Monday, 25 July 2016 07:09

ተቃዋሚዎች፤ የሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች አሳሳቢ ሆነዋል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

· ኢዴፓ የብሄራዊ እርቅ መድረክ እንዲፈጠር ጠየቀ

    የአገሪቱን ወቅታዊ ችግሮች በመጥቀስ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ማበጀት እንዳለበት የገለፁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ችግሮቹ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ሲሉ አስጠነቀቁ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ለፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በፃፈው ደብዳቤ፤ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት መገምገሙን ጠቅሶ፤ መንግስት በመላ ሀገሪቱ ሰላምና ዲሞክራሲ በማስፈን፣ ለህዝቡ የተረጋጋ ህይወት ማስፈን አልቻለም ብሏል፡፡
በኦሮሚያ የተፈጠረው ግጭትና ተቃውሞ፣ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ላደረሰው ጥፋት እስካሁን ዘላቂ መፍትሄ አለመቀመጡን የጠቀሰው ፓርቲው፤ በአማራ ክልልም በወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ መነሻነት የተፈጠረው ግጭት በተመሳሳይ መልኩ ለሰው ህይወት መጥፋትና ለብረት መውደም ምክንያት መሆኑ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክ/ከተሞች ህገ ወጥ እየተባሉ ቤቶች በመፍረሳቸው፣ ዜጎች ያለ መጠለያ መቅረታቸውን ያወገዘው መኢአድ፤ ለእነዚህ ወቅታዊ ችግሮች መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቋል፡፡
ፓርቲው ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ለፌደሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤዎችም ደብዳቤውን እንደላከ ገልጿል፡፡  ፓርቲው እነዚህን በመሳሰሉ ወቅታዊ ችግሮች ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ሲፅፍ መቆየቱን አስታውሶ፤ ለሚፅፋቸው ደብዳቤዎች አንድም ጊዜ ምላሽ እንዳልተሰጠው ይገልፃል፡፡ የአሁኑን ደብዳቤ ለመጨረሻ ጊዜ ለ4ቱ የመንግስት አካላት መላኩን የጠቆመው መኢአድ፤ “ለዚህ ደብዳቤ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ በሌላ መንገድ ጥያቄውን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብሏል፤ ለአዲስ አድማስ በሰጠው መግለጫ፡፡
የሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮችና ግጭቶች በእጅጉ እያሳሰበኝ ነው ያለው ኢዴፓ በበኩሉ፤ በአስቸኳይ የብሄራዊ እርቅ መድረክ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል፡፡
“ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብሄራዊ እርቅ ወሳኝ ነው” ያለው ኢዴፓ፤ መንግስት ለተቃውሞዎች የሃይል እርምጃ መጠቀሙ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፆ፣ ህዝቡም ሀገርን ከሚያፈርስ እንቅስቃሴ እንዲቆጠብና ልዩነቶች በሰላም እንዲንፀባረቁ ጠይቋል፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚተላለፉ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎች ልዩነትን ከማራገብ ተቆጥበው፣ ሰላምን ለማምጣት ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ፓርቲው ጠይቋል፡፡  
ቀደም ሲል ተመሳሳይ መግለጫዎችን ሲያወጣ መቆየቱን የጠቆመው ፓርቲው፤ መንግስት መግለጫዎቹን ቸል በማለቱና የእርምት እርምጃዎች ባለመውሰዱ በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ የሰው ህይወት ከማለፉም ባሻገር ሀገሪቱን ወደ አስከፊ ሁኔታ እየመራት ነው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በበኩሉ፤ መንግስት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ህገ ወጥ ያላቸውን ቤቶች ያለ አማራጭ ማፍረሱና በክረምት ዜጎችን ለብርድና ለእንግልት መዳረጉ ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ ነው በማለት እንደሚያወግዘው አስታውቋል፡፡
በጎንደር የተፈጠረው ችግር ለህዝብ ጥያቄዎች በህገ መንግስቱ አግባብ ፈጥኖ መልስ አለመስጠት ያስከተለው መሆኑን በመግለጫው ጠቅሶ፤ መንግስት ይህን ለመሳሰሉ የህዝብ ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡ በክልሉ በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት በእጅጉ ማዘኑን የገለፀው መድረክ፤ ነዋሪነታቸው በጎንደር ደባርቅ ከተማ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ተለይተው ንብረታቸው እንዲወድም መደረጉንም አጥብቆ ኮንኗል፡፡
በተመሳሳይ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መዐሕድ)፤ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች እንደሚያሳስበው የገለፀ ሲሆን የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይም በሰላም እንዲፈታ በአፅንኦት ጠይቋል። በመዲናዋ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ጉዳይም እንደሚያሳስበውና መንግስት የመጠለያ ቦታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ መዐሕድ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

Read 9176 times