Saturday, 30 July 2016 11:35

የዘመኑ ‘ብልጥነት’ ግራ ሲያጋባ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው የልብ ጓደኛው የሆነው አባወራ በሌለበት ሹክክ ብሎ ቤቱ ይመጣና ከሚስትየዋ ጋር እነሆ በረከት ሲባባል ያመሻል፡፡ ከዛም አረፍ ብለው ለ‘ሩብ ፍጻሜ’ ትንፋሽ ሲሰበስቡ ሳሎን ቤት ስልክ ይደወላል፡፡ ሚስትየው ትሄድና አነጋግራ ትመለሳለች፡፡ ይሄኔ ሰውየው…
“ማን ነው የደወለው?” ይላታል፡፡ እሷም…
“ባለቤቴ ነው…” ስትል ትመልስለታለች፡፡ እሱም ይደነግጣል፡፡
“ብሄድ ይሻላል፡፡ ደርሻለሁ አለ እንዴ?” ይላታል። እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ይልቅ አርፈህ ተኛ፡፡ የት እንደሆነ ስጠይቅው፣ አንተ ቤት ከአንተ ጋር ካርታ እየተጫወታችሁ እንደሆነ ነው የነገረኝ…” ብላው አረፈች፡፡
ባል ሆዬ፤ በእሱ ቤት ‘ብልጥ መሆኑ ነበር፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የ‘ብልጥነት’ ትርጉም መዝገበ ቃላቱ ላይ ተለውጧል እንዴ?! በጣም ግራ ገባና! ማጭበርበሩም፣ ውስልትናውም፣ ክፋቱም…የሚጠሩት በእውነተኛ መገለጫቸው ሳይሆን በብልጥነት ሆኗላ!
“ስማ እንትናን ታውቀዋለህ!”
“በደንብ ነዋ… ምነው ምን ሆነ? ወደ ጆሀንስበርግ በእግሩ ሲያቀጥን ታንዛንያ ውስጥ ተያዘ እንዳትለኝ!”
“እንደውም…ከሆኑ ገንዘብ እስከ አፍንጫቸው ካላቸው ሰዎች ጋር የሆነ ቢዝነስ ይገባልህና፣ ሸውዷቸው ሁለት ነው ሦስት መቶ ሺህ ብር እንዴት ይዞ እንደወጣ ሰምቼ ገርሞኝ ልሞት…”
“ምን ይገርማል…?”
አያችሁልኝ አይደል…አታላይ ነው፣ አጭበርባሪ ነው ምናምን ሳይሆን ‘እሱ እኮ ድሮም ቢሆን ብልጥ ነው’ ነው የሚባለው፡፡
(እግረ መንገዴን በዚህ በአዲሱ ጣቢያ በአማርኛ የምንከታተላቸው ፊልሞች ላይ ትልቁም ትንሹም የሚጠቀምባት ቃል አለች… መሸወድ የሚሏት፡፡ አሀ… ‘ሸወደኝ፣’ ‘ሊሸውደኝ ነው፣’ ምናምን አይነት አባባሎች ወጣቶቹ አካባቢ ይዘወተሩ እንደሁ እንጂ እነ ‘አጎቴ ታየር’ ሳይቀሩ ሲጠቀሙባቸው… አለ አይደል… ትንሽ ለጆሮ አይመችም፡፡ ሌሎችም አልፎ፣ አልፎ እንዲህ አይነት ከገጸ ባህሪያቱ ጋር የማይሄዱ ነገሮች ስላሉ ቃላት ላይ ጥንቃቄ ቢጤ ቢጨመር መልካም ነው፡፡)
እናላችሁ… እኛ ይመስለን የነበረው… አለ አይደል… “እሱ እኮ ብልጥ ነው…” ምናምን ሲባል በቀላሉ የማይታለል፣ የማይጭበረበር፣ ሊያታልሉት ከሞከሩም “ሂድና የግሪክ ቱሪስት ብላ...” ብሎ ኩም የሚያደርግ አይነት ይመስለን ነበር፡፡ ባልሆነ መንገድ ‘ላም አለኝ በሰማይ’ ተስፋ ሊሞሉት ሲሞክሩ፣ መዳቡን “ወርቅ ነው…” ብለው ሊያሞኙት ሲሞክሩ… የወደቀውን “ተሰበረ እኮ…” ብለው ሊያስቀይሱት ሲሞክሩ…አለ አይደል… “እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል…” ብሎ ራሱን የሚያድን ይመስለን ነበር፡፡
እናላችሁ…ብልጥነትና ‘አራድነት’ የሚሏቸው ነገሮች ትርጉማቸው ከተጨባጭ ሁኔታው ጋር አብረው የሚተጣጠፉ አይነት ነገር እየሆኑ ግራ ገብቶናል፡፡
በአንድ ኮሌጅ አዲስ የገቡ ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ስለ ግቢው ህጎች ገለጻ እየተደረገላቸው ነበር፡፡ የተማሪዎች ዲንም ንግግር ያደርጋል፡-
“ወንድ ተማሪዎች ወደ ሴቶች ማደሪያ አካባቢ ዝር ማለት አይችሉም፡፡ ይህንን ህግ የሚጥስ ማንኛውም ተማሪ ሀያ ዶላር ይቀጣል፣” ይላል፡፡ ቀጠለናም…
“ይህን ህግ ለሁለተኛ ጊዜ የጣሰ ስድሳ ዶላር ይቀጣል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ የጣሰ ደግሞ መቶ ሰማንያ ዶላር ይቀጣል፡፡ ጥያቄ ያለው አለ?” ይላቸዋል፡፡
ይሄኔ አንድ የሀብታም ልጅ ይነሳና ምን ብሎ ቢጠይቅ ጥሩ ነው… “ለአንድ ዓመት በተከታታይ የሚጥስ ምን ያህል ይቀጣል?”
ሁሉም እንደየኪሱ ነዋ! ልክ የዓመት የስታዲየም መግቢያ ትኬት እንደ መግዛት ማለት እኮ ነው። ቂ…ቂ…ቂ… (እኔ የምለው…ይሄ የየስታዲየሙ ብጥብጥና ክትክት፣ ነገርዬው የኳስ ብቻ ነገር ነው እንዴ! አይ…ለየትኛው ኳሳችን ነው ‘ደም እንዲህ የሚፈላው?” ብለን ነዋ!)
እናማ…በእኛ ዩኒቨርሲቲዎች ህግ ጥሶ ወደ ሴቶች ማደሪያ የሚሄደው የሚቀጣው ግልጽ ይሁንልን፡፡ ልክ ነዋ...ይሄኔ “ግፋ ቢል ሺህ፡ ምናምን ሺህ ክፈል” ሊባል ነው፡፡ ይሄኔ ደግሞ “ገንዘቤን ይጭነቀው…” የሚል መአት ይኖራላ!
በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን አካባቢ የሚሰማው አንዳንድ ነገር ደስ አይልም፡፡ ደስ አይልም ብቻ ሳይሆን…የነገዎቹ እናቶችና አባቶች ወላጅነቱን እንዴት ሊችሉት ነው ብሎ የሚያስጨንቅ ነው፡፡ ዘላለማቸውን በቤታቸው ተቆልፈው የቆዩ ለጋ ወጣቶች በድንገት ከትውልድ አካባቢያቸውና ከለመዱበት ብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ርቀው ሲሄዱ፣ አጅሬ ዲያብሎስ እግር በእግር እየተከተለ አባል መሆናቸውን እንኳን ሳያውቁ እየመለመላቸው አይነት ነዋ!
እናላችሁ…በስመ ብልጥነት…አለ አይደል…ቆቡን የጣለ ቄስ አይነት የሚያደርገው ሞልቷል፡፡ (ቆቡን የጣለ ቄስ አያድርስባችሁ!)
“ስማ… እሷ ሴትዮ እኮ የከተማውን ወንድ ሁሉ አንገላጀጀችው፡፡” (ራሷን እንደ ‘ናሙና’ አደረገች ለማለት ያህል! ቂ…ቂ…ቂ…)
”ድሮስ አጅሪት አታውቃትም እንዴ! ጓንታናሞ ቢቆልፉባት ይሄ በሬ የዋጠ የሚያካክለውን ማሪን ሁሉ አንከርፍፋ ትወጣ ነበር፡፡ በጣም ብልጥ ነች…”
እናማ…እንዲህ ነው…ነገርየው “ሱሪ ከወረወሩባት አለቀላት ማለት ነው…” ምናምን ሳይሆን “በጣም ብልጥ ነች…” ነው፡፡ በዚሀ አይነት የብልጥነት ትንታኔ ከሆነ፣ አዲስ አበባ ባሏት ‘ብልጦች’ ቁጥር ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ሁለተኛ ምናምን የምንወጣ አይመስላችሁም!
ለምሳሌ የሆነ ቡድን ውስጥ ተከላካይ አለ እንበል፡፡ እናላችሁ ስለ እሱ ሲወራ ምን ይባላል… “እንዴት አይነት ብልጥ መሰለህ! ኳሷ ካለፈችው እኮ ከእነእግሩ አንስቶ ያፈርጠዋል እንጂ የፈለገ ሜሲ፣ ሮናልዶ የምትላቸው እንኳን አያልፉትም፡፡”
‘ብልጥ’ ስለሆነ እግርና ኳስን አንድ ላይ ያጭዳላ!
ደግሞላችሁ…አሁን፣ አሁን በአብዛኛው የአዲስ አበባ መንገዶች እጅን ኪስ ከቶ ‘ዎክ’ እያደረጉ ነፋስ ልቀበል ብሎ ነገር የለም፡፡ መንገዱ ሁሉ ‘በአራዶች’ ተሞልቷላ! ቂ…ቂ…ቂ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሸገር በህዝብ ብዛት ጫፍ ከሆኑት ከተሞች አንዷ ሳትሆን አትቀርም፡፡
ጥያቄ አለን…በግራና በቀኝ ከተማዋን ሁሉ እያፈራረሷት… አለ አይደል…
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ፣
የሚለውን ግጥም ምን እናድርገው? ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ እያለፈበት ነዋ!
እናማ…‘ብልጥነት’ ራስን በሌላ ከመሞኘትና ከመጠቃት ማዳን መሆኑ ቀርቶ… አለ አይደል… ሌላውን ማሞኘት፣ ሌላውን ማታለል፣ ሌላውን መቀማት…በሆነበት ዘመን ‘የሚናፈቅ ነገር’ ይኖራል።
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺ ጉዷን ዘርዝረን የማንጨርሳት አዲስ አበባ ‘ሰለጠነች’፣ ‘ዓለምን ልትስተካከል ነው’...ምናምን ይባል የለ…ድሮም እኮ እንዲህ ይባል ነበር፡፡ በ1958 የወጣ መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን  ግጥም እዩልኝማ፡-
ፓሪስ ሄዳ ነበር ወይንስ ለንደን
ከየት አመጣችው ይህን መሽሞንሞን
ከፓሪስ ከለንደን ልትወዳደር
ጀምራለች ይኸው ልትሽቀረቀር
የአፍሪካን መሪዎች የአውሮፓን ጭምር
ቤት ማያ እየጠራች ከአራቱም አህጉር
ታስተናግዳለች በተሟላ ክብር
ይህ እንግዲህ ከአርባ ስምንት ዓመት ገደማ በፊት ይባል የነበረ ነው፡፡ አንዳንድ ነገር ቃላት አሰካኩ ይለዋወጣል እንጂ ዜማው ያው ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
‘ብልጥ’ መሆንን አሁን ከሚሰጡት የተሳሳቱ ትርጓሜዎች አውጥተን ትክክለኛ ትርጉሙን ካልሰጠነው በስተቀር፣ የዘመኑ ‘ብልጥነት’ ብልህነት እየመሰለ… ‘በዓለም የመጀመሪያዋ በ‘ብልጦች’ የተሞላች አገር እንዳንባል ፍሩልኝማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 3051 times