ባህታ በ38ኛ ደረጃ ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ንጉሴ መንግስቱ ቢሳተፍም ውድድሩን አቋርጦ ወጥቷል፡፡

---------------------------

              የአበበ ቢቂላ ፈርቀዳጅ የወርቅ ሜዳልያ በ18ኛው ኦሎምፒያድ
ጣሊያን፤ ሮም (1960 እኤአ)
በሮም ከተማ በሚገኘው ኦሎምፒክ ስታድዬም የተካሄደው ይህ ኦሎምፒክ ለመጀመርያ ጊዜ የቲቪ ስርጭት በሰሜን አሜሪካ ሊያገኝ የበቃ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ እና በብስክሌት  12 ኦሎምፒያኖች በ8 ውድድሮች አሳትፋበት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ በማራቶን ውድድር የመጀመርያው ወርቅ ሜዳልያ በአበበ ቢቂላ ተመዝግቦበታል፡፡ የአበበ ቢቂላ የወርቅ ሜዳልያ እና የዓለም ማራቶን ሪከርድ በማስመዝገብ፤ ለአገሩ እና ለአፍሪካ የመጀመርያው  ፈርቀዳጅ ውጤት ነው፡፡ በብስክሌት  በግልና በቡድን በተካሄዱ  ውድድሮች  ክፍሉ አላዛር፤ ገረመው ደንቦባ፤ አሙሴ ተሰማ እና መርጊያ አድማሱ የተሳተፉት ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ በ1 የወርቅ ሜዳልያ እና በ1 ሰባተኛ ደረጃ 10 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 18ኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው፡፡

------------------------------

                የአበበ ቢቂላ ዳግማዊ ድል በ19ኛው ኦሎምፒያድ  
ጃፓን፤ ቶኪዮ (1964 እኤአ)
በቶኪዮ ከተማ በሚገኘው ብሄራዊ  ስታድዬም በተካሄደው በዚህ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ   በ3 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ በብስክሌት እና ለመጀመርያ ጊዜ በቦክስ ስትሳተፍ በ12 ኦሎምፒያኖች ሲሆን  በ11 ውድድሮች ተካፋይ ሆነዋል፡፡
በማራቶን አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፀፈ፡፡ የዓለም ሪከርድን በማስመዝገብ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር  ሊያገኝ ችሏል፡፡ በሁለት  ኦሎምፒኮች በማራቶን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን አከታትሎ በመውሰድ  ብቸኛው ኦሎምፒያን ነው፡፡ በቦክስ ስፖርት ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ የተቻለበትም ነበር፡፡ በብስክሌት  በግል እና በቡድን ውድድሮች ለመካፈል የበቁት 4  ኦሎምፒያኖች ሚካኤል ሳጊምቤልኒ፤ ፍስሐ ፅዮን ገብረእየሱስ፤ ሱሌማን አምባዬ እና የማነ ነጋሲ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ በ1960 እኤአ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ  በ1 የወርቅ ሜዳልያ እና በ1 የአራተኛ  ደረጃ ውጤቶች 13 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 18ኛ ደረጃ ነበራት፡፡

--------------------------------

                          የማሞ ወልዴ ጀግንነት 20ኛው ኦሎምፒያድ
ሜክሲኮ፤ ሜክሲኮ ሲቲ (1968 እኤአ)    
በሜክሲኮ ከተማ በሚገኘው ግዙፉ የአዝቴካ ስታድዬም ሲካሄድ በ3 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ በብስክሌት እና በቦክስ በተካሄዱ 13 ውድድሮች 18 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ለመሰለፍ በቅተዋል፡፡
ትልቁን ውጤት  ያስመዘገበው ማሞ ወልዴ ነው፡፡ በረጅም ርቀት 10ሺ እና ማራቶን ውድድሮች ሁለት ሜዳልያዎች በማግኘቱ ነበር፡፡ በማራቶን ለራሱ የመጀመርያውን ለአገሩ ደግሞ በ3 ተከታታይ ኦሎምፒኮች 3ኛው የማራቶን ድል በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳልያውን ከመውሰዱም በላይ በ10ሺ ሜትር ደግሞ በታሪክ የመጀመርያውን የብር ሜዳልያ ክብር ማስመዝገብ  ችሏል፡፡ በቦክስ ስፖርት ለሁለተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ሲደረግ፤ በብስክሌት ለአራተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ መሳተፍ ተችሏል፡፡ በብስክሌት በግል እና በቡድን ማጣርያ ውድድሮች የተሳተፉት ኦሎምፒያኖች ተከስተ ወልዱ፤ የማነ ነጋሲ ፤ ማሃሪ እቁባሚካኤል እና ሚካኤል ሳጊምቤልኒ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በ1968 እኤአ በሜክሲኮ በተካሄደው ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ 1 የወርቅና 1 የብር ሜዳልያዎች እንዲሁም 3 ስድስተኛ ደረጃ እና 2 የስምንተኛ ደረጃ ውጤቶች በማስመዝገብ በ26 ነጥብ ከዓለም 13ኛ ደረጃ አግኝታ ጨርሳለች፡፡

---------------------------------------

                       የማሞ እና የምሩፅ ነሓሶች በ21ኛው ኦሎምፒያድ
በፌደራል ሪፖብሊክ ጀርመን ፤ ሙኒክ (1972 እኤአ)
በሙኒክ  ከተማ በሚገኘው የኦሎምፒክ ስታድዬም የተካሄደ ሲሆን በ3 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ በብስክሌት እና በቦክስ 31 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች 20 ውድድሮችን አድርገዋል፡፡ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን ያስመዘገቡት ደግሞ በማራቶን  ማሞ ወልዴ እና በ10ሺ ሜትር ምሩፅ ይፍጠር ነበሩ፡፡
በዚህ ኦሎምፒክ ከማራቶን እና 10ሺ ሜትርተሳትፎ ባሻገር በአጭር ርቀት እና በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች በነበረው ተሳትፎ ካለፉት ኦሎምፒያዶች የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በ100 ሜትር ማጣርያ እግዚ ገብሬ በ10.89 ሰከንዶች ሲሳተፍ፤ በ800 ሜትር ሙሉጌታ ከበደ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ሽብሩ ረጋሳ ደግሞ በማጣርያ መሳተፍ ችለዋል፡፡ በ4 በ100 ሜትር የዱላ ቅብብል ሲሳይ ፈለቀ፤ ሰለሞን በላይ ከበደ በዳሶ እና እግዚ ገብሬ ቢሳተፉም ውድድሩን አልጨረሱም፡፡ በ1500 ሜትር ሃይሉ ኤባ እና ሽብሩ ረጋሳ እስከ ግማሽ ፍፃሜ የተወዳደሩ ሲሆን፤በ5000 ሜትር አሁን አሰልጣኝ የሆኑት እና ኦሎምፒያኖችን ውጤታማ ማድረግ የቻሉት ቶሎሳ ቆቱ በማጣርያ ተወዳድረዋል፡፡
በቦክስ ስፖርት በተከታታይ በ3 ኦሎምፒኮች በመሳተፍ  በ54 ኪ ግ የቀላል ሚዛን መሃመድ አየለ በኮርያ ቦክሰኛ ፤ በ65 ኪግ ደግሞ ፈቃዱ ገብረስላሴ በጃፓን ቦክሰኛ በመጀመርያ ዙር ተሸንፈው ከውድድር ውጭ ሆነዋል፡፡ በብስክሌት  በቡድን የማጣርያ እና በግል ዋና ውድድሮች 4 የቦክስ ኦሎምፒያኖች ተሳትፈዋል፡፡ በግል ጥሩ ውጤት ያስመዘገበው በ53ኛ ደረጃ የጨረሰው ተከስተ ወልዱ ሲሆን ፍስሃ ፅዮን ገብረእየሱስ፤ ርእሶም ገብረመስቀል እና ሱሌማን አብዱልራህማን ቢሳተፉም አልጨረሱም፡፡
በፌደራል ሪፖብሊክ ኦፍ ጀርመን በ1972 እኤአ በተከናወነው የሙኒክ ኦሎምፒክ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በ2 የነሐስ ሜዳልያዎች 12 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 18ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች፡፡

------------------------

                የምሩፅ ይፍጠር ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በ22ኛው ኦሎምፒያድ
ሶቪዬት ህበረት፤ ሞስኮ (1980 እኤአ)
በሞስኮ ከተማ በሚገኘው ግዙፉ የሌኒን ስታድዬም የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ   በ1976 በካናዳ ሞንትሪያል የተካሄደውን ኦሎምፒያድ ሳትሳተፍ ከቀረች በኋላ ወደ ኦሎምፒክ መድረክ የተመለሰችበት ነው፡፡ በኦሎምፒያኖች ከፍተኛ ብዛት፤ በሴት ኦሎምፒያኖች የመጀመርያ ተሳትፎ እንዲሁም በተገኙት ሜዳልያዎች ብዛት ካለፉት የተሻለ ነበር፡፡ በ3 የስፖርት አይነቶች 41 ኦሎምፒያኖች 39 ወንድ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ሴት ኦሎምፒያኖችን በማካተት በ26 ውድድሮች ተካፍለዋል፡፡ በተለይ በረጅም ፤ በሱሉስ ዝላይ እንዲሁም በጦር ውርወራ ውድድሮች ለመሳተፍ መቻሉም ይጠቀሳል፡፡
ከፍተኛውን ውጤት ለማመዝገብ የበቃው በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አግኝቶ የነበረው ምሩፅ ይፍጠር ሲሆን በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ አዲስ ታሪክ ሊሰራ ችሏል፡፡
በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን ምሩፅ ሲወስድ ሁለት የማጣርያ ውድድሮችን አድርገው በፍፃሜው አብረው የሮጡት መሃመድ ከድር እና  ዮሃንስ መሃመድ በ3ኛ እና በ10ኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ደግሞ ማጣርያ አልፈው መሃመድ ከድር በነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም ቶሎሳ ቆቱ በ7ኛ ደረጃ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አገሩ ተሳትፎ ባደረገችበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር እሸቱ ቱራ የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ፈርቀዳጅ ውጤት ሲያስመዘግብ በተመሳሳይ ውድድርሃይሉ ወልደፃዲቅ እና ግርማ ወልደሃና ተሳትፎ ቢያደርጉም ውድድሩን አልጨረሱም፡፡
በወንዶች ማራቶን  ከተሳተፉት  ኦሎምፒያኖች ደረጀ ነዲ በ7ኛ ደረጃ እንዲሁም መላኩ ደዱብጄ በ24ኛ ደረጃ ሲጨርሱ ከበደ ባልቻ ውድድሩን አልጨረሰም፡፡ በ100 ሜትር በሻ ቱፋ  በሁለት ፤ በ800 ሜትር አበበ ዘሪሁን፤ ንጉሴ በቀለ እና አጥሬ በዛብህ፤ በ1500 ሜትር ባልቻ ካሳ፤ ሃይሌ ዘሩ እና ንጉሴ በቀለ የማጣርያ ውድድሮች ተሳትፈዋል፡፡ በ4 በ400 ሜትር የዱላ ቅብብል የተሳተፉት አራት ኦሎምፒያኖች በሻ ቱፋ፣ ኩመላ ፉቱማ፣ አስፋው ደበሌ እና አጥሬ በዛብህ ውድድራቸውን አልጨረሱም፡፡
በወንዶች የረጅም ዝላይ 6.66 ሜትር በማጣርያው በመዝለል የተሳተፈው አበበ ገሰሰ ሲሆን፤ በሱሉስ ዝላይ ደግሞ ያደሳ ኩማ በማጣርያው 13.60 ሜትር በመዝለል ተሳትፏል፡፡ በጦር ውርወራ ሚሊኬሳ ቻልቺሳ በማጣርያው 51.04 ሜትር በመወርወር 18ኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን በ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር ደግሞ ተከስተ ምትኩ በፍፃሜው ውድድር በመካፈል 23ኛ ደረጃ አስመዝግቧል፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ በሴት ኦሎምፒያኖች ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው የመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር እና 1500 ሜትር የአትሌቲክስ ውድድሮች  ነበሩ፡፡ በ800 ሜትር ፋንታዬ ሲራክ እንዲሁም በ1500 ሜትር ደግሞ አምሳለ ወልደገብሬል ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ ለመወከል የበቁ ኦሎምፒያኖች ሲሆኑ ተሳትፏቸው በማጣርያ ውድድሮች የተወሰነ ነበር፡፡
በቦክስ ስፖርት 4ኛው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ሲደረግ በ48 ኪሎ ግራም ብሩክ አስፋው በመጀመርያው ዙር በፊንላንድ ቦክሰኛ ሲሸነፍ፤ በ51 ኪሎ ግራም ሃሰን ሸሪፍ በመጀመርያ ዙር የጊኒን ቦክሰኛ በማሸነፍ ሁለተኛው ዙር ገብቶ በቡልጋርያው ቦክሰኛ ተሸንፏል፡፡ በ54 ኪሎግራም ደግሞ  አየለ ማሀመድ የመጀመርያ ማጣርያውን በፎርፌ ካለፈ በኋላ በሁለተኛ ማጣርያ የአፍጋኒስታን ቦክሰኛን አሸንፎ በሶስተኛው ማጣርያ በኩባ ቦክሰኛ ተሸንፏል፡፡ በ57 ኪሎግራም የመጀመርያ ማጣርያውን በፎርፌ ካለፈ በኋላ በሁለተኛ ማጣርያ የሲሸልስ ቦክሰኛን አሸንፎ በሶስተኛው ማጣርያ በብራዚል ቦክሰኛ ተሸንፏል፡፡ በ60 ኪግ ታደሰ ኃይሌ፤ በ63.5 ኪግ ኢብራሂም ሴዲ በሮማኒያ እና በፖርተሪኮ ቦክሰኞች በመጀመርያ ማጣርያ ተሸንፈው ከውድድር ውጭ ሆነዋል፡፡
በብስክሌት የተሳተፉት 8 ኦሎምፒያኖች ሲሆኑ በግል ውድድር ዘርጋበር ገብረህይወት፤ ጀማል ሮጎራ፤ ጥላሁን ወልደሰንበት እና ሙሴ ዮሃንስ ሲሆን በቡድን የማጣርያ ውድድር ደግሞ ሃይለሚካኤል ከድር፤ አየለ መኮንን፤ ታደሰ መኮንን እና ጥላሁን አለማየሁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በአጠቃላይ በ2 የወርቅ፤ 2 የነሐስ ሜዳልያዎች እና በ1 አራተኛ እና በ1 የሰባተኛ ደረጃ ውጤቶች 35 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 8ኛ ደረጃ አግኝታ ጨርሳለች፡፡
ይቀጥላል…..

Read 4792 times