Monday, 25 July 2016 09:52

“ኢክላምፕሲያ... ከደም ግፊት ያለፈ ነው”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(8 votes)

በአለም ላይ የእናቶች ሞት ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ተመዝግበው ይገኛሉ።
ከፍተኛ የሆነ መድማት በተለይም ከወሊድ በሁዋላ
ኢንፌክሽን ከወሊድ በሁዋላ
የደም ግፊት ተብሎ የሚታወቅ የጤና ችግር (Eclampsia Preeclampsia)
ደህንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ፣
ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች፣ ለእናቶች ሞት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በአለም አቀፍ ከሚገጥመው የእናቶች ሞት ውስጥ 99% ያህሉ የሚከሰተው ባላደጉ ሀገራት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በታዳጊ አገራት የሚታየው የእናቶች ሞት፣ በእጅጉ እንዲበዛ የሚያደርጉ መነሻ ምክንያቶች አሉ። ገና በለጋ እድሜያቸው ልጅ የሚያረግዙ ሴቶች፣ በብዛት የሚታየው ባላደጉ ሀገራት መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ባላደጉ አገራት ውስጥ፣ በ15 አመታቸው ከሚያረግዙ 1000 ሴቶች መካከል ስድስቱ ይሞታሉ። በበለፀጉት አገራት ግን፣ ከአራት ሺ ሴቶች መካከል፣ አንዷ ብቻ ለሞት እንደምትዳረግ ይገልፃል - የአለም የጤና ድርጅት መረጃ።
በተለምዶ፣ ‘በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት’ ተብሎ የሚታወቀው የጤና ችግር (Eclampsia Preeclampsia)፣ በእናቶች ላይ የሚያስከትለው ህመምና የሞት አደጋም፣ ባላደጉ አገራት ውስጥ የከፋ ነው።
በአለም ዙሪያ በየአመቱ 10 ሚሊዮን ሴቶች፣ በእርግዝና ወቅት ኢክላምፕሲያ ይይዛቸዋል።
በአለም ዙሪያ በየአመቱ ወደ 76,000 እርጉዞች፣ በኢክላምፕሲያና ተያያዥ በሆነ የደም ግፊት ሳቢያ ለህልፈት ይዳረጋሉ።
በእርጉዞች ላይ በሚከሰተው ኢክላምፕሲያና ተያያዥ የደም ግፊት መዘዝ፣ 500,000 ሕጻናት ይሞታሉ።
ከበለፀጉ አገራት ይልቅ ባላደጉ አገራት ውስጥ የሚታየው የኢክላምፕሲያ ችግር፣ በ7 እጥፍ ይበልጣል። ባደጉ አገራት፣ ከኢክላምፕሲያ ታማሚ እርጉዞች መካከል፣ 10 እስከ 25 ከመቶ ያህሉ ህይወታቸውን ያጣሉ።
የኢክምፕሲያን ጉዳት ከሚያባብሱ ምክንያቶች መካከልም፡-
ድህነት
የጤና ተቋም በቅርበት አለመኖር
የእውቀት ወይንም የመረጃ እጥረት
የተሟላ አገልግሎት አለማግኘት
ባህላዊ ወይንም ልማዳዊ ተፅእኖዎች ይጠቀሳሉ።
በዚህ የጤና ችግር ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን ናቸው። ፕሮፌሰር ይፍሩ በአዲስ አበባ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ እንዲሁም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኃላፊ ናቸው።ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን ከአስረስ ብርሀን ጋር በመሆን ማግኔዥየም ሰልፌት የተባለው መድሀኒት በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት ምልክት ለታየባቸው ሁሉ ሊሰጥ ይገባዋልን? የሚል ጥናት በጃፓን የጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር ጆርናል ለህትመት አብቅተዋል።
ጥያቄ፡ ኢክላምፕሲያ ምን አይነት ሕመም ነው?
መልስ፡ Eclampsia Preeclampsia በእርግዝና ወቅት እንደመንቀጥቀጥ እና የሚጥል በሽታ መስሎ የሚከሰት ሕመም ነው። ኢክላምፕሲያ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ከደም ግፊት ጋር የተያያዘ ተብሎ የሚታወቅ ቢሆንም በሽታው ከደም ግፊት ያለፈ ነው። ምክንያቱም ይህ በሽታ የትኛውንም የእናትየውን የሰውነት ክፍል ያጠቃል። በአብዛኛውም በጉበት ፣በአእምሮ ፣በደም ስሮች እንዲሁም በኩላሊት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሲሆን እየጠነከረ ሲመጣም የማያጠቃው የሰውነት ክፍል የለም። የደም ግፊት ለ ኢክላምፕሲያ አንዱ መገለጫው እንጂ ሙሉ በሙሉ የደም ግፊት ሕመም አይደለም። ይህ የጤና ችግር በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በመላው አለም የሚገኝ ነው። ልዩነቱ ምናልባትም በኢትዮጵያና መሰል ታዳጊ ሀገራት ለየት የሚያደርገው ሴቶች ቶሎ ወደሕክምናው አይመጡም ወይንም ደግሞ መጀመሪያውኑ ክትትል ስለማያደርጉ ቶሎ አይታወቅም በእነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች በእናቶችና በጽንስ ላይ ጉዳት ያደርሳል።
ጥያቄ፡ የህመሙ መንስኤ ይታወቃል?
መልስ፡ የህመሙ መንስኤ በየትኛውም አለም አይታወቅም። በእርግጥ ተጋላጭ የሆኑ እናቶች አሉ። ለምሳሌም የመጀመሪያ እርግዝና ከሆነ፣ የመጀመሪያ እርግዝና ከሀያ አመት በፊት ወይንም ደግሞ ከ35 አመት በሁዋላ ከሆነ ፣እርግዝናው መንታ ከሆነ፣ በቤተሰብ እንደዚህ አይነት የጤና ችግር ከአሁን በፊት ካለ ወይንም ያረገዘችው ሴት ቀደም ሲል የደም ግፊት ወይንም ኩላሊት ሕመም ካለባት ፣የሰውነት ክብደት ከፍ ያለ ከሆነና በመሳሰሉ ምክንያቶች በእርግዝና ጊዜ ኢክላምፕሲያ ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ግን ይህ ችግር ያለባቸው ሴቶች ሁሉ ኢክላምፕሲያ ይከሰትባቸዋል ማለት አይደለም። ይህ በሽታ በአለም አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ ስምምነት የተደረሰበት ሕክምና የለም። አንዱም ምክንያቱ መንስኤው ስለማይታወቅ መፍትሔውም በተሻለ እውቀት ላይ አለመገኘቱ ነው። ይህንን በሽታ ለማከምም ሆነ ለመከላከል የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ ቆይቶአል። ነገር ግን ይህ ትክክለኛው መንገድ ነው የሚል መከላከያ መንገድ የለውም። ሕመሙም ደረጃ ተከትሎ የሚሄድ ሳይሆን እንደተፈጠረው አጋጣሚ የሚከሰት ነው። ለምሳሌም ገና ሲጀምር ምንም ሌላ ምልክት ሳያሳይ በመጣል ሊጀምር ይችላል። በራስ ምታት ወይንም ጨጉዋራ ማቃጠል ወይንም ደም ስር ላይ በሚፈጥረው ችግር ሊጀምር ይችላል። በአጠቃላይ ተመሳሳይ እና ወጥ የሆነ ነገር የለውም።
ጥያቄ፡ ኢክላምፕሲያ ሕክምናው ምን ይመስላል?
መልስ፡ ወደሕክምናው ስንመጣ በሽታው ወይንም ምልክቱ ከታየ በሁዋላ የትኞቹ ናቸው መድሀኒት ሊሰጣቸው የሚገባ ? ለየትኞቹ ነው መድሀኒት መሰጠት የሌለበት በሚለው ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት የለም። በተለይም ሓቈስስሰቁሮቂቅቋሽሮ የሚባለው የተለያዩ ደረጃዎች አሉት ። መካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ በሚል ይለያል። ስለሆነም በሕክምናው አለም አንዳንዱ ጋ ደረጃው ከፍተኛ ሲሆን መድሀኒቱ ይሰጥ በሚል የሚስማሙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በመካከለኛው ደረጃ ላይም ሊሰጥ ይገባል በሚል ይከራከራሉ።በዚህ ጥናት እንደተመለከተው ግን በእርግጥ በከፍተኛ ደረጃ ለደረሰው መድሀኒቱን መስጠቱ የሚያስማማ ሲሆን ነገር ግን በመካከለኛው ደረጃ ላይ ያሉትም መድሀኒቱን ማግኘት ይገባቸዋል የሚል ነው። ከተለያዩ ሀገራት እንደታየው እማኝነት ከሆነ ምንም ምልክት ሳይታይባቸው ለጉዳት የሚዳረጉ መኖራቸውን የተሰበሰቡት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስለዚህም ድምዳሜው የሚሆነው ምልክቱ ለታየባቸው ሁሉ መድሀኒቱን መስጠቱ ተገቢ ነው የሚል ነው። የዚህም ምክንያት የእናትየውንም ሆነ የጽንሱን ህይወት ለመጠበቅ ሲባል ነው። ይህ ጥናት የተካሄደው በ26/ ሀገራት ሲሆን በናሙናነት የተወሰዱት ሴቶች ቁጥርም ወደ 21.155 ሀያ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሀምሳ አምስት ይሆናል። በጥናቱ ላይ እንደሚታየውም ይህ የሚከሰትባቸው ሀገራት በመጠኑ የተገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ በሶስተኛ ደረጃ ማለትም ችግሩ በብዛት ከሚታይባቸው ከኢንድያና ከናጄሪያ ቀጥላ ትገኛለች።
ጥያቄ፡ ኢክላምፕሲያ በእርግዝና ጊዜ ብቻ ይከሰታልን?
መልስ፡ ኢክላምፕሲያ በእርግዝና ጊዜ ብቻ አይከሰትም። አንዲት እናት እራስዋን ከሳተች ወይንም የማንቀጥቀጥ ምልክት ከታየባት ይህ መቼ ተከሰተ? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል። ከመውለድ በፊት ነው? በመውለድ ላይ እያለች ነው? ወይንስ ከወለደች በሁዋላ ነው? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል። በእርግጥ በፊት የነበረው ግንዛቤ ኢክላምፕሲያ ከእርግዝና ጋር ተያያዥ ነው የሚል ስለነበረ እናቶች በምጥ ሰአት ወይንም ከወለዱ በሁዋላ ይህ ይከሰታል ብሎ የሚገምት አልነበረም። ነገር ግን ጥናቶች እንደሚያሳዩት የነበረው ግንዛቤ ትክክል እንዳልሆነና ከወለዱ እስከ አስር ቀን ወይንም እስከ አርባ ሁለት ቀን ድረስ ሊከሰት እንደሚችል ያሳያሉ። ስለዚህም ሕመሙ በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ እንዲሁም ከወሊድ በሁዋላ ሊከሰት ይችላል።
ጥያቄ፡ የጥናቱ መነሻና መደምደሚያ ምንድነው?
መልስ፡ በአለም ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ከሁለት የተከፈለ ሀሳብ አላቸው ። ከፊሎቹ ኢክላምፕሲያ የተባለው ሕመም ከፍተኛ ደረጃ ለደረሱት ይሰጥ ሲሉ ሌሎች ደግሞ አይደለም ምልክቱ ለታየባቸው ሁሉ ይሰጥ የሚል ሀሳብ አላቸው። የጥናቱ መነሻም ማግኔዥየም ሰልፌት የተባለውን መድሀኒት ኢክላምፕሲያ ምልክቱ ለታየባቸው ሁሉ ሊሰጥ ይገባል እንጂ ከፍተኛውና ዝቅተኛው እያልን መለየት የለብንም የሚል ነው። ምክንያቱም ዝቅተኛ የተባለው በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊገኝ ስለሚችል ነው። በተለይም ታማሚዎቹ ከቤታቸው የነበሩ ከሆኑ በፍጥነት ወደሕክምና ተቋም ማድረስ ተገቢ ይሆናል። ሕመሙ ሲያንቀጠቅጥ ወይንም እራስን ሲያስት ልክፍት ወይም ሌላ ሕመም ነው በሚል ወደእምነት ወይንም ባህላዊ ቦታዎች በመውሰድ ሕክምና እንዳያገኙ ከተደረገ ለእናቶቹ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ይሆናልና።



Read 11548 times