Saturday, 30 July 2016 11:15

750 ታክሲዎች አገልግሎት መስጠት ሊጀምሩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

በኪ.ሜ የሚያስከፍሉ ናቸው ተብሏል

    በአዲስ አበባ በኪሎ ሜትር የሚያስከፍሉ 750 ታክሲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተገለጸ፡፡ መንግስት በትናንሽ ታክሲዎች አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ባለንብረቶች፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ፣ከ800 በላይ የሆኑ ግለሠቦች በጋራ በመደራጀት፣የተሽከርካሪዎቹን ግዢ ከቻይናው ሊፋን ሞተርስ ጋር መፈጸማቸውን ተወካዮቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
እያንዳንዳቸው 4 ተሣፋሪዎችን የመጫን አቅም ያላቸው ሊፋን 530 የተሠኙ 750 ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ወደ ሃገር ውስጥ በመግባት ላይ መሆናቸውን የገለፁት ተወካዮቹ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በመላዋ አዲስ አበባ መንግስት በሚያወጣውና በሚቆጣጠረው ታሪፍ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል፡፡
አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል በዘመናዊ ማዕከል የተደራጀና የእያንዳንዱን ተሽከርካሪ የጉዞ ደህንነት የሚያረጋግጥ አክሲዮን ማህበር መቋቋሙን የገለፁት ተወካዮቹ፤ተሽከርካሪዎቹ  ኢንሹራንስ የተገባላቸው በመሆኑ ለተሣፋሪዎች ዋስትና ይሰጣሉ ብለዋል፡፡
ተሽከርካሪዎቹ ዘመኑ የደረሰበትን የታክሲ አገልግሎት እንዲሠጡ ተደርገው የተዘጋጁ መሆኑን ያስረዱት ተወካዮቹ፤መንግስት በሚያወጣው ታሪፍ በኪሎ ሜትር ከማስከፈላቸውም በላይ ጂፒ ኤስ የተገጠመላቸው በመሆኑ በተሽከርካሪዎቹ አገልግሎት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የታክሲ አገልግሎት የሚፈልግ ተጠቃሚ፣ አገልግሎቱ ሲጀምር ይፋ በሚሆነው አጭር የስልክ መስመር በመደወል ጥሪ ማድረግ የሚችል ሲሆን በአገልግሎት ወቅትም እክል ከገጠመው ለኩባንያው ደውሎ ማሳወቅ ይችላል ተብሏል፡፡ ታክሲዎቹ አገልግሎት የሚሰጡት ለቱሪስቶች ብቻ ሳይሆን ለከተማዋ ነዋሪዎችም በርካሽ ዋጋ አገልግሎት እንደሚሰጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለታክሲዎቹ ግዢ 70 በመቶውን ብድር ያመቻቸው፣ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ መሆኑን ተወካዮቹ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡  

Read 5931 times