Print this page
Saturday, 16 July 2016 12:19

በጎንደሩ ግጭት የበርካቶች ህይወት አልፏል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(103 votes)

       ባለፈው ማክሰኞ በጎንደር ከተማ በነዋሪዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የበርካቶች ህይወት ማለፉ የተገለፀ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ በግጭቱ የ3 ፖሊሶችና 2 ነዋሪዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ በተለያዩ (የሚዲያዎች የተገለፁ መረጃዎች ይለያያሉ፡፡ አልጀዚራ የአይን እማኞችን ጠቅሶ 10 ሰዎች መሞታቸውን ሲዘግብ፤ ሌሎች ሚዲያዎች የሟቾች ቁጥር እስከ 20 ሊደርስ እንደሚችል ዘግበዋል፡፡ማክሰኞ ዕለት 6 የወልቃይት ማንነት ጉዳይ ኮሚቴ አባላትን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሙከራ ማድረጉን ተከትሎ ግጭቱ መቀስቀሱ የተገለፀ ሲሆን ፖሊስ 4ቱን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና 2ቱ እስካሁን እንዳልተያዙ አስታውቋል፡፡ በተለይ አንደኛውን ተጠርጣሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ፖሊስ ለመያዝ ሙከራ ባደረገበት ወቅት በተከፈተ ተኩስ የነዋሪዎችና የፖሊስ አባላት ህይወት ጠፍቷል ተብሏል፡፡ ትናንት ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሠጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ‹‹ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ፖሊስ ሁለቱን ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ ቦንብ በመወርወር፣ አውቶማቲክ መሣሪያዎችን ተጠቅመው በፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ በመክፈት በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ገድለዋል›› ብለዋል፡፡ማክሰኞ እለት የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ረቡዕ እለት በርካታ የጎንደር ከተማዋ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው በመንግስት ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ መዋላቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ በተቃውሞ መሃል ‹‹ጀግናው ምናለ ሃገሬን ለሰው አልሰጥም አለ››፤ ‹‹ይለያል ዘንድሮ›› የሚሉ ፉከራዎች በስፋት ይስተጋቡ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ነዋሪዎች አደባባዮችን እየዞሩ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደዋሉም የሚጠቅሱት ምንጮች፤ ከፖሊስ ጋርም ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ በግጭቱ የሞቱ አንድ ግለሠብን የቀብር ስነስርአት ለማስፈፀም አያሌ ቁጥር ያለው የከተማው ነዋሪ ወደ አደባባይ መውጣቱን የሚገልጹት የአይን እማኞች፤ የለቅሶ ስነስርአቱም በሽለላና በፉከራ እንዲሁም በከፍተኛ የተኩስ እሩምታ የታጀበ እንደነበር ጠቅሠዋል፡፡ ሆኖም በእለቱ ከፖሊስ ጋር ግጭት አለመፈጠሩን ያወሳሉ፡፡ በትላንትናው እለት ከተማዋ በአንፃራዊነት ተረጋግታ መዋሏን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፤ “ጉዳዩ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር አይያያዝም፤ ከኮሚቴው አባላት መካከል ሊቀመንበሩን ጨምሮ ሌሎች በሠላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ በፖሊስ ሲፈለጉ የነበሩት ግለሰቦች በአንፃሩ ግድያና ዝርፊያ በመፈፀም በትጥቅ ትግል ጭምር ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ የነበሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ግለሰቦቹ ከግንቦት ሰባትና ከኤርትራ መንግስት መሣሪያ ይቀርብላቸው፤ ስልጠናም ይሰጣቸው ነበር ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡ ግጭቱ መረጋጋቱን የገለፁት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ሆኖም ሁከቱን ወደተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋፋት ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

Read 12888 times