Monday, 25 July 2016 09:37

አቤል ተስፋዬ፤ ከአለማችን ከፍተኛ ተከፋዮች አንዱ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• ባለፉት 12 ወራት ብቻ፣ 55 ሚ. ዶላር ገቢ አግኝቷል
• ለ117 ታላላቅ ሽልማቶች ታጭቶ፣ በ36 አሸንፏል
    በወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ መድረክ ጎልቶ በመውጣት ከፍተኛ ስኬትን የተቀዳጀውና የበርካታ ታላላቅ አለማቀፍ ሽልማቶች ባለቤት ለመሆን የበቃው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፤ ከአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ተርታ መሰለፉን ዘ ኢንኩዚተር ዘግቧል፡፡
አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያፈራው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ ፎርብስ መጽሄት ከሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የ2016 ከፍተኛ ተከፋይ 100 የዓለማችን ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካተቱት 15 ዝነኞች መካከል አንዱ መሆኑንና ከእነዚህ መካከልም ከፍተኛውን ገቢ ያገኘው እሱ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የ25 አመቱ ድምጻዊ አቤል ባለፉት 12 ወራት ብቻ 55 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጧል፡፡
“ዘ ዊክንድ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የግራሚ ተሸላሚው አቤል፤ ከዘንድሮ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ 100 ዝነኞች መካከል የ30ኛ ደረጃን መያዙን የጠቆመው ዘገባው፣ “ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘውና ከ2 ሚሊዮን ኮፒ በላይ የተቸበቸበው የሙዚቃ አልበሙ ለድምጻዊው ከፍተኛ ገቢ ማግኘትና በዝርዝሩ ውስጥ መካተት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጧል፡፡
ለ117 አለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማቶች በመታጨት፣ ሁለት የግራሚና ስምንት የቢልቦርድ ሽልማቶችን ጨምሮ 36 አለማቀፍና ክልላዊ የሙዚቃ ሽልማቶችን ያገኘውና በወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ መድረክ፣ አብሪ ኮከብ ሆኖ የወጣው አቤል፤ ባለፉት 12 ወራት ከአልበም ሽያጭ፣ ከሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ከኩባንያዎች ስምምነትና ከመሳሰሉት በድምሩ 55 ሚሊዮን ዶላር ሰብስቧል፡፡

Read 2180 times