Saturday, 09 July 2016 09:49

31ኛው ኦሎምፒያድና የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች በ10ሺ እና በ5ሺ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(9 votes)

በ10ሺ ሜ. ወንዶች በ12     ኦሎምፒያዶች   5 የወርቅ፤ 2 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ10ሺ ሜ. ሴቶች በ7 ኦሎምፒያዶች  4 የወርቅና 2 የብር  2 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ5ሺ ሜ. ወንዶች በ12     ኦሎምፒያዶች  3 የወርቅ፤ 2 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ5ሺ ሜ. ሴቶች በ5 ኦሎምፒያዶች      3 የወርቅና 4 የብር  1 የነሐስ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ፤ መሰረትና ገንዘቤ

በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ ለሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ 26 ቀናት ቀርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ በተለይ በረጅም ርቀት በ10ሺ እና 5ሺ ሜትር  ስኬታማ እንደሆነች ይታወቃል፡፡  በሁለቱ የውድድር መደቦች በ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ  የምታሰልፋቸው ኦሎምፒያኖች  ማንነት በጉጉት እየተጠበቀም ነው፡፡ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴና በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለሚኒማ ማሟላት የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሰኞ ያበቃል፡፡  በረጅም እና በመካከለኛ ርቀት  የውድድር መደቦች  የኢትዮጵያ ሙሉ ቡድን ዝርዝር በቀጣይ ሳምንታት ይታወቃል፡፡  ይህ የስፖርት አድማስ ልዩ ትንታኔ በ31ኛው ኦሎምፒያድ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያን በመወከል ቋሚ ተሰላፊ በሚሆኑት ኦሎምፒያኖች ምርጫ ዙርያ የሚያተኩር ነው፡፡ በረጅም ርቀት በሁለቱም ፆታዎች በሪዮ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለመሆን የሚፎካከሩ እጩ ኦሎምፒያኖች ዝርዝር፤ በውድድር ዘመኑ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ዳሰሳ፤  በተለያዩ ትንታኔዎች እና የሜዳልያ ትንበያዎች ለኢትዮጵያ ስለተሰጡት  ግምቶች፤ ስለተፎካካሪ አገራት የቡድን አመራረጥ እና ምርጥ አትሌቶቻቸው ፤ ባለፉት ኦሎምፒያዶች የኢትዮጵያ  ውጤት ታሪክ እና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎችን የሚዳስስ ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት የውድድር መደቦች በሁለቱም ፆታዎች ስለሚካሄደው ምርጫ በቀጣይ ሳምንት እንመለስበታለን፡፡
እጩዎቹ ኦሎምፒያኖቹ
ኢትዮጵያ ለሪዮ ኦሎምፒክ ስታደርገው የነበረ ዝግጅት ከ3 ወራት በላይ ያለፉት ሲሆን፤ በምታሳትፋቸው ቡድኖች ከሚካተቱ አትሌቶች መካከል በጊዜያዊ ምርጫ  በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የተያዙት እጩ ኦሎምፒያኖች በወቅቱ ተገልፀው ነበር፡፡ በ10 ሺህ ሜትር በጊዜያዊው ዝርዝር የተያዙት እጩ ኦሎምፒያኖች በወንዶች  12  እንዲሁም በሴቶች ደግሞ 6 ነበሩ፡፡ በ10 ሺህ ሜትር  ወንዶች ቀነኒሳ በቀለ፤ ታሪኩ በቀለ ፤ ሙክታር እድሪስ፤  ኢማና መርጊያ፤  ሞሰነት ገረመው፤ አዱኛ ታከለ ፤ ፀበሉ ዘውዴ ፤ ታምራት ቶላ ፤ሙሴ ዋሲሁን ፤ይገረም ደመላሽ፤  ኢብራሒም ጀይላና  ፤ብርሃኑ ለገሰ ፤ በሴቶች ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ ፤ ገለቴ ቡርቃ፤ በላይነሽ ኦልጅራ፤ ዓለሚቱ ሃሮዬ፤ ነፃነት ጉደታና ጐይተቶም ገ/ስላሴ  ናቸው፡፡  በሌላ በኩል በ5ሺ ሜትር በጊዜያዊው ዝርዝር የተያዙት እጩ ኦሎምፒያኖች በወንዶች 7 እንዲሁም በሴቶች 6 አትሌቶች  ነበሩ ፡፡  በ5ሺህ ሜትር  ወንዶች ያሲን ሃጂ ፤ዮሚፍ ቀጀልቻ፤ ሐጎስ ገብረሕይወት፤ ጌታነህ ሞላ፤ ደጀን ገብረመስቀል፤ የኔው አላምረውና ልዑል ገብረ ሥላሴ እንዲሁም በሴቶች አልማዝ አያና ፤ሰንበሬ ተፈሪ ፤ገንዘቤ ዲባባ፤ መሠረት ደፋር፤ ዓለሚቱ ሐዊና ሐብታምነሽ ተስፋዬ ናቸው፡፡  ከላይ ከተጠቀሱት የእጩ ኦሎምፒያኖች ዝርዝር መካከል  በሁለቱም ርቀቶች በቋሚ ተሰላፊነት በ31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ የሚሰለፉት  ይመረጣሉ፡፡ የእጩ ኦሎምፒያኖች ዝርዝር ከሁለት ወራት በፊት ቢገለፅም ፤ ከአወዛጋቢው የማራቶን ቡድን ምርጫ በኋላ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ አሰራራቸው ድብቅ እየሆነ በመምጣቱ ወቅታዊ መረጃ እየተሰማ አይደለም፡፡ ይህም በረጅም ርቀት 10ሺ እና 5ሺ ሜትር  ምን አይነት ቡድን እንደሚዋቀር ለመገመት የሚቻልበትን ሁኔታ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች 3 አትሌቶችን ለመምረጥ በማወዳደርያው መስፈርት የትኞቹ ውድድሮች ከግምት እንደሚገቡ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ምናልባትም የዓለምና አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች እና የኢትዮጵያ   አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤቶች እንደሚታዩ መጀመርያ አካባቢ ግምቶች ነበሩ፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ዋናዎቹ የምርጫ ማወዳደሪያዎች በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂንና በሆላንዷ ሄንግሎ ከተማ በ10ሺ ሜትር የተከናወኑት ማጣርያዎች እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ ውጤቶች እና የተመዘገቡ ሰዓቶች እንደሚሆኑ እየተገለፀ ነበር፡፡  
10ሺ ከሄንግሎው የኦሎምፒክ ማጣርያ በኋላ
ከ2 ሳምንት በፊት በተለይ በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሚኒማን ለማሳካት በሆላንዷ ከተማ ሄንግሎ በኤፍቢ ኬ ጌምስ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አማካኝነት የተዘጋጀ  ውድድር ነበር፡፡ በአይኤኤኤፍ የኦሎምፒክ ሚኒማ ደንብ መሰረት በ10ሺ ሜትር እስከ ጁላይ 11 የተመዘገቡ ውጤቶችን አትሌቶች ለማስመዝገብ ያስችላሉ፡፡ በኤ ደረጃ ሚኒማዎቹ በ10ሺ ሜትር ለወንዶች 28 ደቂቃ ለሴቶች 32 ደቂቃ ከ15 ሰከንዶች ናቸው፡፡ ከሚኒማዎቹ ባሻገር አይኤኤፍ የየአገራቱ ፌደሬሽኖች እና ኦሎምፒክ ኮሚቴዎችን የሚኒማ መስፈርቱን ተከትለው በተጨማሪ የምርጫ አካሄዶቻቸው  ቋሚ ተሰላፊ ኦሎምፒያኖችን እንዲመረጡ ይፈቀዳል፡፡  በሄንግሎው ኤፍቢኪ ጌምስ   በሴቶች  15  እንዲሁም በወንዶች 20 ኢትዮጵያዊ  አትሌቶች   የሪዮ ኦሎምፒክ ትኬታቸውን ለመቁረጥ  ተካፋይ ነበሩ፡፡ በሴቶች ምድብ   ያሸነፈችው በኦሎምፒክ  ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ የምትበቃው አልማዝ አያና ስትሆን ሪዮ ላይ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር የሚኖራትን ድርብ ተሳትፎ  ያረጋገጠችበት ድል ነበር፡፡  አትሌት አልማዝ በሪዮ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት በሁለት ውድድሮች በመሳተፍ ለሁለት ሜዳልያዎች ከሚጠበቁ አትሌቶች በብቸኝነት የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች አትሌቷ በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን በመሆኗ፤ የውድድር ዘመኑን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቧ እና በዳይመንድ ሊግ እያሳየች ባለችው ስኬት የወርቅ ሜዳልያውን መውሰድ እንደምትችል ይገለፃሉ፡፡ በረጅም ርቀት ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን የማግኘት እድል የሚኖራት ግን በ10ሺ ሜትር ከተወዳደረች በኋላ በ5ሺ ከሮጠች መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ የውድድር መርሃግብር መሰረት ግን 10ሺ ሜትር በመዝጊያው ወቅት ከ5ሺ በኋላ መካሄዱ ይታወቃል፡፡
በሄንግሎው ኤፍቢኬ ጌምስ አምና በተመሳሳይ ለዓለም ሻምፒዮና ተደርጎ በነበረው ማጣርያ አሸንፋ የነበረችው እና ከፍተኛ ልምድ ያላት ገለቴ ቡርቃ በሁለተኛ ደረጃ ውድድሯን አጠናቅቃለች፡፡ ገለቴ ቡርቃ በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ማጣርያ ባስመዘገበችው ሁለተኛ ደረጃዋ በኦሎምፒክ ቡድኑ የመሳተፍ እድል የሚኖራት ሲሆን ለመጀመርያዋ የሜዳልያ ስኬት የምታነጣጥር ይሆናል፡፡
በሄንግሎ ከተማ በኤፍቢኪ ጌምስ በተካሄደው የሪዮ ኦሎምፒክ ማጣርያ  አስደናቂ ውጤት የነበራት ሌላ አትሌት በ3ኛ ደረጃ የጨረሰችው ጥሩነሽ ዲባባ ናት፡፡ በወቅቱ በ10ሺ ሜትር ለመጀመርያ ጊዜ ነበር ሽንፈት የገጠማት ጥሩነሽ፤  ለ2 ዓመታት በወሊድ ምክንያት ከውድድር ርቃ የነበረች ሲሆን፤ በሄንግሎው ውድድር በሶስተኛ ደረጃ በመጨረስ ለ4ኛ ጊዜ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን ማረጋገጧ የሚደነቅ ነው፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክም በ10ሺ ሜትር በምርጥ ብቃት መሳተፏ የማያጠራጥር ሲሆን፤ በ10ሺ ሜትር ለ3ኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት በታሪክ የመጀመርያዋ ሴት አትሌት ለመሆን የተሰጣትን ከፍተኛ ግምት የምታሳካበትን እድልም አግኝታለች፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በ2004 እኤአ በአቴንስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ሶስት ኦሎምፒኮችን ተሳትፋ፤ በረጅም ርቀት በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር በድምሩ  5 (3 የወርቅና ሁለት የነሐስ) ሜዳልያዎችን በማግኘት በአንደኛ ደረጃ የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን እንደያዘች ይታወቃል፡፡
በተያያዘ በሄንግሎ ኤፍ ቢኬ ጌምስ በወንዶች ውድድር  ለማሸነፍ የበቃው በ2012 የታዳጊዎች  የዓለም ሻምፒዮን የነበረው ይገረም ደመላሽ ነው፡፡ ታምራት ቶላ፤ አባዲ አምባዬ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡  በማጣርያው ተካፍሎ የነበረው እና በ10ሺ ሜትር የዓለም ምርጥ አትሌት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ ባልታወቀ ምክንያት ውድድሩን አቋርጦ ሲወጣ ኢብራሂም ጄይላንም ውድድሩን አልጨረሰም፡፡  በርግጥ ከሄንግሎ ውድድር በፊት በአሜሪካ ዩጂን ተካሂዶ በነበረው ሌላ የ10ሺ ሜትር ውድድር ኢብራሂም ጄይላንና ታምራት ቶላ ከ27 ደቂቃዎች በታች በመግባት ከኢትዮጵያ   አትሌቶች የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ ነበሩ፡፡
    በሪዮ ኦሎምፒክ የረጅም         ርቀት     ተፎካካሪዎች    
በሪዮ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ወንዶች የወርቅ ሜዳልያው በብዙ ግምቶች ለእንግሊዙ ሞፋራህ እንደተሰጠ ነው፡፡ የብር እና ነሐስ ሜዳልያዎቹ ደግሞ ለኬንያ አትሌቶች ተገምተዋል፡፡  ለኢትዮጵያውያኑ ዋና ተፎካካሪ ሆኖ የሚጠቀሰው  የእንግሊዙ ሞ ፋራህ  ከ4 ዓመታት በፊት በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር  ድርብ ድል ማስመዘገቡ ይታወሳል፡፡  የአሜሪካ ጋለን ሩፕም እና የኬንያው ፖል ታኑዊ ከተፎካካሪዎቹ መካከል  ይጠቀሳሉ፡፡በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ አሃዛዊ መረጃ መሰረት በወንዶች 10ሺ ሜትር  ሞ ፋራህ  በ1380 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ሲይዝ ሁለት የኬንያ አትሌቶች በ2ኛና 3ኛ ደረጃ ይከተሉታል፡፡ ታምራት ቶላ በ1270 ነጥብ 4ኛ፤ ኢብራሂም ጄይላን  በ1263 ነጥብ አምስተኛ፤ የአሜሪካው ጋለን ሩፕ 7ኛ እንዲሁም በሄንግሎ ማጣርያ ያሸነፈው ይገረም ደመላሽ 10ኛ ደረጃና ሙክታር ኢድሪስ 17ኛ ላይ ናቸው፡፡
በሴቶች 10ሺ ሜትር ደግሞ ለወርቅ ሜዳልያው እኩል ግምት የወሰዱት የኢትዮጵያዋ ገለቴ ቡርቃ እና የኬንያዋ ቪቪያን ቼሮይት ነበሩ፡፡ ከሄንግሎው ውድድር በኋላ ግን አልማዝ አያና እና ጥሩነሽ ዲባባ ወደ ግምቱ የተቀላቀሉ ሲሆን ምናልባቱም ሜዳልያውን ኢትዮጵያን ጠቅልለው ሊወስዱ ይችሉታል እየተባለም ነው፡፡ በሌላ በኩል ጥቂት የማይባሉ ግምቶች የብርና የነሐስ ሜዳልያ አትሌቶቹን በተለይ የአሜሪካ እና የኬንያ አትሌቶች እንደሚወስዷቸው የተሰጠው ግምት ያመዝናል፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር  ቡድን ጥሩነሽ ዲባባ፤ አልማዝ አያና እና ገለቴ ቡርቃ ቋሚ ተሰላፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ ለኢትዮጵያውያኑ ዋና ተፎካካሪ ሆና እየተጠቀሰች ያለችው የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ቪቪያን ቼሮይት ስትሆን ሌሎች ተፎካካሪ አትሌቶች ሳሊ ኪፕዬጎ ከኬንያ እንዲሁም ኤምሊ ኢንፊልድ ከአሜሪካ ናቸው፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ አሃዛዊ መረጃ መሰረት በሴቶች 10ሺ ሜትር የኬንያዋ ቪቪያን ቼሮይት በ1294 ነጥብ 1ኛ ስትሆን ሌላዋ የኬንያ አትሌት በ1282 ነጥብ ትከተላታለች፡፡ አልማዝ አያና በ1276 ነጥብ እንዲሁም ገለቴ ቡርቃ በ1271 ነጥብ በ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ተከታትለው ሲቀመጡ የአሜሪካዋ ኢሚል ኢንፊልድ 5ኛ ስትጠቀስ ጥሩነሽ እስከ20ኛ ደረጃ የለችበትም፡፡
በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ5ሺ ሜትር በዳይመንድ ሊግ ጥሩ ብቃት እያሳዩ የሚገኙት ሙክታር ኢድሪስ፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ሃጎስ ገብረህይወት በቋሚ ተሳላፊነቱ ቅድሚያ ግምት ያገኛሉ፡፡  ለወርቅ ሜዳልያው ገብረህይወት እና ዮሚፍ ቀጀልቻ ከፍተኛውን ግምት እየወሰዱ ናቸው፡፡ ለብር እና ነሐስ ሜዳልያዎቹ የታጩት አትሌቶች ሞ ፋራህን ጨምሮ የኬንያ እና የኢትዮጵያ   አትሌቶች ናቸው፡፡ በኦልአትሌቲክስ ድረገፅ አሃዛዊ መረጃ መሰረት በ5ሺ ሜትር ወንዶች በ1347 ነጥብ በ1ኛደረጃ ላይ የሚገኘው ሙክታ ኢድሪስ ሲሆን፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ1330 እንዲሁም ሃጎስ ገብረህይወት በ1317 ነጥባቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ሞፋራህ በዚህ ደረጃ ዝርዝር 6ኛ ሲሆን ደጀን ገብረመስቀል ደግሞ 8ኛ ነው፡፡
በሴቶች 5ሺ ሜትር  ኢትዮጵያን አትሌቶች በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በሚያሳዩት ብቃት ምርጫ ፈታኝ እንደሚሆን፤ በተሳትፏቸውም በእርግጠኝነት የወርቅ ሜዳልያን እንደሚያሳኩ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተለይ ብዙ ትንበያዎች የወርቅ ሜዳልያው በውድድር ዘመኑ ምርጥ ብቃቷን እያሳየች በምትገኘው አልማዝ አያና መወሰዱን እየገለፁ ሲሆኑ፤ ከወርቅ ሜዳልያ ባሻገር የሜዳልያ እድል ካላቸው የኢትዮጵያ   አትሌቶች  ሰንበሬ ተፈሪ ትጠቀሳለች፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ  ላይ በ5ሺ ሜትር ሴቶች የኢትዮጵያን ቡድን ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱ ዘገባዎች ከ15 ደቂቃዎች ከ24 ሰከንዶች በታች የገቡ ከ22 በላይ አትሌቶች መኖራቸውን እንደማስረጃ በማንሳት ነው፡፡ ይሁንና በዳይመንድ ሊግ እያሳዩ በሚገኙት ብቃት ለቋሚ ተሰላፊነት አልማዝ አያና፤ ሰንበሬ ተፈሪ እና ይጠበቃሉ፡፡ የገንዘቤ ተሳትፎ ምን እንደሚሆን በግልፅ አልታወቀም፡፡ ለኢትዮጵያ  ውያኑ ዋና ተፎካካሪ ከሚሆኑት መካከል ደግሞ ቪዮላ ኪቢዮት እና ሜርሲ ቼሮኖ ከኬንያ ናቸው፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ አሃዛዊ መረጃ መሰረት በሴቶች 5ሺ አልማ አያና በ1414 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ስትሆን፤ በሀለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ሁለት የኬንያ አትሌቶች ከተጠቀሱ በኋላ ሰንበሬ ተፈሪ በ1339 ነጥብ ትከተላለች፡፡ ቪቪያ ቼሮይት 5ኛ ገንዘቤ ዲባባ 7ኛ  እንዲሁም ገለቴ ቡርቃ 9ኛ ላይ ናቸው፡፡
ቀነኒሳና ፤መሰረትና ገንዘቤ
በሪዮ ኦሎምፒክ ሶስት ትልልቅ ኦሎምፒያኖች ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ በረጅም ርቀት የትራክ ውድድሮች በኢትዮጵያ  የኦሎምፒክ ቡድን  ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖችን ተሳትፎን በርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ለመሆን የበቁት ቀነኒሳ በቀለ  ፤ መሰረት ደፋር እና ጥሩነሽ ዲባባ በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የሪዮ ኦሎምፒክ እጩ ኦሎምፒያኖች ዝርዝር መያዛቸው ይታወስ  ነበር፡፡ ከእነዚህ አንጋፋ አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ ብቻ በኦሎምፒክ 10ሺ ሜትር የሚያሳትፋትን እድል አሳክታለች፡፡  በኦሎምፒክ የማራቶን ቡድን ሳይመረጥ ከቀረ በኋላ በ10ሺ ሜትር ለመሳተፍ ሌላ እድሉን የሞከረው ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን አቋርጦ በመውጣቱ አልተሳካለተም፡፡  በ10ሺና በ5ሺ ሜትር የዓለምን ሪከርድ የያዘው፤ በኦሎምፒክ ለሁለት ጊዜያት የወርቅ ሜዳልያ ያገኘው እና በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሪከርድ ባለቤት የሆነው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ ሜትር በኦሎምፒክ መድረክ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ  ፍላጎት ነበረው፡፡ በሄንግሎው ማጣርያ ላይ አቋርጦ በመውጣቱ በ10ሺ ሜትር የሚካፈልበት እድል ተበላሽቶበታል፡፡ ቀነኒሳ በተሳተፈባቸው 3 የኦሎምፒክ መድረኮች በረጅም ርቀት ሶስት የወርቅ እና 1 የብር ሜዳልያ  በማግኘት በወንዶች ምድብ ከፍተኛውን ውጤት ያመዘገበ መሆኑ ይታወቃል፡፡   በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ወርቅ በ5ሺ ሜትር ብር፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ10ሺ እና 5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች እንዲሁም በለንደን ኦሎምፒክ በ4ኛ ደረጃ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ነበሩ፡፡ ቀነኒሳ በ2020 እኤአ ጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ በምታዘጋጀው 32ኛው ኦሎምፒያድ በማራቶን የመሳተፍ እድል ቢኖረውም እድሜው ወደ 39 መጠጋቱ አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡
በሌላ በኩል በሄንግሎ በ10ሺ ሜትር በተካሄደው ማጣርያ ያልተሳተፈችው አትሌት መሰረት ደፋር   በ10ሺ ሜትር ከእጩ ኦሎምፒያኖች ዝርዝር ውስጥ ብትገኝም፤ የሪዮ ኦሎምፒክ ያመለጣት ይምሰላል፡፡ ከ12 አመት በፊት በአቴንስ ኦሎምፒክ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ በሴቶች 5ሺ ሜትር ፈርቀዳጁን የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበችው አትሌት መሰረት ደፋር ነበረች፡፡  በለንደን ኦሎምፒክ ለሁለተኛ ግዜ በወሰደችው  ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያም የርቀቱ ንግስት መሆኗ ተረጋግጧል፡፡ አትሌት መሰረት ደፋር በ3 ኦሎምፒኮች የተሳትፎ ታሪኳ በ5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ እና አንድ የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደሙን ውጤት ለማስመዝገብም በቅታለች፡፡
በሌላ በኩል በ1500 ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ሚኒማ ያላት ገንዘቤ ዲባባም በሪዮ ኦሎምፒክ መሳተፏ አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ ከሁለት ሳምንት በፊት በስፔን ባደረገችው የ5ሺ ሜትር ውድድር አጋጥሟታል የተባለው ጉዳት የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
በረጅም ርቀት የሜዳልያ ትንበያዎች
ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት በ12 ኦሎምፒያዶች ለመሳተፍ የበቃችው ኢትዮጵያ  21 የወርቅ፤ 7 የብር እና 17 የነሐስ በአጠቃላይ 45 ሜዳልያዎችን የሰበሰበች ሲሆን  አብዛኛዎቹ ውጤቶች በረጅም ርቀት የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር ውድድሮች እንደተገኙ ይታወቃል፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ  4 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎች ለማምጣት መታቀዱን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያስታወቀው ከ3 ወር በፊት ነው፡፡  የሜዳልያዎቹ ግምት  በሁለቱ የረጅም ርቀት የትራክ ውድድሮች በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር፤ በሴቶች 1500 እና በማራቶን ሊሆን እንደሚችልም መገመት አይከብድም፡፡  ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን በተባለ  ድረገፅ ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፤ 3 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 8 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች  እንደምትሰበሰብ  ተገምቶ ከዓለም 26ኛ ደረጃ በማግኘት  እንደምትጨርስ ተገልጿል፡፡   ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን የሜዳልያ ትንበያውን የሰራው በወቅታዊ ውጤቶች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ትልልቅ ውድድሮች የዓለም ሻምፒዮና እና ሌሎችን በማገናዘብ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን ትንበያ መሰረት ለኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች የሚመዘገቡት በሴት ኦሎምፒያኖች ሲሆን በ1500 ገንዘቤ ዲባባ፤ በ5ሺ ሜትር አልማዝ አያና እንዲሁም በሴቶች ማራቶን ማሬ ዲባባ እንደሚያሸንፉ ተገምቶላቸዋል፡፡ ሁለቱን የብር ሜዳልያዎች በ10ሺ ሜትር ገለቴ ቡርቃ እንዲሁም  በ5ሺ ሜትር ሰንበሬ ተፈሪ እንደሚያገኙ ሲገመት፤ 3 የነሐስ ሜዳልያዎችን በ5ሺሜትር    ገንዘቤ ዲባባ፤  በ5ሺ ሜትር  ሃጎስ ገብረህይወት እና ከማራቶን ቡድኑ ምርጫ ውጭ የሆነው  የማነ ፀጋዬ በወንዶች ማራቶን ያስመዘግባሉ በሚል ተንብዮታል፡፡ ኢንፎስትራዳ በተባለው የስፖርት አሃዛዊ መረጃዎች አቀናባሪ ድረገፅ ደግሞ  ለኢትዮጵያ በአጠቃላይ  10 ሜዳልያዎች 3 የወርቅ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያ ተተንብዮላታል፡፡ ኤምፖራ የተባለ ድረገፅ በተለይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች ላይ በማተኮር በሰራው የሜዳልያ ተፎካካሪዎች ትንታኔ ደግሞ በ10ሺ ሜትር ሴቶች ሁለት የኬንያ ሁለት የኢትዮጵያ አትሌቶች እንዲሁም አንድ አሜሪካዊ ተካተተዋል ፡፡ የሜዳልያ እድል አላቸው የተባሉት ጥሩነሽ ዲባባ እና ገለቴ ቡርቃ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ለእንግሊዙ ሞፋራህ እና ለሶስት የኬንያ አትሌቶች በ10ሺ ሜትሮች የሜዳልያ እድል መኖሩን ሲገመት ኢትዮጵያውያን አልታጩም በ5ሺ ሜትር ደግሞ  ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና እንዲሁም ሰንበሬ ተፈሪ ተጠብቀዋል፡፡ በወንዶች 5ሺ ደግሞ ለዮሚፍ ቀጀልቻ ሃጎስ ገብረህይወት እና ደጀን ገብረመስቀል ግምት አለ፡፡
የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች
በኦሎምፒክ መድረክም በወንዶች  በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ሁለት ክብረወሰኖችን የያዘው  ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ሁለቱንም የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች እኤአ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ሲያስመዘገባቸው በ5 ሺ ሜትር 12 ደቂቃ ከ57.82 ሰኮንዶች እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 27 ደቂቃ ከ04.7 ሰኮንዶች የሰፈሩ ናቸው፡፡  ሌላው በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሪከርድ በሴቶች በ2008 እኤአ ቤጂንግ  ላይ በጥሩነሽ ዲባባ በ29 ደቂቃዎች ከ54.66 ሰከንዶች  አስመዝግባለች፡፡ በ5ሺ የኦሎምፒክ ሪከርድ በሴቶች በ2000 እኤአ ሲድኒ ላይ በሮማኒያዋ ጋብሬላ ዛቦ በ14 ደቂቃዎች ከ40.79 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ የተያዘ ነው፡፡
ያለፉት ኦሎምፒያዶች የውጤት ታሪክ
ኢትዮጵያ   ባለፉት 12 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ በ10ሺ ሜትር ወንዶች  5 የወርቅ፤ 2 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ የመጀመርያውን የሜዳልያ ክብር በብር ሜዳልያ ያስመዘገበው በ1968 እኤአ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ማሞ ወልዴ  ነበር፡፡ ከዚያም በ1972 እኤአ በሙኒክ ኦሎምፒክ ምሩፅ ይፍጠር የነሐስ፤ በ1980 እኤአ ምሩፅ ይፍጠር የወርቅ እና መሐመድ ከድር የነሐስ፤ በ1992 እኤአ ባርሴሎና ኦሎምፒክ አዲስ አበበ የነሐስ፤  በ1996 እኤአ  በአትላንታ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገብረስላሴ የወርቅ ፤ በ2000 እኤአ  በሲድኒ ኦሎምፒክ  ኃይሌ ገብረስላሴ የወርቅ እና አሰፋ መዝገቡ የነሐስ፤ በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅና ስለሺ ስህን  የብር፤  በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እና ስለሺ ስህን የብር እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ታሪኩ በቀለ  የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝተዋል፡፡በ10ሺ ሜትር ሴቶች የኦሎምፒክ ውድድር  ከ1988 እኤአ በሲኦል ኦሎምፒክ ተጀምሮል፡፡  ኢትዮጵያ   ባለፉት 7 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ  4 የወርቅና 2 የብር  2 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ የመጀመርያን የሜዳልያ ክብር በወርቅ ሜዳልያ ያሳካችው በ1992 እኤአ  በባርሴሎና ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ ነበረች፡፡በ1996 እኤአ በአትላንታ ኦሎምፒክ ጌጤ ዋሚ የነሐስ፤ በ2000 እኤአ  በሲድኒ ኦሎምፒክ ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ እና ጌጤ ዋሚ የብር ፤ በ2004 እኤአ  በአቴንስ ኦሎምፒክ እጅጋየሁ ዲባባ የብር እና ደራርቱ ቱሉ የነሐስ፤ በ2008 እኤአ  በቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ  እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡  
በ5ሺ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያ   ባለፉት 12 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ  3 የወርቅ፤ 2 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ የመጀመርያውን የሜዳልያ ክብር በወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበው በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡ ከዚያም በ1992 እኤአ ባርሴሎና ኦሎምፒክ ፊጣ  ባይሳ የነሐስ፤ በ2000 እኤአ በሲድኒ ኦሎምፒክ ሚሊዮን ወልዴ የወርቅ ፤ በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የብር፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ደጀን ገብረመስቀል የብር ሜዳልያዎችን አግኝተዋል፡፡ከ1996 የአትላንታ ኦሎምፒክ ጀምሮ በተካሄደው የ5ሺ ሜትር ሴቶች የኦሎምፒክ ውድድር  ኢትዮጵያ   ባላፉት 5 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ  3 የወርቅና 4 የብር  1 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡
የመጀመርያን የሜዳያ ክብር በነሐስ ሜዳልያ ያሳካችው በ2000 እኤአ ላይ በሲድኒ ኦሎምፒክ ጌጤ ዋሚ ነበረች፡፡ በ2004 እኤአ  በአቴንስ ኦሎምፒክ መሰረት ደፋር የወርቅ እና ጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ፤ በ2008 እኤአ  በቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ እና መሰረት ደፋር የነሐስ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ መሰረት ደፋር የወርቅ እና ጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡ 

Read 4114 times