Saturday, 16 July 2016 12:34

በቤቶቹ ፍርስራሾች ላይ ተፈናቃዮች ተጠልለዋል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“መንግስት እንደፈለገ ያድርገን ብለን ቁጭ ብለናል”

   በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ‹ማንጎ› የተባለው አካባቢ፣በቤት ፍርስራሾች ተሞልቷል፡፡ ቦታው በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ የወደመ ነው የሚመስለው፡፡  የወዳደቁ የቤት ፍራሽ እንጨቶች፣የተጨረማመቱ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ለዓይን ይታክታሉ፡፡ በፍርስራሾቹ ጥጋጥጎች ላይ በተጨረማመተቱ ቆርቆሮዎችና በፕላስቲክ የተሰሩ ዳሶች በብዛት ይታያሉ፡፡ በቤቶቹ ፍርስራሾች ላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አረብ ሀገር ሰርታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ከአርሶ አደር ላይ ቦታ ገዝታ ባለ 3 ክፍል ቤት በመሥራት፣ ላለፉት 10 ዓመታት በቦታው ላይ መኖሯን የምትናገረው ወጣት ትገኝበታለች፡፡  
  ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት ስትሆን፤ ቤቷ ከፈረሰ በኋላ ከእነቤተሰቦቿ እዚያው ፍርስራሹ ላይ በፕላስቲክና በቀዳዳ ቆርቆሮ ከለላ ሰርታ መጠለሏን ገልጻልናለች፡፡   
በህይወቴ እንዲህ ያለ ምስቅልቅሎሽ አጋጥሞኝ ቀኑ ይጨልምብኛል፣ መግቢያ አጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር የምትለው ወጣቷ፤መሄጃ አጥቼ ከእነልጄ ጭቃ ላይ እየተንከባለልኩ ነው የማድረው ብላለች-ግራ በመጋባት ስሜት ተውጣ፡፡ በዳስዋ ውስጥ ለአፍታ በነበረን ቆይታ ጥቂት ጥያቄዎችን አቅርበንላት መልስ ሰጥታናለች፡-
 ይሄ ሁሉ ቤት በስንት ቀን ነው የፈረሰው?
በአንድ ቀን ነው ያፈረሱት፡፡
አስቀድሞ ይፈርሳል ተብሎ ተነግሯችሁ ነበር?
እኛ አካባቢ ይፈርሳል የሚል ወሬ ፈፅሞ አልሰማሁም፡፡ የሰማሁት ኤራኤልና፣ ጨሬ ቀርሳ ነው፡፡ ግን ሳናስበው ያንን አጋጣሚ ተጠቅመው የኛንም አፈረሱብን፤መግቢያ አሳጡን፡፡
ቤታችሁ ከፈረሰ በኋላ ያነጋገራችሁ የመንግስት አካል አለ?
ማንም ያነጋገረን አካል የለም፡፡ እናንተ ናችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ መጥታችሁ የጠየቃችሁን፤ሌላ ዞር ብሎ ያየን የለም፡፡ ሀገር እንደሌለን ሜዳ ላይ ስንወድቅ የጠየቀን ማንም የለም፡፡
እናንተስ ---- ለመንግስት አቤቱታ ለማቅረብ አልሞከራችሁም?
እኛማ ማጣፊያው አጥሮናል’ኮ! የት ብለን ማንን እንጠይቅ፡፡ በቃ የሆነውን እንሁን ብለን እዚችው የቤቷ ፍራሽ ላይ ቀርተናል፡፡ ለራሴም ቤት ሰርቼ፣ አንድ ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶች ከጎን ቀጥዬ እያከራየሁ ገቢ አገኝ የነበረው ቀርቶ፣ዛሬ ይኸውና ለራሴም መጠለያ የሌለኝ ሆኛለሁ፡፡ ሀብት ንብረቴ ሁሉ ወድሟል፡፡
አሁን በምንድን ነው የምትተዳደሪው?
ቤቱ ከፈረሰ በኋላ ምንም ገንዘብ የማገኝበት ነገር የለም፤ሰው እየረዳኝ ነው የምኖረው፡፡
የሚከራይ ቤት ለማግኘት አልሞከራችሁም?
እኔ እዚህ ምንም ዘመድ የሌለኝ ሰው ነኝ፡፡ ማን ጋ ልጠጋ? ቤት ተከራይቼ እንዳልኖር ትንሹ የቤት ኪራይ 1500 ብር ነው፤ ከየት አመጣለሁ? ምንም ገቢ የማገኝበት ነገር የለኝምኮ! አቅሜ አይፈቅድም፡፡ በቃ ባዶዬን ቀርቻለሁ፡፡
መንግስት ምን እንዲያደርግ ነው የምትፈልጉት?
 ቦታውን እፈልገዋለሁ ብሎ እንዲህ ካደረገን በኋላ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ እኛም የዚህች ሀገር ዜጎች ነንና ያስብልን፡፡ ለዚህች ሀገር ልማት እናዋጣ የነበርን ዜጎች ነን፡፡ መንግስትን ምን በደልነው? ልጆቻችንስ በልጅነት አይምሮአቸው ለምን ይጎዱ፡፡
 ልጆቼ እየተሳቀቁ የሚበሉት አጥተው እየተቸገርን ነው፡፡ ወንድሜ እስቲ ንገረኝ ---- የገቢ ምንጭ ከወደመ በኋላ ይህችን ልጅ ምን ላብላት? … ዘንድሮ በኔ የመጣ ቁጣ እንዲህ ነው ተብሎ አይነገርም፡፡
“ከጅብ ጋር እየተፋጠጥን ነው የምናድረው”
አንዱ በአንዱ ላይ የተደረማመሱትን ቤቶች እየተመለከትን፣ከአንደኛው የቤት ፍራሽ ጥግ ላይ ወደተቀለሰች ዳስ አመራን፡፡ በዳሱ ውስጥና በራፉ ላይ አራት ሰዎች ቁጭ ብለው ቡና እየጠጡ ነበር፡፡ ጎራ ብለን ማነጋገር ጀመርን፡፡
ቤታችሁ ከፈረሰ በኋላ በእንዲህ ያለ ሁኔታ እዚህ ለመኖር ለምን መረጣችሁ? ቤት ተከራይታችሁ አትኖሩም?
(ከመካከላቸው አንደኛው በፍጥነት ምላሽ መስጠት ጀመረ …)
እየውላችሁ ወንድሞቼ---እኛ የቀን ሰራተኞች ነን፤ ከተማ ገብተን በ4ሺ እና 5ሺህ ብር ቤት ለመከራየት ይቅርና ለእለት ጉርሳችንም ስንቸገር የኖርን ነን፡፡ በምን አቅማችን ነው ቤት የምንከራየው?
በፊት በምን ነበር የምትተዳደሩት?
አንድና ሁለት ክፍል ቤት ከመኖሪያ ቤታችን ጎን ቀጥለን እየሰራን፣እያከራየንም ገቢ እናገኛለን፡፡ አብዛኞቻችን የቀን ሰራተኞች ነን፡፡ እኔ የምሰራው ድንጋይ ፈላጭነት ነው፡፡ ኮብልስቶንም እንሰራለን … በዚህ ነው የምንተዳደረው፡፡
ቦታውን ከአርሶ አደር ላይ ስትገዙ ህገወጥ መሆኑን አታውቁም ነበር?
በወቅቱማ ማንም አልተቃወመንም፡፡ አንድም ቀን ህገ-ወጥ ናችሁ ተብለን አናውቅም፡፡ ቤት ስንሰራ ደንቦች ይመጣሉ፤ግን አፍርሱ አይሉንም ነበር፡፡ አሁን እንኳ ሊፈርስብን ሰሞን መንገድ ለመስራት ባዋጣነው ገንዘብ፣የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ተገዝቶ ሊቀበር በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ገንዘብ አዋጡ ተብለን እያዋጣን መብራት፣ መንገድ፣ ውሃ አስገብተናል፡፡
ውሃ በየግቢያችን እንዲገባ የተላከ ከወረዳው በማህተም የተደገፈ ወረቀት አይተናል፡፡ ለልማት 9 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብለን ስናዋጣ ነበር፡፡
 ይሄን ሁሉ ስናለማ ዝም ብለውን፣ ዛሬ አንገታችንን ቀና አደረግን ስንል፣እንዲህ መልሶ ቅስማችንን የሚሰብረን መንግስት ምን አድርገነው ነው? ምን በድለነው ነው? ለአንድ ቀን እንኳ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠን ምን አለበት?
ከመፍረሱ በፊት እቃችሁን አውጥታችሁ ነበር?
ድንገት እኮ ነው ማፍረስ የጀመሩት፡፡ የቻልነውን አትርፈናል፡፡ ብፌ፣ ሶፋ ግን እንዳለ ወድሞብናል፡፡
ለምን እቃችሁን ለማውጣት አልቻላችሁም?
ማን ያውጣው!? ወንዶቹን እየለቀሙ ነው ያሰሩት፤ግማሹ ሸሽቶ ከአካባቢው ራቀ፡፡ ሴቶች ብቻ ነበሩ የቀሩት፡፡ በዚያ ላይ 8 ማሽን ነበር ቤቱን ሲያፈርስ የነበረው፡፡ አካባቢው በአቧራ ታጥኖ … ሁኔታው ሁሉ አስፈሪ ነበር፡፡ እንዲህ እንደሚወራው ቀላል እደለም፡፡
አሁን እንዴት ነው የምትኖሩት?
ይኸው እንደምታዩት ጭቃ ላይ ፍራሽ አንጥፈን ነው የምንተኛው፡፡ አሁን የምንጠጣውን … ቡና ዘመድ ነው ያመጣልን፡፡ ልጆቻችን ተበታትነዋል፡፡
 ሁላችንም ዘመድ ከምናስቸግር ብለን በየቦታው በትነናቸው ነው እኛ እዚሁ የቀረነው፡፡ ት/ቤት ሄደው እስኪመጡ የማናምናቸው ሰዎች ዛሬ ምን ይሁኑ አናውቅም፡፡
ያነጋገራችሁ የመንግስት አካል የለም?
ማንም ዞር ብሎ ያየን የለም … ወገን እንደሌለን ሜዳ ላይ ቀርተናል፡፡
(አባወራዎቹ ቦታውን አንዱን ካሬ ሜትር በ100 ብር ሂሳብ እንደገዙት ይናገራሉ፡፡)
ለወደፊት ተስፋ የምታደርጉት ምንድን ነው?
ምን ተስፋ አለን?! ምንም ተስፋ የለንም፤መሄጃ የለንም፡፡ እንደሚባለው ትርፍ ቤት ቢኖረን እዚህ ቦታ ውሃና ጭቃ ላይ አንተኛም ነበር፡፡ መንግስት እንደፈለገ ያድርገን ብለን ቁጭ ብለናል፡፡




Read 3472 times