Saturday, 09 July 2016 09:56

የሀፍረተ - ስጋህን ፀጉር የምታሳየው አለ፣ የብብትህን ፀጉር የምትከለክለው አለ!

Written by 
Rate this item
(21 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት አሮጊት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ የማይታመን ነገር አዩ፡፡ ግቢያቸው በጎርፍ ተጥለቅልቋል፡፡ ውሃው የምድር ቤቱን አጥለቅልቆ ጨርሶ የመጀመሪያውን ፎቅ ሞልቶታል፡፡ አሰቃቂው ነገር ደግሞ ከደቂቃ ደቂቃ፣ ከሰዓት ሰዓት ገና ማጥለቅለቁን እየቀጠለ፣ እያደገ ነው፡፡
አሮጊቷ ከመኝታ ቤታቸው ወደ ውጪ ሲያስተውሉ፣ ጎርፉ ገና ካፋፍ ወደ ታች እየተንደረደረ ነው፡፡ ከፍታውም አፍታ በአፍታ እያደገ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች በእጅ በምትቀዘፍ ጀልባ ሆነው በአሮጊቷ ቤት አጠገብ ሲያልፉ፤
“እማማ፣ እማማ፣ ኧረ እማማ!” ብለው ጮኸው ይጣራሉ!
“እመት፤ ምን ፈልጋችሁ ነው?”
“ይውረዱ፡፡ አብረን እንድናለን፡፡ እባክዎ ይምጡ!” አበክረው አሮጊቷን ለመኗቸው፡፡
“አመሰግናለሁ ሂዱ” አሉ አሮጊቷ፡፡ “ለእኔ እሱ የላይኛው ያውቅልኛል” ብለው ወደ ሰማይ አመለከቱ፡፡ አምላካቸው እንደሚያድናቸው በመተማመን መናገራቸው ነው፡፡
ባለ ጀልባዎቹ ትከሻቸውን ከፍ ዝቅ አድርገው፤ እኛ ምንቸገረን በሚል ስሜት በጀልባቸው እየቀዘፉ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ማታ ገደማ ውሃው አድጎ አድጎ የመኝታ ክፍላቸውን ወደ ማጥለቅለቅ እየመጣ በመሄዱ፤ አሮጊቷ ያላቸው አማራጭ ጣራው ላይ መውጣት ሆነ፡፡ አሮጊቷ ጣራው ላይ ወጡ፡፡ አንድ ባለሞተር ጀልባ እንዳጋጣሚ ብቅ አለና አያቸው፡፡ ከዚያም፤
“እማማ” ሲል ጮኾ ተጣራ፡፡
“አቤት የእኔ ልጅ” አሉ የሞት ሞታቸውን፡፡
“አይጨነቁ፤ መጥቼ አወርድዎትና በሞተር ጀልባ እንሄዳለን!”
አሮጊቷም፤
“ግዴለህም ልጄ በምንም አትቸገር! ለእኔ እሱ የላይኛው ያውቅልኛል፡፡ አንተ ሂድ በሰላም ግባ” ይሉታል፡፡ ጀርባቸውን ያዞሩበታል፡፡ ሞተሩን ቀስቅሶ እሱም መጭ ይላል!
አሮጊቷ ምንም ሳይቆዩ ጎርፍ ጣራውን ማጥለቅለቅ ስለጀመረ፤ ከጣራው በላይ ወዳለው ወደ ብቸኛው፣ እስካሁን ጎርፍ ወዳልነካው፣ ቦታ፤ ወደ ጭስ ማውጫው አናት ወጡ! እንደ ዕድል ሆኖ የቀይ መስቀል ጎርፍ መከላከያ ቡድን ወደ አሮጊቷ ቤት አጠገብ ይመጣል፡፡
“ወደ ትልቁ ጀልባ ይዝለሉ እማማ!” አለ ከመከላከያ ቡድን አባላት አንዱ፡፡
አሮጊቷ ራሳቸውን ነቀነቁና ኮስተር ብለው፤
“እሱ የላይኛው ያውቃል፡፡ እሱ የትም አይጥለኝም!” ይላሉ፡፡ ትልቁ ጀልባም፤ እየተምዘገዘገ የአሮጊቷን ቤት አልፎ ሄደ፡፡ ውሃው ማደጉን አላቋረጠም፡፡ እስከ ጭስ ማውጫው አናት ደረሰና አሮጊቷን ዋጣቸው፡፡ አሮጊቷ ውሃው እየዋጣቸው ሳሉ ፀሎታቸውን ለአምላካቸው አሰሙ፡፡
“ምነው አምላኬ! አንተን አምኜ ጉድ ታረገኝ?” ሲሉ አማረሩ፡፡
አምላክም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤
“አንቺ ሴት! ችግርሽን አይቼ ሶስት ጀልባ ላክሁልሽ፡፡ ያውም በመጀመሪያ በእጅ የሚዘቀፍ ትንሽ ጀልባ፡፡ ምናልባት ጥሩ ኑሮ ትኖሪ ስለነበር ትንሹን ጀልባ አልቀበልም ያልሺው ያንሰኛል ብለሽ ይሆናል ብዬ! ቀጥዬ በሞተር የሚነዳ መካከለኛ ጀልባ ላኩልሽ፡፡ እሱንም አሻፈረኝ አልሽ፡፡ በሶስተኛው ትልቁን ጀልባ፣ ከነትልቅ ሞተሩ፤ ሊያውም ከነሰራተኞቹ ላኩልሽ፡፡ በጭራሽ አልቀበልም አልሽ! ከዚህ በላይ ምን ላድርግሽ?! ከእንግዲህ የራስሽን መንገድ ፈልጊ!” አላቸው፡፡
*       *       *
ጎርፉንም ድርቅንም ካልተቆጣጠሩት ለከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋልጥ እንገንዘብ፡፡ ሲረዷቸው የማይረዱ አያሌ ናቸው፡፡ በዓመታትና በወራት ጊዜ ውስጥ ሳይሆን በቀን ውስጥ ከተከሰተው የማይማሩ ብዙ ናቸው፡፡ ጎርፍ መምጣቱን፣ ክረምት መግባቱን እዩ፤ አጥራቸውን ማጠርን፣ እርከናቸውን መስራትን፣ ጣራቸውን ማጠንከርን የማይሹ በርካታ ናቸው፡፡ ኑሮ መቼም ሞልቶ አያውቅም፡፡ ውጣ ውረድ አለው፡፡ በሁሉም መልክ ጥረትና ትግልን ይጠይቃል፡፡ የአንዳንዱ ኑሮ ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ የአንዳንዱ የዘነጋ ተወጋ ነው፡፡ የአንዳንዱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው፡፡ አንዳንዱ ወፍራም ውሻ፣ አለ ሲሉት ይሞታል ነው፡፡ ወረቀት ላይ ያስቀመጥነው ዕድገት የሰውየውን መሶብ እንዴት አድርጎት ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ድህነት ላይ የምናሰግረው መፈክር የወረቀት ላይ ነበር (Paper tiger እንዲሉ) ያደርገናል፡፡
ነጋ ጠባ የሚወራለት የመልካም አስተዳደር ችግር ዛሬ ቁስሉ ዳነ ሲባል፣ ነገ እያመረቀዘ የቆላ ቁስል ይሆንብናል፡፡ ጨርሶ ወደ ማይድን በሽታ፣ ወደ ጋንግሪንነት፤ እንዳይሄድ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የከፋው ችግር ደግሞ ለሙስናውም፣ ለዲሞክራሲዓዊና ለመብት ጥያቄውም፣ ለፍትሕ መጓደልም ወዘተ “ተጠያቂው መልካም አስተዳደር ነው” ማለቱ ሲሆን ዕውነቱን ከማደብዘዝም አልፎ ፈር ያስተዋል፡፡ የሀገራችን ሌላው ቁልፍ ችግር፣ ቤተ-ሰሪ ለፍቶ ለፍቶ “ደም - የለውም” እስኪባል ድረስ ቅርሱን ጨርሶ፣ ቤት ሰርቶ “ፊኒሺንጉ” ያስቸግራል እንደሚባለው፤ በጣም ያስቸግራል ይላሉ፡፡ ይሄንን በቀላሉ ለመረዳት የኳስ ቡድናችንን ማጤን ነው፡፡ ሁሌ እግብ ጋ ሲደርሱ አይሳካላቸውም እንደሚባለው ነው - “የአፈፃፀም ችግር” አለባቸው የተለመደች አባባል ናት፡፡ ስንት ዘመን የዚህ ችግር ቁራኛ እንሆናለን? ነው ወይስ እየደጋገምነው አዋቂው እንዳለው፤ “ትለምጂዋለሽ” ሆኖ አረፈው፡፡ የበጀት መዝጊያ ሲደርስ “ምንጣፍ መግዛት” የአፈፃፀም ችግርን መቅረፍ ነውን? ወይስ በዘመኑ ቋንቋ “የአፈፃፀም ችግር “ውስጤ ነው” በሚል “ቃና” የምናልፈው ጣጣ ይሆን? የችግሮቻችን ብዛትና የመፍትሔ አሰጣጣችን አቅም ሲታይ፣
“በነጠላ ጫማ፣ ባንቺ አረማመድ
እንዴት ያልቅልሻል ያ ሁሉ መንገድ!” የሚባለው ህዝባዊ ዘፈን ግጥም ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ የወተወትነው በሥራ እንለወጥ ዘንድ እንጂ እንደው የማንጓጠጥ ወግ ለማምጠቅ አይደለም፤ በቀና መንፈስ ነው፡፡
“ለትምክህት አይደለም፣ ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ፡፡
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ!”
እንዳለው ነው፡፡
በህዝብ ተዓማኒነትን ለማፍራት የመሞከር ጉዳይ በመንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው፡፡ በኦሮሚያ ግጭት ነበር፡፡ በአማራ ክልል ግጭት ነበር፡፡ በአዲስ አበባም ግጭት ነበር፡፡ በወለጋም ግጭት ነበር፡፡ ግጭትን በእልህ ሳይሆን በዘዴ፣ በብልህነት ለመፍታት መሞከር፣ ካለፈው ትምሀርት መውሰድ፣ ዋና መንገድ ነው፡፡ ሌላው ቁልፍ መንገድ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ አንዱን በዱላ አንዱን በመላ፤ የሚለው አያያዝ መፈተሽ አለበት፡፡ ዲፕሎማሲያችን፤ “የሀፍረተ-ስጋህን ፀጉር የምታሳየው አለ፡፡ የብብትህን ፀጉር የምትከለክለው አለ፡፡” የሚለውን ልብ ይበል፡፡

Read 7316 times