Saturday, 09 July 2016 10:27

“ፍራሽ አዳሽ”

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(6 votes)

   አቶ ወንዳፍራሽ እኚህ ፍራሽ አዳሽ የዋዛ ሰው እንዳይመስሉዋችሀ፡፡ ሰለሞን ራሱ ከጥበቡ ቆንጥሮ የሰጣቸው ሰው ናቸው፡፡
አሁን ይኸ ልጃቸው አዝብጤ፣ ከነስሙም አዝብጤ በአምስት ዓመቱ የአንድ ሙሉ ሰራተኛ ሥራ ሲሰራላቸው ይውላል፤ የኔታ ትምህርት የለም ያሉ ለታ፡፡
እንግዲህ በፍራሽ ሥራና እደሳ የሚኖሩ እንደሚያውቁት ሁሉ ትራሱን ጥጥ ሞልተው ጠቅጥቀው ከሰፉት በኋላ ሲያዩት ጠማማ ኳስ እንጂ ትራስ አይመስልም፡፡ በስንትና ስንት ትግል፣ በስንትና ስንት ቡጢ ጥፊና ልዩ ልዩ ክርን መሳይ ጉሸማ ነው ልክ የሚገባው፤ ትራስ የሚሆነው፡፡
ታዲያ አዝብጤ መንገድ እየጠበቀ የሚመታው ተለቅ ያለ ልጅ አለ - መኮንን የሚሉት፡፡
አቶ ወንዳፍራሽ ይህን ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ትራስ ጠማማ ኳስ በሚመስልበት ሰዓት አዝብጤን ይጠሩትና እንደሚከለተው የወንድ ልጅ ወግ ያስተምሩታል፤ በጥበባቸው፡፡
ቀኝ እጁን ለቀም አርገው ይይዙና፤
“አንተ ማን ነህ?!” በሚያስፈራ ድምፅ፡፡
“እኔ አዝብጤ!” ይላቸዋል ሳይፈራ እጁን እየጨበጠ ግን ለማምለጥ ሳይቃጣ፡፡
“አዝብጤ ማ?!” ሲሉት
እንደ ነጎድጓድ ጩኸት፤ “አዝብጤ ወንዳፍራሽ!” ብሎ ያመልጣቸውና ቡጢ እንደጨበጠ ነብር መሳይ ዓይን ይመለከታቸዋል፡፡
“ወንዳፍራሽ ፍራሻዳሽ?”
“እንዴታ!”
“ያ ጀግናው? ያ ሰርቶ የሚበላው?”
“አዎና!”
“እውነት አዝብጤ ወንዳፍራሽ ፍራሽ አዳሽ ከሆንክ” ይሉታል ትራሱን እያሳዩት “ይኸውና አመፀኛው መኮንን፡፡ ትንንሽ ልጆች እየደበደበ ያስለቅሳል፡፡ መጫወቻቸውን ይነጥቃል፡፡ ንሳ ደብድበው፤ ቅጣው ይህን አመፀኛ፡፡ የት የት እንደሚመታ ታውቅ የለ?”
“አውቃለሁ”
“በል እንግዲህ ሥራውን አሳየው”
“አንተ! ልጆች ለምን ትመታለህ?” ይለዋል ትራሱን
ትራሱ ዝም፡፡
“ይኸውልህ እንግዲህ፤ ማናለብኝ ብሎ ኮርቶ ዝም ብሎ ያይሃል፡፡”
አዝብጤ ሆዬ፤ ዘሎ በጉልበቱ ትራሱ ላይ ያርፍና በቡጢ እየደበደበው “በል ተናገር” ይለዋል፡፡
“ዝም አልክ? እንካ ቅመስ!” እያለ ስንትና ስንት ቡጢና ክርን ሲያወርድበት አቶ ወንዳፍራሽ ሌላ ትራስ መጠቅጠቅ ይጀምራሉ፡፡
አዝብጤ ትራሱን እያገላበጠ ወዶ እስኪጠላ ድብድብ ካረገው በኋላ አቶ ወንዳፍራሽ “በቃው መሰለኝ፤ እንግዲህስ ሁለተኛ ደፍሮ አይማታም” ሲሉት
“ሁለተኛ ትማታለህ? ሁለተኛ ሽንኮራዬን ትነጥቃለህ? እ? ይለመድሃል? ሁለተኛ ፈሪ ብለህ ትሳደባለህ!?! ት - ት - ትሳደባለህ?” እያለ ምራቅ ቡጢና ክርን ካወረደበት በኋላ!
“በቃው አይለመደውም፡፡ አታይም ያ ያሳበጠው ኩራቱ እንደለቀቀው?” ይላሉ አባትየው “በቃ በቃ ይበቃዋል፡፡ ኧረ በገላጋይ በሽማግሌ ይተዉት እባክዎን!” እያሉ በብዙ ልመና ይገላግሉታል ትራሱን፡፡
አሁንማ ጠማማ ኳስም አይደለ፤ መኮንንም አይደለ፡፡ ትራስ ነው - ዳውላ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
አዲሱን ትራስ በቡላ ክር እየሰፉ
“ይኸ አሁን የምሰፋው ደሞ ማን ይመስልሃል?” ይሉታል አቶ ወንዳፍራሽ፡፡
“ማን ነው?” “ጭራቅ ነው፡፡ ክፉ ኃይለኛ ጭራቅ፡፡ ስንትና ስንት ልጅ የበላ”ይህን ታዲያ ይዞ በቡጢ አፈር ማስጋጥ፡፡”
“አፈር አስግጠዋለሁ፤ ቶሎ ጨርሰው”
“ተው ይበላሃል”
“ኧረ! እሱ ሊበላኝ? እኔ ደሞ ዘልዬ ሆዱ ላይ ቁጭ! አይኑን እሽት! በሽንኩርት እሽት! ማየት ሲያቅተው በጉጠት ጎጥጥ! እውር ሲሆን በሾኬ ጥልፍ!  ሲወድቅ ርግጥ! በጭቃ እግሬ ርግጥ! ከዛ በመዶሻ አፍንጫውን! በእሳት ፀጉሩን! ደሞ ፀጉሩ ሲቃጠል ይገማል አይደል”
“አዎን፡፡ ግን ማቃጠል አያስፈልግም፡፡ እሳት መጥፎ ነው፡፡ አቃጥል የተባለውን ትቶ ያልተባለውን ያቃጥላል፡፡ መደብደብ ይሻላል፡፡”
“እደበድበዋለሁ፡፡ ደሞ ከፈለገ እንደ ወረቀት እቦጫጭቀዋለሁ፡፡ ብጥስጥስ አድርጌ ስወረውረው ነፋስ ደሞ ወስዶ ጭቃ ውስጥ ጭምር! ሰዎች ደሞ ሲያልፉ በእግራቸው ጭፍልቅ ጭፍልቅልቅ ያደርጉታል፡፡ እንደማማ ዠማነሽ ጫጩት፡፡ አባባ?”
“እ” ይላሉ አቶ ወንዳፍራሽ
“አሁን እማማ ዠማነሽ እኔን ቢጨፈልቁኝ እንደጫጩትዋ ጭጭ ያረጉኛል?”
“ምነው?”
“እንደዚች ጫጩት ነው ጨፍልቄ ጭጭ ማረግህ አሉኝ፡፡ ይችላሉ ሊጨፈልቁኝ?”
“ሊጨፈልቁህ ቢመጡ ምን ታረጋለህ?”
“ኧረ ሊጨፈልቁኝ እንደ ጫጩት? እኔን? እኔ ደሞ በቢላ እግራቸውን ቁርጥ! ደሞ አፍንጫቸውን ጉምድ! ምላሳቸውን ካፋቸው አውጥቼ ቁርጥ! ደሞ እንጥላቸውን ቁርጥ! አባባ?”
“ወይ” አሉት አቶ ወንዳፍራሽ ሰፍተው ክሩን ቋጥረው በጥርሳቸው እየበጠሱ፡፡
“የማማ ዠማነሽ እንጥል ይህን ያክላል?”
“እኔ እንጃላቸው፡፡ እኚውልህ እንደጫጩት ጨፍልቃቸው” አዝብጤ ወንዳፍራሽ እማማ ዠማነሽን እያገላበጠ በቡጢ በክርን ሲደበድብ አቶ ወንዳፍራሽ ወደ ፍራሽ ስራቸው ተመለሱ - እቺን ጥያቄ እየመረመሩ፡፡
እቺ አሁን የምሰፋት ፍራሽ ስንት ነገር ልታይ ልትሸከም ይሆን? አዝብጤ የሚመታትስ ትራስ ስንት ነገር ልትሰማ ይሆን? አቶ ወንዳፍራሽ ይህን እያሰላሰሉ ዓይናቸውን ወደ ሰማዩ አቀኑ፡፡ “አዎን፤ ከሁሉም በላይ ያለ ሰማይ ነው፡፡ ከሰማይ በታች ያለው አሮጌ ቆርቆሮ ነው፡፡ ከቆርቆሮ በታች ኮርኒስ፣ ከኮርኒስ በታች አልጋ፡፡ ካልጋ በላይ ፍራሽ ከፍራሽ በላይ ሹክሹክታ ነው፡፡ ከሹክሹክታው ውስጥ ምስጢር ነው፡፡ ሁሉም ምስጢር ነው፡፡” አሉ አቶ ወንዳፍራሽ በጥበባቸው እየሰፉት ያንን ፍራሽ፡፡ ፍራሽ ለመጋደም፤ ፍራሽ ለሹክሹክታ፤ ፍራሽ ለእንቅልፍ፤ ፍራሽ ለህልም …  
 (“አምስት ስድስት ሰባት እና ሌሎችም
ታሪኮች ከተሰኘው መድበል የተወሰደ -
መስከረም 1981 ዓ.ም”)

Read 3727 times