Saturday, 30 July 2016 11:15

በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞና ግጭት አገርሽቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(27 votes)

- “አውዳሚ የሆኑ ኃይሎች የፈጠሩት እንጂ የህዝብ ተቃውሞ አይደለም”
- “የተደራጀ ጥያቄ ስላልቀረበ በጎንደር ሠላማዊ ሰልፍ አይኖርም” የክልሉ መንግስት

   በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተቃውሞ አገርሽቶ፣ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች አይለው መሰንበታቸው የተጠቆመ ሲሆን መንግስት የማረጋጋት ስራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በክልሉ አርሲ ዞን ዶዶላ፣ አሣሣ፣ በቆናጂ ከተሞች፣ በምዕራብ ሃረርጌ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ አካባቢ ነዋሪዎች ካለፈው ሠኞ ጀምሮ ወደ የከተሞቹ የሚያስገቡ መንገዶችን በድንጋይ በመዘጋጋት ተቃውሞአቸውን ሲገልፁ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከአርሲ ወደ ባሌ የሚሄደው ዋናው መንገድም እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ተዘግቶ እንደነበር ምንጮች ለአዲስ አድማስ የጠቆሙ ሲሆን በተቃውሞው ላይ የክልሉን መንግስት የሚያወግዙ መፈክሮች መስተጋባታቸው ታውቋል፡፡ የፀጥታ ሐይሎች ተቃውሞውን ለማብረድ በአብዛኛው የአስለቃሽ ጭስ ሲጠቀሙ እንደነበር የገለፁት ነዋሪነታቸው በአርሲ ዶዶላ የሆነ ምንጮች፤ በፀጥታ ሃይሎችና በተቃዋሚዎች መካከል የከፋ ግጭት አለመከሰቱን ጠቁመዋል፡፡
ከሠሞኑ በተጠቀሱት አካባቢዎች ችግሮችን መፈጠራቸውን ያረጋገጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መሃመድ ሰዒድ፤ “በየአካባቢዎቹ ተደራጅተው አውዳሚ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሃይሎች የፈጠሩት ችግር እንጂ የህዝብ ተቃውሞ አይደለም” ብለዋል፡፡
የተቃዋሚዎቹ እንቅስቃሴ ወንጀል ነክ መሆኑን ያብራሩት ሃላፊው፤ የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራል መንግስት በትዕግስት የሚያልፉት ሳይሆን ችግሩን ከምንጩ የሚያጠሩበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡ በባለፈው ተቃውሞ ህዝብ ያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ መንግስት በህዝቡ ጋር በመወያየት፣ ችግሮችን ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተጀመረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መሃመድ፤ ተደራጅተው የህዝብን ሠላማዊ እንቅስቃሴ የሚያወኩትን መንግስት በትዕግስት አይመለከትም ብለዋል፡፡
ባለፉት ሣምንታት በየአካባቢው ተከስተው የነበሩ ችግሮች መርገባቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በወንጀል እንቅስቃሴዎች ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጎንደር ከተማ ነገ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ሊሳተፍበት ይችላል የተባለ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ጥሪ የተላለፈ ቢሆንም፣ የክልሉ መንግስት ለሠልፉ እውቅና አልሠጠሁም ብሏል፡፡
በአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው የተባለውን ይህን ሠልፍ በተመለከተ የተጠየቁት የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ የሠላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ህጋዊ መስፈርቶችን አሟልቶ የቀረበ የእውቅና ጥያቄ እንደሌለ ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ባደረገው ውይይት፣ ሰልፍ የማድረግ ፍላጎት እንደሌለ በመረጋገጡ በነገው ዕለት ምንም አይነት ሰልፍ አይኖርም ብለዋል፡፡



Read 7978 times