Print this page
Wednesday, 20 July 2016 12:46

አንዳንድ የህውሓት አመራሮች ከፓርቲው መውጣታቸው ለበጎ ነው!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(19 votes)

ብ/ጄነራል አበበ፣ የኛ ትውልድ የዲሞክራሲ ትውልድ አይደለም ይላሉ
- ለአዲስ አበባ ባቡሮች መቆም ተጠያቂው ማነው?

      በዕለት ተዕለት ህይወታችን ብዙም የሚያስደስት ነገር እንደሌለ አገር ያወቀው፣ ጸሃይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ በየጊዜው የሚሰማው ወሬና መረጃ ደግሞ የባሰ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ አገራት የሚወስደው መንገድ እንዲህ ፈታኝ መሆኑን ብናውቅ እኮ ሌላ አማራጭ እንፈልግ ነበር፡፡ (ለእኛ መረጃ የሚያቀብል ግን የለም!) ለማንኛውም ግን የፖለቲካ ወጋችንን ዘና በሚያደርግ የአውሮፓ ወሬ እንጀምረው፡፡
ሰሞኑን አንድ የአልባንያ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በአገሪቱ የሚዲያ ኢንዱሰትሪ ተፎካካሪም ሆኖ ለመውጣት የዘየደው መላ ለብዙዎቻችን የእብደት ነው የሚመስለው (በተለይ ለእኛ ዓይነቱ የሀበሻ አገር!)፡፡ በነገራችን ላይ በእኛም አገር የጦፈ የቴሌቪዥን ጣቢያ ፉክክር በቅርቡ ስለሚጀመር ከወዲሁ ብንዘጋጅ ይበጀናል፡፡ እናላችሁ … ሰሞኑን የአልባንያው ZJarr የተሰኘ ጉደኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ ምን አደረገ መሰላችሁ? ዜና አንባቢ ሴቶች፤ጡታቸውን በሚያሳይ አለባበስ በቲቪ መስኮት ቀርበው ዜና እንዲያነቡ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ (የተመልካቹን ቀልብ ለመሳብ እኮ ነው!) አንድም ትእዛዙን የተቃወመች ዜና አንባቢ አልተገኘችም፡፡
እንደውም አዳዲስ ወጣት ሴቶች ጡታቸውን እያሳዩ ዜና ለማንበብ ፍላጎት አሳይተዋል፤ ተብሏል፡፡ (እዚህ አገር እኮ “ክራራይሶ” ሊያሰኝ ይችላል!) “የዜና አንባቢዎቹ እርቃንነት ዜናችንን የምናቀርብበትን መንገድ ይወክላል፤ ይኸውም እውነቱን ብቻ፣ ምንም ሳይሸፋፈን” እንደምንዘግብ .. ሲሉ የጣቢያው ሃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡ በእርግጥም ዜና አንባቢዎች ጡታቸውን እያሳዩ ዜና ማቅረብ ከጀመሩ ወዲህ የቲቪው ተመልካች ቁጥር እያደገ ነው ብሏል - ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው፡፡ ሆኖም ለዋናው ዜና ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተል ተመልካች ስለመኖሩ ግን አጠራጣሪ ነው ባይ ነው፡፡ (ጡት ይመልከቱ ዜና?!) ይሄ የፈጠራ ሃሳብ ለአልባንያ ቲቪ የገበያ ተፎካካሪነት ሰርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ለጦቢያ ቲቪ ግን ፈፅሞ አይታሰብም፡፡ (ለሙዚቃ ክሊፕ ችግር የለውም!)
እኔ የምለው ---- ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣውን የአዲስ አበባ አስተዳደር የሳይክል ፕሮጀክት ዜና አያችሁልኝ? ያስገርማልም፤ ያሳዝናልም!! እያንዳንዳቸው በ35ሺ ብር ሂሳብ የሚሸመቱት 300 ሳይክሎች የታሰቡት ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ (physical fitness) ቢሆን እኮ ችግር የለውም ነበር፡፡ ዋና ዓላማው ግን የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ነው ሲባል ትንሽ ያሳስባል፡፡ (“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” አሉ!) በነገራችን ላይ ከጥቂት ወራት በፊት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤“ዕቅዳችን ከተማዋን ከታክሲ ተፅዕኖ ማውጣት ነው!” ያለው ትርጉሙ የገባኝ አሁን ነው፡፡ (ታክሲን በሳይክል እንተካዋለን ማለት ነው!) የሚያሳዝነው ግን ምን መሰላችሁ… እቺ ከዘመናዊና ቀልጣፋ የትራንስፖርት ሲስተም ይልቅ የኪራይ ሳይክሎች የተደገሰላት መዲና፤ የአፍሪካ ህብረትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ብቻም አይደለም፡፡ በዓለም ስማቸው የናኘ ዝነኛ ባለ 4 እና ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች እየተገነቡባት ያለች ተስፈኛ ከተማ ነች፡፡ የዓለማቀፍ ስብሰባዎችና ጉባኤዎች ማዕከል እየሆነች መምጣቷንም እያየን ነው፡፡ እሺ እኛስ የልማታዊ መንግስት መሞከሪያ እንሁን?! ዕዳችን ነው!! (አገርህ ናት በቃ አለ ገጣሚው!)
ነገር ግን ለቢዝነስና ለጉብኝት ወይም ለጉባኤ ወደ አገራችን የሚመጡ እንግዶች በምን እዳቸው ነው ከሳይክል ጋር የሚታገሉት? በ50 ሃባ ባሶች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሸገር ባስ፤ለምን “ችግር ባስ” የሚል ቅጽል ስም እንደወጣለት የሚነግረኝ ባገኝ ደስታውን አልችለውም ነበር፡፡ ግን እንደሰማሁት፤ ባሱ ሁሌ መሃል አስፋልት ይዞ መክነፍ ነው - በተለይ ሰው ሰብሰብ ብሎ የሚጠብቀው ከመሰለው አከናነፉ ይብስበታል፡፡ (“ሸገር” ስለተባለ ብቻ ሸገሮችን ይወደናል ማለት እኮ ላይሆን ይችላል!)
ያለፈው ሳምንት ሳያንሰኝ ሰሞኑን ደግሞ ሌላ አስገራሚና አሳዛኝ ዜና ሰማሁላችሁ፡፡ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽን ካሉት 41 ባቡሮች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡት ከ28 አይበልጡም መባሉን ስሰማ --- ድንግጥ ነው ያልኩት፡፡ (ኮርፖሬሽኑ የእኔን ያህል እንኳን የደነገጠ አይመስለኝም?!) ባቡሮቹ በችኮላ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉና ከቻይናው ድርጅት ጋር በተገባው ውል ላይ የባቡር መለዋወጪያ እንዲያቀርብ የሚያስር ስምምነት ሳይደረግ መቅረቱ ለተፈጠረው ችግር ሰበብ ሆኗል፤ ተብሏል፡፡ … ይሄም የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ከተባለ ያመኛል፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፋሉ ተብለው በከፍተኛ ወጪ፣ ያውም በብድር የተገዙት እነዚህ ባቡሮች፤ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጥገና ማሳለፋቸው አሳሳቢ ነው፤ የተባለ ሲሆን፤ ባቡሮቹ መንገዱ ምቾት እየነሳቸው አልፎ አልፎ ከተዘረጋላቸው ሃዲድ እንደሚወጡ፣ በዚህም ሳቢያ ሃዲዱ እንዲጠረብና በግራሶ እንዲለሰልስ መደረጉ ታውቋል፡፡ ይታያችሁ … ከዓመት በኋላ 40 የነበረው በእጥፍ ጨምሮ 80 ባቡሮች ሲርመሰመሱ እናያለን ብለን ተስፋ ያደረግነውን ሁሉ ኩም አደረጉን!... 13 ባቡሮች ከቆሙ ምን ቀረን?! በቴክኒክ ብልሽትም ቢሆን ለምን ይቆማሉ አልወጣኝም፡፡ ተጠግነው በጊዜ ለምን ወደ ሥራ አይገቡም ነው ጥያቄው፡፡ ችግሩን የሚፈታ የባቡር መለዋወጪያ አቅራቢ የለም ተብሏል፡፡ (“ዊርድ” አለ ፈረንጅ!)
እኔ የምለው ግን … ሃዲዱን የሰራው የቻይና ኩባንያ ነው!! ባቡሩን ያመረተው የቻይና ፋብሪካ ነው!! የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለ3 ዓመት የሚመራው የቻይና ማኔጄመንት ነው!! የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽን ውል እንኳን መፈራረም ያቅተው? የፈሰሰ ውሃ አይታፈስምና አሁን የሚያዋጣው ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ መዘየድ ብቻ ነው፡፡ የተሰራው ጥፋት (ስህተት) እንደተለመደው በዝምታ ይታለፍ ግን አልወጣኝም፡፡ “የህዝብ ሀብት ኪሳራ በስኳር ኮርፖሬሽን ይብቃ!”
እናላችሁ------በጅምላ የባቡር ኮርፖሬሽንን መክሰሱ ቀርቶ ጉዳዩ የሚመለከተው ኃላፊ ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል፡፡ በጅምላ መሸፋፈን ተለምዷል! እኛም የጥፋቱ መጠንና ያደረሰው ኪሳራ ተመርምሮና ተሰልቶ ለህዝብ ይፋ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ (ሙስና ብቻ ሳይሆን የብቃት ማነስም ከኃላፊነት ያስነሳል!!) ሌላው አገር ትልቅ ቀውስ ሲፈጠር ኃላፊው በገዛ ፍቃዱ ኃላፊነቱን ይለቃል፡፡ የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፤በሪፈረንደሙ ያልተጠበቀ ወይም ያልተፈለገ አሊያም ያልታሰበ ውጤት በመምጣቱ (ብዙዎች ከህብረቱ እንድትወጣ ድምፅ በመስጠታቸው!) ራሳቸውን ከስልጣን አግልለዋል፡፡ “ሌላ ሰው ደግሞ በአዲስ መንፈስ ይምራችሁ ….” ብለዋል፡፡ (እኛ አገር ግን ከወረዳ ኃላፊነት መውረድም ሞታችን ነው!
በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉትንም ችግሮች (ለ10 ዓመት የተጓተቱትን የስኳር ፋብሪካዎች ጨምሮ) ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር ጉድለት ውስጥ ጠቅልሎ ለመገላገል ይዳዳዋል፡፡፡፡ የህውሓት አንጋፋ ታጋይና የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ ሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሃይማኖት ግን በዚህ ጉዳይ ከኢህአዴግ ጋር አይስማሙም፡፡ አሁን በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ውስጥ ያለው ችግር የመልካም አስተዳደር በሚል የሚታለፍ ሳይሆን የመዋቅራዊ ስርዓት ችግር ነው ብለዋል - ጀነራሉ ፡፡
የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ፤ በቅርቡ ከዚሁ ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ነፃና ደፋር ቃለ ምልልስ ካነበብኩ በኋላ ለራሴ ምን እንዳልኩ ታውቃላችሁ? እንኳንም በ93 ክፍፍል ወቅት ከህውሓት ተባረሩ አልኩ ለራሴ፡፡ (አንድ ከመንጋው የተለየ ነፃ አሳቢ ኢትዮጵያዊ እንድናተርፍ እረድቶናል!) ምን መሰላችሁ … ማንም የፈለገ ቀና አሳቢ ቢሆን በኢህአዴግ ውስጥ እስካለ ድረስ ፓርቲው አስቦ ከሚሰጠው ውጭ ሊያስብ እንደማይችል የሩብ ክ/ዘመን ተመክሮአችን ይነግረናል፡፡ ጀነራሉ ለግንቦት 20 በዓል ከ “ሪፖርተር” ጋዜጠኛው የማነ ንጋሽ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ በ93 ስለተከሰተው ክፍፍልና እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ከፓርቲው ስለተገለሉበት ሁኔታ ተጠይቀው ሲመልሱ፤“ትልቅ ብቃትና ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች በአገር ግንባታ እንዳይሳተፉ ያደረገ ነገር በመሆኑ ያሳዝነኛል … በሰዓቱ የነበረን አስተሳሰብ ‹ከኢህአዴግ መስመር ውጪ ሁሉም የጥፋት መስመር ነው› ብሎ የሚያምን ስለነበር ተቃዋሚዎችን እንደፀጋ የማያይ፣ እግራቸውን እንዳይተክሉ የሚደርግ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ጎልቶ የታየን ግን እኛ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ …” ትክክል ብለዋል-ጄነራሉ፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያሉትም እነሱ ላይ ሲደርስ ነው ጎልቶ የሚታያቸው (ዛሬ የሚወጣ ህግና ደንብ ሁሉ ነገ በአውጪው ወገን ላይም ይሰራል!)
እናላችሁ … የ93 ዓ.ም ክፍፍል ለኢትዮጵያ ፖለቲካ A blessing  in disguise ነው፡፡ የትግራዩ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ገብሩ አስራትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የህውሓት አባላት በክፍፍሉ ባይባረሩ ኖሮ፣ “አረና” የሚባል ተቃዋሚ ፓርቲ ለትግራይ ህዝብ አይፈጠርለትም ነበር፡፡ (ህወሓትም የተፎካካሪን ስጋት አትረዳም ነበር!) የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ፤ በዚያው ክፍፍል ከህወሓት ባይገለሉ ኖሮ፣ዛሬ ለተቃዋሚዎችና ለነፃ ፕሬስ መብት የሚከራከር ነፃ ሰው አናገኝም ነበር፡፡ ለሪፖርተር ከሰጡት ቃለ ምልልስ ጥቂት ልቆንጥርላችሁ፡- “… አሁን ያለው መንግስት ‹ከእኔ በላይ ማን አለ?› የሚል ዕብሪትም ያለበት መንግስት ነው፡፡ የዲሞክራሲ ምህዳር እያጠበበ እያጠበበ ሄዷል፡፡ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እየተገደገበ ነው፡፡ አሁን ያሉትን ተቃዋሚዎች እንደ ፀጋ አያይም፡፡ … የተደራጀ የህዝብ እንቅስቃሴ ስጋት ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎችን የማዳከም ሥራ ነው የሚሰራው፡፡ ይህ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት  አደጋ ነው፡፡ …” ከህውሓት ወይም ኢህአዴግ ሳይወጣ ይሄን ዓይነት ነፃ ትንተና መስጠት አይሞከርም፡፡
ከትጥቅ ትግልና አገር ከመገንባት የትኛው ይከብዳል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ
ጀነራሉ እንዲህ መለሱ፤ “…የትጥቅ ትግል አስተሳሰብና የአገር ግንባታ አስተሳሰቦች መሰረታዊ ልዩነት አላቸው፡፡ ኢህአዴግ ራሱን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ግብዓት ከሆኑ እሳቤዎች ጋር አጣጥሞ የሄደ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የእኛ ትውልድ አማፂ ነው፡፡ የአማፂ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ መሆን አይችልም፡፡
ስለዚህ ሌሎች ፓርቲዎች ራሳቸውን በህገ መንግስቱና በዓለም ላይ ካሉ ዘመናዊ እሳቤዎች ጋር ማጣጣም ይኖርባቸዋል፡፡ የእኛ ትውልድ ከራሱ እሳቤና ተግባር ውጭ ያለን አካል መብት የማያከብር፣‹እኔ ብቻ ነኝ ልክ› የሚል አክራሪነት የሚታይበት ትውልድ ነን፡፡ ተ
ማሪ ሆነን ሰላማዊ ሰልፍ እንውጣ በምንልበት ጊዜ እምቢ ያለ ተማሪ ካለ ይመታል፡፡ ይህ በመሰረቱ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ እንጭጭነትም ነው፡፡ ስለዚህ የኛ ትውልድ የዲሞክራሲ ትውልድ አይደለም፡፡ የአመፅ ትውልድ ነው፡፡ የፀረ - ዲሞክራሲ ዘበኛ የነበረን ሥርዓት ግን በማስወገዱ እኮራበታለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ አዲሱ ትውልድ ተረክቦ መሄድ ነበረበት፡፡
ሆኖም የእኛ ትውልድ አሁንም ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ አልለቅም በማለቱ አሁን ለሚታየው ቀውስ ምክንያት ሆኗል” እኔ በበኩሌ ከ60ዎቹ ፖለቲከኞች ይሄን የመሰለ ሃቀኝነትና ቀና ግምገማ (ትችት) ሰምቼ አላውቅም፡፡ እናላችሁ የዲሞክራሲ ባህልና ሥርዓት ለምን እንደራቀን አሁን በደንብ ገባኝ፡፡ አሁን ጥያቄው ምን መሰላችሁ? በርግጥ ጥያቄው ለኢህአዴግ ነው! የአመፅ ትውልድ፤ለዲሞክራሲ ትውልድ ሥልጣን የሚያስረክበው መቼ ነው??

Read 12288 times