Saturday, 16 July 2016 12:57

ለራስ ስንቆርስ ባናሳንስ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(11 votes)

አንዳንድ ጊዜ …
… ድንገት የሚጣሩ መፅሐፍት አሉ፤ “ውል” ይሉናል፡፡ “በአልጋ ቁራኛ ቨደዌ ዳኛ” ተይዞ ድንገት አማረኝ እንደሚላቸው እህል ውኃ ፈጥርቀው ይይዛሉ፡፡ ከህይወት ወደ ሞት መዳረሻ “ስንቅ” ይመስል፡፡ ይሄን ጊዜ በራሴ መሳቅ ይከጃጅለኛል፡፡ አንድ መፅሐፍ (ቀደም ሲል የተነበበ) ድንገት ደርሶ የህይወትና ሞት ጥያቄ ሆኖ በአስፈላጊነት እራሱን መሾሙ ከምን እንደሚመነጭ ግራ ያጋባኛል፡፡
አንዳንድ ጊዜ …
… መፅሐፍ የማይገኝ ይሆናል፡፡ ሲታሰስ ቢውል የሚሸጥ ሆነ የሚያውስ ይጠፋል፡፡ ያኔ “የፍቅር እስከ መቃብሩን” አያ ቦጋለ መብራቱን መሆን ነው፡፡ ባለቤታቸውን “ውዴ፣ ጠላ አማረኝ፤ ወፍራም ጠላ አማረኝ” ያሉት ህመምተኛ፡፡ ተጨንቆ ማስጨነቅ ይከተላል፡፡ እመት ውድነሽ በጣሙ ይታወሱዋችሁ ፡፡ እንዲህ ያሉት፡-
“ብሪቱ፣ ሻሼ፣ ደብሪቱ፣ በላይነሽ ቶሎ ጠላ አምጡልኝ፡፡ የሞት መድሃኒት የሚሆን ጠላ!”
“የሞት መድኃኒት የሚሆን መፅሐፍ”
… አሁን ከወራት በፊት እንዲህ አድርጎኝ ነበር፡፡ ካንዴም ሁለት ሶስቴ ያነበብኩት መፅሐፍ “የሞት መድኃኒት” መስሎ “ውል” አለኝ፡፡ መፅሐፉ የነገሮ-ዋቅጅራ ወይም የአለቃ ተክለኢየሱስ “የጎጃም ታሪክ” ነው፡፡ ዝግጅትና ሐተታን እንዲሁም አርትኦት ጨምረው ከግዕዝ ወደ አማርኛ የመለሱት ዶ/ር ስርገው ገላው፣ የርዕሱን መጥበብ፣ የይዘቱን መስፋት በማየት “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል አሳትመውት ነበር፡፡ ሳነበው ልብ ያላልኩት የኖረ የነፍስ ጥማቴ ሲረካ ታውቆኝ ነበር፡፡ መልሶ መላልሶ ሊጠማኝ፡፡ እና ፈለኩት፤ በፈለኩት መጠን ጠፋ፤ በጠፋ መጠን ፈለኩት፡፡ አስታውሳለሁ፤ አንድ አሮጌ መፅሐፍ ሻጭ “ጠብቀኝ” ብሎ ከሰዓታት በኋላ አንድ መፅሀፍ ይዞልኝ መጣ፡፡ መፅሀፉ የአለቃ ተክለኢየሱስ ይሁን እንጂ ሌላ ነው፡፡ “የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ” በሚል ግርማ ጌታሁን የተረጎሙት፡፡ ልጁን አየሁት፤ ላብ በላብ ሆኗል፡፡ መፅሀፉን በማግኘቱ ፊቱ ላይ “አልቻልም” ያነበብኩ መሰለኝ፡፡ መፅሐፉን “አይደለም” ማለት የሚፈጥረውን የስሜት መናጋት በማሰብ፣ አመስግኜ ባለኝ ዋጋ ገዛሁት፡፡
አንዳንድ ጊዜ …
… ይሄ ነው… ያልከውን ታጣለህ፣ ያላልከውን ይዘህ ትመለሳለህ፡፡ ግርንቢጥ አለም፡፡ ቢቸግረኝ እራሳቸው ዶ/ር ስርግው ገላው ጋ ስልክ መታሁ፡፡ በትህትና ተቀበሉኝ፡፡ መፅሀፉ ግን አልነበራቸውም፡፡ ያላቸውን አንድ ቅጂ ለአርትኦት ስራ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ነገሩኝ፡፡
“ሊታተም ነው?” ስል ጠየኳቸው
“አዎ፤ እስከዚያው ለተወሰኑ ቀናት ያለኝን አንድ ቅጂ ላውስህ?” ሲሉ የጭንቅ ግብዣ አቀረቡልኝ፡፡
“አመሰግናለሁ፤ ግን እኔ ተውሼዎት አርትኦቱ ከሚደናቀፍ ቢቀርና ቶሎ ቢታተም ይሻለኛል፡፡” በዚሁ ተስማምተን ተለያየን፡፡
አንዳንድ ጊዜ …
… ለፍላጎት ከመነዳት፤ ፍላጎትን መለስ ብሎ መመርመር ማስታገሻ መድኃኒትነት አያጣም፡፡ መፅሐፉን ለምን እንዲህ ፈለኩት? መፅሀፉስ እንዲህ ለምን ፈተረኝ? ውስጤ ምን ጎድሎ ደመነፍሴ ወደዚያ መፅሀፍ መራኝ? ያነበቡትን መፅሀፍ ከማሰስ፣ ያልተነበቡት ውስጥ ተስማሚ መፈለግ አይሻልም?
… ይኼም ሆኖ መፅሀፉን መጠየቄን አላቆምኩም ነበር፡፡ አንድ ወዳጄን ስጠይቀው በትዝብት አየኝ፡-
“ምነው?” አልኩት
“ይሄን መፅሀፍ ለሶስተኛ ጊዜ ስትጠይቀኝ ነው” አለኝ፡፡
“ጠይቄህ ነበር?”
“እ -- ግን መፅሀፉን እንዳነበብከው ነግረኸኛል፡፡ እኔም አንብቤዋለሁ፡፡ እንዳንተ መውደድ ቀርቶ እንደውም አናዶኛል”
“እንዴት?”
“ፀሐፊው እራሱን ይቆልላል፡፡”
“ማን? አለቃ ተክለኢየሱስ”
“አዎ፣ ብዙ ቦታ እራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ሲያጋጥመኝ ቋቅ ይለኛል፡፡ አንብቤ ስጨርስ መፅሐፉን አንድ ቀን ቤቴ አላሳደርኩም፡፡ ለሰው ሰጠሁት፡፡ አንዳንድ ሰው ይሄው ነው፡፡ ማሸነፍ የሚችልበት ተሰጥኦ እያለው ሽልማቱን በጉልበት ለመውሰድ ይተናነቃል፡፡” (ቃል በቃል እንዲህ ያለኝ ይመስለኛል፡፡)
ከዚህ አንፃር መፅሀፉን የማየት ሌላ ጉጉት ….
… መፅሀፉ እስከሚገኝ የወዳጄ አስተያየት አብሮኝ ቆይቷል፡፡ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” የሚለው ነባር ብሂል በውስጡ ትልቅ ማህበራዊ ሂስ አርግዟል፡፡ ነቀፌታ ልንለው እንችላለን፡፡ ይሄ ብሂል ካፎቱ የተመዘዘበት ሰው መሞካሸት አይሰማውም፡፡ እንደውም “ራስ ወዳድ” የምትለውን ስድብ ተፈጥሯዊ አስመስለው እንደማቅረብ ያለ አዝማሚያነት አለው፡፡ እንግዲህ በዚህ ብሂል እየተሞረድን አድገን፣ ከእኛ የሚጠየቅን ከመፈፀም እናልፍና ከሰው ሲያጋጥመን ወደ መጎፍነኑ ያዘነብልብናል፡፡
አንዳንድ ጊዜ …
…. ይሄ ብሂላችን የሚገርም ነገር ያስተናግዳል፡፡ ፉከራን ያህል ግዳይ የመዘርዘር (ጉራ የመንፋት ልንለው እንችላለን) ባህል እያበረታታን፣ ከዚያ ውጭ ያለውን ሳያሳንሱ ለራስ መቁረስ እናወግዛለን፡፡ ግራ ግብት አይልም?
*           *         *
መፅሐፉ ሲታተም አንድ ወዳጄ ቤቴ ድረስ ላከልኝ፡፡ ጉጉቴ አልበደረም፡፡ ከ430 በላይ ገፆች አሉት፡፡ ከዚህ ውስጥ አዘጋጁ ዶ/ር ስርግው 95 ገፁን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ምርምራቸውን አቅርበውበታል፡፡ የመፅሐፉን ምላትና ቀርነት ከመተንተን አልፈው እንደ ማሟያ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ያቀርባሉ፡፡ የአለቃ ተክሌን ዋና ዋና ሰዎች ተከትለው የማፍታቻ ገለፃ ይሰጣሉ፡፡ ዶ/ር ሰርግው በመፅሐፉ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ብዙ ጥያቄዎችንና እንቅፋቶችን ቀድሞ የመጥረግ ትልቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ አንዳንድ የታሪክ መፅሐፍ አርታኢም እያለው የአባት ስም እንኳን ሳይሟላ፣ በገረፍ-ገረፍ መውጣቱን ተመልክተን፣ እንዲህ የተደከመበት ስራ ሲቀርብልን፣ የምስጋና ንፍገት ማሳየት ተገቢነት አይኖረውምና ዶክተር ስርግውን አመስግነን እንቀጥል፡-
አለቃ ተክሌ ይሄን መፅሀፍ ከ1901 እስከ 1916 ዓ.ም ባሉት ዓመታት መካከል እንደፃፉት ዶ/ር ስርግው አገናዝበው ደርሰውበታል፡፡ አለቃ በአካል የነበሩትን በምስክርነት ከማቅረብ አልፈው የታሪክ መዛግብትን አገላብጠው፣ አዛውንትን አነጋግረው የመፅሀፉን ግዛት ወደ ኋላ እስከ አዳም ድረስ ይገፋታል፡፡ አለቃ ተክሌ ከመዛግብት መርምረው ከወሰዱት በላይ በአካል የተገኙበት ዘመን ላይ 1881 እራሳቸውን እያስገቡና ፍርድ እየሰጡ በሰፊው ያትታሉ፡፡ እርግጥ እንዲኖሩበት ዘመን አይብዛና አይጠንክር እንጂ በታሪክ መዛግብት ያገኙት ሁነት ላይ አቋማቸውን መግለፃቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌ ያህል ማህሌታይ ያሬድንና ተዋነይን የሚተቹበት አግባብ ከተለመደው ኢትዮጵያዊ አቋም ጋር ቀጥታ የሚላተም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ማህሌታይ ያሬድን ገፅ 114 ላይ እንዲህ ይሉታል፡-
‹‹…በዚያም ዘመን በትግሬ የዛር ዘፈን በዛ፤ በቤተክርስቲያን እስቲዘፈን ድረስ፡፡ በዚያውም ወራት አንድ ድምፁ መልካም ደብተራ ተነሳ፤ በግዕዝ ቋንቋ የሚዘፍን ማኅሌታይ፤ ስሙ ያሬድ የተባለ፡፡ … ያሬድ ዜማ ከተጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ ትምህርት ጠፋ፡፡ በኢትዮጵያ ሊቃውንት ህፃናቱም ኑሮዎቸውን ብቻ በዜማና በቅኔ አድርገውት ይኖራሉ፡፡ ሌላ ትምህርት አላገኙም፤ በዚህ ምክንያት ምስጢረ ሥጋዌን የሚያውቅ ሰው ታጣ፡፡ የቴዎሎጎስ (የቴዎሎጂ፣ ነገረመለኮት) ትምህርትና ክርክር አልተሰበከም፡፡ በክርስቶስ ላይ ይሟገታሉ፤ ወዲያው ይጠነቁላሉ፤ ወዲያው ኃይማኖታቸውን ይጥላሉ፡፡ ደግሞ የያሬድ ጥበብ ብዙ ሰው አቦዘነ፡፡ የቅኔውም ግጥም የተጀመረ በዚያ ወራት ነው፡፡ ምልክቱም ያስታውቃል፡፡ በልደትና በፀሎት ሐሙስ፣ በቅዳሜ ስዑር፣ በትንሳኤ፣ የእጣነ ሞገር ምልክት በትንሳኤ ዘጉባኤ ቃና እስከመወድስ እስከዛሬ ያመለክተናል፡፡ የቅኔ ብልሃት ኢትዮጵያን አደኸየው፡፡ አንድ ሰው ቅኔ ሲማር አሥር ዘመን ተቀመጠ፡፡ በሰው አሳብ ቁራሽ እየለመነ፤ ላይረባ ዕድሜውን በከንቱ ጨረሰው፡፡››
አለቃ ተክሌ ለታሪክ ድርሳን ባልተገባ አኳኋን ከጠሉና ከወደዱ ጣልቃ ለመግባት አያንገራግሩም፡፡ ፀብ የገጠሙን የታሪክ ሰው፤ ከራቀ በብዕር ቅዝምዝም፣ ከቀረበ በምክቶሽ ይፋለሙታል፡፡ እንደ ማህሌታይ ያሬድ ሁሉ የቅኔውን ሊቅ ተዋነይን፤ ‹‹የጎንጅ ደብተራ ጠንቋይ የነበረው…›› ይሉታል፡፡ በተረፈ መፅሐፉ የትርክት አፈሳሰስና የቋንቋ ትባቱ ከስሩ እንዳይለዩ ፈትሮ የሚይዝ ነው፡፡ በተለይ በብዙ የታሪክ መፅሐፍቶቻችን ላይ የማይስተዋል ጠባዩ አስገራሚና አስደማሚ የተራ ሰዎች ገጠመኞችን ማካተቱ ነው፡፡ ታሪካችን (አሁንም ቢሆን) ከንጉሱ እራስ የማይወርድ ዘውድ አከል ባህርይ መያዙ ለቆጫቸው በከፊልም ቢሆን የአለቃ ተክሌ መፅሐፍ ምላሽ ይዞ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ስም የለሾች ስም ያለው ሥራ ሰርተው እንዳለፉ ሲነገረን ከመገረም በላይ የመዝናኛነት ጠባይም አለው፡፡ ለምሳሌ ባሻ ውድነህ እናንሳ፡፡ ባሻ ውድነህ አፄ ቴዎድሮስ ጋፋት በግዳጅ ስራ ያሰሯቸው ከነበሩ ፈረንጆች ልምድ ቀስሞ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊት መድፍ የሰራ ነው፡፡ ባሻ ውድነህ ከራስ አዳል ጋር ሆኖ፣ ከራስ ደስታ ጋር ሲዋጋ የሰራውን መድፍ ተጠቅሞ እንደነበር አለቃ ይነግሩናል፡፡
‹‹ያን ቀን ውዴ የኮሶ እሸት፤
በሰራው ገዳይ እንደ መለኮት፤… ብሎ ቢተኩስ የራስ ደስታ በቅሎ ደንግጣ ተንበረከከች›› ይሉናል፡፡ ባሻ ውድነህ ለምን አልቀጠለም? ከሱ ወዲያ መድፍና ነፍጥ ፈረንጅ ስንለምን አልኖርንም?.....
…. የአለቃ ተክሌ ሥራ ከአገር ጉዳይ አልፎ በሰው ጠባይም እንድንደመም ግድ የሚሉ ታሪኮች ይዟል፡፡ በአፄ ምኒሊክ ዘመን በከብት ማለቅ በተነሳው ረሃብ ማግሥት የሚቀርብልን የአንዲት ስም የለሽ ታሪክ፤ በእርግጥም የሰው ልጅን ፍላጎት መዝምዞ ለማሳየት ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ ‹‹ጥጋብ በሆነ ባመቱ›› ይላሉ አለቃ ተክሌ ‹‹የሰናን ኢየሱስ ደገኛ (የደጋ ሴት) ድንች ያወፈራት እንኳን ባመቱ በኑኃ ዘመን (ዝንተ አለም) የማይረሳውን ዘመነ ረሃቡን ድሮ ረስታው ጠገበችና እንዲህ አለች፡-
    ጉንጨም ቅጥ አጣ፣ ቂጤም ቅጥ አጣ
      እባክህ ጌታየ የአምናውን ቀን አምጣ፡፡…. ብላ ዘፈነች፡፡ ይህ ነገር በንጉሡ በተክለሃይማኖት ጆሮ በደረሰ ጊዜ አስመጥቶ አርባ ገርፎ ወህኒ አስሮ ወፍሩዋ ጎድሎ፤ እንደጨርቁዋ ቅል ገላዋ ሲጨማደድ ፈትቶ ለቀቃት፡፡›› (ገፅ 294)
ይቺ ታሪክ ወደ ሰው ልጅ ሁሉ ተፈናጥራ የምትደርስ የእሳት ፍንጣቂ ትመስላለች፡፡ ከተራበ ለጠገበ መታዘኑ ለምን ይሆን? የሚያደርጉትን የሚያሳጣው ረሃብ ሳይሆን ጥጋቡ በመሆኑ አይደለም? ድሎት ከችግር በላይ የሚፈትነን አፈጣጠራችን ምን ቢሆን ነው? የዛሬውን እዚህ ላይ ገትተን፣ ሳምንት አለቃ ተክሌን ለመቀጠል ይቺን ተረት ይዘን እናመንዥክ እስቲ ፡፡
‹‹ትፀድቅ ትኮነን ቢሉት ቆይ መክሬ አለ አሉ››

Read 6094 times