Saturday, 16 July 2016 13:10

ምርጫው ለእናትየው ይሰጥ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

በእግሩ የሚመጣን ልጅ የማዋለድ ሂደት በተፈጥሮአዊው መንገድ ይሻላል ወይንስ በኦፕራሲዮን?
ከአሁን ቀደም የወጡ ጥናቶች በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ከላይ በጥያቄ የተቀመጡትን ነጥቦች ለመመለስ የተጠናው ጥናት ርእስ (The risks of planned vaginal breech delivers versus planned caesarean section for term breech birth) ይባላል።
ይህ ጥናት ያተኮረው በመወለድ ወቅት በእግሩ የሚመጣን ልጅ በተፈጥሮአዊ መንገድ ከማዋለድ ይልቅ ካለምንም አስገዳጅ ሁኔታ በኦፕራሲዮን ለማዋለድ መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል ውጤት ያለው ነው። የዚህም ጥናት ባለቤቶች ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀንና ኃይለመላክ ሲሆኑ ይህ ጥናት በሮያል የጽንስና ማህጸን ኮሌጅ አማካኝት በ2015 ዓ/ም በህትመት እና በድረ ገጽ ለመላው አለም አንባቢዎች ተሰራጭቶአል።
ይህ ጥናት ይፋ በሆነበት ወቅት ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በዩኒቨርሲቲውም መምህር የነበሩ ሲሆን ዛሬ ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ እንዲሁም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኃላፊ ናቸው። ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን በርከት ያሉ ጥናቶችን እንዳጠኑና ለተለያዩ አለምአቀፍ ጆርናሎች እንዳበረከቱ የገለጹ ሲሆን ምናልባትም ከ50 በላይ ለንባብ መብቃታቸውን ገልጸዋል።
ጥናቱ ያተኮረበት breech birth የተባለው አንድ ሕጻን መወለጃው ሰአት ላይ በትክክለኛው መንገድ ወይንም በጭንቅላቱ ሳይሆን በእግሩ የመጣ ከሆነ የሚገለጽበት የህክምና ቋንቋ ነው። በአለም ላይ በአንድ ወቅት አንድ ጥናት ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ጥናቱ ግን ከዳር ሳይደርስ ከመሐል ተቋርጦአል። ያ ጥናት ግን በተወሰነ ደረጃ በእግር የመጡ ልጆች በተፈጥሮ በሚወለዱበት ወቅት የበለጠ ጉዳትና የበለጠ የመሞት እድል አላቸው የሚል ነገር አለው። ነገር ግን እኛ ባጠናነው ጥናት Relative risk & Absolute risk በሚል በአለም ላይ ያሉትን ጥናቶች በሙሉ Meta -Analysis በሚል ጥናት ለመዳሰስ እና እውነተኛው የትኛው ነው የሚለውን ለማሳየት ሞክረናል ብለዋል ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን። የ Meta -Analysis ጥናት ማለት ተመሳሳይ በሆነ ርእሰ ጉዳይ ላይ ከአሁን ቀደም በተለያዩ ሰዎች የተሰሩ እውቅ የሆኑ የተለያዩ ጥናቶችን ውጤት በመገምገም እና በወቅቱ ያለውን እውነታ በማገናዘብ የሚሰራ ጥናት ነው።ፕሮፌሰር Relative risk ያሉት በንጽጽር ሲታይ የሚደርሰውን ጉዳት ሲሆን Absolute risk የሚባለው ደግሞ በእርግ ጠኝነት የሚደርሰውን ጉዳት ለማመላከት ነው። ስለሆነም በእግሩ የመጣ ልጅ በተፈጥሮአዊ መንገድ ሲወለድ የሚደርሰው ጉዳት በጭንቅላቱ የመጣ ልጅ ሲወለድ ከሚደርሰው ጉዳት በጣም በትንሹ የሚለይ እንጂ የሚጋነን አለመሆኑን የሚያመላክቱ መረጃ ዎች አሉ። እንደፕሮፌሰር ይፍሩ ጥናት እማኝነት በኦፕራሲዮን መውለድ በተፈጥሮ ከመውለድ ይልቅ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል።
Baby Center Media Advisory Board በድረ ገጹ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው እናቶች ለመውለድ ሲዘጋጁ አስቀድመው ለአእምሮአቸው በኦፕራሲዮን መውለድ የሚባለውን መልእክት ባይነግሩ ጥሩ ነው። በተፈጥሮአዊ መንገድ መውለድ ጠቀሜታው ከፍ ይላልና። በተረፈ ግን ማንኛዋም ሴት በኦፕራሲዮን ለመውለድ ስትፈልግ አስቀድማ ለእራስዋ መመለስ ያለባት ጥያቄዎች አሉ።
ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነው በተፈጥሮአዊ መንገድ መውለድ ነው ወይንስ በኦፕራሲዮን መውለድ?
በኦፕራሲዮን ብወለድ ምን ችግር ሊገጥመኝ ይችላል?
ከኦፕራሲዮን ጋር በተያያዘስ ምን ውስብስብ ነገር ሊገጥመኝ ይችላል?
በኦፕራሲዮን መውለድ ለምወልደው ልጅስ ምን ችግር ይፈጥራል?
ለወደፊት በምፈልገው እርግዝና ላይስ የሚያስከትለው ችግር አለ?
ኦፕራሲዮን ከሆንኩ በሁዋላ እራሴን በደንብ ለመጠበቅና ለማዳን ምን ማወቅ ይገባኛል?
በኦፕራሲዮን መውለድ ጠቀሜታስ አለው?
የሚሉትንና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አስቀድሞ በማንሳት ከባለሙያ ጋር በቂ ምክክር ማድረግ ይበጃል። ምክንያቱም ምንጊዜም አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልገጠሙ በስተቀር በኦፕራሲዮን መውለድ አይመከርም። በተፈጥሮአዊ መንገድ መውለድ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።
እንደጽሁፉ በኦፕራሲዮን መውለድ እፈልጋለሁ የሚለው ውሳኔ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ተግባራዊ ቢደረግና የእናትየውን ወይንም የልጁን አለበለዚያም የሁለቱንም ህይወት ለማትረፍ ሲባል አማራጭ የሌለው መንገድ ሲከሰት ተግባራዊ ቢደረግ ይሻላል። በተለይም እናትየው
የሰውነት ክብደትዋ ከፍ ያለ ከሆነ፣
ቀደም ሲል በኦፕራሲዮን ልጅ የወለደች ከሆነ፣
በሕክምና የምትረዳ ከሆነ..ለምሳሌ...የልብ ታማሚ ከመሳሰሉት ከሆነች፣
በምጥ ለመውለድ አስፈላጊው ሰአት ተጠብቆና የተለያዩ የምጥ መርጃ እርምጃዎች ተወስደው የማያወለድ ከሆነ...ወዘተ...
ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን እንደሚሉት በኦፕራራሲዮን መውለድ ለእናትየውም ሆነ ለሚወለደው ሕጻና የወደፊት ጤንነት ችግር የሚፈጥርባቸው መንገዶች አሉ።
 .....በእርግጥ በኦፕራራሲዮን ሲወለድ ወዲያውኑ ለህጻኑ ምንም አይነት ጉዳት ላይደርስበት ይችላል። ነገር ግን አዳዲስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከተወለዱ በሁዋላ ቆይቶ የሚመጡ ችግሮች ግን ይስተዋላሉ። በእናትየው ላይ የሚደርሰው የደም መፍሰስ፣ የአካል መጎዳት ፣የማህጸን ወይንም ከዛ ውጪ ያለው የአካል ጉዳት፣ ኢንፌክሽን የመሳሰሉት እንዳሉ ሆነው በሕጻናቱ ላይ ደግሞ የተለያዩ ጉዳቶች ያስከትላል። አሁን ለምሳሌ በአለም ላይ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው እና ትክክለኛ መልስ ያላገኘው በኦፕራራሲዮን የሚወለዱ ልጆች ለአስም በሽታ የመጋ ለጣቸው ሁኔታ በ20 % ይጨምራራል። በዚህም የተነሳ በተለይም በአውሮፓ አገሮች ኦፕራራሲዮን ትልቅ መነጋገሪያ እየሆነ ነው። በኦፕራራሲዮን ከሚወለዱ ልጆች 20% የሚሆ ኑት ደግሞ በኦቲዝም ከአእምሮ ጋር የተያያዘ መያዛቸውም መነጋገሪያ ሆኖአል። ይህ ችግር የሚከሰተው በእርግጥ በኦፕራራሲዮን ስለተወለዱ ነው? ወይንስ በሌላ አጋጣሚ ነው የሚለውን ግን ማንም መገመት የቻለ የለም። በአጠቃላይ ግን በኦፕራራሲዮን በሚወለዱት ልጆች ላይ የተለ ያዩ የጡንቻና የጉሮሮ አካባቢ ሕመሞች በተለምዶው ሳይነስ የሚባለው ጎልቶ ይታያል።..
ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ ብለዋል ፕሮፌሰር ።
 .....ኦፕራራሲዮን መደረግ አስገዳጅ መሆን የለበትም። ልጁ በእግሩ ቢመጣም በተለይም ከአሁን ቀደም የወለደች ከሆነች በተፈጥሮአዊው መንገድ መውለድ እንደምትችል ስለሚታወቅ ምርጫውን ለእናትየው መስጠት ያስፈልጋል። በእግር የመጣን ልጅ ማዋለድ የሚችል ባለሙያ ካለ ልጁ በተፈጥሮአዊ መንገድ መወለድ ይችላል። በእርግጥ ጽንሱ የመታፈን አዝማሚያ ካለው ወይንም የምጥ መርፌም ተሰጥቶአት የማይሰራራ ከሆነ ወይንም ከፍተኛ መድማት ካጋጠማት ወይንም ሌላ አይነት የአመጣጥ ችግር ካለ አሳማኝ ምክንያት ስለሆነ ኦፕራራሲዮን መደረግ ግድ ይሆናል። ውሳኔውን ግን ለእናትየው መስጠትም ያስፈልጋል። በነገራራችን ላይ በእግሩ የመጣን ልጅ ማንኛውም አዋላጅ ሊያ ዋልድ አይችልም። የተለየ ብቃትን ይጠይቃል።
 ኦፕራራሲዮን ተደርጎ ልጅ መውለድ በአብዛኛው የታዳጊ አገሮች ፋሽን ነው። በአደጉት አገሮች ግን ቀደም ሲል እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1970 እና 1980ዎቹ ዓ/ም ልክ አሁን ባላደጉት አገሮች እንደሚደረገው ያለምንም ምክንያት ምንም አስገዳጅ ሁኔታ ሳይፈጠር ይፈጽሙት ነበር። አሁን ግን ምናልባት እናትየው ምክንያቱን ሳታውቅ ኦፕራራሲዮን ብትደረግ እንኩዋን ለምን ብላ እስከክስ ድረስ የምትደርስበት ሁኔታ ላይ ናቸው። በቅድሚያም በኦፕራራ ሲዮን ነው የምትወልጅው ስትባል ለምን ብላ የምታምንበት ምክንያት እስኪነገራራት የምትሟ ገትበት ሁኔታ አለ። በእርግጥ በውጭው አለም የምጥን ሕመም እንዳይሰማ የሚያደርግ መድሀኒት አለ። ይህ ባላደጉት አገሮች እስኪደርስ ገና ይቆያል።
 ማንኛዋም እናት በቤት ውስጥ ከመውለድ መቆጠብ አለባት። ምክንያቱም ሁልጊዜ የተስተካከለ ነገር ስለማይገጥምና ከመውለድ ጋር ተያይዞ ብዙ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ነው። በተለይም በእግሩ የመጣን ልጅ በቤት ውስጥ ማዋለድ እጅግ ይከብዳል። የእርግዝና ክትትል በሚያደርጉበትም ወቅት በዘጠኝ ወር ላይ ልጁ በእግሩ የመጣ መሆኑ ሲታወቅ ወደ ጽንስና ማህጸን ሐኪም መመራራት ይኖርባቸዋል። በስተመጨረሻም በወሊድ ወቅት ልጁ በእግሩ የመጣ መሆኑ ሲታወቅ እናትየውን ማማከርና በውሳኔው መሳተፍ ኖርባታል። ሐኪሞች ሊወስኑ የሚገባቸው አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ካለኦፕራራሲዮን መውለድ የማትችል መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ስለዚህም በእግር የመጣውን ሁሉ በኦፕራሲዮን ማዋለድ ትክክል አይደለም። ብለዋል ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀን።

Read 3649 times