Saturday, 30 July 2016 11:17

መንግስት ቤት ለፈረሰባቸው ተለዋጭ ቤት መስጠት አለበት - የህግ ባለሙያዎች

Written by 
Rate this item
(20 votes)

“በወረዳ አመራሮች የሚሰሩ ስህተቶች መንግስትን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው ነው”

   መንግስት ‹‹ህገ ወጥ›› ያላቸውን ቤቶች ያፈረሠበት መንገድ በአለማቀፍ የሠብአዊ መብቶች ድንጋጌና በህግ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹ የህግ ባለሙያዎች፤ድርጊቱ የህግ ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል ተናገሩ፡፡ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ዜጎች፣መንግስት ተለዋጭ ቤት መስጠት አለበትም ብለዋል - የህግ ባለሙያዎቹ፡፡  
ዓለማቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት፤ማንኛውም ሰው ደህንነቱ እንዲጠበቅና መኖሪያ ቤቱ እንዲከበር በፅኑ ይደነግጋል ያሉት አለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ወ/ማርያም፤በተለያዩ የሠብዓዊ መብት ስምምነቶች፣ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በዋናነት ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡   
‹‹ሠዎች ህገ-ወጥ ቤት ቢሠሩ እንኳን ቤቶቹ ሲሠሩ በዝምታ የታለፉ እንደመሆናቸው በድጋሚ አይፈርሱም›› ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ‹‹በተለያዩ ሃገራት በህገ ወጥ መንገድ ቤት የሠሩ ሰዎች ካሳ ከፍለው ቤቱ ህጋዊ ይሆንላቸዋል” ሲሉ የሌሎች አገራትን ተመክሮ ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ያፈረሳቸው ቤቶች አፈራረስም የኢትዮጵያንም ሆነ ዓለማቀፍ የሠብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የጣሰና ዜጎችን ያለ አግባብ ለእንግልት የዳረገ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ የግድ ማፍረስ አለብኝ ካለም በቅድሚያ ቤት ሊያዘጋጅላቸው ወይም ቤት ሊያሰራቸው የሚችል ተመጣጣኝ ካሣ መክፈል ነበረበት፤ይህን አለማድረጉ በሠብአዊ መብት ጥሰት ሊያስጠይቀው ይችላል›› ብለዋል፡፡
“አስተዳደሩ ቤቶቹ ሲሠሩ እያየ ዝም ካለ፣የቤቶቹን መሰራት እንደፈቀደ ይቆጠራል” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ነዋሪዎች መብራትና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን ሲያሟሉ በዝምታ ማለፉ ብቻውን ቤቶቹን ህጋዊ ያደርጋቸዋል ሲሉም ይሞግታሉ፡፡ ቤቶቹ መፍረስ አይገባቸውም ነበር፤ ስለዚህ አስተዳደሩ የፈፀመው ህገ-ወጥ ድርጊት ነው” ብለዋል፡፡
ይህን የአስተዳደሩን ድርጊት ማረም የሚቻለው መንግስት ለተጎጂዎቹ በቂ ካሳ ሲከፍልና ቤት ሰርቶ ሲሰጣቸው ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤‹‹ወቅቱን ባላገናዘበ መልኩ ቤቶችን በጅምላ አፍርሶ ዜጎችን ሜዳ ላይ መጣል አለማቀፍ የሠብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ፈፅሞ የተቃረነ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ነው” ብለዋል፡፡ ቤቶቹን በማፍረስ ተግባር ላይ የተሣተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ባለስልጣናትም በግላቸው በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ዶ/ር ያዕቆብ ይናገራሉ፡፡
የህግ መምህርና ባለሙያ አቶ ቁምላቸው ዳኜ በበኩላቸው፤የመጠለያ ጉዳይ በአለማቀፍ የሠብአዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ በህይወት ከመኖር መብት ጋር ተያይዞ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፣መጠለያን በዚህ መልኩ ማሳጣት የሠብዓዊ መብት ክብርን የመግፈፍ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ አለማቀፉ የሠብአዊ መብት ድንጋጌ፣ የመንግስት በሲቪል መብቶች ላይ ጣልቃ መግባትን እንደሚከለክል የጠቀሱት ባለሙያው፤መንግስት ቤቶቹን ያፈረሠበት መንገድም በዚህ የህግ ጥሰት የሚታይ ነው ሲሉ አሰረድተዋል፡፡
መንግስት ለዜጎች መጠለያ ማቅረብ ካልቻለ ለራሳቸው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለበት የጠቀሱት የህግ ባለሙያው፤ለዚህ አንደኛው መፍትሄ ቤቶቹን ከማፍረስ ይልቅ ወደ ህጋዊ መስመር የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት ነበር ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ሲገነቡ መጀመሪያ ማስቆም ይገባ ነበር ያሉት የህግ ባለሙያው፤ቤቶቹ ከተገነቡ በኋላና ዜጎች በተለያየ መንገድ ህጋዊነት እንዲሰማቸው ከተደረገ በኋላ ማፍረሱ የሠብአዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ መብራት ያስገቡበት፣ ሌሎች የልማት መዋጮዎችን ያወራረዱበት ሰነድ ካላቸውና ወረዳው እያወቀ መሰረተ ልማቶችን ያሟሉ ከሆነ፣ በከፊል ህጋዊ እንደሆኑ ይቆጠራል ያሉት ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ባለሙያ፤ መንግስት ከዚህ አንፃር መሰረታዊ ስህተቶች መሰራታቸውን አምኖ፣ለተጎጂዎች ተገቢውን ካሳና መጠለያ ሊያቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ ህገወጥ ናቸው ከተባሉም ግልፅ አማራጮች ተቀምጠው፣በቀጥታ የሚያርፉበት ምትክ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸው፣ፍትሃዊ በሆነ ሂደት ተዳኝተው፣ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ሲገኝ ብቻ ነው ቤቶች ሊፈርሱ የሚገባው ሲሉ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ “በቂ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን ነው ቤታችን እንዲፈርስ የተደረገው” የሚለው የዜጎች አቤቱታም ከህግ አንፃር መንግስትን ሊያስጠይቀው ይችላል ብለዋል፤የህግ ባለሙያው፡፡
 የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤መንግስት ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት ደጋግሞ ማሰብና የተለያዩ አማራጮችን ማስቀመጥ ይገባው ነበር ይላሉ፡፡ ህዝቡ መኖሪያ ቤት የሚያገኝበትን መንገድ መንግስት በሚገባ ማሰብ አለበት የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “ሰዎቹ ከገበሬ ላይ ቦታ ገዝተው ቤት ሰርተው የሚኖሩ ከሆነ፣መጠነኛም ቢሆን ገንዘብ ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ፣መንግስት ራሱ ዲዛይን አውጥቶላቸው በህጋዊ መንገድ በማህበር ተደራጅተው ኮንዶሚኒየም እንዲሰሩ ቢያደርግ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል” ብለዋል፡፡  
“ፈረሱ የተባሉት ቤቶች መሰረተ ልማት እስኪሟላላቸው ድረስ ወረዳና ክ/ከተማ ያሉ የመንግስት አካላት የት ነበሩ?” ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤“በወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች የሚሰሩ ስህተቶች መንግስትን በከፍተኛ መጠን ዋጋ እያስከፈለው ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት በወረዳ ደረጃ በአመራርነት መመደብ ያለበት ብቃት ያላቸውን ሰዎች ሊሆን ይገባል የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤እነዚህ የፈረሱ ቤቶች ይሄን ያህል አመት የቆዩት በተለያየ መንገድ የወረዳ አመራሮች ቢፈቅዱላቸው ነው፤በቤቶቹ ግንባታ ላይ የወረዳ አመራሮች እጅ አለበት ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ሌሎች አማራጮች በስፋት ሊታዩ ይገባ ነበር ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤በቀጣይም ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ቤት ማግኘት መቻል አለባቸው፤መንግስትም መፍትሄ ያገኝለታል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡



Read 3910 times