Saturday, 16 July 2016 12:19

ቤታቸው የፈረሰባቸው፣“የመንግስት ያለህ!” እያሉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(32 votes)

በቅርቡ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ‹ማንጎ› በተባለው አካባቢ ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች “መውደቂያ፣ መድረሻ
አጥተናል፤ ጫካ ውስጥ ከአውሬ ጋር እየተጋፋን ለመኖር ተገድደናል” ሲሉ እያማረሩ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን የት ናችሁ ብሎ ያነጋገራቸው
የመንግስት አካል እንደሌለና አስታዋሽ አጥተው እንደተጣሉ እኚሁ ተፈናቃዮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከነልጆቻቸው በክረምት
ዝናብና ጭቃ ሜዳ ላይ ወድቀው እየተሰቃዩ መሆኑን በምሬት የሚያስረዱት አባወራና እማወራዎቹ፤መንግስት የኤርትራ ስደተኞችን እንኳን
ካምፕ አዘጋጅቶ እየተቀበለ መሆኑን ጠቁመው ለዜጎቹ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል፡፡ ቤታቸው ፈርሶ በማንጎ ጫካ ከተጠለሉ
ነዋሪዎች ሶስቱ ስለቀድሞ አሰፋፈራቸውና አሁን ስላሉበት አስከፊ ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡ “የመንግስት ያለህ!” እያሉም ነው፡፡

 “የሚደርስልን አካል ካለ ይድረስልን!”
(አዛውንቱ ሃጂ አብደላ ሁሴን ቤታቸው ከፈረሰባቸው አንዱ ናቸው፡፡ እርጅና የተጫናቸው ሃጂ አብደላ እንባቸውን እያፈሰሱ ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል፡፡)
“---ይፈርሳል ተብለው ቀደም ሲል ተነግሯቸው ሲከራከሩ የነበሩት ቀርሳ ኮንቶማና ኤርቶ ሞጆ የሚባል አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች እንጂ እኛ የማንጎ አካባቢ ነዋሪዎች ይፈርሳል ተብለን አናውቅም፡፡ የነሱን ነበር እየሠማን የነበረው፡፡ እነሱ አመት ከመንፈቅ በዚህ ጉዳይ ሲከራከሩ  ነበር፤ ነገር ግን ቤታችን ከመፍረሱ አንድ ሁለት ቀን በፊት የእናንተም ሰፈር ይፈርሳል የሚል ነገር በሰፈሩ ላሉት የኢህአዴግ አባሎች በሚስጥር ተነገራቸው፡፡ እነዚህም ሚስጢረኞች ለአንዳንድ ሰው ነገሩን፤ በነጋታው ስብሰባ ወጣን፡፡ ከዚያ በፊት የመኖሪያ አካባቢ ነው ተብለን ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ዓመት የኖርንበት ቦታ ነው፡፡ መብራት አስገቡ ተባልን፣ መንገድ ስሩ ተባልን፣ ዘመናዊ የፖሊስ ጣቢያ ስሩ ተባልን፤ በአጠቃላይ የመኖሪያ ቦታ ነው አትስጉ አይነሳም ስንባል ነው የኖርነው፡፡ እንዴት እንዲህ ያደርጉናል ስንል ስብሰባ ወጣን፡፡ ኧረ የሚመለከተውን ጥሩልን ያወያዩን ስንል ለፖሊሶች አመለከትን፡፡ ፖሊሶች የወረዳውን አስተዳደር ጠሩልን፡፡ መጥተው “እውነት ነው የሚባለው?” ብለን ስንጠይቀው፤ “አዎ! እናፀዳዋለን ትጠረጋላችሁ” አለን፡፡ “እንዴ! ቆሻሻ ነው የሚፀዳው፤ እንዴት እንዲህ ትላላችሁ?; ስንል “የራሳችሁ ጉዳይ ነው” አለን፡፡ “በዚያው እኛ ስብሰባ ላይ ሆነን፣ እሱ ወደ ቀርሳ ኮንቶማ አመራ፤በዚያው ሰው ሞቷል፤ የሚል ነገር ሰማን፡፡ በማግስቱ ቀርሳ ኮንቶማን አቋርጠው በሌሊት ገቡብን፤እቃ አውጡ የለ! ልጆቻችሁን አውጡ አላሉን!... ለየትኛው እንድረስ… ሌሊት ነው። ስንነሳ ልጆቻችን በሌሊት እየተባረሩ ወደ ወንዝ ሮጡብን (ሲቃ እየተናነቃቸው) …. እንደገና ልጆቻችን ለመያዝ መሯሯጥ ጀመርን፤ 6 ዶዘር ለማፍረስ ተሠልፏል፡፡ አንድ ላይ ነው የደረመሱብን… ቆይ እኛ መንግስትን ምን በድለነው ነው?! ይሄን ያህል ስናለማ ከቆን በኋላ ምን አድርገን ነው፡፡ ከእንግዲህ ጉልበታችን ደክሟል… የሚረዳን የሚጦረን የለም!፡፡ ምን አደረግን? ዘመድ ያለው ዘመዱ አንስቶታል፤ እኛ ዘመድ የሌለን እዚያው ጭቃ ላይ ወድቀን ቀርተናል። እና ልጆቻችንን እንዴት እናድርጋቸው? በድንጋጤ ጠፍተው ያልተመለሱ ልጆች አሉ!
“እነዚህ ሰዎች ቤቶቹ ሲሰራ ዝም ይሉ ነበር፤ ጉቦ ይቀበሉና ዝም ብላችሁ ስሩ ብለው ነበር የሚሄዱት። ዛሬ ጉልበታችንን፣ ገንዘባችንን ከጨረስን በኋላ እንደዚህ ሃገር ወገን እንደሌለን አድርገውናል። መብራት እንኳ ሳይቀር ነው ነቃቅለው የጣሉት። በሌላ ቦታ መውደቂያ የሌላቸውን እንመዘግባለን እያሉ ያወራሉ፤ይሄ ግን ውሸት ነው… እኛ እዚያው ሆነን ሞታችንን ነው የምንጠባበቀው፤ የሚደርስልን አካል ካለ ይድረስልን!;
“10 ሺህ ብር አዋጥተን ፖሊስ ጣቢያ አቋቁመናል”
(ሌላው ጎልማሳ አቶ የሱፍ አሊ፤እንባቸው እየቀደመ ስለ ሁኔታው እንዲህ ይላሉ…)
“እኔ በወረዳው ስኖር በትክክለኛው የቤተሰቤ ሰነድ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ የመኖሪያ አካባቢ ነው፤ አርፋችሁ ልማት አልሙ ተብሎ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ አስገቡ ተብለን ይሄን ሁሉ አደርገናል። ፖሊስ ጣቢያም አቋቁሙ ተብለን ከየግላችን 200 ብር አዋጥተናል፡፡ በእድራችንም ከሸማቾች ካዋጣነው 200 ብር በተጨማሪ 10 ሺህ ብር አዋጥተን ፖሊስ ጣቢያ አቋቁመናል፡፡ ይሄ ሁሉ ተሰርቶ ካለቀ በኋላ ነው ድንገት ተነሱ የተባልነው፡፡ “እንዴት ይሆናል? የበላይ አካል መልስ ይስጠን ስንል” በእለቱ የበላይ አካል የተባለው መጥቶ፣ “ትጠረጋላችሁ” ነው ያለን። “ቆሻሻ ነን ወይ” የሚል ነበር የህዝቡ ምላሽ፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ተገንጥላ ያለችውን የኤርትራ ህዝብ መጠለያ ሰርቶ እየተቀበለ ነው፤እኛ እዚህ ለአባይ ግድብ---ለአገሪቷ አስተዋጽኦ የምናደርገውን ህዝብ እንዴት ነው እንዲህ የሚያደርገን?” ስንል መልሳቸው አንድና አንድ ነበር፤“ትጠረጋላችሁ” ነው ያሉን፡፡ ይሄን ባሉን በሁለት ቀን በዶዘር ነው መጥተው የደረመሱብን፤ አንዱ ቤት በአንደኛው ላይ ነው የተደረማመሰው፤ እቃ፣ ቴሌቪዥን፣ ዲሽ የተባለ ነገር የለም፤ በሙሉ አወደሙብን፡፡ እንዲህ አውድመው ጨርሰውትም የት ደረሳችሁ ያለን የለም፤ እዚያው ፍራሹ ላይ ነው ያለነው፡፡
“እኔ እምለው፣ አንድ መንግስት ይሄን ይሰራል? ወገንስ የለንም? የአለም ተከራካሪስ የለንም? … እኔ በህይወቴ እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም። ደርግ እንኳ መሬት ላራሹ ብሎ ነው የሰጠው እንጂ መሬት የመንግስት ናት አላለም፡፡ ይሄን ሙሉ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፡፡ ደርግ በመሬት ሰቆቃ አላደረሰም፡፡ ያኛውን መንግስት ልናማርር አይገባንም፡፡ አሁንም መግቢያ አጥተናል፤የመንግስት ያለህ እንላለን፡፡ ክረምት ነው፤ልጆቻችንን ቢንቢ ጨረሳቸው፡፡ ትላልቆቹ ቤታቸው ሲፈርስ ታንቀን እንሙት እያሉ ነው፡፡ እኔ አሁን ስራ ትቼ ልጆቼን ነው የምጠብቀው፡፡ 5 ልጆች አሉኝ፤ እነሱን ነው የምጠብቀው፡፡ የግለሰብ ሰራተኛ ነኝ፤ ካልሰራሁ ደመወዝ የለኝም ግን ልጆቹ ይበልጡብኛል ብዬ ልጆቼን ከአውሬ እየጠበቅሁ ነው፤ ኧረ የመንግስት ያለህ! መንግስት ይስማን! …”
“ዝም ብለን ጫካ ውስጥ ነው ያለነው”
 የ5 ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ቤታቸው ከፈረሰባቸው በኋላ ከነቤተሰባቸው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን በሲቃ ይገልጻሉ፡፡ ቆርቆሮ ከልለው በአካባቢው በሚገኘው ማንጎ ጫካ ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር በስጋት እየኖሩ መሆኑን የሚናገሩት እማወራዋ፤“የደረሰች ሴት ልጅ አለችኝ፤ እሷን ክፉ እንዳይነካብኝ አቅፌ ነው እዚያ ጭቃ ላይ የምተኛው” ብለዋል፡፡
እንዴት ነው ቦታውን መጀመሪያ ያገኙት?
ትንሽዬ ቤት ያለችበትን ቦታ ነበር የቤቷ ባለቤት (ገበሬ) የሸጠልኝ፡፡ እንደገዛኋት ቤቷን አሳደስኳት፡፡
እየኖሩበት ነበር ቤቱን?
አዎ! 5 ልጆቼን የወለድኩት እዚያው ቤት ነው፤11 ዓመቴ ነው እዚያ ከገባሁ፡፡
ቀበሌው ያውቅዎታል?
እንዴታ! መታወቂያ ሁሉ አለኝ፤እታወቃለሁ፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኜ ሁሉ ብዙ ጊዜ አገልግያለሁ፤ የሴቶች ፎረም ውስጥ ነበርኩ፡፡
በ11 ዓመት ውስጥ ቤትዎ እንደሚፈርስ ተነግሯችሁ ነበር?
በጭራሽ አልተነገረኝም፡፡ ኮሚቴዎች ተጠርተው ቤታችሁ ይፈርሳል ነው የተባልነው በድንገት። የመንደር ወሬ ሰምተን ነው ስብሰባ የወጣነው። በስብሰባው ማግስት ቤታችን ፈረሰ፡፡ አንዲት የማስጠንቀቂያ ወረቀት እንኳ አልተሰጠንም፡፡
አሁን የት ነው ያሉት?
እዚያው ማንጎ ጫካ ውስጥ ነው፡፡ ዞር ብሎ ያየንም የለም፡፡ እኔ ያለሁበት ቦታ ብቻ 15 ገደማ አባወራዎች ከነልጆቻቸው ጫካ ውስጥ ጭቃ ላይ ነው ያሉት፡፡ እንደኔ መሄጃ የሌላቸው፣ድፍን ያለባቸው ጫካ ውስጥ እየኖሩ ነው፡፡
አውሬ ምናምን አያስቸግራችሁም?
ምን እናድርግ ታዲያ! በቃ ቢበሉንም ይብሉን ብለን ነው፡፡ እነሱ ቢበሉን ይሻላል፡፡ ስራ ትተናል። እኔ በበኩሌ ልጆቼን ቁጭ ብዬ ነው ስጠብቅ የምውል የማድረው፡፡ ዘመድና ሌላው ሰው ዝም ብሎ ዳቦ ያቀብለናል፡፡ ሱቅ ለማግኘት ብዙ ርቀት መሄድ አለብን፤ ስለዚህ ሰው ዝም ብሎ ስኳር፣ ዳቦ፣ ቡና ምናምን ያቀብለናል፡፡ እውነቱን ልንገርህ እንጀራ ለመጨረሻ ጊዜ የበላሁት ቤቱ ከመፍረሱ በፊት ነው፡፡ ትንፋሼ ሁሉ እየራቀኝ ነው፤እንጀራ የሚባል ነገር ከዚያ በኋላ አይቼ አላውቅም፡፡
መውጣት መግባት ትችላላችሁ ወደ አካባቢው?
 አዎ! አፍርሰው ከጨረሱ በኋላ ትተውናል፡፡ ቦታውን ባለሀብት ተረክቦታል፡፡
ቦታው ታጥሯል አሁን ?
አልታጠረም ግን መሃንዲሶች በፈረሰ በማግስቱ መጥተው ቀርፀውት ሄደዋል፡፡
 ያነጋገራችሁ የመንግስት አካል የለም?
በጭራሽ! ቢያነጋግሩንማ ተስፋ ነበር፡፡ ዝም ብለን ጫካ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
ቤትዎ በምንድን ነው የተሰራው?
ሁለት ክፍል ቤት ነች፡፡ በጭቃና በቆርቆሮ ነው የተሰራችው፡፡
ቤተሰብዎን በምንድን ነው የሚያስተዳድሩት?
ባለቤቴ ሸምገል ያለ ነው፤ያመዋልም፡፡ አንዳንዴ አይሰራም፤ ያው በወር 800 ብር ያገኛል፤ በሷ ነበር የምንተዳደረው፡፡ እቺንም እንዳናገኝ አሁን ስራ ፈቶ ቁጭ ብሏል፡፡
ገንዘብ ከየት አግኝተው ነው ቦታውን የገዙት?
አረብ ሀገር ሰርቼ ነው የመጣሁት፡፡ እሷንም ቤቴና እቃዬ ላይ አጥፍቼ፣ ዛሬ ባዶ እጄን ቀርቻለሁ፤ ከንቱ ሆኜ ቀርቻለሁ፡፡ አሁን ባዶ እጄን ነኝ፤ ከእነልጆቼ፡፡
ቤቱ ሲፈርስ ንብረትዎን አላተረፉም?
ምንም አላተረፍኩም፡፡ አንድ የሰው አደራ የሆነ ቴሌቪዥንና የራሴ ቴሌቪዥንም ነበር፤ እነሱን ብቻ አትርፌያለሁ፡፡ ሌላው ወንበር፣ ሶፋ እንክትክቱ ነው የወጣው። ጣራውን እንኳ ልነቅል ስል፤ውረዱ ነው ያሉን፡፡ ቤቱን እንዳለ ነው የናዱብን፡፡
ስንት ሰአት ላይ ነበር የፈረሰብዎት?
ሌላ ቦታ ሲያፈርሱ ውለው፣ እኔ ቤት ጋ የደረሱት ቀን አስር ሰዓት ላይ ነበር፡፡
ስንት ዶዘር ነበር የሚያፈርሰው?
እኔ ያየሁት 3 ዶዘሮችን ነው፡፡
ስንት ቤቶች ናቸው እናንተ አካባቢ የፈረሱት?
ከጫፍ እስከ ጫፍ ነው ያፈረሱት፡፡ እኔ በቁጥር አላውቀውም፡፡ እነሱም ከዳር እስከ ዳር--- ዳገት ቁልቁለት የለም፤እንዳለ ነው የምናፈርሰው ነው ያሉን፡፡  


Read 9242 times