Saturday, 16 July 2016 12:26

“በአቃቂ 15 ሺህ ቤቶች ይፈርሳሉ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

     በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤታቸው የፈረሰባቸው ተፈናቃዮች፣ “ሜዳ ላይ ወድቀናል” ሲሉ እያማረሩ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ከረቡዕ ጀምሮ “ህገ ወጥ” የተባሉ ቤቶች እየፈረሱ ነው፡፡ በላፍቶ ከሚፈርሱ 20 ሺህ ቤቶች በተጨማሪ በአቃቂ 15 ሺህ ቤቶች እንደሚፈርሱም ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በህገወጥ የመሬት ወረራ የተሰሩ ናቸው በሚል በንፋስ ስልክ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች እየፈረሱ እንደሆነ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በርካታች ተፈናቃዮች እዚያው የፈራረሰ ሰፈር ውስጥ፣ የፕላስቲክና ቆርቆሮ ዳሶችን በመስራት ለመኖር መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
ሰሞኑን በአቃቂ ቃሊቲ በተጀመረው የማፍረስ ዘመቻ 15 ሺ መኖሪያ ቤቶች እንደሚፈርሱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ የጠቆሙ ሲሆን፤ ቤቶቹ እንደ ንፋስ ስልክ ላፍቶዎቹ በግሬደር ሳይሆን በአፍራሽ ግብረሃይል እንዲፈርሱ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡  
ትናንት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በህገወጥ ወረራ የተመሠረቱ ሠፈራዎችን የማፍረስ ስራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ መንግስት እስከ 1997 በህገ ወጥ እንቅስቃሴ የተሠሩ ቤቶችን ተቀብሎ ማጽደቁን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ “ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ባለሃብቶች በርካታ ሰው አሰማርተው ሰፈራ ካቋቋሙ በኋላ፣ ራሳቸው ቤቶቹን ገዝተው ሲቆጣጠሩ ቆይቷል፡፡ እንዲህ ያለውን ህገ ወጥነት መንግስት እያየ ዝም አይልም” ብለዋል፡፡“አዲስ መንደር ለመመስረት የሚደረግ ጥረት ህጋዊ መሠረት የለውም፤ ህገ ወጥ ቤቶች መፍረስ አለባቸው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተፈናቃዮቹን ዕጣፈንታ በተመለከተ ተጠይቀው ሲናገሩ፤ “ለተፈናቀሉ ግለሰቦች መንግስት ተገቢውን ጥበቃ ያደርጋል” ብለዋል፡፡ መኢአድ እና ኢዴፓ፤ “ህገ ወጥ ቤቶች” በሚል የተወሰደው በጅምላ የማፍረስ እርምጃ ግብታዊ ነው ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ ኢዴፓ ከሁሉ በፊት ውይይት መቅደም ነበረበት ያለ ሲሆን፤ መኢአድ በበኩሉ፤ የተፈናቃዮቹ ጉዳይ በሠላም መፈታት አለበት ብሏል፡፡ ዜጎች መጠለያ የማግኘት መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት የገለፁት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ ለተፈጠረው ውድመት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል፡፡
የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በህገ ወጥ የሰፈራ ምስረታው ላይ የተሳተፉ የመንግስት አካላት መኖራቸው ከተረጋገጠ በየደረጃው ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ እንደሚናገሩት፤ በአካባቢው ለ10 ዓመታት ቤት ቀልሰው የኖሩ ሲሆን፣ ወረዳው ለፖሊስ ጣቢያና ለልማት በሚል ገንዘብ እንዲያዋጡ ሲጠይቀን “አንድም ጊዜ ህገ ወጥ ናችሁ አላለንም” ይላሉ፡፡

Read 7836 times