Saturday, 16 July 2016 13:04

የዘረኝነት ልሳናትና ቀለማት መብዛታቸው!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(13 votes)

ከወልቃይት ጠገዴ ይልቅ ስለ ቦስተንና ፈርግሰን

  ከወልቃይት ጠገዴ እስከ ፈርግሰንና ቦስተን፣ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤስያ እስከ ደቡብ አሜሪካ፤ የዘረኝነት ሰበቡ ቢለያይም፣ መጨረሻው ተመሳሳይ ነው፡፡ ምናልባት፣ በደንብ ለመወያየትና የራሳችንን አስተሳሰብ ለመፈተን፣ የውጭ አገራት ክስተቶች ጥሩ መነጋገሪያ ሊሆኑን ይችላሉ፡፡ ለዛሬ ወደ አሜሪካ እናምራ - ራሳችንን ለመፈተን፡፡
“ብላክ ላይቭስ ማተር” በሚል መፈክር በርካታ አሜሪካዊያን፣ ለተቃውሞ አደባባይ ቢወጡ ይፈረድባቸዋል?
በአሜሪካ እስር ቤት ውስጥ ከታጎሩት 2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል፣ ግማሾቹ ጥቁሮች ናቸው፡፡ ከአገሪቱ ህዝብ ውስጥኮ፣ 15 ከመቶ ቢሆኑ ነው - ጥቁሮች፡፡ እስር ቤት ውስጥ ግን፣ 50 ከመቶ ጥቁሮች!
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ዘጋርዲን በእለት በእለት መዝገብ ላይ እንዳሰፈረው፣ ባለፈው ዓመት 300 ጥቁሮች በፖሊስ ሳቢያ ሞተዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ፣ 145 ጥቁር አሜሪካዊያን ህይወታቸውን አጥተዋል - በፖሊስ ምክንያት፡፡
“ፋኖ፣ ፋኖ … ጥራኝ ዱሩ …” ያሰኛል፡፡ “የጥቁር ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት” ለማቋቋም፤ ፀረ ነጮች ትግል ለማካሄድ፤ … ታዲያ ልብ በሉ፡፡ ይሄ ሁሉ፣ ዘረኝነትን ለመቃወም ነው፡፡ ጥያቄው ግልፅ ነው፡፡ አንደኛ ነገር፣ “ጥቁሮችን እስር ቤት ውስጥ ማጎር ይቁም፡፡” ሁለተኛ፣ “ፖሊስ ጥቁሮችን ከመግደል መታቀብ አለበት”፡፡
እነዚህ መፈክሮች፣ አዲስ ፈጠራ አይደሉም፡፡ በአሜሪካ ከተሞች፣ መንገድ በመዝጋት የተቃውሞ ድምፅ የሚያስተጋቡ ሰልፈኞች፣ እነዚህን መፈክሮች ሲደጋግሙ ሰንብተዋል፡፡ በርካታ የአገሪቱ የሚዲያ ተቋማት፣ ትልልቆቹ ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሳይቀሩ፤ እነ ሂላሪ ክሊንተንና በርኒሰንደርስ ጭምር፣ “የጥቁሮች ነፃ አውጪ” ለመባል የሚፎካከሩ ይመስላሉ፡፡
ችግሩ ምንድነው?
“ፋኖ ፋኖ” ብለን ዱር ሳንገባ፣ “ዛሬውኑ ሁሉም ነገር ይስተካከላል” ቢባል … ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡
በሦስት ዓመታት ውስጥ ከተፈፀሙት 40ሺ የግድያ ወንጀሎች መካከል ግማሾቹ፣ በጥቁር አሜሪካውያን ወንጀለኞች አማካኝነት የተፈፀሙ ናቸው፡፡ “ጥቁር አሜሪካዊያን” ብዬ በጅምላ እየፈረጅኩ አይደለም፡፡ “በጥቁር አሜሪካዊያን ወንጀሎች” ነው ያልኩት፡፡ እሺ፣ እነዚህን 20ሺ ወንጀለኞች ምን እናድርጋቸው?
“ጥቁሮችን እስር ቤት ማጎር ይቁም” ብለናል፡፡ እና ወንጀለኞቹ ይለቀቁ? ከእስር ከተለቀቁ እንደገና ለተቃውሞ ሰልፍ መውጣት ይኖርብናል፡፡ እነዚያን ወንጀለኞች ከእስር መልቀቅ ማለት፣ “ለጥቁሮች ህይወት ዋጋ አለመስጠት ነው” ብለን መጮህ የግድ ይሆናል፡፡ ለምን? 20 ሺዎቹ ጥቁር ወንጀለኞች፣ ግድያ የፈፀሙት 90 ከመቶ በጥቁሮች ላይ ነው፡፡ በወንጀለኞቹ ድርጊት 18 ሺ ጥቁሮች ሞተዋል፡፡ ይሄ ነገር እንዴት ነው?
ግን ምኑ ይገርማል? ብዙ ግድያ የሚፈፀመው፣ በቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ 20 በመቶ ያህል ግድያዎች፣ በባለትዳሮችና በፍቅረኛሞች መካከል ነው የሚከሰተው፡፡ ሚስቱን አልያም ፍቅረኛውን የሚገድል ወንድ፣ በዓመት ከአንድ ሺህ በላይ ይሆናል፡፡ ሌላስ? ጓደኛሞች፣ ጎረቤታሞችና በቅርብ የሚተዋወቁ ሰዎች ናቸው በብዛት የሚገዳደሉት፡፡ እናም፣ ጥቁር ወንጀለኞች 90 ከመቶ ግድያ የሚፈፅሙት በጥቁሮች ላይ መሆኑ አይገርምም፡፡ ነጭ ወንጀለኞችም እንዲሁ፣ 90 ከመቶ ግድያ የሚፈፅሙት በነጮች ላይ ነው፡፡
እና እነዚህን መረጃዎች ስንመለከት ምን እንበል? “ጥቁሮችን እስር ቤት ማጎር ይቁም” የሚለውን መፈክር ምን እናድርገው? ያው፤ እንደድሮው መፈክራችንን ይዘን እንቀጥላለና፡፡ መረጃ ገደል ይግባ! በወንጀለኞቹ የተገደሉት 18ሺ ጥቁሮችስ?
እንዲህ አይነት ጭቅጭቅ አያስፈልገንም፡፡ “ደግነቱ”፣ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች፣ እነዚህን መረጃዎች የመጥቀስ ዝንባሌ የላቸውም፡፡ “ዘረኛ” ተብለው እንዳይፈረጁ ይሰጋሉ፡፡ ስለዚህ “ጥቁሮችን እስር ቤት ማጎር ይቁም” የሚለው መፈክር ይቀጥላል፡፡   
ይሄ መፈክር ተቀባይነት ቢያገኝና ተግባራዊ ቢሆን፣ ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች እነማን ይሆናሉ? ጥቁር ወንጀለኞች ይጠቀማሉ፡፡ ተጎጂዎችስ? በእነዚህ ወንጀለኞች ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰላማዊ ጥቁር ሰዎች ናቸው ተጎጂዎቹ፡፡
“ጥቁሮች”፣ “ነጮች” በሚል የጅምላ ፍረጃ የሚካሄድ የዘረኝነት ዘመቻ፤ ቋንቋውና ቀለሙ ምንም ቢሆን፤ በየትኛውም ዘመንና አገር መጨረሻው አያምርም፡፡ መጥፎ ሰዎች ናቸው ተጠቃሚ የሚሆኑት፡፡
እሺ፣ የእስር ቤቱ ጉዳይ ይቅር፡፡ ግን፣ በፖሊስ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ጥቁሮች ጉዳይስ? ይሄንን መቃወምስ ተገቢ አይደለም?
ጥቁርም ይሁን ነጭ፣ ቢጫም ይሁን ቡናማ፣ ማንም ሰው፣ አላግባብ ህይወቱን ማጣት የለበትም፡፡ አይደለም እንዴ? ግን በዚህ ሃሳብ የማይስማሙ ይኖራሉ፡፡ ጥቂት ቢሆኑም፣ ዘረኛ ነጮች፣ ይህንን ላይደግፉ ይችላሉ፡፡ በዚያው መጠን፣ “የጥቁሮች ህይወት ነው የሚያሳስበኝ” ብለው የሚከራከሩ ጥቂት ዘረኛ ጥቁሮች አሉ - “ብላክ ላይቭስ ማተር” እንዲሉ፡፡
ምሬታቸው ሲዘረዝሩም፤ በፖሊስ ምክንያት በአማካይ በየቀኑ አንድ ጥቁር ይሞታል በማለት ይከራከራሉ፡፡ በቪዲዮ የተቀረፁ አሳዛኝ የግድያ አጋጣሚዎችንም በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ በእርግጥም፣ አንዳንዶቹ ይዘገንናሉ፡፡ ዘጋርዲያን እና ዋሺንግተን ፖስት ደግሞ፣ የየእለቱን ክስተት በቁጥር እየመዘገቡ፣ ዘመቻውን በደጀንነት የሚደግፍ መረጃ ይመግባሉ፡፡ ባለፈው ዓመት 300 ጥቁሮች፣ ዘንድሮም በስድስት ወራት 145 ጥቁሮች እንደሞቱ የሚዘረዝር መረጃ ያየ ሰው፣ ፖሊስን እያወገዘ ለተቃውሞ ሰልፍ መትመም የለበትም? የጥቁር ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት ቢያቋቁምስ ምን ይገርማል?
በእርግጥ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በፖሊስ ምክንያት እጥፍ ያህል ነጮች ይሞታሉ፡፡ እዚያው የዘጋርዲያን እለታዊ መዝገብ ውስጥ መረጃውን ማግኘት ይቻላል፡፡ አምና 580 ነጮች ሞተዋል፡፡ ዘንድሮ በስድስት ወራት ደግሞ፤ 290 ነጮች በፖሊስ ምክንያት ሞተዋል፡፡
ለዚህስ መፍትሄው ምንድነው?
የነጮች ነፃ አውጪ ድርጅት ማቋቋም ይሆን መድሃኒቱ?
እዚህ ላይ፣ አንድ ማስተካከያ መረጃ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ አዎ፣ በፖሊስ ምክንያት የሞቱ ነጮች፣ በቁጥር እጥፍ ያህል ይበልጣሉ፡፡ ነገር ግን፤ ከጠቅላላው የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር፣ ነገርዬው የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ነጮች መካከል፣ ሶስቱ በፖሊስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ጥቁሮች መካከል ስምንቱ በፖሊስ ምክንያት ይሞታሉ፡፡ በዚህ አቅጣጫ ስናየው፤ “ጥቁሮች ላይ ግድያ በዛ” ሊያስብል ይችላል፡፡ ግን ይህንን በማየት፤ ግድያውን ከዘር ልዩነት ጋር ለማቆራኘት መሯሯጥ አለብን ወይ?
ሁሉም ነጭ ሰው አንድ አይነት ባህርይ እንደሌለው፣ ሁሉም ጥቁር ሰው አንድ አይነት ዝንባሌ እንደሌለው፣ ሁሉም አስተማሪ፣ ሁሉም ሾፌር፣ ሁሉም ሀኪም፣ ሁሉም ፀሐፊ አንድ ዓይነት ባህርይ እንደሌለው እናውቃለን፡፡ ፖሊሶችም እንዲሁ፣ የጋራ ማብሪያና ማጥፊያ፣ የጋራ ቆጣሪ፣ የጋራ አእምሮ የተገጠመላቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ አንዱ ፖሊስ ከሌላኛው ፖሊስ፣ በሃሳብ፣ በችሎታ፣ በባህርይ ይለያል፡፡ የዘረኝነት አባዜ የተጠናወታቸው ጥቂት ፖሊሶች እንደሚኖሩም አያጠራጥርም፡፡ እናም፣ እነዚህኑን ማውገዝ፣ ለህግ እንዲቀርቡም መጣጣር፣ ለሙያና ለፍትህ የቆሙ ፖሊሶችን ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ አሁን የምናየው የተቃውሞ ዘመቻ ግን፣ “ፖሊስ ጥቁሮችን እየጨፈጨፈ ነው” የሚል ስሜት ለመፍጠር ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ እነ ሲኤንኤን እና ዘጋርዲያን የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማትም ያለማሰላስ አቧራውን ያራግባሉ፡፡ “የጥቁሮች ተቆርቋሪ” የሚል ማዕረግ ለማግኘት ይፎካከራሉ፡፡ ስሜታቸውና ሃሳባቸው ከመረጃ ጋር ይጣጣማል ወይ ብለን ስንጠይቅ ግን ችግር ይገጥመናል፡፡
በፖሊስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን በእድሜ ከፋፍሎ ለማየት የሚሞክር ሰው፣ ሁለት የተራራቁ ልዩነቶችን መገንዘብ ይችላል፡፡ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ወይም ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ላይ፣ በፖሊስ ምክንያት ብዙም የሞት አደጋ አይደርስም - የዘር ወይም የቀለም ልዩነት አይስተዋልም፡፡ ከጠቅላላ የአገሪቱ ህዝብ ውስጥ 60 ከመቶ ነጮች የመሆናቸው ያህል፣ ከሟቾቹ መካከልም 60 ከመቶዎቹ ነጮች ናቸው፡፡ የሟች ጥቁሮች ቁጥር ደግሞ የዚያኑ ያህል አነስተኛ ነው፡፡
እድሜያቸው ከ18 እስከ 34 የሆኑ ሰዎች ላይ ግን፤ በፖሊስ ምክንያት የሚሞቱ ነጮችና ጥቁሮች ቁጥር ተቀራራቢ ነው፡፡ ለምን?
ፖሊሶች በአንዳች ሰበብ፣ ወጣት ጥቁሮች ላይ ልዩ ቂም ይዘው ይሆን?
በቂም፣ በዘረኝነት ወይም በእኩይ ባህርይ የተነሳ፣ ሰላማዊ ሰዎችን፣ የሚገድሉ በጣም ጥቂት ፖሊሶች አሉ፡፡ በተለምደው ህጋዊ ስርዓት መክሰስና መቅጣት ነው መፍትው፡፡ አብዛኞቹ የሞት አደጋዎች የሚከሰቱት ግን በዚህ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ ነገርዬው፣ ቀደም ሲል ካነሳነው ተጨባጭ መረጃ ጋር የተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ ማለትም፤ በአገሪቱ ውስጥ ከሚከሰቱ የግድያ ወንጀሎች መካከል፤ ግማሽ ያህሉ የሚፈፀመው በወጣት ጥቁር ወንጀለኞች ነው፡፡ በዚያው መጠን ከፖሊስ ጋር የመፋጠጥ አጋጣሚውም ብዙ ይሆናል፤ በዚያው ልክ የመሞት አደጋውም ይበዛል፡፡
ይሄ የግምት ጉዳይ አይደለም፡፡ በፖሊስ ጥይት ከተገደሉት ሰዎች መካከል፣ 90 በመቶዎቹ መሳሪያ ታጥቀው ነበሩ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ለመግደል የሚተኩስ ወንጀለኛ በብዛት የሚያጋጥምባት አገር ናት አሜሪካ፡፡ በየቤቱ 400 ሚሊዮን የጦር መሳሪያ የተሰራጨባት አገር ናት፡፡ ከሽጉጥ እስከ አውቶማቲክ ጠመንጃ የታጠቁ ወንጀለኞችን፣ በልመናና በልምምጥ መያዝ ማሰር አይቻልም፡፡
እናም በዓመት 580 ነጮች፣ 300 ጥቁሮች ሲሞቱ፣ በዚያው ዓመት 120 ፖሊሶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ያው፤ ወንጀለኞችን መከላከልና ማሳደድ አደገኛ ስራ ነው፡፡ ፖሊሶች በዘፈቀደ፣ በየጎዳናው ሰላማዊ ሰዎችን እንደሚገድሉ እያስመሰልን የምንናገረው ታዲያ ለምንድነው? የዘር ታፔላ ለመለጠፍ፣ የቀለም ባንዲራ ለማራገብ ለምንቸኩለውስ ለምን ይሆን? “የጥቁሮች ተቆርቋሪ” ለመባል?
እንዲያው፣ ፖሊሶችን በጅምላ የሚፈርጅና የሚያወግዝ ዘመቻችን ቢሳካ፣ ምን እናተርፋለን? ማን ይጠቀማል? ወንጀለኞች እንደልብ ይፈነጫሉ፡፡ ለምን በሉ፡፡ ውግዘት የበዛባቸው ፖሊሶች፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ለመቀነስ ተገደዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በአብዛኞቹ ከተሞች የወንጀል ድርጊት ባለፉት ስድስት ወራት ጨምሯል፡፡ በወንጀለኞች ምክንያት በብዛት ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ፣ ሰላማዊ ጥቁሮች ናቸው፡፡ የዘር ታፔላንና የጅምላ ጥላቻን የሚያራግብ የዘረኝነት ሆይሆይታ፣ ውሎ አድሮ ወንጀለኞችን የሚጠቅም ነው፡፡

Read 6565 times