Saturday, 16 July 2016 12:09

ኢትዮ ሴራሚክስ 5ኛውን ትልቅና ዘመናዊ ሾውሩም በቦሌ ከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    ላለፉት 20 ዓመታት ከተለያዩ የዓለም አገራት የባኞ ቤት የህንፃ ማጠናቀቂያ (Finishing) የሳውና የጃኩዚና መሰል የሴራሚክ ምርቶችን በማስመጣት ለአገር ውስጥ ገበያ ሲያቀርብ የቆየው ኢትዮ ሴራሚክስ፤ አምስተኛውን ትልቅና ዘመናዊ የሴራሚክስ መሸጫ ማዕከል ቦሌ ኖቪስ ሱፐር ማርኬት ፊት ለፊት አዲስ በገነባው ህንፃ ላይ ከፈተ፡፡ ከትላንት በስቲያ በይፋ ስራ የጀመረው ይሄው መደብር፤ ከሌሎቹ መደብሮች በተለየ የተደራጀና እቃዎች ተገጣጥመው ዲስፕሌይ የተደረጉበት ሲሆን ማንኛውም ደንበኛ እቃዎቹን ሲገዛ ምን እንደሚመስሉና ምን ቅርፅ እንደሚኖራቸው በማየት የሚገዛውን ለመወሰን እንዲችል የሚረዱ መሆናቸው በእለቱ ተገልጿል፡፡
ከዱባይ፣ ስፔይን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ ጀርመንና ከቻይና የመጡ የሴራሚክስ እቃዎች እንደየመጡበት አገርና ሁኔታ ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን በአገራችን የቤት ውስጥ ዲዛይነር ህንፃው ላይ ተሰርተው ተቀምጠዋል፡፡
በ1ኛና 2ኛ ፎቅ ላይ በአይነት በአይነት የተደረደሩ የተለያዩ አገራት የሴራሚክስ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን 3ኛ እና 4ኛ ፎቅ ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ሶፋዎች፣ አልጋዎች፣ የቢሮና የመመገቢያ ወንበርና ጠረጴዛዎች፣ ቁም ሳጥኖች ይገኙበታል “ይህ የሽያጭ ማዕከሉ አደረጃጀት አንድ ሰው ቤት ሰርቶ ሲያጠናቅቅ ቤቱን ለመጨረስና ሁሉንም እቃ በአንድ ቦታ ለማግኘት እንዲችል የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮ ሴራሚክስ የሽያጭና ግብይት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚፍታህ አክመል ገልፀዋል፡፡ እያንዳንዱ የሴራሚክስ እቃዎች አዳዲስና የ2015 ሥሪት እንደሆኑ የገለፁት ኃላፊው፤ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ከመላላጥና ከኬሚካል ጉዳት የፀዱ ናቸው ብለዋል፡፡
ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተናገድና ስለ እቃዎቹ ስሪትና ምንነት በቂ መረጃ እንዲሰጡ የሰለጠኑ ከ15 በላይ የሽያጭ ሰራተኞች መኖራቸውን የድርጅቱ የሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሳሌህ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በሽያጭ ማዕከሉ የአልጋ ትልቁ ዋጋ 80 ሺህ ብር ሲሆን ሶፋ ትልቁ ዋጋ 381 ሺህ ብር መሆኑም ታውቋል፡፡ የአልጋ መሸጫ ትንሹ ዋጋ 18 ሺህ ሲሆን የሶፋ ትንሹ ዋጋ 28 ሺህ 500 ብር እንደሆነ አቶ መሀመድ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 4110 times