Saturday, 16 July 2016 12:12

“መመሪያችን፡- ቅንጦትን ሁሉም ሰው እንዲገዛው ማድረግ ነው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(8 votes)

• ሆቴሎች የሰለጠነ ባለሙያ ከሚሰራረቁ በጥምረት ቢሰሩ የበለጠ ያድጋሉ
• ዋጋው የቱሪስቶችንና የከተማዋን ነዋሪ አቅም ያገናዘበ ነው

     ዓርማው ዘውድ ነው - ስሙም ሞናርክ፡፡ ትርጉሙ “እንግዶች ስትመጡ የንጉሥ መስተንግዶ ይደረግላችኋል” ማለት ነው ይላሉ፤የሆቴሉ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ያየህይራድ የምወደው፡፡ ንጉሥ ፈልጎና ጠይቆ የሚያጣው ነገር እንደሌለ ሁሉ እናንተም ተደስታችሁ እንድትሄዱና በሌላ ጊዜ ሌላ ሰው ይዛችሁ እንድትመጡ የጠየቃችሁትና የፈለጋችሁት ሁሉ ይሟላላችኋል፤ ሲሉም ያብራራሉ - የማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ፡፡  
እንግዶች ወደ ሆቴሉ ሲገቡ በስተቀኝ የመዋናኛ ስፍራ ያለው ሲሆን አስደሳችና መንፈስ የሚያድስ ግቢም አለው፡፡ በስተግራ ባር ሬስቶራንትና ካፌ ያገኛሉ፡፡ እውስጥ ካለው ጋር ሁለት ባርና ሁለት ሬስቶራንት ማለት ነው፡፡ ደጅ ባለው ሬስቶራንት እንግዶች እያዩ የሚሰናዳው ፒዛና ባርቢኪው ተወዳጅ ነው፡፡ ባርቢኪው የሆቴሉ ተመራጭ ምግብ እንደሆነ አቶ ያየህ ይራድ ይናገራሉ፡፡ ሐሙስና አርብ ላይቭ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርባል፡፡ ሆቴሉ 74 የመኝታ ክፍሎችና 3 የመሰብሰቢያ አዳራሾች አሉት፡፡ 350 ክፍሎች የሚኖሩት የሆቴል ማስፋፊያ በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተነግሯል።  
ሆቴሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ንብረት ነው፡፡ የድርጅቶቹ ዓላማ ከውጭ የሚገቡትን ዕቃዎች መቀነስ ነው፤ይሄም ለዕቃዎቹ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ያድናል ይላሉ የማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ፡፡ ባለሀብቶቹ ዛሙ የተባለ የፈርኒቸር ማምረቻ ድርጅት አላቸው፡፡ በሆቴሉ ውስጥ የሚታዩት ቁሳቁሶች በሙሉ እዚሁ የተሰሩ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ፍራሽም ያመርታል፡፡ ሆቴሉ እየተጠቀመበት ያለው ስፕሪንግ ፍራሽም እዚሁ የተመረተ ሲሆን ለሌሎች ሆቴሎችም እየተሸጠ ነው ተብሏል፡፡ ዛሙ ወደ ቀለምና ኮንስትራክሽን ዘርፍ የመግባት ዕቅድ እንዳለውም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የመኝታ ክፍሎቹ ሰፋፊ ናቸው፡፡ እንግዳው ከፈለገ አብስሎ መብላት ይችላል፣ ትናንሽ ኪችኖች አላቸው፡፡ መታጠቢያ ክፍሎቹ ሻወርና ስቲም ያላቸው ናቸው፡፡ አየር ማቀዝቀዣና ማሞቂያ ኤሲ፣ ቲቪ፣ ፍሪጅ፣ ካዝና፣ የመፃፊያና የመመገቢያ ጠረጴዛና ወንበር፣ ስልክ፣ …. ተሟልቶላቸዋል።  የስልኩ አገልግሎት መደወል ብቻ አይደለም። የተለያዩ ሞባይሎች ቻርጅ ማድረጊያ ገመድ አለው፡፡ እንግዳው ከያዘው ሞባይል ወይም ሌላ የሙዚቃ ማጫወቻ ሙዚቃ መስማት ቢፈልግ ስልኩ ማይክሮፎን ስላለው ሰክቶ ማጫወትና ማዳመጥ ይችላል፡፡ ክፍል የያዙ እንግዶች ብቻ በነፃ የሚጠቀሙበት ዋና፣ ጂም፣ ሳውናና ስቲም ባዝ እንዲሁም የቢዝነስ ማዕከልም አለው፡፡  
ክፍሎቹ የየራሳቸው ዲዛይንና ቀለም ሲኖራቸው፤ ቀለሙ በየዓመቱ እንደሚቀየር አቶ ያየህይራድ ይናገራሉ፡፡ ክፍሎቹን የሚጠቀሙ እንግዶች ብዙ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ የሚል እሳቤ አለ፡፡ አንድ  ክፍል ውስጥ ብዙ ጊዜ መቆየት ሊያሰለች ይችላል፡፡ ስለዚህ ክፍሎች በየዓመቱ አዲስ ቀለም ይቀባሉ፡፡ ከዚህ በፊት በሆቴሉ የተጠቀመ እንግዳ ቢመጣ፣ ባለፈው ጊዜ ያረፈበት ሳይሆን ሌላ ክፍል እንደሚሰጠው ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ሆቴሉ ለምዷል፣ ጥሩ እየሠራን ነው ያሉት ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ፤አዲስ ሆቴል ሲከፈት በሙሉ አቅሙ ለመሥራት አንድ ዓመት ይፈልጋል፡፡ እኛ ግን በሙሉ  አቅማችን መሥራት የጀመርነው በ6 ወር ውስጥ ነው፡፡ ይህ የሆነው የምንሰጠው ጥራት ያለውና የባለ 5 ኮከብ ደረጃ በመሆኑ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሆቴል ካሉት ክፍሎች ውስጥ 60 በመቶ ከተያዘ ጥሩ እየሠራ እንደሆነ ይቆጠራል። የእኛ ክፍሎች ከ60 በመቶ በላይ ስለሚያዙ ጥሩ እየሠራን ነው ማለት ነው፡፡ ከደንበኞቻችን መካከል 35 በመቶ ቱሪስቶች፣ ለቢዝነስና ለሥራ እንዲሁም በአገሪቷ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ናቸው ብለዋል፡፡ የሆቴሉ ዓላማ ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ብቻ ሳይሆን በመዲናዋ ነዋሪ ለሆኑትም ጭምር  አገልግሎት መስጠት እንደሆነም አውስተዋል፡፡
ሞናርክ ሆቴል ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ። ዋጋው የቱሪስቶችንና የከተማዋን ነዋሪ አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ቀደም ሲል በመዲናዋ ያሉ ትላልቅ ሆቴሎች የአልጋ ዋጋ አይቀመስም በማለት የከተማዋ ነዋሪ ሆቴል ገብቶ እንደማይዝናና የጠቀሱት አቶ ያየህይራድ፤ይህን ችግር ለመቅረፍና ሕዝቡ ሆቴል ገብቶ እንዲዝናና የሞናርክ ሆቴል ዋጋ የሕዝቡን አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ይህንንም ሁኔታ የባህል ቱሪዝምና ሚኒስቴር እንዲሁም የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ያውቃሉ ብለዋል፡፡ አሁን ሁኔታው ተለውጧል፡፡ የእኛ መመሪያ Making Luxury Affordable ወይም Making Luxury for the people “የቅንጦት ነገሮችን ሁሉም ሰው እንዲገዛቸው አድርግ” የሚል ነው፡፡ አንድ 100 ዶላር የሚገዛው ነገር በ50፤ 50 ዶላር ለሁለት ሰው መሸጥ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው ይላሉ፡፡
ሌላው ሞናርክን ለየት የሚያደርገው፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ባለሙያዎች እያስመጣ የሆቴሉን ሠራተኞች ማሠልጠኑ ነው፡፡ በዓለም ቁጥር አንድ የሆኑ  የካናዳ ባለሙያዎችን አስመጥተን ለሁለት ወር በምግብ እንዲያሰለጥኑ አድርገናል፡፡ የፈረንሳይ ምግብና መጠጥ ክፍላችንም በከፍተኛ ደረጃ  በተካኑ ባለሙያዎች የሰለጠነ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
የሆቴል ሥራ ወቅታዊ (ሲዝናል) ነው፤ ሞቅ የሚልበትና ቀዝቀዝ የሚልበት ጊዜ ስላለ ዋጋችንም እንደዚያው ከፍና ዝቅ ይላል ያሉት አቶ ያየህይራድ፤ ቱሪስቶች አገሩ በሚጨቀይበት ክረምት ወቅት እነሱ ዘንድ በጋ ስለሆነ ወደዚህ መምጣት አይፈልጉም። በዚህ ወቅት ወጣ እያልን አንዳንድ ፕሮራሞችን (ኢቨንት) እናዘጋጃለን፡- ለምሳሌ የሙዚቃ ቡድኖችን ከውጭ በማስመጣት ገቢያችንን እንደጉማለን፤ብለዋል፡፡
ከተለያዩ ስብስባ አዘጋጆች ጋር በመነጋገር ስብሰባዎች ወደዚህ እንዲመጡ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ይህን ሥራ ለመሥራት ያቀድነው ከሌሎች ሆቴሎች ጋር በመጣመር ነው፡፡ እኛ ያለን 74 ክፍሎች ነው፡፡ 600  ተሰብሳቢ ቢመጣ ማስተናገድ አንችልም፡፡ አንድ ሰው ከሚጠግበው በላይ አይበላም ይባላል፡፡
ስለዚህ ለምን ከሌሎች ሆቴሎች ጋር በትብብር አንሠራም የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ አንድ ሆቴል 200 ክፍሎች ቢኖሩት ሌላው ደግሞ 300 እንዲሁም አንዱ 100 ክፍሎች ቢኖሩት 600 ተሰብሳቢ በጋራ ማስተናገድ እንችላለን፡፡
እዚህ አገር ብዙ ጊዜ በጋራ የመሥራት ችግር አለ፡፡ በግል ከመሯሯጥና ሰራተኛ ከመሰራረቅ በጋራ ሰርተን ብንጠቀም ጥሩ ነው፤እኛ የምናሠለጥናቸውን ሠራተኞች አባብለው ከሚወስዱ፣ እነሱም ዓለም አቀፍ አሠልጣኞች አስመጥተው ሠራተኞቻቸውን ቢያሠለጥኑ የሠራተኛ ፍልሰት አይኖርም ወይም በጣም ይቀንሳል፡፡
አሁን የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ በደንብ አላደገም፤ ገና እያቆጠቆጠ ነው ያለው። ተባብረን በጋራ ብንሠራ ከዚህ የበለጠ ማደግ እንችላለን ሲሉ አስረድተዋል፤አቶ ያየህ ይራድ የምወድህ፡፡





Read 3464 times