Monday, 25 July 2016 09:21

ቅኔያዊ ህልም

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(20 votes)

…. ወተት በበራድ ከመጣዴ፣ በሩ ተንኳኳ፡፡ “ይግቡ” ከማለቴ ጐረቤቴ በሩን ገፋ አድርጐ ብቅ አለ፡፡ ግንባሩ እንደ ጥይት የሾለ፤ ካውያ ራስ፡፡ ወደ ክፍሉ እንድመጣ አጣደፈኝ፡፡
‘ምን ገጠመው’ በሚል ተከትየው ወደክፍሉ ገባሁ፡፡
“ተቀመጥ… የማነብልህ ጽሑፍ አለኝ”…
“ይቅርታ መቆየት አልችልም… ወተት ጥጄ ነው የመጣሁት፤ ይገነፍልብኛል፡፡”
“የማነብልህ አጭር ልቦለድ ነው… የጣድከው ወተት ከመገንፈሉ በፊት ታሪኩ ይቋጫል፡፡”
ምላሼን ሳይጠብቅ ጀመረ - ትረካውን…
…. ድቅድቅ ጨለማ፡፡ ውድቅት ሌሊት። ዶፍ እየጣለ ነው፡፡ አስፈሪ ቁጡ… የመብረቅ ብልጭታዎች እንደ ሰይፍ ብልጭ! ብለው ድርግም! ግም! … እግዚአብሔር የተቆጣ… መላእክቱ ያኮረፉ….
ሁሌም የሚጀምረው ይህንን በመሰለ ነውጥ ነው፡፡ ቁጡ የመብረቅ ብልጭታዎች ዓይነት …. ማንን ለማስፈራራት ይሆን? የእሳተ-ጐመራ ፍንዳታ፣ የማዕበል ወጀብ፣ ርዕደ-መሬት ይከተል ይሆን?
ይህንን ከመሰለ የምጽአት ቀን ውርጅብኝ መሀል ገጸባህሪያቱ ብቅ ይላሉ… መብረቅ ወርዶ ሁለት ቦታ በሰነጠቀልኝ ና ወደ ወተቴ…..
ማንበቡን ቀጥሏል….
የንጋት ፀሐይ መውጫ ቀዳዳ አጥታ በደመና ብርድልብስ መሐል አሸልባለች፡፡…………………………
በስንብት ላይ ያለው የቀኑ ብርሃን፤ የእሳት ወጋገን እየመሰለ፣ ጀንበር ወርቃማ ጨረሮቿን ፈንጥቃ፣ የእለቱን ግብአቷን ፈጸመች-የአድማሳቱን ከንፈር ስማ፡፡ ….
ከዋክብት አልባ ጥቁር ሰማይ ላይ ጨረቃዋ ብቻዋን ተንጠልጥላለች፡፡ ጨለማው ሲበረታ ከዋክብት ከመሸጉበት ወጥተው በጥቁሩ ሰማይ ላይ እንደአሸዋ ፈሰሱ….
አቋረጥኩት!  “የፈረደበት ሰማይ ጨረቃ ብቻዋን ተንጠልጥላበት ነበር፤ ከአፍታ በኋላ ደግሞ ከዋክብት ፈሰውበታል-ያውም ከመሸጉበት ወጥተው…. በቀጥታ ወደ ታሪኩ ግባ… ወተት ጥጄ ነው የመጣሁት”…
ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎኝ ትረካውን ቀጠለ…
ማለዳም የፀሐይ ጮራ ሽራፊ እንደውብ ኮረዳ እየተጣቀሰች ብቅ አለች…
“ወይ ጣጣ! ፀሐይ ተመልሳ ወጣች?!” ምርር ብሎኝ፡፡
“ምን ይገርማል! የተፈጥሮ ህግ ልትሽር ነው” አለኝ፤በንዴት
“የአድማሳቱን ከንፈር ስማ ጠለቀች ያልከኝ መሰሎኝ… አሁን ደግሞ ወጣች… ጠለቀች! ወጣች! ወሃ ቅዳ ውሃ መልስ”
“ከቅድም ጀምሮ አፍ አፌን እያልከኝ ነው፤ የመስማት ፍላጐቱ የለህም፤ በቃ ይቅርብህ አዝናለሁ” አለኝ፤ በተሰበረ ቅስም፡፡
“እንዲህማ አይሰማህ ስለ ቁጡ መብረቅ….. እንደ ጦረኛ ከምሽጋቸው ወጥተው ሰማዩን ስለወረሩት ከዋክብት…. በደመና መሐል አሸልባ ህልም ስለምታልመው ፀሐይ መግባትና መውጣት ትተህ፤ ታሪኩን በቀጥታ ንገረኝ…. መነሻህ…. ምንድነው?”
“መነሻዬ የአዳም ረታ ‘መረቅ’ ልቦለድ መጽሐፍ ነው… ሰብለወንጌል አዲስ አበባ መጥታ …ተመቻችቶላት ትዳር መስርታ ወልዳ”…
“ስለ ሰብለ ትዳር አመሰራረት አልጠየኩህም… አንተስ የሰብለን ህይወት በምን መልኩ ልታቀርበው አሰብክ … ልብ! በል የመጨረሻዎችን መስመሮች ብቻ አንብብልኝ….በተለይም ስለ ጨረቃና ከዋክብት በፍጹም መስማት እንደማልፈልግ በአጽንኦት ልነግርህ እወዳለሁ”
ቀጠለ- ትረካውን…
በዛብህ በዝምታ የቀረበለትን ብርዝ እየጠጣ ነበር፡፡ የሰብለወንጌል አንፀባራቂ ከዋክብት መሳይ አይኖች ወደ በዛብህ ያማትራሉ… አይኖቿ የብርሃን ፀዳል ይረጫሉ በዛብህ አይኑን ከሰብለ ላይ መንቀል አልቻለም፡፡…. ‘አይተውኝ ይሆን?’ በሚል ጥርጣሬ ወደ ፊታውራሪ መሸሻና እናቷ አማተረ፡፡ ከአባ ሞገሴ ጋር ሞቅ ያለ ወግ ይዘዋል፡፡
ካብትሽ ብርዝ የምትቀዳለት መስላ፤ “ዓይን የተፈጠረው ሁሉ ለማየት ነው” ብላ ሹክ አለችው…
ሰብለ በድንገት ብድግ ብላ …”አባዬ፤ የምጠይቅህ ጉዳይ አለኝ-በዛብህ”…
ፊታውራሪ ወደ ሰብለ ዞር ብለው “አንዴ ፋታ ስጪኝ… የቄስ ሞገሴን ወግ ልጨርስ”…
በዛብህ ውስጡ ተናወጠ፡፡ ሰብለ የፍቅሩን ግለት መቋቋም እንዳቃታት አመነ፡፡ ‹‹በዛብህን ዳርልኝ›› ስትልም እንደ ዱብ እዳ ፍርጥ ልታደርገው ነበር… ፊታውራሪ ይህን ጉድ ሲሰሙ… ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ ዘገነነው… እናም ተሰናብቶ ወጣ፡፡ ወደ ማደሪያው አቀና-በፈጣን እርምጃ፡፡ ….ስለነቢብ ፍቅሩ እያውጠነጠነ አዘገመ፡፡… የስለት ልጅነቱ እንደ ሰቅጣጭ ቅዠት ውስጡን አባጠለው። የተረገመ እጣ ፈንታ፡፡ በእጣ ፈንታዬ ላይ ማመጽ አለብኝን? መልስ ያላገኘለት የህይወቱ እንቆቅልሽ፡፡ በሰብለ በኩል የቀረበለት የፍቅር ደመራ አመድ ሊሆን!.... ውቧ ሰብለ!፡፡ ውብ ሳዱላ!፡፡ ጠምበለል፡፡ ጠይም አሣ መሳይ፡፡ ምትሀታዊ ውበት፡፡ የሚያቃጥል ፍቅር። የመጀመሪያ ፍቅር፡፡ ቅኔያዊ ህልም- ሰብለወንጌል …. ጣዝማ መሳይ ማር አካሏ ላይ ተጣብቆ…. እንጆሪ ከንፈሮቿን ሲመጥ… ድግን ጡቷቿ መሐል ሲሟሟ… ንጥር ስሜቷን ያለንፍገት - እና እልም ወደ ምትሀታዊ ህልም መሰል የተረት አለም -ወደ ጽረ አርያም…
በዛብህ እንደወጣ ሰብለ በሀሳብ ጭልጥ ብላ ነበር… ወጣትነት እና ውበት… ህይወትን ውብ ያደርጉታል… ግን ሲረግፉስ? ራሷን ጠየቀች… እናም በጊዜዋ መዋብ… ማጌጥ አለባት …ድንገት ፊታውራሪ ወደ ሰብለ መለስ ብለው፤
“ምን ነበረ ጉዳይሽ? በዛብህ ያልሽኝ መሰለኝ”…
“አዎ በዛብህ”
“በዛብህ ምን!!” ቱግ አሉ ፊታውራሪ
“በዛብህ ምንህ ነው”? ጠየቀች ሰብለ፡፡
“እኔ ፊታውራሪ መሸሻ፤ ለበዛብህ ጌታው ስሆን፤ እሱ ደግሞ ልሸጠው ልለውጠው የምችል ባሪያዬ!”
ሰብለ ቀልጠፍ ብላ፤ “በዛብህ ባሪያህ ከሆነ ለምን አይሸጥም… በሽያጩም የጆሮ እንቁና የአንገት ሐብል  ቢገዛልኝ”…
በሩ ድንገት ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡ አዜብ ብቅ አለች - የአከራዩ ልጅ፡፡….
“እዚህ ወሬህን ትሰልቃለህ… ወተቱ ገንፍሎ አገር ምድሩን አዳርሶልሃል”….
“ወይኔ ወተቴ!” - ወደ ክፍሌ ተወነጨፍኩ…





Read 4745 times