Saturday, 02 July 2016 12:35

ምናባዊ ናፍቆት!

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(14 votes)

    ስለዚህች ሴት ለማሰብ የምችለው ከእኔ ርቃ ስትሄድ ብቻ ነው፡፡ አጠገቤ እያለች ስለሷ ለማሰብ አልችልም፡፡ አንድን ነገር በደንብ ለማየት እንዲቻል ነገርዬው ከርቀት መሆን ይኖርበታል፡፡ ከርቀት ሲኮን ነው የእውነት የሚገለፀው፡፡
የምን ነገር ማወሳሰብ ነው?!
በቃ አሁን እቺ ሴት ትዝ እያለችኝ ነው፡፡ ቤቱ ውስጥ የእሷ ጠረን ብቻ ነው ያለው፡፡  የሄደችው ዘመድ ለመጠየቅ መሆኑ ናፍቆቴን አልቀነሰውም፡፡ ስልክ ብደውልላት ድምጽዋን መስማት እችላለሁ፡፡ ከምሰማው በላይ ግን የማስታውሰውን የበለጠ አዳምጣለሁ፡፡
እዛች ትንሿ የቀለም ቆርቆሮ ላይ ቁጢጥ ማለት ትወዳለች፡፡ እዛ ጋ ስትቀመጥ አንጀቴ ለምን ሁሌ እንደሚላወስ አይገባኝም፡፡ በተለይ እሷ ልብ ሳትል ስራዋ ላይ ተመስጣ ሳለች ከኋላ መጥቼ ስመለከታት አዝናለሁ፡፡ ግን በእሷ ምክኒያት ማዘኔን እንድታውቅ አልፈልግም፡፡ ቅርብ ሆኖ ሩቅ የሄደች ሲመስለኝ ነው የማዝነው፡፡ ከእውነታው በላይ በመምሰል ውስጥ የምፈጥረው ስሜት ይጥመኛል፡፡ ደስ የሚል ህመም ይፈጥርብኛል፡፡ ለስሜቱ ስል ቁጢጥ ባለችበት እየተመለከትኳት እቆያለሁ፡፡
የምትሰራው ነገር ይገርመኛል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የሆኑ አሻንጉሊቶች ስትሰራ ነበር፡፡ ያኔ ለምን ስዕልሽ ላይ አታተኩሪም ብዬ ስጨቀጭቃት ነበር፡፡ ሀሪፍ ሰዓሊ ናት፡፡ አሁን እሷ በሌለችበት አሻንጉሊቶቹ ሌላ ትርጉም ጫሩብኝ፡፡ የልጅ ፍላጎት ነበር እንዴ አሻንጉሊት የሚያሰራት? አልኩኝ፡፡
ስልክ ደውዬ “መቼ ነው የምትመለሺው?” ብላት ደስ ይላታል፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው መናፈቅ ደስ ይላታል፡፡ እሷ ግን ከማንኛውም ሰው የበለጠች ናት፡፡ የበለጠች መሆኗን ላውቅ የምችለው ደግሞ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ደጋግሜ ነግሬአታለሁ፡፡ ግን ደጋግሞ መናገር ትርጉም የለውም፡፡ ትርጉም እንዲፈጥር መፃፍ አለበት፡፡ ከሄደች አራት ቀን ሆኗታል፡፡ በእያንዳንዱ ቀን አዲስ ስሜት እሷን ተመርኩዞ እየተፈጠረብኝ ነው፡፡ ይሄ ስሜት እሷ ከጎኔ ስትኖር የሌለ … ወይንም ቢኖርም የተድበሰበሰ ነበር፡፡ የሄደችው ልትመለስ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
ግን ባትመለስ ምን ሊከሰት እንደሚችል በማሰብ ናፍቆቴን ማጋነን ፈልጌአለሁ፡፡
የሚዘንበው ዝናብ በመስኮቶቹ ላይ ሲንሸራተት ውሀ መሆኑ ተለውጦ ዕንባ የሆነ መሰለኝ፡፡ ሁሉም ነገር ባዶ ሲሆን ተሰማኝ፡፡ ሁሌ በእሷ ትከሻ ላይ የሚንጠለጠለው የቆዳ ቦርሳ በበሩ እጄታ ላይ ሆኗል፡፡ ትታው ስለሄደች መሆኑን እያወኩም … አዲስ ስሜት በናፍቆት ምክኒያት ተፈጠረ፡፡ ቦርሳው እሷን፣ እጀታው ደግሞ ትርጉም የሌለውን ግዑዝ ብቸኝነቴን አስታወሰኝ፡፡
እናቱ የሞተችበትም ልጅ… እናቱ ገበያ የሄደችበትም እኩል እዬዬ… ይላሉ የሚለው አባባል ትርጉም አልቦ መሆኑ ተሰማኝ፡፡ ለአሁኗ ቅፅበት ያለኝ ነገር እሷ አለመኖሯ ነው፡፡ ጊዜያዊ እጦትም ሆነ ዘላቂ እጦት ቅፅበቷ ውስጥ ሆኖ ስሜቱን ለተሸከመው ሰው እጦት ናቸው፡፡ የእኔን ስሜት ትንሽ ልዩ የሚያደርገው፣ ስሜቱን አጣጥሜ ለእሷ ያለኝን ፍቅር ጥልቀት ለመለካት ስል እጦቱን እየዋኘሁበት ያለው መሆኑ ነው፡፡ እጦቱ አንድ ነው፤ በፍላጎት የመጣም ያልመጣም ቢሆን፡፡
ድንገት የምሞት መሰለኝ፡፡ እንደማልሞት ግን አውቃለሁ፡፡ የመሰለኝ አሁንም ለስሜቴ ጥልቀት መሆኑንም አውቃለሁ፡፡ ነገርዬው እውነትም ውሸትም ነው፡፡ የምሞት ይመስለኛል፤ግን እንደማልሞት አውቃለሁ፡፡ እሷ ለዘላለም የተለየችኝ ይመስለኛል … ግን ከሶስት ቀናት በኋላ እንደምትመለስ እርግጠኛ ነኝ፡፡
እዚህ ውስጥ ግን ባዶነቱ ገዝፎ … ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡ በፊት ስትሄድ--- “ቤት በጊዜ ግቢ” እላት ነበር፡፡ (ነበር ከሶስት ቀናት በፊት መሆኑ ይገርማል፡፡) ዛሬ እኔ ቤት ውስጥ ሆኜ እሷን የማስጠነቅቃት ነገር አለመኖሩ ራሱ ሆዴን ባር ባር አለው፡፡ ሆዴን ባር ባር ሲለው፣ ባር ፈልጌ መጠጣት ነበር ሁነኛ መፍትሄ፡፡ ግን ደግሞ ብጠጣ ስልክ ስትደውል ታውቅብኛለች፡፡ አልጠጣም ብለህ አልነበር ትለኛለች …. ስለዚህ አያዋጣም፡፡
ጉድለቱ አለ፡፡ ግን ጉድለቱን ለመሙላት የሚደረጉ ነገሮች በማንም ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ እናቱ ገበያ የሄደችበት ልጅ ቢያለቅስ … ለቅሶው ማንንም እንደማያሳምነው፡፡ ሞልቃቃ  እንደሚያስብለው፡፡ ሞልቃቃ  ቢያስብለውም … ለቅሶው ግን ለልጁ የእጦት ስሜት፣ እውነተኛ ነው፡፡ ራሷን እናቲቱን ባያሳምናትም እንኳን፡፡
ወጥ ሰርታ ፍሪጁ ውስጥ አስቀምጣ ነው የሄደችው፡፡ ምግቡን እንደ መድሀኒት ከእነ አወሳሰዱ በተደጋጋሚ አስረድታኝ ነበር፡፡ እዛም ስምንት መቶ ኪሎ ሜትር ርቃ በሄደችበት እየደወለች ለማረጋገጥ ትሞክራለች፡፡ እኔም አረጋግጥላታለሁ፡፡ ቀይ ወጡን አሙቄ መብላቴን፡፡ ያሞቅሁት አንዴ ብቻ ነው፡፡ ስቀምሰው አስጠላኝ፡፡ ስለዚህ እንደ ድሮው ከቤት ውጭ መመገብ ጀምሬአለሁ፡፡ ለእሷ ግን እዋሻታለሁ፡፡ ውሸቱም የሆነ የናፍቆት ጣዕም ይመስለኛል፡፡ ለፍቅር እንደተከፈለ መስዋዕትነት አይነት ጣዕም፡፡ ውሸቱ ከወጡ የበለጠ ጣዕም ሰጥቶኛል፡፡ ጣዕሙ ደግሞ ለእሷ በስልክ ስናገረው ድንገት የሚገንን ነው፡፡ ወጥ መስራት ትወድ ነበር፡፡ የሄደችበት የዘመዶቿ ቤት፣ሴቱ ተሰብስቦ ሲቀቅል አለመሳተፏን ነገረችኝ፡፡ መብላትም ሆነ መስራት እንዳስጠላት ይገባኛል፡፡ ወጥ የፍቅር መገለጫ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ እሷ ወጥ መስራት የወደደችው እኔ እስካለሁ ድረስ ነው፡፡ እኔም መብላት የምወደው ለካ እሷ እስከሰራችውና እሷ አብራኝ ቀርባ እስከጨለፈችው ድረስ ነው? … ከዚህ ቀደም ሳላውቀው አልቀርም፡፡ ግን በቅርበት ስለነበር እውቀቱ ይርቀኝ ነበር፡፡ አሁን እሷ በመጠኑ ስትርቅ ደግሞ እውቀቱ ቀርቦ አነቀኝ፡፡ … መታነቁን ፈልጌዋለሁ … ላጣጥመው እሻለሁ፡፡
የሰራቻቸውን አሻንጉሊቶች እንደ ልጆቿ በተለየ እይታ ተመለከትኳቸው፡፡ እንደ ልጆቿ ታቀፍኳቸው፡፡ እነሱም ገበያ ለሄደችው እናታቸው የሚያለቅሱ መሰለኝ፡፡ እኔም አባበልኳቸው፡፡ ግዑዝ አይደሉም፡፡ እሷ እስክትመለስ ህይወት አላቸው፡፡ ልጆቼ ናቸው፡፡
ግድግዳው ላይ ያለው የእሷና የእኔን ፎቶ ፊቱን ገለበጥኩት፡፡ የሆነ እኔነቴ የእሷን በህይወት መኖር የተቀበለ አልመሰለኝም፡፡ ምክንያቱም “ያለፈው ነገር” እና “የአሁኑ” በሚል መስመር የሌለው የጊዜ መስመጥ አለ፡፡ እሷ ስትመለስ ያለፈው ነገርና የሚመጣው አንድ ስለመሆናቸው የተቀበለ አይመስልም፡፡ ድንገት ፍርሀት ወረሰኝ፡፡ ወዲያው ስልኩን አነሳሁ፡፡ አይ ቀልዱ ይብቃ፤ አልኩኝ፡፡ ስልኳ አይነሳም፡፡ አሁን ደነገጥኩ፡፡ ቀልዱ እውነት የሆነ መሰለኝ፡፡ እንደው ስሜቱን በጥበባዊ መንገድ ላጣጥመው ስል ጭራሽ መጥፎ ነገር ጠራሁኝ እንዴ!? በስመአብ ወወልድ … ጭራሽ ግራ ገባኝ! ክፍሉ ይጨምቀኝ ጀመር፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፡፡ ደጋግሜ ደወልኩኝ፡፡ ጭራሽ ተዘግቷል ይላል፡፡ባትሪ አልቆ ነው … ስልኩን ማነጋገር የማትችልበት ቦታ ሆና ነው … ሳትሰማው ቀርታ ነው … ስልኳ ተሰርቆ ነው …ብዙ አማራጭ ቢኖርም ለእኔ የታየኝ ግን የአጭር ልብ ወለድ አጨራረስ ነው፡፡ ያውም ጀማሪ የአጭር ልብ ወለድ ፀሐፊ፤ገና የመጀመሪያውን ልብ ወለዱን ሲጠነስስ እንደሚያደርገው አይነት አጨራረስ ነው ያሰብኩት፡፡ አሰቃቂ አጨራረስ፡፡  
ሁለት ፍቅረኛሞች ነበሩ … ፍቅራቸው ወደር አይገኝለትም … እሱ ያው ደራሲ ነው … እሷ ሰዓሊ … ገንዘብ ባይኖራቸውም ፍቅራቸው ግን መልአክቶቹ ሁሉ የሚቀኑበት አይነት ነበረ፡፡ በኋላ አንድ ቀን ደራሲው ቤቱ ሲገባ ሚስቱ የለችም … ሲጠብቃት … ሲጠብቃት … ስልክ ሲደውልላት አታነሳም፡፡ … ሊፈልጋት ይወጣል … ሲንከራተት አድሮ ሳያገኛት ይቀራል፡፡ … ጠዋት ስልክ ይደወላል … ሲያነሳው መኪና ገጭቶ እንደገደላት ይረዳል፡፡
ይኸው ታሪክ የተደገመ መሰለኝ፡፡ መጀመሪያ ስልክ አይነሳም አይደል የሷም አልተነሳም፡፡ … የልብ ወለዱ ገፀ ባህርይ ቢያንስ ሚስቱን ወጥቶ የመፈለግ እድል ተሰጥቶታል፡፡ እኔ የት ነው እምፈልጋት፡፡ መቀሌ አልሄድ ነገር፡፡ ተቀምጩ መጠበቅ ብቻ ነው የእኔ እጣ ፈንታ፡፡ ቅድም ክፍሉ ውስጥ የናፍቆት ስሜት ይፈጥሩብኝ የነበሩት እቃዎች የአሰቃቂ ሞት ቅሪት መሰሉኝ፡፡ ተቀምጬ መጠበቅ አልቻልኩም፡፡ ስልኬን ይዤ ተፈትልኬ ወጣሁ፡፡ የት ለመድረስ እንደሆነ ባላውቅም፡፡ ስልኩን ደጋግሜ እሞክረዋለሁ፡፡ ምላሹ ያው ነው፡፡ በጣም የሚያስጠላ ነገር ነው፡፡ ከአመጣጡም ታውቆኛል፡፡
ጀማሪ የልብ ወለድ ፀሐፊ የፃፈው ድርሰት ነኝ ለካ፡፡ ፈጣሪ፤ ጀማሪ የልብ ወለድ ፀሐፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰይጣንም ቢሆን ከዚህ በላይ ከፍ አድርጎ ትራጀዲ መስራት ይችል ነበር፡፡ እኔ የምንቀው አይነት ልብ ወለድማ በእኔ ላይ አይፃፍም፡፡ እንደው ቢያንስ በጥበብ ስም እንኳን ተገቢ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የአማተር ልብ ወለድ ለሚወዱ ይድረስባቸው እንጂ ለእኔና ለእሷ እንኳን ይሄ አይነት አስተላለቅ አይመጥነንም፡፡
ቢያንስ ምን አጋጥሟት ስልኳ እንደተዘጋ መታወቅ አለበት? … እንደው የደረሰችበት ሳይታወቅ ቀረ! ሊባል? ኧረ በፈጣሪ!
        *********    *********
እንዲህ እያሰብኩ … በእግሬ ምን ያህል እንደተጓዝኩ አላውቅም፡፡ በባስ መለኪያ ብዙ ፌርማታ ነው፡፡ ሰዎች ሲያልፉ ይታዩኛል፡፡ በአካሎች ፋንታ ሀሳቦቼን ነው የማየው፡፡ ለፅሁፉ ስሜት መፍጠሪያ ብዬ የተመኘሁት ናፍቆት፣ ጥርስ አውጥቶ እኔኑ ራሴን ሲቀረጥፈኝ ይሰማኛል፡፡ መጮህ ግን አልቻልኩም፡፡ እህ! … እላለሁ እየደጋገምኩ፡፡ የምደገፈው ነገር አጣሁ፡፡ ስልኬ ላይ ተጨማሪ ካርድ ሞላሁ፡፡ ምንም ለውጥ የለም፡፡ መጠጥ ቤት ገባሁ፡፡ ሰፈሩን አላውቀውም፡፡ ለመስከር ሳይሆን ለመሞት መጠጣት ፈለኩ፡፡ ትንሿን ጠርሙስ ገዝቼ በእግሬ እየሄድኩ መጠጣት ቀጠልኩ፡፡ ምናልባት ከመሞቷ በላይ ሌላ ሰው አፍቅራ ይሆናል የሚለው ደግሞ እንደ ክፉ ሽፍታ በስቃዬ መሀል እልህ ይጭርብኛል፡፡
     ************    ***********
እንግዲህ በዚህ መሀል እያለሁ ነው … ስልኩ የተደወለው፡፡  ስልኩ ሲደወል በአንድ ጊዜ ሁለት ቦታ ሆኜ ነበር፡፡ አንደኛው፤ መጠጥ በጠርሙስ ይዤ በጎዳና ላይ ወደ ማበድ እያመራሁ፡፡ ሌላኛው ጠረጴዛ ላይ ተቀምጬ እየፃፍኩ፡፡ ስልኩ ሲጠራ … በሁለቱም ማንነቴ በኩል አነሳሁ፡፡
“እ…! እንዴት ነህ አላየሁትም እኮ … በቃ ስለሰለቸኝ ተኝቼ ነበር፡፡ በዛ ላይ መብራቱ ደግሞ ጠፍቷል፡፡ አልናፈቅሁህም! … ምሳ በላህ …”
“በቃ” አልኳት በንዴት … “ነገ ያለ አንዳች ማቅማማት … እንድትመጪ---- የማትመጪ ከሆነ … እኔና አንቺ እንለያያለን … ሰማሽኝ” ብዬ ጆሮዋ ላይ ጠረቀምኩት፡፡
ተቀምጬ የምፅፈው ሰውዬ፣መጠጥ ይዞ ሲንከራተት እንደነበረው ገፀ ባህሪዬ ሰክሬአለሁ፡፡ ላብድ ደርሻለሁ፡፡ ከስካሬና ከቅፅበታዊ ሽብሬ ተመልሼ እስክረጋጋ የተወሰነ ጊዜ ሳይወስድብኝ አይቀርም፡፡ የምፅፈው ታሪክን ባለበት ተውኩት፡፡ አጨራረሱን የማስበው መጀመሪያ እሷ በሰላም ቤቷ ስትገባ ነው፡፡ ሰላም መሆኗን አገላብጬ ካየሁ በኋላ፡፡
አሁን መረጋጋት ነው የምፈልገው፡፡ ስለ ናፍቆት ማሰብም አልሻም፡፡ በቃ እሷ አልሄደችም፡፡ እዚሁ ናት፡፡ … አልናፍቃትም ምክኒያቱም አብረን ነው ያለነው፡፡ ከተረጋጋሁ በኋላ ስልክ ደወልኩላት፡፡ አሁን ለመለማመጥ ዝግጁ ነኝ፡፡ እየተለማመጥኩ ነገ ለመመለስ እንድትዘጋጅ ላባብላት፡፡




Read 6522 times